መስከረም 14 ፣ 2014

የቤቲንግ ትኩሳትና ውጤቶቹ

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች

ጅማሬው በአሜሪካ የሆነው የስፖርት ውርርድ ወደ አፍሪካ የገባው በአውሮፓ እና በኤዢያ አህጉራት በከፍተኛ መጠን ከተስፋፋ በኋላ ነው። ዘርፉ ዓለምን በማዳረስ ግዙፍ ትርፋማ ኢንዱስትሪ መሆን ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።

Avatar: Dawit Araya
ዳዊት አርአያ

Dawit has been the Amharic assignment editor at Addis Zeybe. He has worked in printing, electronics, and online news platforms such as Fitih, Taza, and Ye Erik Ma'ed for the past five years.

የቤቲንግ ትኩሳትና ውጤቶቹ
Camera Icon

Photo: Solomon Yimer

የስፖርታዊ ጨዋታዎች ውርርድ “ቤቲንግ” በዓለም ዙርያ ከ3 ትሪልዮን ዶላር በላይ የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ የቢዝነስ ዘርፍ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ጅማሬው በአሜሪካ የሆነው የስፖርት ውርርድ ወደ አፍሪካ የገባው በአውሮፓ እና በኤዢያ አህጉራት በከፍተኛ መጠን ከተስፋፋ በኋላ ነው። ዘርፉ ዓለምን በማዳረስ ግዙፍ ትርፋማ ኢንዱስትሪ መሆን ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።

የስፖርት አወራራጅ እና አቋማሪ ድርጅቶቹ ከ55 ሺህ በላይ የስፖርት ውድድሮች ላይ ተመስርተው ከተመልካችና ደጋፊዎች ጋር ይወራረዳሉ። ከእነዚህ መካከል በተወራራጅ ግለሰቦች ቀዳሚው ተመራጭ የእግር ኳስ ሲሆን የገበያውን 65 በመቶ ድርሻ ይይዛል። ቴኒስ እና ክሪኬት እያንዳንዳቸው የ12 በመቶ ድርሻ በመያዝ በሁለተኝነት ይከተላሉ።

የስፖርታዊ ጨዋታዎች ውርርድ (ቤቲንግ) የኢትዮጵያን ገበያ ከተቀላቀለ አንስቶ በርካታ ውዝግቦች አስተናግዷል። በጨዋታው ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን ያስተዋሉ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተውበታል። በሴቶችና ሕጻናት ቢሮ እንዲሁም በተወካዮች ምክርቤት ደረጃ በርካታ ውይይቶች፣ የሚድያ ዘመቻዎች፣ የጥሩ ነው- መጥፎ ነው ውዝግቦች ተደምጠዋል። የዕድል ጨዋታዎችን እንዲመራ በአዋጅ ሕጋዊ ፈቃድ በተሰጠው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ፈቃድ ሰጪ፣ የዓመታዊ እድሳት አከናዋኝ እና ተቆጣጣሪነት እየተካሄደ ይገኛል። አስተዳደሩ አጫዋች ድርጅቶችን ለመቆጣጠር እንዲያግዘው ያወጣውን መመሪያ በቅርቡ አሻሽሏል። መመሪያ ቁጥር 172/2013 ላይ የተጨዋቾችን እድሜ፣ የማጫወቻ ቤቶች የሚከፈቱበትን አካባቢ፣ የሽልማት ጣሪያን፣ የእድሳት እና የፈቃድ ማውጫ ክፍያዎችን የተመለከቱ አንቀጾች ተሻሽለዋል።

