ሰኔ 26 ፣ 2014

ብዙዎችን ያሳሳተውና የበላይ ዘለቀ እንደሆነ የታሰበው ፎቶግራፍ

City: Addis Ababaታሪክወቅታዊ ጉዳዮች

ይህንኑ የበላይ ዘለቀ እንደሆነ ታስቦ የሚዘዋወረውን የደጃች ዘውዴ ጥላሁንን ፎቶ ነው ባለሃብቱ አቶ ወርቁ አይተነው ለጠ/ሚ አብይ አህመድ በስጦታ ያበረከቱላቸው

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ብዙዎችን ያሳሳተውና የበላይ ዘለቀ እንደሆነ የታሰበው ፎቶግራፍ
Camera Icon

ፎቶ፡ ዊኪፔዲያ እና “የክቡር ደጃዝማች ዘውዴ ቤተሰቦች” (ከግራ-በተደጋጋሚ የበላይ ዘለቀ ነው ተብሎ የሚሰራጨው ፎቶ)

የኢትዮጵያ አርበኞች ታሪክ በተደጋጋሚ ስማቸው ሳይነሳ አያልፍም ከሚባሉት እንደነ በላይ ዘለቀ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ጃገማ ኬሎ አይነት ጀግኖችና አርበኞች በየጊዜያቸው ከሰሯቸው ገድሎች ጋር ስማቸው ሲወሳና በታሪክ አጋጣሚ በተሰነዱ ምስሎቻቸው ይዘከራሉ። 

እነዚህ ጀግኖች በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከበሩት የአድዋ ድል እና የአርበኞች ቀን ላይ ይወደሳሉ። በእነዚህ እለቶች በታሪክ አጋጣሚ የቀሩ የአርበኞች ምስሎች በማስታወቂያ ሸራዎች፣ በመገናኛ ብዙኃን አውታሮች፣ በአልባሳት እና በተለያዩ መንገዶች የሚታተሙና የሚታሰቡ ቢሆንም በርካቶች ይህ ምስል የእገሌ ነው ብሎ አርበኞቹን ከመለየት ይልቅ በጋራ የሚዘከሩበት ሁኔታ ይስተዋላል።

ከእነዚህ በተደጋጋሚ የሚዘከረው ታሪካቸው በፎቶግራፋቸው ተደግፎ ከሚቀርቡ አርበኞች መካከል አንዱ በላይ ዘለቀ ነው። ሆኖም የዚህን ምስል ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መልዕክት ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ለአዲስ ዘይቤ ደርሶታል። 

ለዝግጅት ክፍላችን የተላከው ይህ የኢ-ሜይል መልዕክት፣ በስፋት የአርበኛ በላይ ዘለቀ እንደሆነ ተደርጎ በተለያዩ ህትመቶች፣ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች እና በተለያዩ የማህበረሰብ አንቂ ግለሰቦች የማህበራዊ ትስስር ገፆች ጥቅም ላይ የሚውለው ምስል የበላይ ዘለቀ እንዳልሆነ በማስረዳት ማስተካከያ እንዲደረግ ይጠይቃል። 

በመልዕክቱ እንደተገለፀው ይህ የበላይ ዘለቀ እንደሆነ የሚታሰበው ፎቶግራፍ የአርበኛ ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ነው። 

የደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ቤተሰቦች በልጃቸው የወይንሸት ዘውዴ አማካኝነት በኢሜይል ለአዲስ ዘይቤ ባደረሱት የፅሁፍ እና የምስል ማስረጃ ላይ እነዚህ በስፋት የበላይ ዘለቀ ተብለው የሚቀርቡት ምስሎች ተያይዘዋል።

የደጃዝማች ዘውዴ ቤተሰቦች በመልዕክታቸው “የፎቶግራፉ በዚህ ደረጃ ሀገር አቀፍ በሆነ መሰራጨት፣ በታላላቅ ሚዲያዎች፣ በልዩ ልዩ የመረጃና የዶክመንተሪ ዘገባዎች፣ የዜና እና ማህበራዊ እንዲሁም ታሪካዊ ትርክቶች ላይ መቅረብ፣ የተከበሩና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በሚያደርጓቸው ንግግሮችና ጽሁፎች ተያይዞ መታተም፣ በወጣቶች ፍላጎት በልብስና በልዩ ልዩ የማስታወሻ ንብረቶች ላይ መታተምና መቅረጽ የሚያስደስተንና የሚያኮራን ቢሆንም ቅሉ፤ የፎቶግራፉን ታሪክና ባለቤት ማንነት አስረግጠን የማስተካከል አስፈላጊነቱን በማመናችን ይኸንን ማረሚያ ደብዳቤ ለማዘጋጀት ተገደናል” ይላሉ። 

