ህብረተሰቡን በጉቦ ያማረሩት ሰራተኞች

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታነሐሴ 21 ፣ 2013
City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች
ህብረተሰቡን በጉቦ ያማረሩት ሰራተኞች

አዲስ አበባ ከተማ አፍንጮ በር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በአንዱ መንደር ውስጥ ከሚኖሩት ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑት የኤሌክትሪክ ኃይል ከተቋረጠባቸው ሶስት ቀናት እንዳለፋቸው ይናገራሉ። 

አቶ ስዩም ስባኒ የመንደሩ ነዋሪ ናቸዉ፡፡ ከመብራት መቋረጡ ከዛ ጋር ተያይዞ የገጠማቸውን ችግር  አንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ “በብልሽት ምክኒያት የመብራት መቆራረጥ እና በዛዉ ጠፍቶ የመቅረት ችግር በተደጋጋሚ ያጋጥሙናል። ብዙ ጊዜ ይሄ የሚፈጠረው አካባቢያችን ያለው ትራንስፎርመር ሲቃጠል ነው” ይላሉ፡፡

ለአቶ ስዩምና ሌሎች የሰፈሩ ነዋሪዎች ፈተና የሆነባቸዉ ከመብራት ብልሽቱ ጋር ተያይዞ በጥገና ሰራተኞች የሚጠየቁት ገንዘብ አንደሆነ ይናገራሉ፡፡ 

መስሪያ ቤቱ ብልሽቱን እንዲጠግኑ የሚልካቸዉ ሰራተኞች ያለአግባብ ገንዘብ ይጠይቃሉ የሚሉት አቶ ስዩም ገንዘቡ ካልተከፈላቸዉ ደግሞ የተለያየ ምክኒያት እያቀረቡ ሳይሰሩት አንደሚሄዱ ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ችግር ያጋጠማቸው የገላን ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎችም ይህን ይናገራሉ። ወ/ሮ ህብስት አሰፋ የተባሉ የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪ "በጨለማ መቀመጡ ለኛው ስለሆነ እዳው የሚጠይቁንን ከፍለን ይሰሩልናል፣ ግን ሁለት ወር አይቆይም መልሶ ይበላሻል ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ራሳቸው እንደሆኑ ነው የምንገምተው፣ በቀጣይም ሲሰሩ የሚያገኙትን ገንዘብ በማሰብ ጥራት የጎደለው ስራ ነዉ የሚሰሩት" ሲሉ ስሞታቸውን ይናገራሉ።

እነዚህን ስሞታዎች ለመስሪያ ቤቱ ሀላፊዎች አሳዉቀዉ አንደሆነ አዲስ ዘይቤ ለአቶ ስዩም ላቀረበችላቸዉ ጥያቄ ሲመልሱ “መሄዱንስ ሄደናል ነገር ግን እንከታተላለን እናስተካክላለን የሚል መልስ ነዉ በተደጋጋሚ የሚሰጡን” ይሁን አንጂ ነገሮች ሲስተካከሉ ግን አለማየታቸዉን ይናገራሉ፡፡

እንዲህ አይነት ቅሬታዎች የሚቀርቡት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች ላይ ብቻ አንዳልሆነና አንዳንድ የኢትዮ ቴሌኮም እና የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሰራተኞችም ተመሳሳይ ቅሬታ እየተሰማባቸዉ አንደሚገኝ አዲስ ዘይቤ ተረድታለች፡፡ 

ወጣት በእምነት እንዳልካቸው የጀሞ ሁለት ኮንዶሚኒየም ነዋሪ ናት። “የዋይፋይ አገልግሎት ለማግኘት መስመር አንዲዘረጋልኝ ካዘዝኩ ከሶስት ወር በላይ ሆኖኛል ግን ራውተሩን ገዝቼ ብጠብቅም ሰራተኞቹ አንዴ ገመድ መቀየር አለበት አንዴ የመኖርያ ቤቱን የስልክ መስመር ማስተካከል አለብሽ እና የመሳሰሉ ሰበቦችን እየደረደሩ እስካሁን አገልግሎቱን አላገኘሁም” ትላለች።

