የዘንድሮ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች እነማን ናቸው?

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታመስከረም 28 ፣ 2014
City: Addis Ababaዜና
የዘንድሮ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች እነማን ናቸው?

በዓለማችን ከሚሰጡት ግዙፍ እውቅናዎች መካከል አንዱ የሆነው የኖቤል የሰላም ሽልማት በዛሬው እለት ባካሄደው የ2021 ሽልማት ፕሮግራም ላይ ፊሊፒናዊቷ ጋዜጠኛ ማሪያ ሪሳ እና ሩስያዊው ጋዜጠኛ ዲሚትሪ ሙራቶቭ ኃሳብን የመግለፅ ነፃነት እንዲከበር ባደረጉት አስተዋፅኦ ከ329 ተወዳዳሪዎች መካከል አሸናፊዎች ሆነው ተመርጠዋል።  

የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ቤሪት ሪዝ አንደርሰን “ጋዜጠኞቹ የሰላም ሽልማቱ የተሰጣቸው በፊሊፒንስ እና በሩሲያ ውስጥ ኃሳብን የመግለፅ ነፃነት እንዲከበር ባላቸው ቁርጠኝነት ሃሳባቸውን እና አመለካከታቸውን በነጻነት ለመግለጽ ባደረጉት ድፍረት የተሞላበት ትግል ምክንያት ነው” ብለዋል።

“የዴሞክራሲ እና የፕሬስ ነፃነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ በመጣበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳን በድፍረት ላመኑበት አላማ ለሚታገሉ ጋዜጠኞች በሙሉ ተወካይ ሆነው መቆም የሚችሉ ታላላቅ ጋዜጠኞች ናቸው” 

የፊሊፒንስ እና የአሜሪካ ዜግነት ያላት ጋዜጠኛ እና ደራሲ ማሪያ ሪሳ ‘ራፕለር’ በመባል የሚታወቀው የድረ ገፅ ዜና ጣቢያ መስራች ስትሆን፣ እ.ኤ.አ በ2020 በበይነ መረቡ መድረክ ላይ የስም ማጥፋት አድርሰሻል ተብላ በተከሰሰችበት የሀሰት ውንጀላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ጋዜጠኞች ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።  በሌላ በኩልም የፊሊፒንሱ ፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ዱተርቴ በሀገሪቱ ባደረገው የፀረ-አደንዛዥ ዕፅ ንቅናቄ ሳቢያ ፖሊሶች ዜጎች የሚያደርሱትን ኢ-ሰብአዊ ጥቃት በመቃወም ባደረገችው ተጋድሎም ትታወቃለች። 

ሙራቶቭ ዲሚትሪ በበኩሉ በአሁኑ ጊዜ በሩሲያ ውስጥ ካሉት ጋዜጦች መካከል በጣም ገለልተኛው እንደሆነ የሚነገርለት የኖቫያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና ሪፖርተር ሲሆን፡ ጋዜጣው በፖሊስ የሚፈጸም በደልን ፣ ሙስናን ፣ ጦርነትን እና ወታደራዊ ፕሮፓጋንዳዎችን ጨምሮ በሩሲያ ውስጥ የሚካሄዱ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በሚያደርገው የምርመራ ዜናዎች ይታወቃል። እ.ኤ.አ ከ2000 ወዲህ በዚህ ጋዜጣ ላይ ከሚሰሩት ጋዜጠኞች መካከል ሰባት ጋዜጠኞች በሰሩት ዘገባ ምክንያት ተገድለዋል።

ባደረጉት የጋዜጠኝነት ትግል አሸናፊ የሆኑት ሁለቱ ጋዜጠኞች በኦስሎ ከሚገኘው የኖቤል ተቋም ይፋ እንደሆነዉ 10 ሚሊዮን የስዊድን ክሮና ወይም 1.1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያገኛሉ።

በዚህ ዓመት ለኖቤል የሰላም ሽልማት በተፎካካሪነት ተጠቁመዉ ከቀረቡት መካከል የአየር ንብረት ተሟጋቿ ግሬታ ተንበርግ ፣ የመገናኛ ብዙኃን መብት ተከራካሪ የሆነዉ የዘጋቢዎች ቡድን እና የዓለም ጤና ድርጅት በእጩነት ቀርበዉ ነበር።

ከዚህ ቀደም ከተደረጉት ውድድሮች መካከል ረሃብን ለመዋጋት እና ለሰላም ሁኔታዎች መሻሻል ባደረገው ጥረት የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ባለፈው ዓመት አሸናፊ የነበረ ሲሆን በ2019 ደግሞ የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሸናፊ እንደነበሩ ይታወሳል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist is working as a reporter and content creator at Addis Zeybe to explore her passion for storytelling. She has Bsc. in medical laboratories & BA in media and Communications.