ፎቶግራፉ የወላጅ አባታቸው ምስል እንደሆነ የሚናገሩት የደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ልጆች፣ ፎቶግራፉ በአማራ ክልል የመገናኛ ብዙሃን ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ሲተላለፍና ሲቀርብ መመልከታቸውን ገልፀዋል። ከዚህም ባሻገር እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር እና መሰል የማህበራዊ ትስስር ገፆች አማካኝነት በሚፅፉና በርካታ ሰዎች የሚከታተሏቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ገፆች ምስሉን የበላይ ዘለቀ አድርገው በማቅረብ ተደጋጋሚ ስህተቶች ሲሰሩ አስተውለናል ይላሉ። 

ከዚህም ባሻገር በአብዛኛው የአርበኞች ቀን በሚከበርበት ቀን የደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ፎቶ የበላይ ዘለቀ ፎቶግራፍ በሚል ሲቀርብ በመመልከታቸው እንደተገረሙ የሚናገሩት ቤተሰቦቹ፣ ጉዳዩን በለዘብታ ከማየት ባሻገር ሁኔታው በአጋጣሚ አልያም ደግሞ ባለማወቅና በስህተት የተደረገ ነው በሚል፤ እርስ በርስና የፎቶግራፉ ምስል ማን እንደሆነ በእርግጠኝነት ከሚያውቁ በርካታ የቤተሰቡ አባላትና ወዳጆች ጋር እንዲሁም ታሪኩንም ከሚያውቁ ሰዎች ጋር እንደሚነጋገሩበት ገልፀዋል። 

ይሁን እንጂ ጉዳዩን አጥብቀው በመያዝ በጋዜጣ ወይንም በሌላ የዜናና የመረጃ አውታር ለማንሳትና እርማት ለመጠየቅ እምብዛም ጥረት አለማድረጋቸውን ለአዲስ ዘይቤ በላኩት መልዕክት አስፍረዋል።

የእርምት ጥያቄው አሁን ለምን ተነሳ?

በተለያዩ ሀገራት ኑሯቸውን መስርተው የሚገኙት የደጃዝማቹ ቤተሰቦች ከሁለት ዓመት በፊትም ተመሳሳይ እርምት እንዲደረግ በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለፁ ሲሆን አዲስ ዘይቤም መሰል መረጃን መመልከት ችሏል። 

የአርበኛ ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ቤተሰቦች እርማቱ እንዲደረግ ለዋና ዋና የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች ሳያሳውቁ ይህንን ያህል መቆየቱ ስህተት እንደሆነ አምነው ከዚህ ቀደም በማህበራዊ ትስስር ገፆች ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን እንዲሁም ስህተቱን በተደጋጋሚ ከሚሰሩ የቴሌቪዥን የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገው ይስተካከላል የሚል ተስፋ አድርገው ነበር።

የደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ቤተሰቦች እንደነገሩን በስፋት ከሚሰሩት የአደባባይ ስህተቶች በተጨማሪ የአባታቸው የደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ፎቶግራፍ ሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. አቶ ወርቁ አይተነው የተባሉት ባለሀብት ደብረማርቆስ ላይ ያስገነቡትን የምግብ ዘይት ፋብሪካ ሥራ ባስጀመሩበት ማግስት በተደረገ የሽልማትና እውቅና የመስጠት ስነስርዓት ላይ ባለሀብቱ የደጃዝማች ዘውዴን ምስል “ጀግናው በላይ ዘለቀ (አባ ኮስትር) 1904-1937” በሚል ርዕስ ከ1.5 ሜትር በገዘፈ ፍሬምና ሕትመት አሰርተው በስጦታ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሲያበረክቱ በመላው ኢትዮጵያ በቴሌቪዥን ተላልፏል። 

“ይህ ክስተትም ይሄንን ደብዳቤ እንድንጽፍና እርምት እንዲካሄድ እንድንጠይቅ መግፍኤ ሆኖናል” ሲሉ ገልፀዋል። 

የፎቶግራፉ በዚህ ደረጃ ሀገር አቀፍ በሆነ ሁኔታ መሰራጨት የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው ያሉት ቤተሰቦቹ “ቢሆንም የፎቶግራፉን ታሪክና ባለቤት ማንነት አስረግጠን የማስተካከል አስፈላጊነቱን በማመናችን ይህን ማረሚያ ደብዳቤ ለማዘጋጀት ተገደናል” በማለት ተናግረዋል።

በተጨማሪም በ2014 ዓ.ም. በተከበረው የአርበኞች ቀን ክብረ በዓል ላይ የተለመዱት ስህተቶች ከየአቅጣጫው  መደገማቸው በድጋሚ ስለጉዳዩ እንዲወተውቱ እንዳስገደዳቸው ያስረዳሉ። 

