ግንቦት 8 ፣ 2014

የህፃናት የዱቄት ወተት እጥረት ያስከተለው አሳሳቢ ችግር

City: Addis Ababaጤናወቅታዊ ጉዳዮች

የምግብ እና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ማህበረሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

የህፃናት የዱቄት ወተት እጥረት ያስከተለው አሳሳቢ ችግር
Camera Icon

Credit: crowdvoice.org

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የህፃናት ፎርሙላ ዱቄት ወተት ከገበያ ላይ ከመጥፋቱም በላይ የሚሸጥበት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ መነጋገርያ ሆኗል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የእነዚህ የቆርቆሮ ወተቶች ልጆቻቸው ጥገኛ የሆኑባቸው ወላጆችን በፅኑ እያስጨነቀ ይገኛል። 

በአዲስ አበባ የሚገኙ አንዳንድ የፎርሙላ ዱቄት ወተት አከፋፋይ ድርጅቶች እና ቸርቻሪዎች የተፈጠረው የወተት እጥረት በአለምዓቀፍ ደረጃ የተከሰተ መሆኑን በመጥቀስ ለደንበኞቻቸው በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ እየተቸገሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እንደሚታወቀው የፎርሙላ ዱቄት ወተት ፍላጎት እና አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል፣ ይህ ወተት የእናት ጡት ወተትን ሙሉ ለሙሉ ባይተካም በሁለተኛነት የሚመረጥ የተሟላ የህፃናት ምግብ ነው። 

ከጨቅላ ህፃናት በተጨማሪ ምግብ የጀመሩ ልጆችም በልዩ ልዩ ችግሮች እና ምክንያቶች እነዚህን የፎርሙላ ዱቄት ወተቶች እንዲጠቀሙ ይመከራሉ። ከነዚህም መካከል የተለያዩ የምግብ አለርጂዎች፣ የጨጓራ መቆጣት፣ እና ሌሎች የጤና እክሎች ያጋጠማቸው ህፃናት ከምግባቸው ጎን ለጎን እነዚህን ወተቶች እንዲጠቀሙ ይደረጋል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በወተት አምራች ድርጅቶች ውስጥ ባጋጠመ የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር እና የዋጋ ግሽበት ሳቢያ ይህ የዱቄት ወተት በበቂ ሁኔታ እየተመረተ ባለመሆኑ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ልጆች እና ወላጆች የአማራጭ ችግር ውስጥ ገብተዋል። 

ታዋቂ ከሆኑ የወተት አምራች ድርጅቶች መካከል የሆኑት እና መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ‘ሲቪኤስ’ እና ‘ዋልግሪንስ’ ከሳምንት በፊት ለኤንቢሲ ዜና አውታር እንዳረጋገጡት በመላው ዓለም እየተስተዋለ በሚገኘው የኢኮኖሚ ግሽበት ምክንያት የፍላጎት መጨመር እና የአቅርቦት አቅም ሊመጣጠን ባለመቻሉ የምርት ተግዳሮት ማጋጠሙን ተናግረዋል።

ከኢኮኖሚው ቀውስ በተጨማሪ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዘው የወጡ ዘገባዎች እና ጥናቶች ለወቅቱ የሕፃናት ፎርሙላ እጥረት እንደ መንስኤ የሚያነሱት አንዳንድ ስመጥር የወተት አምራች ድርጅቶች በገበያው ውስጥ የሚፈጥሩትን በጎም ሆነ መጥፎ ተፅዕኖ ነው።

ከወራት በፊት በአለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ያለው አቦት ላብራቶሪ የሚያቀርበው ሲሚላክ በመባል የሚታወቀው የህጻናት ፎርሙላ ወተት አንዳንድ ምርቶቹ ውስጥ ሳልሞኔላ እና ክሮኖባክተር የተባሉ ባክቴሪያዎችን እንዳገኘ በማሳወቅ የተሰራጩትን ምርቶች በአስቸኳይ ከገበያ የመሰብሰብ ጥሪ አድርጎ ነበር። 

