የትግራይ ተወላጆች ብሄርን መሰረት ላደረገ እስር ተጋልጠዋል?

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታኅዳር 6 ፣ 2014
City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች
የትግራይ ተወላጆች ብሄርን መሰረት ላደረገ እስር ተጋልጠዋል?

መጽናናት ኢሳያስ የ37 ዓመት ውጣት ስትሆን  ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነዉ። ወላጆቿ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ትናገራለች። ወላጅ እናቷ ከአመታት በፊት ከአዲስ አበባ አቅራቢያ በሚገኝ ገዳም መኖር መጀመራቸውን በማንሳት ባሳለፍነው ሳምንት “ጥቆማ ደርሶን ነው” በሚል ፖሊሶች ይዘዋቸው እንደነበር ትናገራለች።

“እናትሽ በቁጥጥር ስር ውላለች ተብሎ ከጣቢያ ሲደወልልኝ አላመንኩም ነበር የ65 ዓመት አዛውንት ምንድነው የሚጠቆምባት ብዬ ግራ ገባኝ፣ ነገር ግን ትግሬ መሆኗ ነው ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባት የሚል ነገርን ከገዳሙ ነዋሪዎች ሰማሁ፣ ከዛ ጣቢያው ሄደን ጉዳዩን ስናጣራ ገዳሙ ውስጥ ህገወጥ መሳርያ በመገኘቱ እናቴን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ተነገረኝ” ስትል ከሶስት ቀን እስር በኋላ እናቷ በዋስ የተፈቱበትን አጋጣሚ ታስረዳለች። 

ተስፉ ክብረዓለም ሁለት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለገው ጓደኞቹ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት በተመሳሳይ ቀን ጥቅምት 24፤ 2014 ዓ.ም መሆኑን ይናገራል።  “ሁለቱም የትግራይ ተወላጆች ከመሆናቸው ውጪ በወቅታዊው የፖለቲካ ቀውስ ላይ ምንም አይነት ተሳትፎ የላቸዉም” የሚለዉ ተስፉ ሲታሰሩ ሁለቱም በየግል መኖርያ ቤታቸው እንደነበሩ እና አንደኛው ጠዋት ወደ ጣቢያ ሲወሰድ ሁለተኛው ከሰዓት ላይ ነው የተወሰደው ይላል። 

“የጓደኞቼን መታሰር ከቤተሰቦቻቸው እንደሰማሁ ወደ ተጠቆምኩት ፖሊስ ጣቢያ ብሄድም ‘በምትፈልገው ስም እዚህ ጣቢያ የተያዙ ግለሰቦች የሉም’ በሚል ምላሽ ስጉላላ ቆይቼ ስላሉበት ሁኔታ ማወቅ የቻልኩት ከተያዙ ከአራት ቀን በኋላ ነው፣ እንዲቆዩ የተደረጉትም ጣቢያ ውስጥ ሳይሆን በጊዜያዊነት የተዘጋጀ ነው በተባለ መሿለኪያ አካባቢ ባለ ቦታ ነው” ሲልም ያስረዳል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ አዲስ ዘይቤ የሰማቻቸውን አይነት ታሪኮች እና ስጋቶች በተለያዩ ቦታዎች ሲደመጡ ይስተዋላል። በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም ሆነ በተለያዩ መንገዶች መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉ የትግራይ ተወላጆች ድንገት በማንነቴ ብታሰርስ በሚል ሥጋት እንቅስቃሴያቸውን ሳይቀር እንደገደቡ ይገልጻሉ።

ከነዚህ መካከል አንዱ የሆነው ሰሙ ባይጠቀሰ የፈለገ ወጣት በመዲናዋ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ሰዎች እየተያዙ ነው የሚሉ መረጃዎች መናፈስ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በስጋት ስራ አቁሞ ከመኖሪያ ቤቱ መውጣት እንዳቆመ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

ከማክሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ‘በአገር ህልውናና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል’ በሚል የታወጀው አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 “ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ተብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ማድረግ” የሚል ህግ መደንገጉ የሚታወስ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማፅደቅ ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የተሰበሰበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አዋጁን ተንተርሶ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሳይኖር ዜጎችን በማሰርና በማንገላታት የመብት ጥሰት እንዳይፈጸም ማሳሰቡም ይታወቃል። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ቦርድ መቋቋሙን በመጥቀስም ይህን መሰል አላግባብ ስራ እንዳይሰራ ክትትል እንደሚያደርግ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞቴዮስ (ዶ/ር) ገልጸው ነበር።

