ጥር 27 ፣ 2014

ለልጄ: በእርግዝና እና በልጅ አስተዳደግ ዙሪያ መረጃ ለመስጠት ያለመ ጀማሪ ተቋም

City: Addis Ababaጤና

እርግዝና እና የልጅ አስተዳደግ ላይ የተሟላ መረጃ የሚሰጥ የመረጃ ማዕከል የሆነው ይህ አገልግሎት ከእርግዝና በፊት አንስቶ በወሊድ ወቅትና ልጆች አስራዎቹ እድሜ ላይ እስኪደርሱ ያለዉን ጊዜ በተመለከተ መረጃ ይሰጣል።

Avatar: Mahlet Yared
ማህሌት ያሬድ

Mahlet is an intern at Addis Zeybe who explore her passion for storytelling

ለልጄ: በእርግዝና እና በልጅ አስተዳደግ ዙሪያ መረጃ ለመስጠት ያለመ ጀማሪ ተቋም
Camera Icon

ፎቶ፡ ለልጄ ድረገጽ

አዲስ አሰፋ የ35 ዓመት ወጣት የሥራ ፈጠራ ባለቤት ነው። የኮምፒዩተር ሳይንስ ምሩቅ ነው የህክምናን ትምህርትም ተከታትሏል። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በርካታ ሥልጠናዎች እንደወሰደ የሚናገረው አዲስ በሥልጠና እና ማማከር፣ እንዲሁም በጽሑፍ ሥራ ላይም ተሰማርቷል።

በቅርቡ በእርግዝና እና የልጆች አስተዳደግ ላይ በበይነመረብ መረጃዎችን የሚሰጥ የመረጃ ማዕከል አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ተጠቃሚዎች ወደ ድረ ገፁ በመግባት በኢሜል አድራሻቸዉ በመመዝገብ በእርግዝና ቅድመ-ወሊድ እና ድህረ-ወሊድ በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ የተለያዩ መረጃዎችን ያቀርባል። ለልጄ በኦርቢት የፈጠራ ማዕከል የሥልጠና፣ የማማከር እና የመነሻ የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርግ ተቋም ታግዞ ወደስራ ከገባ ሶስት ወራትን አስቆጥሮዋል።

እርግዝና እና የልጅ አስተዳደግ ላይ የተሟላ መረጃ የሚሰጥ የመረጃ ማዕከል የሆነው ይህ አገልግሎት ከእርግዝና በፊት አንስቶ በወሊድ ወቅትና ልጆች አስራዎቹ እድሜ ላይ እስኪደርሱ ያለዉን ጊዜ በተመለከተ መረጃ ይሰጣል ።

“የለልጄ ሐሳብ የመጣው ከራሴ የአባትነት ጉዞ ነው” የሚለው የሃሳቡ መስራች  ለልጄ’ን ሃሳብ የጀመርበትን ሁኔታ ሲያስረዳ ባለቤቱ የመጀመሪያ ልጃችውን ባረገዘችበት ጊዜ ኦንላይን  እርግዝናን የተመለከቱ መረጃዎችን ይፈልግ እንደነበርና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንዲህ ያለ ለህብረተሰቡ የሚጠቅም ነገር በራሳችን ቋንቋ ለአገራችን ወላጆች ቢኖር የሚል ሀሳብ እንደመጣለት ይናገራል። 

“ኢንተርኔት ላይ መረጃዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማግኘት ቢቻልም የእኛን ባሕል ከግምት አያስገባም በራሳችን አውድ የተዘጋጀ በራሳችን ቋንቋ የቀረበ፣ ደረጃውን የጠበቀ ህብረተሰቡ በቀላሉ የሚረዳው ነገር ቢኖር ከሚል ሐሳብ ነው የተነሣሁት” 