በአዲሱ መመሪያ መሰረት የአወራራጅ ድርጅቶቹ ሱቆች ከትምህርት ቤቶች፣ ከጤና ተቋማት፣ ከእምነት ቦታዎች መራቅ ይገባቸዋል። ከተጠቀሱት ማኅበራዊ እና ሐይማኖታዊ ስርአት ማከናወኛ ሥፍራዎች ቢያንስ ከ5 መቶ ሜትር ርቀት በታች መከፈት አይችሉም። የሽልማት መጠናቸውም ከአንድ ሚልዮን ብር መብለጥ የለበትም ተብሏል። ከዚህ በፊት በፈቃድ እድሳት ይከፈል የነበረው ገንዘብ ወደ ብር 100ሺህ አድጓል። አዲስ ፈቃድ ለማውጣት ደግሞ 500ሺህ እንዲከፈል ታዟል። በጨዋታው ላይ የሚሳተፍ ሰው ትንሹ እድሜ 18 የነበረ ሲሆን ወደ 21 ከፍ ብሏል። የትምህርት ቤት መለያ ልብስ የለበሰ ማንኛውም ሰው የውርርድ ጨዋታውን መሳተፍ እንዳይችል ታግዷል። 

ከቅርብ ጊዜው መመሪያ በፊት የእድሳት ክፍያው ብር 400፤ የአዲስ ፈቃድ ክፍያው ደግሞ 200 ብር ሆኖ ሲሰራበት ቆይቷል። አዲሱ የክፍያ ስርአት ከቀደመው ክፍያ ጋር የተጋነነ እንደሚመስል በማስታወስ “እንዴት አገኛችሁት?” ስንል ኢትዮጵያ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ አወራራጅ ተቋማትን ጠይቀናል። አቡሽ በሚል ስም የተዋወቀን የ“ቢቲካ” አወራራጅ ተቋም ወኪል “በእኛ በኩል አዲሱ ውሳኔ መጥፎ የሚባል አይደለም” ብሎናል። “አዲሱ መመሪያ አትራፊ ነው በሚል ግምት ብቻ ያለ በቂ ዝግጅት ሁሉም ሰው በዘፈቀደ የሚገባበት ቢዝነስ እንዳይሆን ያደርጋል። ለተጨዋቹም ደስታ፣ ድርጅቶችም ዝቅ ባለ አቅም ገበያውን ተቀላቅለው በኪሳራ እንዳይሰናበቱ ያግዛል የሚል ሐሳብ አለኝ” ሲል ሐሳቡን ደምሟል።

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ነዋይ ማስተካከያው ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩ “ቤቲንግ” ለነጻው ገበያ በዘፈቀደ የሚተው የንግድ ዘርፍ አለመሆኑን ከማብራራት ይጀምራሉ። “የስፖርታዊ ጨዋታዎች ውርርድ እንደሌሎች የንግድ ወይም የአገልግሎት ዘርፎች አይደለም። ከፍ ያለ ቁጥጥር ያስፈልገዋል። የማኅበረሰቡን እሴት በማይነካ መልኩ መካሄድ ይገባዋል። አዲሱ መመሪያ ካሻሻላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ይሄ ነው። የቤቲንግ ተቋማቱ የሚከፈቱበት ቦታ የእምነት እና የትምህርት ሂደቱን እንዳያውኩ 500 ሜትር እንዲርቁ ተደርጓል። ዕድሜው ከ21 ዓመት በታች ያለ ሰው እንዳይጫወት የተከለከለበት ምክንያትም የማኅበረሰብን ደህንነት መጠበቅ ነው” ብለውናል።

የስፖርታዊ ጨዋታዎች ውርርድ በአፍሪካ

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ 27 አገራት የስፖርት ጨዋታዎች ውርርድ ይካሄዳል። የአወራራጅ ተቋማቱ ቁጥር በሕገ-ወጥ የሚንቀሳቀሱትን ጨምሮ ከ2ሺህ በላይ እንደሚሆን አጥኚዎች ገምተዋል። የስፖርታዊ ውርርድ ጨዋታዎቹ ከተስፋፉባቸው የአፍሪካ ሐገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ በቀዳሚነት ስትጠቀስ ከፊት ረድፍ ላይ ከሚገኙት ሦስት ሐገራት ውስጥ ናይጄሪያ እና ኬንያ ይገኙበታል።

