መጋቢት 8 ፣ 2015

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ የሚደርሰው እርዳታ በቂ እንዳልሆነ ታወቀ

City: Addis Ababaፖለቲካማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

ባለፉት 2 ዓመታት ብቻ ድርቅ በተከሰተባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከ6 ሚሊየን በላይ እንስሳት ሲሞቱ 11 ሚልየን ዜጎች የምግብ ዋስትናቸውን አጥተዋል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ የሚደርሰው እርዳታ በቂ እንዳልሆነ ታወቀ
Camera Icon

(ፎቶ፡ የተባበሩት መንግስታት ደርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት /ኦቻ/)

ባለፉት 2 ዓመታት ብቻ ድርቅ በተከሰተባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች 11 ሚሊየን ዜጎች ለከፋ የምግብ እጦት መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አስታወቀ። በድርቁ ሳቢያ  ከ6 ሚሊየን በላይ እንስሳትም መሞታቸው ተጠቁሟል። 

አዲስ ዘይቤ በደቡብ ኢትዮጵያ እንዲሁም በምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች እንዲሁም በኮንሶ፣ ጋሞ፣ ጎፋ ዞኖችና ቡርጂ፣ አማሮ፣ አሌ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎችን ጨምሮ ከ13 በላይ አካባቢዎች ለተከታታይ አምስት ዓመታት በተከሰተው ድርቅ በሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለከፋ የርሃብ አደጋ መጋለጣቸውን ሰምታለች።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ባለሞያ አቶ ሙሉዋስ አጢሶ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት "አሁን ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ የሚፈልጉ ሲሆን የሚደረጉት እርዳታዎች በቂ አይደሉም” ብለዋል። 

የደቡብ ኦሞ ዞን አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ ዱባ ያራ እንደሚሉት ደግሞ በዞኑ በስድስት ወረዳዎች በተከሰተዉ ድርቅ ከ337 ሺህ በላይ ሰዎች ለከፋ ርሃብ አደጋ ሲጋለጡ ከ15 ሺህ በላይ እንስሳት መሞታቸውን እንዲሁም 2 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ለዉሃና ለመኖ እጥረት ተጋልጠዋል። 

በተመሳሳይ በአማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ከ136 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ይሻሉ ተብሏል። አዲስ ዘይቤ ከአመራሮቹ ባገኘችዉ መረጃ በአማሮ ልዩ ወረዳ በ22 ቀበሌዎች ድርቅ ሲከሰት ከ3 ሺህ 500 በላይ እንስሳቶች መሞታቸዉን ለማወቅ ተችሏል። ከ30 ሺህ በላይ እንስሳት ያለቁባት ቡርጂ ከተከሰተዉ ድርቅ አኳያ እየቀረበ የሚገኘዉ እርዳታ አነስተኛ መሆኑን ከስፍራው የሚወጡት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በሌላ በኩል በአሌ፣ ኮንሶ እና ጎፋን ጨምሮ በ13 ልዩ ወረዳዎችና ዞኖች በአጠቃላይ ከ3 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለረሃብ ሲጋለጡ ምክንያቱ ደግሞ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ የሚነሱ ግጭቶችና ለአምስት ዓመታት የተከሰተዉ የዝናብ እጥረት ናቸዉ። በሶማሌ ክልል በተለይም በዳዋ፣ አፍዴር እና ሊበን አካባቢዎች ለተከታታይ ሶስት ዓመታት በተከሰተው የዝናብ አጥረት ሳቢያ ከ3.7 ሚሊየን በላይ ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉ የክልሉ የአደጋና ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ያሲን ተናግረዋል።

ከ300 ሺህ በላይ እንስሳት በድርቁ ምክንያት ሲሞቱ ከ18 ሚሊየን በላይ እንስሳት በመኖና በዉሃ እጥረት አደጋ ላይ መውደቃቸው የታወቀ ሲሆን እየተደረጉ ያሉ እርዳታዎችም በቂ እንዳልሆኑ አዲስ ዘይቤ ሰምታለች። በድርቁ ምክንያት በክልሉ የሚገኙ 250 ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን ከ92 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸዉ መፈናቀላቸዉ ተነግሯል።

የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት "ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ኢትዮጵያ ያሳለፈችው የረሃብ አደጋ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀሟ” መሆኑን ገልጸው በደርግ ወቅት መሬት ላራሹ ቢባልም በዋናነት የሚቆጣጠረዉ መንግስት እንደነበርና አሁንም ተመሳሳይነት ያለዉ የአሰራር ሂደት መኖሩን ተናግረዋል።

የሀገሪቷ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ፈተና ላይ ወድቋል የሚሉት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ተፈጥሮ ይዞት የሚመጣዉን ድርቅ ለመከላከል የዝናብ ዉሃ አጠቃቀማችን ጥበብ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል። በሌላ በኩል ግጭት የሚያስከትለዉን ጦርነት መግታት የሚቻል ቢሆንም ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ጦርነት በሚኖርበት አካባቢ ምርት አለመኖሩንና ምርት ከሌለ ደግሞ ረሃብና በሽታ እንደሚኖር ይገልፃሉ።

የተፈጥሮ ሀብትን መጠቀም የምንችልበት ሥርዓት መፍጠርና ካለፉት ጊዜያት ትምህርት በመዉሰድ "የመሬት ይዞታ ጥያቄ በስርዓቱን ማስተካከልና አምራች መሆን የመፍትሄው ቁልፍ” ስለመሆኑ ፕሮፌሰር አህመድ ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ 24 ሚልየን ሰዎች ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች እንደሚኖሩ እና 11 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ የምግብ ዋስትና እጦት እንደተጋረጠባቸው መረጃዎች ያሳያሉ። 

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በቅርቡ ባወጣዉ ሪፖርት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና በሌሎች ሰባቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዘንደሮ ተከስቷል በተባለዉ ድርቅ ብቻ ከ36.1 ሚሊየን በላይ ሰዎች የረሀብ ሰለባ ሆነዋል ተብሏል።

አስተያየት