ሐምሌ 1 ፣ 2013

ሰሞኑን በአፋር በኩል ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የዮኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምን ይላሉ?

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል በመውጣቱ በክልሉ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎች ያለመንግስት ከለላ በትግራይ ክልል መቅረታቸውን ተከትሎ ወላጆች በተደጋጋሚ ቅሬታ በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

Avatar: Haymanot Girmay
Haymanot Girmay

ሰሞኑን በአፋር በኩል ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ የመጡ የዮኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምን ይላሉ?

የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች ጉዳይ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው።

አዲስ ዘይቤ የ‹‹ልጆቻችን ሁኔታ አስጨንቆናል›› ያሉ የተማሪዎቹ ወላጆች በየመንግሥት ተቋማቱ በመሄድ አቤቱታቸውን ባሰሙበት ወቅት ሲያሰሙ ተከታትላ መዘገቧ ይታወቃል። 

በዚህ ሳምንት የተወሰኑ ተማሪዎች ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ አይደር፣ አዲሀቂ እና አሪድ ግቢ ተነስተው ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ ተማሪዎቹ አዲስ አበባን የረገጡት በUN መኪና፣ በእግር እና ትራንስፖርት በመጠቀም በአፋር ክልል በኩል ተጉዘው ነው፡፡

አዲስ ዘይቤ ከተማሪዎቹ መካከል ከተወሰኑት ጋር ቆይታ ከአድርጋለች። ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አንዲት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ግቢ ውስጥ የነበረው የተማሪዎች ምግብ በመኪና ተጭኖ ሲወጣ መመልከቷን ነግራናለች፡፡ እንደ ምንጫችን ገለጻ ዩንቨርሲቲው የምግብ እጥረት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡

በዩንቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ከቀይ መስቀል ማኅበር አማካኝነት ለተማሪዎች ምግብ ለማድረስ መታሰቡን መስማቷን ተናግራለች። ''ከቀይ መስቀል የሚገኘው በቂ ላይሆን ይችላል'' የምትለው ተማሪዋ በዙርያዋ የነበሩ ተማሪዎች በእጃቸው በቂ ገንዘብ እንዳልነበራቸውም ታስታውሳለች።

''ገንዘብ እንኳን ቢኖራቸው እስከ ትግራይ ክልል ድንበር ድረስ ለመውጣት ከቀናት በኋላ ትራንስፖርት ላይኖር ይችላል'' በማለት የነዳጅ እጥረት መኖሩን ከከተማው ከመውጣቷ በፊት የ10 ወይም የ20 ብር የነበረ መንገድ እስከ 80ብር መክፈሏን ትናገራለች። በተመሳሳይ ሌሎቹም ተማሪዎች እንደሚናገሩት ከመቐለ ከተማ ወደ መሆኒ ለመሄድ ቀደም ብሎ ከነበረው ገንዘብ በእጥፍ ለክፍያ እንደሚጠየቅ ገልጸዋል።

በክልሉ የነዳጅ አቅርቦት እየቀነሰ በመምጣቱ የቀሩት ተማሪዎች ከክልሉ ለመውጣት እስከ ትግራይ ክልል ድንበር ለመድረስ የመኪና ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት መኪና ከጓደኛዋ ጋር በመሆን እስከ ሰመራ ድረስ በመሄድ ከዚያ ወደ አዲስአበባ መምጣታቸውን የምትናገረው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ''በተባበሩት መንግሥታት መኪና ባይሆን በቀላሉ ለመጓዝ በተለይ ከክልሉ ለመውጣት ሂደቱ ሊከብደን ይችል ነበር፤ ከመሆኒ እስከ አላማጣ በእግር መጓዝ ይጠበቅብን ነበር'' ትላለች።

ከምግብ፣ ገንዘብ እና ነዳጅ እጥረት በተጨማሪ አንዳንድ የሚያሰጉ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ የመጡ ተማሪዎች ይናገራሉ። ምንም እንኳን ዩኒቨርሲቲው ትምህርት ይቀጥላል ቢልም እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ቢሆንም ተማሪው በተወሰነ መልኩ የጸጥታ ስጋት ስሜት ውስጥ እንደሚገኝ ተማሪዎቹ ገልጸዋል። በአንዳንድ ጊቢዎች ለአጭር ጊዜም ቢሆን በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል በሀሳብ ልዩነት ምክንያት መቃቃር እና ግጭቶች መኖሩን በመጥቀስ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ተማሪዎቹ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ በበለጠ አዲግራት እና አክሱም ስለሚገኙ ተማሪዎች የሰሙት ነገር ባለመኖሩ ስጋት እንደገባቸው ይናገራሉ። በክልሉ የመኪና እንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ቀጥሏል ነገር ግን ወደ መቐለ ከተማ ለመምጣት የትራንስፖርት ገንዘብ ላይኖራቸው እንዲሁም ሁኔታዎች ላይመቻችላቸው ይችላል የሚል ግምታቸውን አጋርተዋል።

