ጦርነቱ ሰበብ የሆናቸው ህገወጦቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታጥቅምት 19 ፣ 2014
City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች
ጦርነቱ ሰበብ የሆናቸው ህገወጦቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች
Camera Icon

Photo: Solomon Yimer

ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ጦርነት ውስጥ ከገባች አንድ አመት ማስቆጠሯ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች አጋጥመዋል። እንዲሀ ያለዉ ወቀት ለተለያዩ ህገወጥ ድርጊቶች በር እየከፈተ መምጣቱም ታይቷል። በልዩ ልዩ አሻጥር ከሚጠቁት ዘርፎች መካከልም የትራንስፖርት አገልግሎት አንዱ መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል። 

በኢትዮጵያ የየብስ የህዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ በተለያየ መልኩ የሚነሱ ስሞታዎችን መስማት አዲስ ነገር አይደለም። አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ደግሞ አዲስ ዘይቤ ከሰሞኑ ከሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ቅሬታዎች ደርሰዋታል። 

ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ሲከፍሉ ከነበረው ታሪፍ ከዕጥፍ በላይ እየከፈሉ መሆናቸውን እና ትኬት የለም በሚል ተደጋጋሚ ሰበብ እየተጉላሉ እና ላልተፈለገ ወጪ እየተዳረጉ እንደሆነ ይናገራሉ። የታሪፍ ጭማሬው የሚስተዋለዉ ከአዲስ አበባ ግጭት እንዳለ ወደሚታወቅባቸው የሀገሪቱ የሰሜን ክፍሎች ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ወደሆኑት የተለያዩ ክፍሎች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይም እንደተከሰተ አዲስ ዘይቤ ተረድታለች። 

ቅሬታው በተለያዩ የሕዝብ ማመላለሻ ዘርፎች ላይ ማለትም በትራንስፖርት ባለሥልጣን ቁጥጥር ሥር  በማኅበር፣ በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በአክሲዮን ተደራጅተው የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ የትራንስፖርት ዘርፉ ተዋንያን ላይ ነዉ።  

ኤልሳ ነጋሽ የተባለችው ወጣት “ከቀናት በፊት ወደ ሀዋሳ ደርሼ ተመልሻለሁ፣ ከዚህ በፊት ከምከፍለው ዋጋ 300 ብር ጨምሬ 650 ብር ከፍዬ ነው የሄድኩት” በማለት ትናገራለች። ኤልሳ ይህ ጉዳይ ያጋጠማት በአክሲዮን ተደራጅተው የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡት ድርጅቶች መካከል አንዱ በሆነው ዋሊያ ባስ እንደሆን ትናገራለች።

አያይዛም “ይህን ያህል ታሪፍ ለመጠየቅ እንዲያመቻቸው ከጉዞው ቀን ቀደም ብለን ትኬት ለመቁረጥ በምንጠይቅበት ወቅት ትኬት የለም የሚል ተደጋጋሚ ምክንያት በመስጠት ‘የጉዞው ዕለት ግን የሚቀር ተጓዥ ስለሚኖር እና ቦታ ሊኖር ስለሚችል መጥታችሁ ሞክሩ’ ይሉናል። በዕለቱ ስንሄድ ግን ባሱ ከግማሽ በላይ ቦታ እያለው አብዛኛው ሰው ለኛ የተሰጠን ምክንያት ተሰጥቶት ቦታው ላይ በጭማሪ ክፍያ እንዲቆርጥ ሲደረግ ነው የምናየው” ስትልም ታስረዳለች። 

አክላም “በአነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶች ላይም ከኔ ጋር ተመሳሳይ ገጠመኝ ያጋጠማቸው ወዳጆች አሉኝ›› በማለት ብዙ ሰው ላላሰበበት ወጪ ከመዳረግ አልፎ ትኬቶችን ከመናኸሪያዎቹ ለመግዛት ሲል በሚኖረው ጥድፊያ እየተጉላላ መሆኑን የገለጸች ሲሆን የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል ስትል አስተያየቷን ሰንዝራለች። 

እንደ ኤልሳ ገለጻ በስምሪት የሚሰሩት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከአክሲዮን ትራንስፖርቶቹ በተቃራኒ ከጉዞው ቀድሞ ትኬት መቁረጥ አይቻልም ለሚለው ምላሻቸው የሚሰጡት ማብራሪያ አሁን ላይ የመኪና ዕጥረት በመኖሩ ከጉዞው ዕለት ጠዋት ውጪ መቁረጥ አይቻልም የሚል መሆኑንም ትናገራለች።

አዲስ  ዘይቤ የቃሊቲ መናኸሪያ የሕዝብ ትራንስፖርት መንገድ ስምሪት ኃላፊ የሆኑትን ሲሳይ ባንተይሁን እንዳነጋገረችው ትኬት በዕለቱ መቁረጥ አልተቻለም የተባለበት ቅሬታ ትክክል መሆኑን በማሳወቅ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ መኪናዎች ግዳጅ በመውጣታቸው የተሽከርካሪ እጥረት በማጋጠሙ ትኬት የጉዞ እለት ብቻ እንዲቆረጥ መወሰኑን ነግረውናል። 

ከዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ደግሞ በትክክለኛው የአሰራር መንገድ እንደየጉዞ መዳረሻዎቹ ልዩነት ከ35 እስከ 50 በመቶ ጭማሪ መደረጉን ጠቅሰው “ለእናንተ እንደደረሳችሁ አይነት ጥቆማ ከልክ በላይ የሚያስከፍሉት አሽከርካሪዎች ግን ወቅታዊውን ችግር ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ጠምዝዘው የሚሰሩ ህገወጥ ሹፈሮች ሲሆኑ ከህብረተሰቡ ጋር እየተባበርን ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድባቸው እያደረግን ነው” ብለዋል።

በሌላ መልኩ ጥቆማ ከተደረገባቸው የአክሲዮን ትራንስፖርቶች መካከል አንዱ የኛ ባስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ሲሆን በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የመስርያ ቤቱ የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ቅርንጫፍ ተቆጣጣሪ አቶ አንድነት ተበጀ “የምንሰጣቸው ትራንስፖርት አገልግሎቶች በክፍያ በተለምዶው ከመደበኛዎቹ እንደሚጨምሩ ይታወቃል፣ ነገር ግን ከትኬት ሽያጭ ጋር በተያያዘ በብዛት ሰው ይጓዝባቸዋል ተብለው ወደሚታሰቡ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሄዱ የተመደቡ ሹፌሮች ከትኬት ሽያጭ ክፍል ጋር በመመሳጠር የተጠቆሙትን አይነት ህገወጥ ተግባራት እንደሚፈጽሙ መረጃው አለን” በማለት ጉዳዩ ላይ የህግ አካላትን በማካተት ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። 

አክለውም “ይህን ህገወጥ ተግባር የሚያደርጉት አካላት አመቺ ሰዓትን በመጠቀም በመሆኑ እጅ ከፍንጅ ለመያዝ አስቸጋሪ ሆኖብናል፣ ሆኖም እንዲህ ያሉት ተግባራት የሚያጋጥማቸው ደንበኞች ወዲያውኑ በድርጅቱ ስልክ በመደወል መጠቆም ቢችሉ መፍትሄውን ቀላል ያደርገዋል” ብለዋል።

አዲስ ዘይቤ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ስሞታ የቀረበበትን የዋሊያ ባስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ሃላፊዎች ለማናገር ሞክራ ፍቃዳቸውን ማግኘት ባለመቻሏ ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም። 

ሕገወጥ የስምሪት እንቅስቃሴን በተመለከተም የትራንስፖርት ባለስልጣን ቢሮ የመንገድ ስምሪት አገልግሎት ዋና ኃላፊ አቶ አበባው መላኩን እንዳነጋገርናቸው ህገ-ወጥ ስምሪት በሕጋዊ መልኩ ሕግና ደንብን አክብረው የሚሠሩ የትራንስፖርት ስራዎችን ያቀጨጨ እና ጥቂት ህገ-ወጦችን ያበለፀገ የሥራ ሒደት ሆኖ እንደሚታይ ያላቸውን ምልከታ በማስቀመጥ “የኛም ተቋም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሕገወጦችን የማስቆም ተከታትሎም ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነቱን ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው” ሲሉ ሕገወጦች እስኪጠፉ ጥረቱ እንደማይቋረጥ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ከተቆጣጣሪው አካል ለመሸሽ ሲሉ በሌሊትና በከፍተኛ ፍጥነት በመጓጓዝ ራሳቸውን ለማጎልበት እና ሕገወጥ ሥምሪትን ለማበራከት በሚሰሩ አካላት ላይም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመንገድ ፍሰት፣ በትራንስፖርት እና ተዛማች ጉዳዮች ላይ ጥናት ያደረጉት ታደሰ አለሙ (ዶክተር) “በሀገራችን የትራንስፖርት ዘርፉ እንኳን ጦርነትን የሚያክል ችግር ተጨምሮ በደህናውም ጊዜ እጅግ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚታዩበት ዘርፍ ነው” ይላሉ። ችግሮቹን ሲጠቅሱም በባለስልጣን መስርያ ቤቱ የወጡ ሕጎችና ደንቦች በአግባቡ አለመፈጻመቸውን እና የኅብረተሰቡን ቅሬታ፣ አቤቱታና ገንቢ አስተያየቶች የመቀበል ሥርዓት የሌለውና በድርጊት ያልተደገፈ በወረቀት ላይ ብቻ የሠፈረ ቻርተር በማዘጋጀት እና ሪፖርት በማቅረብ የዘርፉን ችግሮች መሸፋፈኑን ያነሳሉ፡፡

በመሆኑም እንዲህ ያሉ ለህገወጥ ተግባራት አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የሚበራከቱትን ችግሮች ለመፍታት ዘርፉን የሚመራው ተቋም አገልግሎትን ከሚያቀርብለት የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ሊያገናኝዉ የሚችል የግንኙነት መድረክ ፈጥሮ አለማወቁን በማውሳት ስለትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ከኅብረተሰቡ በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የሚቀርቡ ትችቶችን አዳምጦ በትክክለኛው ጊዜና ወቅት በሚዲያ ወይም ኅብረተሰቡ ሊያገኛቸው በሚችሉ የመገናኛ ዘዴዎች በመቅረብ ምላሽ ያለመስጠት ትልቅ ችግር መኖሩንም አስረድተዋል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist works at Addis Zeybe as a reporter while exploring her passion for storytelling and content creation.