ትኩረት የተነፈገው የወሎ ረሃብ

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታመስከረም 28 ፣ 2014
City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች
ትኩረት የተነፈገው የወሎ ረሃብ
Camera Icon

ምስል: ከማህበራዊ ሚዲያ

“እንደ ቀላል ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የጀመርነው ዘመቻ በፍጥነት አድጎ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነበርን ነገር ግን እዚያ ደርሼ ያየሁት ልብ የሚሰብር ነበር” የምትለው ‘እኔ እያለሁ ወሎ አይራብም’ በሚል ዘመቻ በፌስቡክ የእርዳታ ገንዘብ ካሰባሰቡት ወጣቶች ውስጥ አንዷ የሆነችው ሜላት ንጉሴ ናት።

"በእኛ በኩል ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል። በተሰበሰበው ገንዘብ እርዳታውን ገዝቶ ለማድረስ ወደ ወሎ ስንሄድ ትልቅ ገንዘብ ይዘን እንደሄድን ነበር የተሰማኝ" የምትለው ሜላት በቦታው ያለውን ነገር ከተመለከቱ በሏላ ግን ችግሩ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ትገልፃለች።

"ነፍሰ ጡሮች ፥ አረጋውያን ፥ ህጻናት በብዛት ያለምንም ተስፋ የእርዳታ እህል ጥበቃ ቁጭ ብለው ማየት ልብ ይሰብራል” ስትል በቦታው ያየችውን ትናገራለች። "ህጻናት የያዙ እናቶች ለልጆቻቸው የሚሆን ምግብ ለማግኘት ሲለማመጡ ማየት በጣም በጣም ያሳዝናል” 

ተጎጂዎቹ ምግብ ቢያገኙ እንኳ የሚያበስሉበት እንደሚቸገሩ አይተናል የምትለው ሜላት ከምግብ ባለፈ የመድሀኒት፣ የአልባሳት፣ የመጠለያና የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች እጥረት ተፈናቃዮቹን እየፈተነ እንደሚገኝ ትገልፃለች፡፡ 

ችግሩን የከፋ የሚያደርገው እርዳታዎች እየደረሱ ያሉት ደሴና ኮምቦልቻ አካባቢ በመሆኑ ጦርነቱ በሚካሄድባቸው ወረዳዎች የሚገኙ በርካቶች ለከፉ የምግብ እጥረት እየተጋለጡ ነገር ግን እርዳታ እያገኙ አለመሆኑ ነው።

“እኛ የያዝነውን እርዳታ ይዘን ከከተማ ውጪ ያሉ ከ10 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎችለሚገኙ ተጎጂዎች ለማዳረስ ሞክረናል፡ አሁንም እርዳታ መስጠቱ ይቀጥላል ግን ችግሩ እንዲህ ባለ የተበጣጠሰ ድጋፍ የሚፈታ አይደለም” ትላለች።

የደሴ ከተማ ከንቲባ የሆኑት አበበ ገብረ መስቀል ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ትግራይን ለቆ መውጣቱን ከተናገረበት ጊዜ አንስቶ በአካባቢው የተንሰራፋውን ግጭት በመሸሽ ከ300,000 በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ደሴ ከተማ ፈልሰዋል። ከንቲባው የፍሰቱ ፍጥነት በቁጥር ደረጃ መጠነኛ መዛባት ሊያመጣ እንደሚችል ጠቅሰው የአማራ ክልል የገቢ ማሰባሰቢያ ኮሚቴ የተፈናቃዮችን ፍላጎት ለማሟላት እየጣረ ቢሆንም አሁንም በቂ ሚባል ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ተናግረዋል።

እንደ አበበ ገለጻ ተፈናቃዮቹ በደሴ ከተማ በሚገኙ 13 ትምህርት ቤቶች ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን መንግስት እስካሁን ድረስ 22 ሺህ  ለሚሆኑ ተረጅዎች ምግብ ማቅረብ እንደቻለም አብራርተዋል። አክለውም “መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም እርዳታ እያደረጉ ነው፣ ለምሳሌ በአማራ ክልል የሚገኘው የመልሶ ማቋቋምና ልማት ኤጀንሲ 100ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች የምግብ እርዳታ አድርጓል” ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ከከተማዋ ውጭ ለሚገኙ የተቀሩት ወረዳዎች ለመድረስ የመጓጓዣ እጥረት ፈታኝ እንደሆነ ያነሳሉ። 

"ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚኖሩባቸው ሁለት የደቡብ ወሎ ሁለት እና የሰሜን ወሎ 21 ወረዳዎች የግጭቱ ቀጥተኛ ተጎጅዎች ቢሆኑም ተገቢው እርዳታ እየደረሳቸው አይደለም"

ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ተለይተው መንግሥት አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረስ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርን ጨምሮ ከሌሎች አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ከንቲባው ነግረውናል።

“ረሀቡ የከፋ ደረጃ ደርሷል ማለት ይቻላል ወይ?” ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱም ፣ “በሰሜን ወሎ አካባቢ በታጠቁ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በዋሉት ቦታዎች ላይ ረሀብ ቢከሰትም ጠኔ ተብሎ ሊጠራ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሷል ለመባል ግን ትክክለኛ ሁኔታ ነው ማለት አልችልም” ሲሉ አስተያየታቸውን ተናግረዋል። 

ከንቲባው በተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ የተከሰተው ረሃብ ህወሃት የፈጠረው ከፍተኛ ቀውስ ውጤት መሆኑን በማውሳት ለተጎዱት ሰዎች እርዳታን የማመቻቸት ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። “ሀገሪቱ በሰው ሰራሽ ጉዳት ነው የተጠቃችው፣ ስለዚህ አሁንም ይህን ጥፋት እያጠፋ ያለው ቡድን ሃላፊነቱን መውሰድ እስከቻለ እና ከተሞቹ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ማቆም እስከተቻለ ድረስ አሁንም ወሎን ለማዳን አልረፈደም” ይላሉ። 

አክለውም “እስካሁን ድረስ በረሃብ ምክንያት የሞተ ዜጋ መኖሩን የሚያረጋግጥ ምንም አይነት ማስረጃ የለም፤ የረሃብ ትንሽ ባይኖረውም አሁን የተከሰተውን ግን 'ጠኔ' ብሎ ለመጥራት ግን አያስደፍርም” ብለዋል።

በደሴ ከተማ የበጎ ፈቃደኞች ዕርዳታ አስተባባሪ የሆነችው እና የካዳም መረዳጃ ማህበር አባል የሆነችው ተምር ሀሰን ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፀችው በወሎ የሰብዓዊ ቀውስ የገጠማቸው ሰዎች ቁጥር ከ500 ሺህ በላይ የሚገመት ሲሆን ፤ ከእነዚህ መካከልም አብዛኛዎቹ በደሴ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው ይገኛሉ።

ተምር ለችግሩ ተጋላጭ ከሆኑት አብዛኞቹ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን በመጥቀስ  “መንግስት ያደረገው እርዳታ አነስተኛ ነው ወይም በቂ የሚባል አይደለም። ግለሰቦች ፣ በጎ ፈቃደኞች እና የዳያስፖራው ማህበረሰብ እየረዱ ቢሆንም ያለውን ችግር ለመቅረፍ ግን በቂ አይደለም” ብላለች።