‘ፕራይስ ዎተርስ ኩፐርስ’ የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ባካሄደው ጥናት እንደተነበየው በቀጣዮቹ ዓመታት ከሦስቱ ሐገራት የሚገኘው የኢንዱስትሪው ገቢ ከ50 ሚልዩን ዶላር ሊዘል ይችላል። አፍሪካውያኑ የውርርድ ተቋማት አንድ ተሳታፊ 1 ዶላር አስይዞ የሚገምተው የጨዋታ ውጤት ከሰመረለት እስከ 500 ዶላር እያስያዙ/እየሸለሙ ይገኛሉ። ከአፍሪካ ቀዳሚውን ደረጃ በያዘችው ደቡብ አፍሪካ ኢንዱስትሪው በየዓመቱ 21 በመቶ እድገት ሲያሳይ ዓመታዊ ገቢው 25 ሚልዮን ዶላር ደርሷል። ይህ አሃዝ ከአህጉሪቱ የስፖርት መስክ ገቢ 14 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዝ ነው። የምዕራብ አፍሪካ ሐገራቱ ናይጄሪያ እና ጋና ደግሞ ከ60 ሚልዮን የሚልቁ ደንበኞች ከ9 ሚልዮን ዶላር በላይ በማውጣት ይሳተፋሉ። ከምዕራብ አፍሪካ ሐገራት በስፖርት ውርርድ ቀዳሚዋ ኬንያ ነች። በሐገሪቱ የሚገኙት የውርርድ ተቋማት በዓመት በድምሩ 20 ሚልዮን ዶላር ያንቀሳቅሳሉ።

በደቡብ አፍሪካ በስፋት ከሚካሄዱት የስፖርት ውርርዶች እግር ኳስ፣ ራግቢ፣ ክሪኬት፣ አትሌቲክስ ተዘውታሪዎች ናቸው።

የስፖርታዊ ጨዋታዎች ውርርድ በኢትዮጵያ

በስፓርታዊ ጨዋታዎች መወራረድ በተቋም ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው በ2005 ዓ.ም. እንደሆነ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ነዋይ ይናገራሉ። የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳብራሩት በ1999 ዓ.ም. እና በ2001 ዓ.ም. በተተገበሩት መመሪያዎች ላይ የስፖርታዊ ጨዋታዎች ውርርድ የተካተተ ቢሆንም ተግባራዊ የተደገው ግን 4 ዓመታት ዘግይቶ ነው። ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮም ይበልጥ እየተስፋፋ መጥቷል ሲሉ አጀማመር እና እድገቱ ምን እንደሚመስል አስረድተውናል።

የብሔራዊ ሎተሪ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ቴዎድሮስ “በአሁን ሰዓት ወደ 42 የሚጠጉ ተቋማት ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ፈቃድ ተሰጥቷቸው የውርርድ ጨዋታ በማጫወት ላይ ይገኛሉ” ያሉን ሲሆን ከመካከላቸው እስከ 50 የሚጠጋ ቅርንጫፍ ቢሮ በየአካባቢው የከፈቱ እንደሚገኙበት ይናገራሉ።  

የስፖርት ውርርድ ሙሉ ለሙሉ ጎጂ ነው ብሎ የማያምነው ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ቁጥጥሩን አጠናክሮ እየቀጠለ እንደሆነ ቢናገርም፤ በጅማሬው ሰሞን የሚሰሙት የድጋፍና ተቃውሞ ድምጾች ቢቀንሱም ጨርሶ አልጠፉም። ከቀደመው መመሪያ አንጻር ጠንከር ያለ የሚመስለውን የአዲሱን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገው ከማኅበረሰቡ በመጣ ግፊት ስለመሆን አለመሆኑ ከአዲስ ዘይቤ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ “አስጠንተነዋል” ብለዋል። “ከዩንቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የተካሄደው ጥናት በቅርብ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ገበያ ጋር የተዋወቀው የውርርድ ጨዋታ ያሳደረውን በጎ እና መጥፎ ተጽዕኖ በስፋት ተመልክቷል” የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ የጥናት ሰነዱ ለገቢዎች ሚንስትር መላኩን እና በቅርቡም ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ነግረውናል። “የጉዳት እና የጥቅሙን ደረጃ፣ የትርፍና ኪሳራውን መጠን እንደሚያሳይ የሚጠበቀው ጥናት በሚያመላክተው አቅጣጫ መሰረት ለውጦች እና ማሻሻያዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል። 

