ሰኔ 3 ፣ 2014

በደቡብ ሶማሌ፣ ደቡባዊ ኦሮሚያና የደቡብ ህዝቦች አጎራባች አካባቢዎች ዝናብ የማይጠበቅ ሲሆን በተቀሩት የሀገሪቱ ክፍሎች የጎርፍ አደጋ ስጋት እንደሚኖር ተገለፀ

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

ከሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት በተገኘው መረጃ መሰረት በአብዛኛው የሃገሪቱ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ስለሚኖር ውሃውን ጥቅም ላይ ማዋልና ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

በደቡብ ሶማሌ፣ ደቡባዊ ኦሮሚያና የደቡብ ህዝቦች አጎራባች አካባቢዎች ዝናብ የማይጠበቅ ሲሆን በተቀሩት የሀገሪቱ ክፍሎች የጎርፍ አደጋ ስጋት እንደሚኖር ተገለፀ
Camera Icon

Credit: Getty Images

የበልግ ወቅት ላይ መደበኛ ዝናብ የሚያገኙት ደቡብና ደቡብ ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች ማለትም ደቡብ ሶማሌ፣ በደቡብ ኦሮሚያ እና ደቡብ ህዝቦች ክልል አጎራባች አካባቢዎች የሚገኙት ጉጂ እና ቦረና በዘንድሮው የክረምት ወቅት ዝናብ የማይጠበቅ በመሆኑ በደረቅ የአየር ሁኔታ ውስጥ እንደሚቆዩ የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። 

በኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንበያና ቅድመ-ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ጫሊ ደበሌ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት በድርቅ ሁኔታ ውስጥ የሚቀጥሉት አካባቢዎች ከአጎራባች ስፍራዎች ከሚገኘው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላል።

በዘንድሮው የክረምት ወቅት በመደበኛ ሁኔታ ከሚጠበቀው ጋር ሲነፃፀር በዝናብ ስርጭት እና መጠን ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ የተቋሙ ትንበያ አመላክቷል። በእዚህም መሰረት አዲስ አበባና አካባቢው፣ ትግራይ ክልል፣ አማራ ክልል፣ አፋር ክልል፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እና ሰሜናዊ የሶማሌ ክልል መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚጠበቅባቸው መሆኑንም ዳይሬክተሯ ገልፀዋል። 

መካከለኛው ሶማሌ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ኦሮሚያ፣ መካከለኛው ኢትዮጵያ እንዲሁም ደቡብ ህዝቦች ደግሞ ወደ መደበኛ የተጠጋ የዝናብ ምጣኔ ይኖራቸዋል። መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚያገኙት አካባቢዎችም በተለይ በሐምሌ እና ነሐሴ ወራት ከፍተኛ ዝናብ እንደሚኖራቸው የትንበያው ውጤት አሳይቷል።     

ይሁን እንጂ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ በሚጠበቁ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ያልታሰበ የዝናብ መጠን ሊኖር እንደሚችል የትንበያና ቅድመ-ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተሯ ጫሊ ደበሌ ገልጸዋል። የትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ ምስራቅና መካከለኛ ክፍል በላይኛው የውሃ አካል ላይ ከመደበኛ በላይ ሙቀት እየተስተዋለ በመሆኑ በዘንድሮው ክረምት ከፍተኛ ዝናብ እንዲጠበቅ የሚያደርግ የአየር ሁኔታ መኖሩንም ጭምር አስረድተዋል።

ዝናብ በሚያገኙት አካባቢዎች ላይ ድንገተኛ ከባድ ዝናብም የሚጠበቅ ሲሆን ቅፅበታዊ የጎርፍ አደጋ እንዲሁም የአፈር መንሸራተት ሊከሰትባቸው የሚችሉ አካባቢዎችም ይኖራሉ። “በተለይም በከባድ ዝናብ ወቅት አፈር እርጥበቱን መሳብ የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠርና ውሃው በመሬት አካል ላይ የመንከባለል እድል ሲኖረው ደራሽ ወይም ቅፅበታዊ የጎርፍ አደጋ እንደሚያስከትል ይጠበቃል። በተጨማሪም አነስተኛም ሆኑ ትላልቅ ወንዞች እንዲሁም ግድቦችም ሊሞሉ ይችላሉ” ሲሉ ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።

ረቡዕ ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በጣለው ከባድ ዝናብ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኝ ትምህርት ቤት የወጣ አንድ ተማሪ በጎርፍ መወሰዱ ተሰምቷል። ይህን ክስተት ያስታወሱት ዳይሬክተሯ ገና በክረምቱ ጅማሬ ይሄን መስማት አሳዛኝ ቢሆንም ቅፅበታዊ ጎርፍ ከመከሰቱ በፊት ጥንቃቄ ማድረግ የግድ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

“በየሰፈሩ የሚገኙ ትናንሽ የሚመስሉ ወንዞች መሙላት፣ የውሃ መፍሰሻ ትቦዎች አለመጠረግ እንዲሁም በግንባታ ሰበብ በየአካባቢው የሚገለበጡ የግንባታ ግብዓቶች የውሃ ፍሰት አቅጣጫን ማስቀየስ እና ወደ መኖሪያ ቤት እንዲገባ የማድረግ እድል ስላላቸው ሰዎች ላይ ጉዳት እንዲያደርስ ሊያደርጉ ስለሚችሉ ሁሉም አካባቢውን በትኩረት መጠበቅ ይኖርበታል” ብለዋል በተቋሙ የትንበያና ቅድመ-ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተሯ ጫሊ ደበሌ።

ትንበያውን መሰረት በማድረግ ይሞላሉ ተብለው የታሰቡ የውሃ አካላት የሚገኙ ሲሆን ጣና ሀይቅ፣ ባሮ አኮቦ፣ አባይ፣ የላይኛው አዋሽ ወንዞችና በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ ግድቦች ላይ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲኖር መረጃዎች ተሰራጭተው በተቋማት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ተብሏል። 

ከሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት በተገኘው መረጃ መሰረት ሊጠናከሩ እንደሚችሉ ከሚጠበቁ የደመና ክምችቶች ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ እንዲሁም የአባይ ተፋሰስ ምዕራባዊ አጋማሽ ላይ ከከፍተኛ እስከ በጣም ከፍተኛ የእርጠበት መጠን የሚኖር ሲሆን ውሃውን ጥቅም ላይ ማዋልና ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ከሰኔ ወር ጀምሮ እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ የዝናብ ወቅት በመሆኑ በእዚህ ወቅት የዝናብ መጠንና ስርጭት ይጨምራል ያሉት የትንበያና ቅድመ-ማስጠንቀቅ ዳይሬክተሯ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ወቅት ነው ብለዋል።

በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል የክረምት ወቅቱ የሚገባበት ወቅት ላይ ብዙ ልዩነት የሌለ ሲሆን የክረምት ወቅት መውጫ ላይ ግን የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ለተወሰኑ ቀናት ዘግይቶ የመውጣት ሁኔታ እንደሚኖረው በተቋሙ ትንበያ ተመላክቷል።

በግብርና ዘርፉም ቢሆን እንደ ማዳበሪያ እና ዘር የመሳሰሉ ግብዓቶችን ከመጠቀም በፊት የአየር ሁኔታውን ማገናዘብ አስፈላጊ ነው፤ ይህ ታሳቢ ካልተደረገ በዝናብ ታጥበው ከጥቅም ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ከውሃ መጠን መብዛት ጋር ተያይዞ የአረም መብዛት እና የሰብል በሽታዎች እንዳይስፋፉ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ተቋሙ አሳስቧል።