በተጨማሪም በአጋጣሚ ወተቱን የተጠቀሙ ልጆች ካሉም በአፋጣኝ ወደ ህክምና እንዲወሰዱ ድርጅቱ ማሳሰቡ፣ ጥቂት ህፃናትም ለህመም መጋለጣቸው እና ህይወታቸው ያለፉም እንደነበሩ ተዘግቦ ነበር። 

በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ከአቦት ውጪ ያሉ ሌሎች ላብራቶሪዎች፣ አምራች ድርጅቶች እንዲሁም ተጠቃሚ ወላጆች ከፍተኛ መረበሽ ውስጥ ገብተው ስለነበር የምርት ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ክፍተቱ ገና ሳይጠራ፣ በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ ያንዣበበው የኢኮኖሚ መዋዠቅ አምራቾቹ እንዲንገዳገዱ አድርጎ እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

አዲስ ዘይቤም በአዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተዘዋውራ እንደተመለከተችው ይህ የወተት እጥረት በተለይ በከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወላጆችንም እየፈተነ እንደሚገኝ ታዝባለች። ካነጋገርናቸው ወላጆች አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ትግስት ማሞ “ልጄ ገና ምግብ አልጀመረም፣ ጡቴን ማጥባት ስለማልችል የቆርቆሮ ወተት ብቻ ነው የሚጠቀመው፣ እሱ የሚስማማውን ወተት አሁን ገበያ ላይ ስላጣሁት አጋጣሚ ገበያ ላይ የማገኛቸውን ሌሎች ምርቶች በውድ ዋጋ እየገዛሁ ነው። ባይስማማውም አማራጭ ስለሌለኝ በግድ የተለያዩ  ምርቶችን እንዲጠቀም ማስገደድ ይዣለሁ” ሲሉ ጭንቀታቸውን አካፍለውናል።

ሌላኛዋ አስተያየታቸውን ያካፈሉን እናት ማህሌት ምንዳ ይባላሉ። “በጣም ችግር ሆኗል፣ በየመደብሩ በቀላሉ ማግኘት ዘበት ሆኗል። ምናልባት ከተገኘም የተለያዩ ሰዎች እጃቸው ላይ ይዘው በሰው በሰው አግኝተናቸው ነው የሚሸጡልን” ይላሉ።

ታዲያ ይሄ እጥረት ወላጆች ጊዜያቸው ያለፋባቸውን ወተቶች ሳያገናዝቡ እንዲገዙ እንዳያደርጋቸው ያሰጋል። ተዟዙረን እንደተመለከትነው ጥቂት ቦታዎች ላይ በአቦት ላብራቶሪ የመልሶ መሰብሰብ ጥሪ የተላለፈባቸውን ወተቶች ሁሉ እየተረከቡ የሚሸጡ ቸርቻሪዎች አጋጥመውናል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አንድ የፋርማሲ ባለሙያ ይህን የተከለከለ ወተት ባለማወቅ በምትሰራበት የመድሃኒት መደብር ውስጥ ይዘውት እንደነበረ በመጥቀስ ለመገልገል ወደ ሱቁ ጎራ ባለችና መረጃው ቀድሞ በደረሳት አንዲት ደንበኛ አማካኝነት ጉዳዩን አውቀው ከሱቃቸው ማስወገዳቸውን ስትናገር፣ “አንዳንድ ጊዜ ነጋዴዎች ከትክክለኛ አስመጪዎች ላይ እንኳን ስንቀበል ምርቶቹን መመርመርና መረጃዎችን መከታተል አስፈላጊ ሲሆን፣ ወላጆችም ሲገዙ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው” ትላለች።

የኢትዮጵያ የምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የአቦትን ጥሪ ተቀብሎ ሲሚላክ ፕሮ አድቫንስ፣ ሲሚላክ አልመንተም እና ኤሌ ኬር የተባሉ፣ ከታሸጉበት ቆርቆሮ ጀርባ የሚገኘው መለያ ቁጥር (batch number) ከ22-37 በሆኑ ቁጥሮች የሚጀምሩ፣ በተጨማሪም K8፣ SH፣ Z2 የኮድ ቁጥር ያላቸውን የዱቄት ወተቶች ህብረተሰቡ እንዳይገዛ ማሳሰቡ ይታወሳል። ይሁን እንጂ መረጃው ያልደረሳቸው ነጋዴዎች እና ገዢዎች ለጉዳት ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአጋጣሚዎች ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ የተበላሹ እና የተከለከሉ ምርቶችን የመግዛት ችግርን በምን መልኩ ትከታተላላችሁ ስንል የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ የምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ በትረ ጌታነህ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት የህፃናት ምግቦች ላይ በተለየ መልኩ ምርት ተኮር ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ እንደገለጹልን በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚዘጋጁ የምግብ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ብቃታቸው በተረጋገጠ ድርጅቶች የተመረቱ መሆናቸው ተፈትሾ ነው። በተጨማሪም ምግቦቹ ጤናማ መሆናቸው በላብራቶሪ እንደሚመረመርም ተናግረዋል። በመሆኑም በምግብ እና በመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እውቅና የተሰጣቸው ምግቦች ችግር እንደሌለባቸው ያስረዳሉ።

“ታዲያ በገበያው ውስጥ አልፎ አልፎ የሚገኙት የተከለከሉ እና ጊዜያቸው ያለፈባቸው ወተቶች እንዴት ተከሰቱ?” ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “አንዳንድ ምርቶች አግባብ ባልሆነ መንገድ ገበያ ውስጥ ይገባሉ። አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች በህገወጥ መልኩ ያለፍቃድ እንደሚያስገቡ እናውቃለን። ይህን ለመከታተል በምናደርገው ድንገተኛ የገበያ ቅኝትና የድህረ ገበያ ናሙና ፍተሻ እንዲሁም ከህብረተሰቡ በሚደርሰን ጥቆማ መሠረት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እና ችግር እንዳለባቸው የተገለጹ ፤ በብሔራዊ ደረጃ የተቀመጠውን መስፈርት የማያሟሉ፤ ምንም ዓይነት ገላጭ ጽሁፍ የሌላቸው፤ የአምራች አድራሻ እና መለያ ቁጥር የሌላቸው እና ተመሳሳይ እክል ያለባቸውን ምርቶች የሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።

በሌላ መልኩ መድሃኒት እና ምግብ የማስገባት እንዲሁም የመሸጥ ፍቃድ እያላቸው ህጋዊ አሰራሩን ተከትለው የማይሰሩ እና በባለስልጣን መስርያ ቤቱ ያልተፈተሹ ምርቶችን የሚሸጡ ቸርቻሪዎች ሲገኙ ፍቃዳቸውን ከመሰረዝ ጀምሮ ከፍ ያሉ ህጋዊ እርምጃዎች እንደሚወሰድባቸው አስረድተዋል።

በመሆኑም ባለስልጣን መስርያ ቤቱ እነዚህን የህፃናት ወተቶች እንዲሸጡ እና እንዲያስመጡ ለፈቀደላችው ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚሰጥ በማስታወስ ይህ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው ከሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ማህበረሰቡ በፍጹም የተጠቀሱትን ምርቶች እንዳይገዛ አሳስበዋል።