በአዲግራት እና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ቤተሰቦች ከመቐለ በበለጠ ከሁለቱ ቦታዎች ምንም ዓይነት መረጃ አለመኖሩ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ደህንነት ለማወቅ ቤተሰቦቻቸው ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት ቢሮዎች በአካል በመቅረብ ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ''ጥያቄያችንን ለማቅረብ ከሳይንስ እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚንስተር ጽ/ቤት ሄደናል፡፡ ይሁን እንጅ እስከአሁን ምንም መፍትሄ የለም'' ያሉት ወ/ሮ እስከዳር ሰንበቱ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ እና 4ኛ ዓመት እየተከታተሉ የነበሩ ልጆች አሏቸው። 

ልጆቻቸውን ካገኙ 15 ቀን መቆጠሩን የሚናገሩት ወ/ሮ እስከዳር ደህንነታቸውን ከልጆቹ አንደበት ካልሰማን በስተቀር በቀይ መስቀል በኩል ብቻ 'ደህና ናቸው' የሚለው መልእክት ፋይዳ አይኖረውም ይላሉ። ምክንያቱ ደግሞ ቀይ መስቀል በቦታው ቢገባ ቢያንስ 'ደህና ነን' የሚል ድምጽ ከተማሪዎቹ እንሰማ ነበር የሚል ነው። አክለውም ዓይናቸው እንባ ተሞልቶ መንግሥት በሰላም ልጆቹን ለቤተሰብ እንዲያስረክብ እና ለትግራይ ህዝብ ልጆቻቸውን አደራ በማለት ተማጽነዋል።

እሮብ ሰኔ 22 ወደ መቐለ የሚደረግ የስልክ አገልግሎት ከመቋረጡ አስቀድሞ ወደ አዲግራት ከተማ ሰኔ 14 የስልክ ግንኙነት መቋረጡን አቶ ተስፋዬ አበበ ይናገራሉ። አቶ ተስፋዬ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሚማረው ልጃቸው ጋር ቢበዛ በ3 እና 4 ቀናት ይገናኙ እንደነበር አስታውሰው በተፈጠረው ሁኔታ የልጃቸውን ድምጽ ከሰሙ 2 ሳምንታት መቆጠሩን ይናገራሉ።

''ልጄ አዲግራት ስላለ ምንም ተስፋ የሚሰጥ ነገር አልሰማሁም'' የሚሉት ወላጅ አባት ይህም የተባበሩት የቀይ መስቀል ማኅበር የሰው ኃይል እጥረት ስላለ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመድረስ ደህንነታቸውን ማረጋገጥ እንዳልቻለ መስማታቸው ነው። እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ከ4 ወራት በፊት ተማሪዎቹ ወደ ክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ሲያመሩ ስጋት ገብቷቸው ለሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ሲሆን አሁንም ሰራዊቱ ከክልሉ ሲወጣ ተማሪዎቹን ይዞ መውጣት እንደነበረበት ነው የሚናገሩት።

''በህይወት ይኑሩ ወይም ይሙቱ አናውቅም ጥቁር መጋረጃ ነው የተጋረደብን ቢያንስ ወደ አቅራቢያ ክልሎች እንዲወጡ ቢደረግ ከእዛ በኋላ እኛ ማምጣት እንችላልን'' ብለዋል አቶ ተስፋዬ።

የአቶ ተስፋዬን ሀሳብ በመጋራት ''ልጆቻችንን መንግሥት ማስወጣት ነበረበት'' የሚሉት አዲግራት ዩኒቨርስቲ የ6ኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ልጅ ያላቸው ወ/ሮ ትነበብ አሰፋ መከላከያ ከመውጣቱ አስቀድሞ ሀገራዊ ምርጫ ሳይካሄድ በፊት ወደ ቤተሰቦቻቸው መሽኘት ነበረባቸው ብለዋል።

የስልክ ግንኙነት በነበረበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው በመከላከያ ተከቦ የትምህርት ሂደቱ እንደሚካሄድ እና በዙሪያቸው የተኩስ ልውውጥ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ልጃቸው እንደነገራቸው የሚያስታውሱት እኒህ እናት እንዲህ ስጋት ባለበት ቦታ ቢያንስ በስልክ ለመገናኘት መንግሥት ማመቻቸት ነበረበት ይላሉ። 

''የትግራይ ህዝብ ልጆቻችንን ይንከባከብ እንደነበር እናውቃለን አሁንም በሁሉም ነገር ከጎናቸው እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን'' በማለት መንግሥትም አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ አሳስበዋል።

አስተያየት