ቤተሰቦቹ ይህንን ስህተት ተመልክተው ለጊዜው በመሰላቸውና ተገቢ ነው ብለው ባመኑበት መንገድ ይህንን ስህተት በግለሰብ ደረጃ ለመጀመሪያ ግዜ ካወጡት ሰው ጋር እርማት እንዲደረግ ጥብቅ ውይይት ማካሄዳቸውን ገልፀው ግለሰቡ ሁኔታውን ተገንዝበው የማረሚያ መግለጫ እንደሚሰጡ ቃል ከገቡላቸው በኋላ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ጉዳዩ እርማት ሳይደረግለት ተዳፍኖ ቀርቷል።  

ቤተሰቦቹ ለአዲስ ዘይቤ ባደረሱት መልዕክትም፣ “የምስሉ እውነተኛ ባለቤት አባታችን አርበኛ ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ካብትይመር መሆናቸው መታረሙ ከታሪክ አንፃር አስፈላጊ መሆኑን በማመን ይሄንን ስንልክላችሁ የደጃዝማች በላይ ዘለቀ (አባ ኮስትር) ታሪክ በምንም መልኩ የማይሸረፍ እንደሆነ” በመገንዘብ ነው ሲሉም አሳውቀዋል።

ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ካብትይመር እና የፎቶዎቹ ገጠመኞች

ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ካብትይመር በልጅነት እድሜያቸው በፈተና የተፈተሸ እና የፀና የሀገር ፍቅር ስሜት ነበራቸው። በልጅነት እድሜ ወደ ውትድርና አለም የተቀላቀሉት ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን በ1928 ዓ.ም. የፋሺስት ጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ማይጨው ዘምተው የአርበኝነት ህይወታቸውን መጀመራቸውን ቤተሰቦቻቸው ያደረሱን መረጃ ይገልፃል። 

የጣሊያን ጦር የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አውሮፕላን ባለቤትነቱን በመጠቀም በአለም አቀፍ ደንብ እና ህግጋት የተወገዘውን የመርዝ ጋዝ በመርጨት ጊዜያዊ የበላይነትን ለመቀዳጀት በቅቶ ነበር። በዚህ ጊዜ የጣሊያን ጦር በቴክኖሎጂ ከታገዘው ጥቃቱ ባለፈ ፊት ለፊት ሊመክት እና ሊመልስ የሚችልበት ሁኔታ አለመኖሩን በመረዳት የኢትዮጵያ አርበኞች በአንድ ልብ ሆነው በአንድ አላማ ጸንተው በየትውልድ አካባቢያቸው እና በመረጡት የትግል ስፍራ በተናጠል እና በጥቂት ቁጥር ሆነው ሀይል በማሰባሰብ መታገል ጀመሩ። 

ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁንም ከማይጨው ግንባር ተመልሰው፣ ወራሪ ኃይሉ ተሸንፎ ከኢትዮጵያ እስኪወጣ ድረስ፣ አምስቱን ዓመት ዱር ቤቴ ብለው በቅርብ በሚያውቁት ስፍራ፣ በተለይም በአብዛኛው በምዕራብ ሸዋ እና አካባቢው ከጠላት ጋር በልዩ ልዩ አውደ ውጊያዎች የአርበኝነት ግዳጃቸውን ተወጥተዋል።

በዚህ ተጋድሎ አርበኝነት ዘመናቸው ወቅት ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን በተለይም በአዲስ አለም፣ በጀልዱና በአካባቢው ከጣሊያን ጋር ባደረጓቸው ከባድ ፍልሚያዎች ወቅት፣ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በርካታ ፎቶዎች የመነሳት ዕድል ገጥሟቸው ነበር። 

ልጆቻቸውም እነዚህን የደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን እና የተከበሩ አያሌ ጓዶቻቸውን ፎቶግራፎችና ከእነዚህ ጋር ተያያዥ ታሪኮች፣ ከራሳቸው ከደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን እና ከትግል ጓዶቻቸው አንደበት እየሰሙ እና ፎቶግራፋቸውንም እያዩ ለማደግ ልዩ ዕድል ገጥሟቸዋል።

ይህ ታሪካዊ ገድልና ሀብት በቤተሰቦቻቸውና በወዳጆቻቸው ዘንድ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በህይወት እያሉ ከወዳጆቻቸው ጋር ታግለው በመሰረቱት የአርበኞች ማህበር የታሪክ ማህደር የተመዘገበ ሃቅ እንደሆነ ቤተሰቦቹ ገልፀዋል።

አስተያየት