ከነዚህም መካከል የህጻናት ልብስ መሸጫዎች፣ ኮስሞቲክስ ቤቶች፣ በኦንላይን ገበያ የሚሸጡ እንዲሁም አንዳንድ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች በአብዛኛው የባለስልጣኑ ፍቃድ የሌላቸው ናቸው። በመሆኑም ማህበረሰቡ ለህፃናት ምግብ የሚገዛበትን ቦታ የብቃት ማረጋገጫ እንዳለው ጠይቆ እና አይቶ እንዲገዛ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል። አክለውም ህዝቡ ያለፍቃድ የሚሸጡ እና ፍቃድ ኖሯቸው የተከለከለ ምርት የሚሸጡ ነጋዴዎችን ሲያገኝ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመጠቆም በህግ እንዲጠየቁ በማድረግ ከተበላሹ የታሸጉ ምግቦች የፀዳ ሀገር እንፍጠር ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በሌላ በኩል በዚህ የወተት እጦት እየተፈተኑ ያሉ ወላጆች እና አሳዳጊዎች ከላይ የተገለፁት እጥረቶች ከሚያስከትሏቸው ያልተፈለገ የአጠቃቀም ችግር እና ተያይዘው ከሚመጡ ጉዳቶች ሊድኑ የሚችሉበት አማራጭ ምንድነው ስንል የጠየቅናቸው የህፃናት ጤና አጠባበቅ እና ስነ-ምግብ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ፋሲል መንበረ “የፎርሙላ ዱቄት ወተት ከእናት ጡት ቀጥሎ ለህፃናት ተመራጭ መሆኑ አያጠያይቅም፣ ነገር ግን አሁን እንደተከሰተው እጥረት ሲመጣ ወይም ደግሞ ዋጋው የማይቀመስ ሆኖ ኪስን ሲጎዳ የላም ወተትን በከፍተኛ ጥንቃቄ መጠቀም ይቻላል” ሲሉ ይመክራሉ።

እንደ ዶክተር ፋሲል ገለፃ ከአንድ አመት በታች የሆኑ ህፃናት የላም ወተትን እንደወረደ ሲጠቀሙ የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል። ጨቅላ ህፃናት የላም ወተትን ሙሉ በሙሉ አንጀታቸው መፍጨት ስለሚያዳግተው ለትውከት እና ለተቅማጥ ሊዳርጋቸው ይችላል። በተጨማሪም ለደም ማነስ፣ ለአእምሮ እድገት እክል፣ ለስኳር ህመም፣ እንዲሁም ለአላስፈላጊ ውፍረት የማጋለጥ እድሎች አሉት።

ዶክተር ፋሲል አክለውም ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ለጨቅላ ህጻናት  የላም ወተት የመስጠት የመጨረሻ አማራጭ ውስጥ ከገቡ እሰከ 2 ወር ለሚገኙ ህጻናት 60 ሚሊ የላም ወተት በ30 ሚሊ ውሃ በርዞ አፍልቶ አቀዝቅዞ መስጠት፣ ከ3 እስከ 4 ወር ለሚገኙ ህፃናት 80 ሚሊ ወተት በ40 ሚሊ ወተት በርዞ አፍልቶ አቀዝቅዞ መስጠት፣ ከ5 እስከ 6 ወር ለሆናቸው ህፃናት 100 ሚሊ ወተት በ50 ሚሊ ወተት በርዞ አፍልቶ አቀዝቅዞ መስጠት እንዲሁም ከ6 ወር በላይ ላሉ ህፃናት ወተቱን ምንም ውሃ ሳይገባበት አፍልቶ መስጠት ይመከራል ብለዋል። በጥቅሉ ግን ከአንድ አመት በታች የሆኑ ህፃናት በቀን ከ600 ሚሊ በላይ የላም ወተት ባይወስዱ እንደሚመረጥ ገልፀዋል።

ምግብ የጀመሩ ህፃናት ደግሞ ወተትን የሚተኩ የጥራጥሬ፣ የስጋ እና የአሳ ምርቶችን አቅም በሚችለው መልኩ መጠቀም እንደሚችሉ አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በአሁን ወቅት የሚስተዋለው የዱቄት ወተት እጥረት ሊፈጥር የሚችለውን ጎጂ ግብይት ከግምት ውስጥ በማስገባት ወላጆች፣ አሳዳጊዎች እንዲሁም ይመለከተኛል የሚል የማህበረሰብ ክፍል ሁሉ በግዢ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ባለሙያዎች ያሰምሩበታል።