እንደ በእምነት ገለፃ ጉዳዩን ለኢትዮ ቴሌኮም እየደወለች ብታሳውቅም የሚመጡት ሰራተኞች ራሳቸው መሆናቸውን እና ለአካባቢዉ የተመደቡት እነሱ መሆናቸው እንደሚነገራት ትገልጻለች። 

“ሰራተኞቹ አገልግሎቱን ለመስጠት ከተቋሙ እዉቅና ዉጭ ገንዘብ አንደሚጠይቁና ካልተከፈላቸዉ አንደማይሰሩ ገንዘብ ከፍለዉ አገልግሎቱን ካገኙ ሰዎች ተነገረኝ” ትላለች፡፡ “አፍ አውጥተው ገንዘብ አምጡ ስለማይሉ ለመስሪያ ቤቱ መጠቆም አልቻልኩም”

የበእምነት ጎረቤት የሆነችው ወጣት ቃልኪዳን በበኩሏ “አገልግሎቱን ያጠናቀቁልኝ የሻይ ብዬ ብር ከሰጠኋቸው በኋላ ነው። ቲፕ ወይም ጉርሻ የሚታወቀው ከአገልግሎት በኋላ የሚሰጥ ምስጋና እንደሆነ ነው እነሱ ግን ቀድመው ተቀብለው ስለሚሰሩ ጉቦ እንጂ ሌላ ስም የለውም” ስትል ምስክርነቷን ትሰጣለች። 

በውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ቆጣሪ አንባቢዎች እና ተቆጣጣሪዎች ላይ የሚቀርበው ቅሬታ ደግሞ ለየት ይላል አንዳንድ ቆጣሪ አንባቢዎች በተቋሙ ከተለመደዉ ቀደም ብሎ ማስጠንቀቂያ ከሚሰጥበት አሰራር ዉጭ የውሃ ክፍያ ስላልከፈላችሁ ከነገ ጀምሮ ይቆረጥባችኋል በማለት ከደንበኞች ገንዘብ እንደሚጠይቁ ይነሳል፡፡

“አጋጣሚ ክፍያ ሳንከፍል ሲያልፍብን ድንገት ይመጡና ነገ ሊቆረጥባችሁ ነው በሚል ‘ቢሮው ሄደን ትንሽ ጊዜ እንዲሰጥ እናደርጋለን’ በሚል ማባበያ ገንዘብ ይቀበሉናል እኛም ድንገት ስለሚሆንብን እና ውሃ መቆረጡ ስለሆነ የሚታየን እንሰጣለን ”የሚሉት ነዋሪነታቸውን በሳሪስ አደይ አበባ ያደረጉት አቶ ለማ ሀይሉ ናቸው።

አዲስ ዘይቤም እነዚህን ስሞታዎች በመያዝ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የስራ ሃላፊዎችን አነጋግራለች፡፡

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ዲስትሪክት የኅይል የሰው ሀብት አስተዳደር አቶ አታላይ አበበ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ “እንደዚህ አይነት የተበላሸ አሰራር ውስጥ የተዘፈቁ ሰራተኞች መኖራቸው አያጠራጥርም። እንደውም አንዳንድ ሰራተኞች ላይ በሚደርሰን ጥቆማ መሰረት ከፖሊስ ጋር በመተባበር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ለህግ ያስረከብናቸው ሰራተኞችም እንዳሉና በተለያየ ጊዜ በዜና ይፋ እንደምናደርግም ይታወቃል” ብለዋል።