ከወላጅ እና አሳዳጊዎች ጋር ልጆችን አብረን ኮትኩተን ለማሳደግ ነው የተነሣነው’’ የሚለው አዲስ ማንኛውም ሰው ድረ ገጻችን ላይ LeLije.com ተመዝግቦ በልጁ እድሜ ወይም በእርግዝና ደረጃዉ መሠረት መረጃ በቋሚነት ማግኘት ይችላል ሲል ነግሮናል። አሁን ላይ በተቋሙ ይዘቶችን የሚያዘጋጁ እና የሚገመግሙ ሃኪሞች፣ የቢዝነስ እና የቴክኖሎጂ ባለሞያዎች የተሳተፉበት የይዘት ዝግጀት ስራ እየተከናወነ ሲሆን በአጭር ጊዜ ዉስጥ በድረገጹ ላይ ተጭነዉ ለመረጃ ፈላጊዎች ተደራሽ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል።    

በተጨማሪም በስልክ እና በቴሌግራም አማካኝነት መመዝገብ የሚቻልበት ዘዴ የተቀመጠ ሲሆን  አዲስ እንደሚለዉ ማንኛውም ሰው ድረ ገጻቸዉ ወይም ማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ላይ LeLijeInc በሚል አድራሻ መረጃዎችና መልእክቶችን እሰራጩ ይገኛል። አገልግሎቱን ለማግኘት ምንም አይነት ክፍያ እንደማያስከፍሉም መስራቹ ተናግረዋል። 

በመጨረሻም ስለ ወደፊት እቅዳቸዉ የጠየቅነው አዲስ አሁን ላይ አማካሪ ቦርድ በማዋቀር ላይ መሆናቸው እና የአማካሪ ቦርዱ ከሕክምና፣ ከሥነ ልቦና፣ ከአመጋገብ፣ ከትምህርት፣ ከቢዝነስ እና ከመሳሰሉት አኳያ የለልጄን ይዘት እና አካሄድ እየቃኘ ምክረ ሐሳብ የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል ። 

“ለልጄን በሚገባ ማዘመን እና ተደራሽነቱን ማስፋት እንፈልጋለን የሞባይል መተግበሪያም በቅርቡም ይኖረናል” ይዘቶችን በዓይነትም በብዛትም በማዘጋጀት ከጽሑፎች በተጨማሪ በድምጽና በቪዲዮዎች በታገዘ መልኩ አሳድገን የምናቀርብ ሲሆን በተጨማሪም እናቶች እና አባቶች እርስ በርስ ሐሳብ የሚለዋወጡበት የውይይት ፎረም እንዲኖረን ለማድረግ እየሰራን ነው” ብሏል።

በመጨረሻም ለወላጆች እና ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚሆኑ ልዩ ልዩ የሕትመት ውጤቶችን ማውጣት፣ ለልጆች ተስማሚ የሆኑ ነገሮችን በራሳችን እና ከሌሎች ጋር በአጋርነት ማቅረብም የወደፊት እቅዳችን አካል ነው ብለው ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።

ከወሊድ ጋር በተገናኘ የሚሞቱ እናቶች ቁጥር እንዲቀንስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ይነገራል። በተመድ የምዕተአመቱ የልማት ግብ በተለይ በአፍሪቃ ሃገራት የእናቶችን ሞት በ75 በመቶ ለመቀነስ ታልሞ፤ ኢትዮጵያም ያንን ለማሳካት እየሠራች መሆኑን ታመለክታለች። ዛሬም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ  ከወሊድ ጋር በተገናኘ በዓመት 12 ሺህ እናቶች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ባለሙያዎች ይናገራሉ። 

የአናቶች ሞትን ለመቀነስ መሰራት ካለባቸዉ ስራዎች አንዱ የድህረ ወሊድ የምክርና የህክምና ክትትል ማድረግ መሆኑ ይጠቀሳል። በህክምና ተቋማት ከሚሰጡ የምክርና የመረጃ አገልግሎቶች ባለፈ በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች እርግዝናን የተመለከቱ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረዉ እሙን ነዉ።