በተጨማሪም በዚህ ቀውስ ምክንያት ሴቶች ከጤና ተቋማት ርቀው ጫካ ውስጥ በመውለድ ላይ እንደሚገኙ የገለጸችው ተምር ተፈናቃዮቹ በአብዛኛው ከሰሜን ወሎ በተለይም ከራያ ፣ አላማጣ ፣ ሃራ ፣ ወልዲያ ፣ መርሳ እና ላሊበላ አካባቢዎች የተፈናቀሉ መሆናቸውን አብራርታለች “ከሁለት ወረዳዎች በስተቀር አብዛኛው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ከባድ የሰብአዊ ቀውሶች እንዳጋጠማቸው ማረጋገጥ ችያለሁ” በማለት ትናገራለች።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የደቡብ ወሎ ዞን የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት በደሴ ከተማ አስተዳደር ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ በኩል በደሴ ከተማ ከ354 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን እየደገፈ መሆኑን መግለጹን አስመልክቶ አዲስ ዘይቤ የጽህፈት ቤቱን ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ እንዳነጋገረቻቸው ለነዚህ ተፈናቃዮች በመንግስት በኩል ከ350 ሺህ ኩንታል በላይ ዕለታዊ የሰብዓዊ ዕርዳታ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህ በደሴ ከተማ የሚገኙት ተፈናቃዮች ከሰሜን ወሎ ፣ ከደቡብ ወሎ እና ከአፋር ክልል ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በደሴ 14 ትምህርት ቤቶች በኮምቦልቻ ደግሞ 8 ትምህርት ቤቶች ለተፈናቃዮቹ በመጠለያነት እያገለገሉ እንደሚገኙ የጠቀሱት መሳይ መሠረታዊ የሰብዓዊ ዕርዳታ እየተደረገ ቢሆንም ፣ አሁን ላይ የምግብ ዘይት እጥረት እንዳለ ጠቁመዋል። በመሆኑም የተፈናቃዮቹን ሕይወት ለመታደግ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እና የእርዳታ ድርጅቶች አሁንም የተቀናጀ እርዳታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በ1977 ዓ.ም. ተከስቶ በሰሜን ኢትዮጵያ የከፋ ጉዳት አድርሶ ያለፈው ረሃብ ለረዥም ጊዜ ኢትዮጵያን የሚወክል ምሳሌ ሆኖ መቆየቱም ይታወሳል። በዚህ ክፉ ወቅት የወሎ አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቶ እንደነበር በማንሳት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘከሪያ “በ1977 በተከሰተው ረሃብ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ዋነኞቹ አውራጃዎች መካከል ቀዳሚው ወሎ ነበር፣ አሁንም ተመሳሳይ ጉዳት እያጋጠመ ይመስላል” ይላሉ።

“ይሁን እንጂ አሁን ያለው ሁኔታ ግን እንደቀድሞው በተፈጥሮ የሚሳበብበት ሳይሆን ሰው ሰራሽ ረሃብ ነው” በማለት የምርት እጥረት ሆነ ሌላ የተፈጥሮ አደጋም ከዚህኛው ረሃብ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው እና  ለተራቡት ሕፃናት ፣ እናቶች እና አዛውንቶች ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አካባቢው ላይ ሰው ሰራሽ ቀውስ እንዲፈጠር ያደረጉ አካላት መሆናቸውን ተናግረዋል።

“ለዚህ ደግሞ ቀውሱን እየፈጠረ ያለው ህወሃትም ሆነ የአንድ ወገን የተኩስ አቁሙ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለነዋሪዎቹ ግልፅ ሳያደርግ አካባቢውን ለቡድኑ ትቶ የወጣው መንግሥትም ሃላፊነት አለበት” ብለዋል።

አሁንም ቢሆን የወሎ ህዝብ በቂ የምግብ ፣ የውሃ እና የመድኃኒት አቅርቦት እንዲያገኝ ሳያደርግ መንግስት አንድም ቀን ማባከን የለበትም ያሉት አህመድ ጊዜው በሄደ ቁጥር በድጋሚ የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ጠባሳ ትቶ እንዳያልፍ መስራት ያሻል በማለት ይመክራሉ።

የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) “በአፋር እና በአማራ ክልል ያለው ግጭት 1.7 ሚሊዮን ሰዎችን ወደ ረሃብ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ እያደረገ ሲሆን የምግብ ፕሮግራሙ ተደራሽ ለመሆን እየሰራ ቢገኝም በመላው ሰሜን ኢትዮጵያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የነፍስ አድን እርዳታ ለማድረስ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልገናል” ማለቱን በመጥቀስ ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።

የትግራዩ ግጭት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ በአካባቢዎቹ ከፍተኛ ቀውስ እየደረሰ እንደሚገኝ ይታወቃል። እስካሁን በግጭቱ እንዲፈናቀል የተደረገው ህዝብ ትክክለኛ  ቁጥር ይፋ ባይደረግም በነሀሴ መጀመርያ ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ተፈናቅለው የገቡት ዜጎች ከ10,000 - 15,000 እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ  ቁጥሩ ወደ መቶ ሺዎች አሻቅቧል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist is working as a reporter and content creator at Addis Zeybe to explore her passion for storytelling. She has Bsc. in medical laboratories & BA in media and Communications.