አስተዳደሩ አያይዘው የሙስና ወንጀሎችና ብልሹ አሰራሮችን የሚፈፅሙ የተቋሙ ባልደረቦች ሲያጋጥሙ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና በተለያዩ የስራ አጋጣሚዎች ሃላፊዎችን ማግኘት ካልተቻለ ተቋሙ ባዘጋጀው የቅሬታ ማቅረቢያ ስልክ ደውለው ማሳወቅ እንደሚችሉ ጠቁመው በእነዚህ ስልኮች የሚደረጉ የሃሳብ ልውውጦች ስለሚቀዱ ቅሬታ ተቀባዩ ጋር ችግር ካለ ለመያዝ እንደሚቻል ጠቅሰዋል። በተጨማሪም በየአካባቢው ለሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችም ቅሬታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉም ተናግረዋል። 

የኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም አህመድ በበኩላቸው “በዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ከደንበኞች ቅሬታ ቀርቦልን ብዙ ሰራተኞች ላይም እርምጃ ተወስዷል፤ ይህ ወደፊትም የሚቀጥል ነው” ብለዉናል።

አክለውም “ሙሰኛ ሰራተኞች ቢኖሩም በአንጻሩ ደግሞ ከወረፋ መደራረብ፣ ከአንድ ቤት ሌላ ቤት በሚለያዩት የመስመር ዝርጋታው ሲስተም ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች እና የተለያዩ ቴክኒካል ችግሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሁሉም ላይ ጣት ከመጠቆም በፊት ህብረተሰቡ እሱንም ግንዛቤ ውስጥ ሊከት ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

ዳይሬክተሩ በተለይ አንዳንድ በከተማ ዳር የሚገኙ ሰፈሮች የዋይፋይ ሲስተም ባለመዘርጋቱ እና ገና ስራ ላይ ያሉ በመኖራቸው መሰል ችግሮች ሲፈጠሩ አለመግባባት እንደሚከሰት እና የተሳሳተ ቅሬታ እንደሚደርሳቸው በማስረዳት ይህ አሰራር ላይ ተዓማኒነትን ስለሚያጠፋ ህዝቡ ልዩነቱን እንዲያገናዝብ ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰርካለም ጌታቸው በተቋማቸው ላይ ስለቀረበው ቅሬታ ሲያብራሩ “በመጀመርያ ደረጃ ሰራተኛ ሳይሆኑ በተለያዩ መኖርያ ቤቶች የውሃ ቆጣሪ አንባቢ ነን በማለት ገብተው ስርቆት ሁሉ የሚፈፅሙ እንዳሉ ይታወቃልና እንደዚህ አይነት ሊቆረጥባችሁ ነው እና መሰል ማስጠንቀቂያዎችን በመንገር ገንዘብ የሚቀበሉትንም ለመለየት እና ለአጠቃላይ ጥንቃቄ ሲባል ማንኛውም ነዋሪ ቆጣሪ አንባቢ ነን የሚሉትን ሰዎች መታወቂያ አሳይተው እንዲገቡ ያድርግ፡ ከዛ በኋላ ላለው ነገር ግን ሰራተኛም ከሆነ ተገልጋዩ ስሙን ማወቅ ስለሚችል በቀላሉ ተቋማችን እርምጃ ለመውሰድ ይቀለዋል” ብለዋል።

አያይዘውም ሁሉም ሰው የውሃ ክፍያ ደረሰኙን በመከታተል የመጨረሻ የክፍያ ቀኑን ማወቅ እንደሚችል ጠቅሰው “ቆጣሪያችሁ አላግባብ እየቆጠረ ይመስላልና እንመርምርላችሁ በሚሉ ማታለያዎች የተጭበረበሩ ደንበኞችም ለተቋማችን ቅሬታ ያመጣሉ” ሲሉ ህዝቡ እንዲጠነቀቅ እና ችግር ሲገጥመው ግን አሁንም ከመጠቆም ወደ ኋላ እንዳይል አሳስበዋል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist is working as a reporter and content creator at Addis Zeybe to explore her passion for storytelling. She has Bsc. in medical laboratories & BA in media and Communications.