ትርፍ እና ኪሳራ

የውርርድ ጨዋታው የዕድል በር ሆኗቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ማትረፍ የቻሉ እንዳሉ ሁሉ የሕይወት መስመራቸውን ያዛባባቸው ጥቂት አይደሉም። አዘውትረው ከመሸነፋቸው የተነሳ “ያሸነፈ ይሸለማል” የሚለው የአወዳዳሪዎቹ ቃል ሐሰተኛ ነው ለማለት የተገደዱ፤ የሚወዱትን የስፖርታዊ ጨዋታ ጣዕም አጥፍቶብናል የሚሉ እና ጨዋታውን በጉጉት የመከታተያ ተጨማሪ ቅመም እንደሆነላቸው የሚያስቡም እንዲሁ ይገኛሉ። ለዚህ ዘገባ ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎችም ይህንኑ አረጋግጠውልናል።

አዲስ አበባ በልዩ ስሙ በጀሞ አንድ አካባቢ በሚገኝ የወንዶች ጸጉር ቤት ውስጥ በጸጉር በአጣቢነት እና በገንዘብ ተቀባይነት በማገልገል ላይ የምትገኘው ትእግስት ታፈረ የስፖርታዊ ውርርድ ጨዋታን የተዋወቀችው የወንዶች ጸጉር ቤት ሥራ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ ታስታውሳለች። አስቀድሞ እግርኳስ ተመልካች እና ደጋፊ ባትሆንም መወራረድ የጀመረችው በዙርያዋ በሚገኙ የሥራ ባልደረቦቿ እና ደንበኞቿ ግፊት ነው። የሚያስገኘውን ትርፍ ብቻ በማሰብ የጀመረችው ቁማር የገንዘብ ትርፍ እንዳላስገኘላትም አልሸሸገችንም። “ያተረፍኩት ንዴት እና ኪሳራ ነው” የምትለው ወጣቷ መወራረድ ከጀመረች ከ6 ወራት በላይ ብታስቆጥርም አንድም ጊዜ አሸንፋ እንደማታውቅ ነግራናለች። “የውርርድ ትኬቱን የሚቆርጡልኝ የሥራ ባልደረቦቼ ናቸው። እኔ ስለ ተፎካካሪ ቡድኖቹ ዕውቀት ስለሌለኝ አሸናፊውን ለመገመት እቸገራለሁ” ማለቷ ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ አድርጎታል። አንድም ጊዜ ሳታሸንፍ ለተከታታይ 6 ወራት የተወራረደችበት ምክንያት ሱስ ሳይሆን እንደማይቀርም ትገምታለች። “ጉዳቱን ባውቀውም ለማቆም በእጅጉ ተቸግሬአለሁ። ከተሸነፍኩ በኋላ ደግሜ ላለመወራረድ ብዝትም አይሳካልኝም” ትላለች። በየእለቱ ከደንበኞቿ የምታገኘውን ጉርሻ (ቲፕ) ለውርርድ እንደምታውለውና ጊዜ እየሄደ ሲመጣ ያለምንም ጥቅም የባከነው ገንዘቧ እየቆጫት እንደሆነ አብራርታለች።

“በአወራራጅነት ተመዝግበው በኪሳራ ምክንያት ከገበያው የወጡ ተቋማት አሉ” ያሉን ደግሞ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው። እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ የቢዝነስ ዘርፉ ትርፍ ብቻ የሚታፈስበት አይደለም። ከስረው የአወራራጅ ተቋም ፈቃዳቸውን የመለሱ ድርጅቶችን ትክክለኛ ቁጥር ለመናገር ግን መረጃዎችን ማገላበጥ እንደሚገባ ነግረውናል። የ“ቢቲካ” አወራራጅ ተቋም ተወካይ እስከ 1 ነጥብ 8 ሚልዮን ብር ለአንድ አሸናፊ ከፍሎ እንደሚያውቅ ነግረውናል። “አንድ ተወራራጅ በውርርዱ ማሸነፍ አለማሸነፉን የሚያውቀው ጨዋታው ሲጠናቀቅ ነው። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በውርርዱ ለመሳተፍ የቆረጠውን ትኬት ይዞ መገኘት ይገባዋል። ትኬቱን ቢጥል ወይም ቢቀድ ክፍያው አይፈጸምለትም” ብለውናል። በተለይ የውርርድ ስፖርቱ እንዲህ እንዳሁኑ ተስፋፍቶ በርካቶች የጨዋታውን ሕግ ከመገንዘባቸው በፊት “አሸንፌ ነበር” የሚሉ ትኬት ያልያዙ ግለሰቦች የክፈሉን ጥያቄ አቅርበው እንደሚያውቁም አስታውሰዋል።

አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ ከአወራራጅ ተቋማት የገዛውን ትኬት ከጨዋታ ውጤት ጋር ሲያመሳክር ያገኘነው ወጣት ሄኖክ አበባው “የምወራረደው ጨዋታው የበለጠ ስሜት እንዲሰጠኝ ነው” ይላል። “የታክሲ እንኳን ባይኖረኝ ተበድሬ ቤቴ እገባለሁ እንጂ በተለይ ተጠባቂ ጨዋታዎች ካሉ እወራረዳለሁ” ያለን ሲሆን እሱ ሱስ ባይኖርበትም ከፍተኛ ደረጃ ሱስ ውስጥ የገቡ ሰዎችን እንደሚያውቅ ነግሮናል። “ሱስ ውስጥ ስትገባ ሁለት ኪሳራ ነው የሚኖርብህ። አንደኛው የምትደግፈው ክለብህ መሸነፉ ሲሆን ሁለተኛው ገንዘብህ መክሰሩ ነው። እኔ በምጫወትበት ጊዜ የምተማመንበት ክለብ ከሆነ ስንት ለስንት እንደሚያሸንፍ ገምቼ እወራረዳለሁ። ኪሳራው ግን አሳስቦኝ አያውቅም። ከሥራ የተረፈኝን ጊዜ በመዝናኛ እያሳለፍኩት እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። ሌላው ሰው በምግብም፣ በመጠጥም፣ ከቦታ ቦታ በመዘዋወርም ይዝናናል። እኔ ደግሞ ኳስ በማየት እና በመወራረድ እዝናናለሁ። የተለየ ነገር የለውም።” ሲል መከራከሪያውን ያቀርባል።

ከቢንያም አባቡ ጋር የተገናኘነው ላፍቶ አካባቢ በሚገኝ አወራራጅ ተቋም ውስጥ ነው። የ50 ብር እና የ20 ብር ዋጋ ያላቸው 5 ትኬቶች ቆርጧል። ከዚህ በፊት በ10 ብር በቆረጣት ትኬት 400 ብር እንደበላ ይናገራል። መጫወት ከጀመረ ከ3 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን “ሦስት ጊዜ በልቻለሁ። 400 ብር፣ 3,000 ብር እና 1,600 ብር በተረፈ በጣም ብዙ ጊዜ እበላለሁ” ይላል። እሱ አዘውትሮ የሚወራረድበት ተቋም ውስጥ ትኬት የገዛ ሰው 60 ሺሀ ብር እንዳሸነፈ መስማቱንም አጫውቶኛል። በአካል ባያውቀውም 270 ሺህ ብር በልቶ የጋራ መኖርያ ቤት እዳውን የከፈለ ሰው በአካባቢያቸው እንዳለ ሰምቷል። በቀን ቢያንስ 5 ጨዋታዎችን የሚወራረደው በስፖርት ፍቅር ብቻ ሳይሆን በቁማሩ ሱስ ምክንያት እንደሆነም ያምናል። በቀን 1 ጨዋታ በ10 ብር በመቁረጥ የጀመረው ውርርድ እስከ 5 አድጓል። በ10 ብር ትኬት አልረካ ብሎ ኪሱ የሞላ ቀን የ50 እና የ100 የሌለው ቀን የ20 ብር ይቆርጣል። ያለበትን ሁኔታ በመገምገምም ሰዎች እዚህ ዐይነት ጨዋታ ውስጥ እንዳይገቡ መክሯል። “አወጣጡ እንደ አገባቡ አይቀልም” ሲልም ተደምጧል።