ይሁን እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከፀደቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ዜጎች እስር እንዳሳሰበው ሲጠቅስ “አያያዙ ማንነትን/ብሔርን  መሠረት ያደረገ  በሚመስል መልኩ መከናወኑን፣ በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች የቤተሰብ ጥየቃ፣ ልብስና ስንቅ ማቀበል መከልከሉ እንዲሁም እስሩ ህጻናት ልጆች ያሏቸውን እናቶች እና አረጋዊያንን ጭምር ያካተተ መሆኑ አረጋግጬያለሁ” ብሏል።

በተመሳሳይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አርብ ህዳር 03 2014  ባወጣው ሪፖርት በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ተወላጆችን ትኩረት ያደረገ እስር እየተካሄደ መሆኑን ሲገልፅ በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ ያነጣጠረ እስር እየተካሄደ መሆኑን እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኃላ እስሩ እየተባባሰ መሆኑን መጥቀሱ ይታወሳል።

በሪፖርቱ ሰዎች ከቤት ወደ ቤት በሚደረግ አሰሳ በቁጥጥር ስር ይውላሉ ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች በመሙላታቸው በቁጥጥር ስር የዋሉ የመንግስት ሰራተኞች፣ የኦርቶዶክስ ቄስ እና የህግ ጠበቃን ጨምሮ ሌሎች እስረኞች በወጣቶች ማእከላት እና ሌሎች መደበኛ ባልሆኑ የማቆያ ጣቢያዎች መታሰራቸውን አረጋግጫለሁ ማለቱም ይታወቃል።

በመሆኑም በነዚህ ጉዳዮች አተገባበር ዙርያ ቅሬታዎችን የተቀበለችው አዲስ ዘይቤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታን ስለጉዳዩ ጠይቃ “በቅንጅት እየተሰራ በሚገኘው ደህንነትን የማስጠበቅ ስራ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እየዋሉ ያሉት ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ሳይሆን በተጠረጠሩበት ወንጀል ብቻ ሲሆን ከተጣራ በኋላ ነጻ ሆነው ከተገኙ በአግባቡ ይለቀቃሉ” ሲሉ የሚናፈሰው ወሬ ሀሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

አክለውም እስካሁን ድረስ የተያዙት ግለሰቦች አሸባሪውን ቡድን በመደገፍ፣ ሀሰተኛ መታወቂያ ይዘው በመንቀሳቀስ፣ መረጃ አሳልፈው በመስጠት፣ ገንዘብ በማዘዋወር እና በመሳሰሉ ወንጀሎች በመጠርጠር ነው በማለት “እንደሚባለው ብሄርን መሰረት በማድረግ እያሰርን አለመሆኑን ለማየት መንግሥት መዋቅር ውስጥ ሳይቀር ያለስጋት እየተንቀሳቀሱ ያሉትን የትግራይ ብሔር ተወላጆች ማየት ይቻላል” ብለዋል።

በሌላ በኩል እነዚህ የተጠቀሱት ተጠርጣሪዎች የሚገኙበትን አያያዝ በተመለከተ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የቅርብ ሰዎቻቸው ያሉበትን ሁኔታ እንዲያውቁ እየተደረገ ስላለበት ሁኔታ የቀረበውን ቅሬታ አስመልክቶ የፌደራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄይላን ኢብራሂምን እንዳነጋገርናቸው በተመሳሳይ ማንነት ላይ የተመረኮዘ እስር የሚለውን ስሞታ ውድቅ በማድረግ በቁጥጥር ስር የሚገኙ ተጠርጣሪዎችም በቤተሰብ እንዳይጠይቁ አልተከለከለም በማለት “ህጋዊ እና አግባብ በሆነ መልኩ እየሰራን ስለምንገኝ ተጠርጣሪዎችን የምንሸሸግበት ምንም ምክንያት የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ በበኩላቸውም  “ሀገርን ለማዳን እየተወሰደ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም የብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠረ አይደለም፣ ከዛም ባለፈ አያያዘ ፍጹም አግባብነት ያለው ሲሆን ተጠርጣሪዎች ንጽህናቸው ሲረጋገጥ ከይቅርታ ጋር ነው የሚለቀቁት” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዛሬው ዕለት ህዳር 04፣ 2014 መግለጫ የሰጡት የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ “የአሸባሪውን ህወሃት አጀንዳ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በማጥራት ሂደት ንጹኃን ሰለባ እንዳይሆኑ በጥንቃቄ እየተሰራ ነው” ማለታቸው ተገልጿል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist works at Addis Zeybe as a reporter while exploring her passion for storytelling and content creation.