ሚያዝያ 11 ፣ 2014

የብሔራዊ ደም ባንክ አሁን ያለው የደም ክምችት ከአምስት ቀን በላይ እንደማያቆይ አስታወቀ

City: Addis Ababaዜና

በመደበኛ ጊዜያት በአዲስ አበባ በቀን ከ300 እስከ 500 ከረጢት ይሰበሰብ የነበረው ደም በፆም ወቅት በግማሽ ቀንሷል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የብሔራዊ ደም ባንክ አሁን ያለው የደም ክምችት ከአምስት ቀን በላይ እንደማያቆይ አስታወቀ
Camera Icon

Credit: National Blood Bank

የዐቢይ ፆም ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፤ እንዲሁም በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የረመዳን ፆም መግባቱን ተከትሎ የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ያለው የደም ክምችት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ባንኩ ለአዲስ ዘይቤ አስታውቋል።

የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን አበጀ ለአዲስ ዘይቤ እንደገልፁት የሚሰበሰበው የደም መጠን እና የደም ክምችት ከፆሞቹ መግባት በኋላ መቀነስ የታየበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ደም ባንኩ ቢበዛ አምስት ቀናት ብቻ የሚያቆይ ክምችት መኖሩን ገልፀዋል። 

“ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ በመደበኛ ጊዜያት በቀን ከ300 እስከ 500 ከረጢት ደም ይሰበሰብ ነበር፤ የተለያዩ ሁነቶች ሲኖሩ ደግሞ በቀን እስከ 1 ሺህ ከረጢት ደም የሚሰበሰብበት ጊዜም አለ። የፆም ወቅቶች ከገቡ በኋላ የሚሰበሰበው የደም መጠን በግማሽ ቀንሶ ወደ 150-250 ከረጢት ወርዷል” ብለዋል ዶክተር ተመስገን።

ሰዎች ከፆሙ ጋር አያይዞ የድካም ስሜቶች እና የመፍራት ዝንባሌዎች መኖራቸው ለመቀነሱ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው። የዐቢይ እና የረመዳን ፆሞች ከገቡ በኋላ በቀን 90 ከረጢት ብቻ ደም የተሰበሰበበት ጊዜ መኖሩንም ዶክተር ተመስገን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ500 በላይ የጤና ተቋማት እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ከ100 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት ከደም ጋር ተያያዥ የሆኑ ህክምናዎችን ይሰጣሉ ያሉት ዳይሬክተሩ እነዚህ የጤና ተቋማት ታካሚዎችን የሚያስተናግዱት ከብሔራዊ ደም ባንክ በሚያገኙት የደም አቅርቦት መሆኑን ገልፀዋል።   

“አንድ ታካሚ ቢያንስ ከ4 እስከ 5 ከረጢት ደም ያስፈልገዋል፤ ይህም ማለት ከአራት ወይም ከአምስት ሰዎች የሚሰበሰብ የደም መጠን” መሆኑን የገልፁት ዶክተር ተመስገን አበጀ፤ “እንደህክምናዎቹ ዓይነት የሚያስፈልገው የደም መጠን እየጨመረ ቢሄድም የሚሰበሰበው የደም መጠን ጋር ካልተጣጣመ ነው እጥረት ተፈጥሯል የሚባለው፤ አሁንም የደም ባንኩን የገጠመው ይህ ነው” ብለዋል።

ከዘመናዊ የህክምና መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚሰጡ ዘርፈ ብዙ የህክምና አገልግሎቶችን ተከትሎ ደም የሚያስፈልጋቸው የህክምና ዓይነቶች በየጊዜው እየጨመሩ ይገኛሉ። በኢትዮጵያም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰጡ የህክምና ዓይነቶች እያደጉ በመሄዳቸው እውነታው ከእዚህ የተለየ አለመሆኑን የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

እንደ ባለሙያው ገለፃ ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ህክምናዎች፣ የእናቶች ወሊድ፣ የካንሰር ህክምና በተለይም የደም ካንሰር ታካሚዎች፣ የውስጥ ደዌ ህክምናዎች እንዲሁም የደም ማነስ ያለባቸው የተለያዩ ታካሚዎች በህክምናቸው ወቅት ደም ያስፈልጋቸዋል።

“ለህክምና እጅግ አስፈላጊ የሆነው 'O' የደም ዓይነት ለሁሉም የደም ዓይነቶች የሚያገለግል ቢሆንም በእንደዚህ ዓይነት ወቅቶች የሚሰበሰበው የደም መጠን ይቀንሳል” ብለዋል። በተጨማሪም 'ፕላትሌት' የተሰኘው የደም ተዋፅኦ ከአምስት ቀን በላይ የማይቆይ በመሆኑ የደም ለጋሾች ቁጥር መበራከት እንደሚገባው አሳስበዋል። 

አሁን የተፈጠረውን እጥረት ለመቅረፍ የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት በመፍትሔ ደረጃ የጀመራቸው ስራዎች አሉ። የመጀመሪያው የሚገኘውን የደም ክምችት ከህክምና ተቋማት ጋር በመናበብ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ታካሚዎችን በማስቀደም በአግባቡ መጠቀም ነው። 

ሌላኛው ደም የሚሰበሰብባቸውን መንገዶች ማስፋት ሲሆን፣ በመገናኛ ብዙኀን ጥሪ ማቅረብ፣ ለመደበኛ ደም ለጋሾች በየስልካቸው እየደወሉ የማስታወስ ስራ መስራት እንዲሁም ሰዎች ባገኙት አጋጣሚ ደም መለገስ እንዲችሉ በተመረጡ አደባባዮች ላይ ጊዜያዊ የደም ልገሳ ማዕከላትን የማዘጋጀት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። 

በእነዚህ ተግባራት የተወሰኑ መሻሻሎችን ማምጣት ተችሏል የሚሉት ዶክተር ተመስገን ባለፉት ቅዳሜ እና እሁድ ሚያዝያ 8 እና 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በሁለቱ ቀናት 1 ሺህ ከረጢት ደም መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን የፆም ወቅቶቹ ከገቡ ከፍተኛ የተሰበሰበው በእነዚህ ቀናት ነው ብለዋል። 

በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ደም የመሰብሰብ ስራ ለመጀመር ጥረቶች ተጀምረዋል። ዶክተር ተመስገን አበጀ “ከመጪዎቹ በዓላት ጋር ተያይዞ በጤና ተቋማት የሚገኙ ታካሚዎችን በማሰብ ደም መለገስ አንዱ የመረዳዳት መንገድ በመሆኑ” ህብረተሰቡ አሁንም ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየት