ሚያዝያ 9 ፣ 2015

5 ኢትዮጵያዊያን በሱዳን ካርቱም በተነሳው ግጭት መገደላቸው ተገለፀ

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮች

ሦስተኛ ቀኑን በያዘው የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ሃይል እና ብሔራዊ ጦር ውጊያ ከሞቱት በተጨማሪ ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን መቁሰላቸው ታውቋል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

5 ኢትዮጵያዊያን በሱዳን ካርቱም በተነሳው ግጭት መገደላቸው ተገለፀ

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ሶስተኛ ቀኑን በያዘው ግጭት ሳቢያ አምስት ኢትዮጵያውያን መሞታቸው እና ቢያንስ ዘጠኝ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን መቁሰላቸው ታወቀ። 

በመሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ በሚመራው የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና በጀነራል አብዱልፈታል አልቡርሃን በሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ጦር መካከል በካርቱም እያካሄዱት ባለው ውጊያ ሳቢያ ነው የአምስት ኢትዮጵያዊያን ሞት የተሰማው። 

የካርቱም ነዋሪ የሆኑት የአዲስ ዘይቤ ምንጮች እንደገለፁት ጦርነቱ እየተስፋፋና በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ መሆኑ ጉዳቱ እንዲጨምር አድርጓል። ኢትዮጵያዊያን በብዛት በሚኖሩበት እና "ዴም" ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተደረገ ጦርነት ሦስት ኢትዮጵያን መሞታቸውን የገለጹት የመረጃ ምንጩ አደጋው የደረሰው ጠዋት ቢሆንም የሟቾች ቀብር አለመፈጸሙን ገልጸው፣ የሟቾች አስክሬን በአካባቢው አል-ጃውዳ ሆስፒታል እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዴም በርእሰ ከተማዋ ካርቱም ብዙ ኢትዮጵያዊን የሚኖሩበት አካባቢ ሲሆን የአካባቢው የቤት አሰራር ለአደጋ የተጋለጠ እንደሆነም አስተያየት ሰጪዎቹ ይገልጻሉ። በሌላ የከተማው ክፍል በደረሰ ጥቃት  ሁለት ኢትዮጵያን ባል እና ሚስት መገደላቸው ታውቋል።

ከሞቱትና ማንነታቸው ከታወቁት አምስት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ኤርትራዊ ይሁኑ ኢትዮጵያዊ ማወቅ ያልተቻለ ሰዎች መገደላቸውን የተናገሩት የአዲስ ዘይቤ ምንጮች በተጨማሪ ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

በጦርነቱ የበላይነት ያለው ሃይል ባለመኖሩ እየተደረጉ ያሉ ተደጋጋሚ ውጊያዎች አውዳሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ይገልጻሉ።

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በቂ ድጋፍ እየተደረገ አለመሆኑን የሚናገሩት ኢትዮጵያዊያን በመብራት መጥፋት እና በብዙ ቦታዎች የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ያለው የሟቾች እና ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ስጋታቸውን ይናገራሉ

አስተያየት