“ለማሸነፍ እድልም፣ እውቀትም ይፈልጋል” የሚለው ደግሞ ምስጋናው ተሻለ ነው። በቅርብ የሚያውቀው ጓደኛው 170 ሺህ ብር ሲያሸንፍ ተመልክቶ እርሱም የእድሉን ለመሞከር በሚል ገብቶ ሱሰኛ ከሆነ 4 ዓመታት እንዳለፉ ይናገራል። እርሱም በተራው በ20 ብር ተጫውቶ 3ሺህ በ10 ብር ተጫውቶ 7ሺህ ብር እንደበላ ያስታውሳል። “ሌሎች ጥቃቅን ብሮችንም አሸንፌአለሁ” የሚለው ምስጋናው የሚወደውን ቡድን በቤቲንግ ምክንያት ሊጠላው እንደተቃረበ አልሸሸገንም። “አንዳንድ ጊዜ ከወረደ ቡድን ጋር ተጫውተው ሲሸነፉ ሆነ ብለው እየተሸነፉ ይመስለኛል። በጣም ብዙ ጊዜ ቡድኔን ብዬ አስይዤ ተበልቻለሁ” ብሎናል። ከኢትዮጵያ ፕሮምየር ሊግ ጀምሮ እንግሊዝ፣ ጣልያን፣ ስፔን፣ ስኮትላንድ፣ ቱርክ ያሉ ቡድኖች ጨዋታ ሲኖራቸው ያስይዛል። የማያውቃቸው ቡድኖችም ቢሆኑ ገምቶ ይወራረዳል።  

“ብሌን ቤቲንግ” የተባለ አወራራጅ ተቋም ከስሮ ከገበያው እንደወጣ የነገረን ወጣት ደግሞ በዚህ ጽሑፍ ላይ ስሙ እንዲጠቀስ አልፈለገም። በመኖርያ ሰፈሩ አካባቢ ይገኝ የነበረው አወራራጅ ድርጅቱ ከዓለም አቀፍ የውርርድ አቅራቢዎች የሚደርሰው መረጃ ዘግይቶ ደርሶት ለኪሳራ ተዳርጓል። ተጠናቆ ውጤቱ የታወቀ ጨዋታን እንዳልተጠናቀቀ አድርጎ ያቀረበው የተቋሙ የዘገመ ድረ-ገጽ ሰዎች ውጤቱን አውቀው በከፍተኛ ገንዘብ እንዲወራረዱ አድርጓቸዋል። ሁኔታውን ያልተገነዘበው ብሌን ቤቲንግም ለአሸናፊዎቹ ክፍያ ፈጽሟል። በዚህ ምክንያት ከስሮ ከገበያ ወጥቷል።

በተለይ ሰፊ እውቅና የሌላቸው ቡድኖች የአወራራጅ ድርጅት ጋር በመሆን ይሰራሉ የሚል ሐሜትም ይነሳባቸዋል። ቡድኖቹ ሆነ ብለው በመሸናነፍ አወራራጅ ተቋማቱ እንዲያሸንፉ በማድረግ የጥቅም ተጋሪ ይሆናሉ። ይህ ዓለም አቀፍ ማጭበርበር ኢትዮጵያ ውስጥም ስለመኖሩ የሚታዩ ምልክቶች አሉ። “ቪአይፒ” የሚል ስያሜ ላላቸውና ከውጭው ተቋም ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚናገሩት ግለሰቦች 500 ብር በማስከፈል የትኛው ቡድን ስንት ለስንት በሆነ ውጤት እንደሚያሸንፍ ይናገራሉ። ከዋናው ተቋም አገኘነው የሚሉት መረጃ ሰምሮለት አንድ ጊዜ ማሸነፍ እንደቻለ መረጃውን የሰጠን የቤቲንግ ደንበኛ ይናገራል።

ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ከታወቁት ተቋማት መካከል “ዋን ኤክስ” ተጠቃሽ ነው።

