መጋቢት 6 ፣ 2015

የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ከመንግስት ተቋማት መረጃ ማግኘት ፈተና ሆኖብናል አሉ

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

የዜጎችን የመረጃ ነፃነት መብት ለማረጋገጥ ከ14 ዓመት በፊት በነጋሪት ጋዜጣ የወጣው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 የጋዜጠኞች የመረጃ ማግኘትን መብት አላስከበረም ተባለ

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ከመንግስት ተቋማት መረጃ ማግኘት ፈተና ሆኖብናል አሉ

በክልል ደረጃ በተለያዬ የሚዲያ ተቋማት ተቀጥረው የሚሰሩ ጋዜጠኞች ዘገባዎችን ለማስራት መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት መቸገራቸውን ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል። በአሁኑ ሰዓት ርዕሰ ጉዳይ መርጦ የዜና ዘገባ ለመስራት ለተንቀሳቀሰ ጋዜጠኛ ከመንግስት ተቋማት መረጃን ፈልጎ ከማግኘት የበለጠ ፈተና አይገጥመውም የሚሉት የሚዲያ ባለሙያዎቹ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 መረጃ የማግኘት መብታቸውን እንዳላስጠበቀላቸው ይናገራሉ።

በአንድ የግል ሚዲያ ተቋም የድሬደዋ ቅርንጫፍ ሪፖርተር ሆኖ እየሰራ ያለው ጋዜጠኛ አለሙ አስፋው፣ ብዙ ጊዜ ዘገባ ለመስራት አቅዶ ወደ አንድ ተቋም ለመሄድ ሲነሳ መረጃ ለማግኘት እንደሚቸገር ይገልጻል።

በፋና ብሮድካስት ኮርፕሬት ስር ከሚተዳደሩ የክልል ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች መካከል የአንደኛው ጣቢያ ኃላፊ የሆኑትና ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው፣ “የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በቀጥታ ስልክ የሬድዮ ፕሮግራም ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ምላሽ እንዲሰጡ ቀጠሮ ተይዞላቸው በተደጋጋሚ በመቅረታቸው ፕሮግራሞችን እስከማጠፍ ደርሰናል” በማለት ይናገራሉ።

ከፌደራል መንግስቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ይልቅ ጋዜጠኞች መረጃ ለማግኘት የሚገጥማቸው እንግልትና ፈተና በክልል ከተሞች ላይ ይብሳል የሚሉት የሬድዮ ጣቢያ ኃላፊው፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጁ ተግባራዊ አለመሆኑ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል ብለዋል።

መንግስት የመረጃ ነፃነት አዋጅን “ለይስሙላ” አወጣው እንጂ ተግባራዊ ሆኖ ተፈፃሚ እንዲሆን ሙሉ ፍላጎት የሌለው መሆኑን የሚገልፀው በሶማልኛ ቋንቋ በዲጂታል ሚዲያ የምርመራ ዘገባዎችን በማውጣት የሚታወቀው ሀስ አፕቲዶን፣ “በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን እና በአፋር ክልል አዋሳኝ ቀበሌዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን ሆን ብሎ ለመደበቅና ምንም እንዳልተፈጠረ አደባብሶ ለማለፍ የሚሞከርብት አካሄድ እንዲሁም አሁን በኢትዮጵያ ደቡብና በደቡብ ምስራቅ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመደበቅ የሚደረገው ሙከራ የመረጃ ነጻነት አለመኖሩን አመላካች ነው” ሲል ሃሳቡን ይገልፃል።

በተለያዩ የመንግስተ ተቋማት በህዝብ ግንኙነት ባለሞያነትና በኃላፊነት ደረጃ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ያገለገሉት አቶ ጎሽዬ መዘክር በበኩላቸው ከቅርብ አመታት ወዲህ ተቋማት በመረጃና ህዝብ ግንኙነት የስራ ክፍሎች በዳይሬክቶሬት ደረጃ ባለሙያዎች እንዲመደብላቸው መደረጉ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎችና መረጃ ምንጭነት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን ይገልፃሉ። ይሁን እንጂ የሚዲያ ተቋማት ግን መረጃን በቀላሉ ለማግኘት የሚያጋጥማቸውን ችግር መቅረፍ አለመቻሉን ይጠቅሳሉ።

በየተቋማቱ ያለውን መረጃ ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ የሚዲያ ባለሙያዎች ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት የሚገጥማቸው ተግዳሮት ቀላል አለመሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የችግሩ ዋነኛ መንስዔ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በትክክል ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ እንደሆነ ያምናሉ። 

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስት ላይ በግልጽ እንደተመላከተው የመንግሰት አሰራር ለህዝብ ግልፅና ተጠያቂነት የሚኖርበት መሆን አለበት። መንግስት አሰራሩን ለዜጎች ግልፅ ከሚያደርግባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ደግሞ የመረጃ ተደራሽነት ሲሆን ይህንንም ለመተግበር ያመች ዘንድ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ፀድቆ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምም እንዲያስተገብር ስልጣን ተሰጥቶቷል።

በአዋጁ ላይ ዜጎች በመንግስት እጅ የሚገኙ መረጃዎችን የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት የተሰጣቸው ሆኖ ሳለ የመገናኛ ባለሙያዎች መረጃን በቀላሉ ለማግኘት መቸገራቸውን አስመልክቶ ለጉዳዬ ምላሽ ይሰጡን ዘንድ አዲስ ዘይቤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘውዱ ወንድምን አነጋግራለች።

በአብዛኛው ከላይ የሚዲያ ባለሞያዎቹ ባነሱት ሃሳብ እንደሚስማሙ የሚናገሩት አቶ ዘውዱ የሚዲያ ባለሞያዎችም ሆነ ዜጎች በማንኛው ጊዜ የሚፈልጉትን መረጃ የመጠየቅና የማግኘት መብት እንዳላቸው ተቋማቱም በአዋጁ ከተከለከሉት ውጪ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገልጻሉ።

ከዚህ ቀደም በሚዲያ ባለሞያዎችና በጋዜጠኞች ተደጋግመው ሲነሱ የነበሩ ችግሮች ለመቅረፍ በአዋጁ ላይ ከአራት ዓመት በፊት የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች መሰራቸውን አስታውሰው በቀጣይ አዋጁ ተግባራዊ ለማድረግ ስራዎች በጋራ መሰራት እንዳላቸውም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የመገናኛ ብዙኃንና መረጃ ነጻነት አዋጁ በተጠናከረ ሁኔታ አለመተግበርና የመንግስት ኃላፊዎችም መረጃ በሚጠየቁበት ጊዜ መረጃ ላለመስጠት ሆን ብለው በሚፈጥሯቸው አድካሚ ውጣ ውረድና እንግልት ሳቢያ ወቅታዊና ሚዛናዊ ዘገባዎችን ለመስራት እጅግ አዳጋች እየሆነባቸው መምጣቱ የሚዲያ ባለሙያዎቹ ጥያቄ ነው። 

አስተያየት