የጨዋታው ሂደት

በስፖርታዊ ጨዋታዎች ለመወራረድ አወራራጅ ተቋማትን ደጃፍ የረገጠ ሰው አማራጮች ይቀርቡለታል። ተጫዋቹ የዛሬ፣ የነገ ወይም የሳምንቱን ጨዋታዎች ዝርዝር ተመልክቶ ከአማራጮቹ መካከል ቀልቡ የፈቀደውን ይመርጣል። ከቀረቡት የእግር ኳስ፣ ቴኒስ ቅርጫት ኳስ እና ሌሎች የጨዋታ አማራጮች ያሻውን መርጦ እንደ ጨዋታዎቹ ሁሉ ሐገራቱንም ይመርጣል። ከዚህ በኋላ ለጨዋታዎቹ በተሰጠው “ኦድ” (የአሸናፊነት ግምት) መሰረት ይወራረዳል። ለእያንዳንዱ ተጫዋች ቡድን ወቅታዊ አቋሙ፣ በዕለቱ የሚሰለፉት ተጫዋቾች ማንነት፣ የተጋጣሚ ቡድኑ ሁኔታ ታይቶ “ኦድ” ይሰጠዋል። በወቅታዊ አቋሙ ምክንያት ከፍተኛ የማሸነፍ እድል እንዳለው የሚገመት ቡድን ዝቅተኛ “ኦድ” በቅድመ ግምቱ መሰረት የማሸነፍ እድል እንደሌለው የሚገመተው ደግሞ ከፍተኛ “ኦድ” ይሰጣቸዋል። በሜዳው የሚጫወት ቡድን ከፍ ያለ “ኦድ” የማግኘት እድል አለው። አንዳንድ አወራራጅ ድርጅቶች የ100 ብር ትኬት ለሚገዛ ተወራራጅ ቦነስ የሚሰጡበት አሰራር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጀምሯል።

ተወራራጁ የመረጣቸው ተፎካካሪ ቡድኖች ጨዋታቸው የሚጠናቀቅበትን መንገድ ያገምታሉ። ከግምት አማራጮቹ መካከል ያሸንፋል ወይም ይሸነፋል (ከሁለቱ ቡድኖች አንዱን በመምረጥ)፣ ይሸናነፋሉ (ቡድን ሳይመርጡ ጨዋታው በመሸናነፍ ይጠናቀቃል)፣ የጎል ብልጫ (ከ1 እስከ 5 ጎል ድረስ የትኛው ቡድን ስንት ለስንት እንደሚያሸንፍ)፣ በጨዋታው ላይ ጎል አይቆጠርም፣ በአቻ ይለያያሉ፣.. የሚሉ አማራጮች አሉ። የማእዘን ምት ብዛትም የግምት ውርርዱ አንድ ማራጭ ሆኖ ቀርቧል።

ቅድመ ግምቱ የሰመረለት አሸናፊ የሚያገኘው ገንዘብ የሚሰላው ካስያዘው ገንዘብ ላይ ለመንግሥት ገቢ መሆን የሚገባው 15 በመቶ ተቀንሶ ነው። ተወራራጁ ግለሰብ የተወራረደባቸው ጨዋታዎች የተሰጣቸው “ኦድ” ተባዝቶ ነው። የትልልቅ ሊጎች ጨዋታ በሁሉም አወራራጅ ተቋማት የሚገኝ ሲሆን እምብዛም ታዋቂ ባልሆኑ ቡድኖች መካከል የሚካሄዱ ጨዋታዎች ግን ሁሉም የቤቲንግ ድርጅቶች ላይ ላይገኝ የሚችልበት አጋጣሚ አለ። 

የውርርድ ጨዋታውን የሚሰራ አልጎሪዝም አለ። የዚህ አልጎሪዝም ባለቤቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አይደሉም። በከፍተኛ ባለሙያዎች ብዙ ነገሮች ታይተው የሚሰራ ሂሳብ ነው። አብዛኛዎቹ የቤቲንግ ተቋማት ለተወራራጆቻቸው ትኬት የሚሸጡት ከእነዚህ ድርጅቶች የሚያገኗቸውን መረጃዎች መሰረት በማድረግ ነው። በኢንተርኔት አማካኝነት በየሰዓቱ የሚለዋወጡ መረጃዎችን እያዘመኑ ያጫውታሉ። ድርጅቶቹ ይህንን አገልግሎት ለሚሰጣቸው ተቋም ክፍያ ይፈጽማሉ።

የውርርድ ሱስ

“አንድ ነገር ወይም ድርጊት “ሱስ” ነው የሚባለው 2 ነገሮችን ሲያሟላ ነው” የሚሉት አቶ ጴጥሮስ ሐብታሙ የስነ-ልቦና ህክምና ባለሙያ ናቸው። “በሱስ የተያዘው/ችው ሰው ሱስ ሆኖበታል በተባለው ድርጊት ምክንያት መደበኛ እንቅስቃሴውን ማከናወን ካቃተው እንዲሁም ሱስ አስያዥ የተባለው ነገር/ድርጊት በመጠን እየጨመረ ከመጣ ሰውየው ወይም ሴትየዋ ሱስ ይዟቸዋል ማለት ይቻላል” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ያለ እርሱ መኖር የማንችል የሚመስለን ድርጊቶች ሁሉ ሱስ ሆነውብናል። “ብዙ ጊዜ ሱስ ተብለው የሚጠቀሱት አደንዛዥ እጾች ብቻ ናቸው። ዘመን የወለዳቸው የማይበሉ ወይም የማይጠጡ ነገር ግን ሱስ የሚሆኑ ድርጊቶችም ግን አሉ” ካሉ በኋላ የቴሌቪዥን፣ የማሕበራዊ ሚድያ፣ የወሲባዊ ፊልሞች፣ የቁማር ወይም ውርርድ፣… እና መሰል ሱሶችን እዚህ ምድብ ውስጥ ያስገቧቸዋል።

ወጣቱ በቤቲንግ ጨዋታዎች ሱስ ውስጥ እየገባ መሆኑን በማስታወስ ወጣቶች ራሳቸውን ከእንዲህ ዐይነት አደጋ እንዴት ይጠብቁ ስንል ያቀረብንላቸውን ጥያቄ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተገኘ ኃይለ ቃል መልሰዋል “ሁሉ በአገባብ እና በስርአት ይሁን” እንደ ባለሙያው ገለጻ ማናቸውም ነገሮች በጎ እና በጎ ያልሆነ ገጽታ አላቸው። የነገሮቹ ውጤት በጎ ወይም መጥፎ እንዲሆን የሚያደርገው የሰዎች አጠቃቀም ነው። “ምግብ ጥሩ ቢሆንም ሲበዛ ያሳምማል ወይም ይገድላል። ውሃ ዋና አዝናኝ ቢሆንም አለ እውቀት ከሆነ ሕይወት ያሳጣል። እሳት ጠቃሚ ቢሆንም ከአጠቃቀም ጉድለት ሰውን እና ንብረቱን ያጠፋል። ቤቲንግም አዝናኝ ሊሆን ይችላል፣ አትራፊ ሊሆን ይችላል ነገር ግን እውቀት እና ልክ ያስፈልገዋል” 

ሌላው በባለሙያው የተነሳው የእንዲህ ዐይነት የእድል ጨዋታዎች ጠንቅ የሥራ ባህልን ማጥፋታቸው ነው። “ወጣቶች በረዥሙ የሥራ መንገድ ተጉዘው፣ በላባቸው ገንዘብ ከማግኘት ይልቅ በአጭሩ አቋራጭ መንገድ መክበርን እንደ ጥሩና ትክክለኛ መንገድ እንዲቆጥሩ ያደርጋል። በሎተሪ ወይም በቤቲንግ ብቻ ነገሩን መገደብ የለብንም። ነገሩ ሲያድግ ሂደቱን ትቶ ውጤቱ ላይ ብቻ የማተኮር አባዜ ውስጥ ይከታል። ተማሪ ላይ ስታመጣው ከረዥሙ ንባብ አጭሩ ኩረጃ ሊበረታታ ይችላል። በጣም መስፋፋቱ እና እንደ ትክክለኛ የቢዝነስ አማራጭ ዕየታየ መምጣቱ ከባድ ማኅበረሰባዊ ቀውስ የሚያስከትል ነው” ሲሉ ሐሳባቸውን ደምድመዋል።

አስተያየት