ሚያዝያ 25 ፣ 2015

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፌደራል መንግስት የሚያደርጋቸው ድርድሮች ግልፅነት መጉድል እንዳሳሰባቸው ገለፁ

City: Addis Ababaዜናፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት ከተፈረጀው ኦነግ ሸኔ ጋር በጀመረው ድርድር ከህወሓት ጋር ከተደረገው ድርድር ልምድ እንዲወሰድ ተጠይቋል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፌደራል መንግስት የሚያደርጋቸው ድርድሮች ግልፅነት መጉድል እንዳሳሰባቸው ገለፁ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመረ አንስቶ በተለያየ ጊዜ የሚፈፅሙ ድርድሮች ግልፅነት መጉደል እንዳሳሰበው ገለፀ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዛሬ ሚያዝያ ሚያዝያ 24፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በጦርነቱ ወቅት የተከፈለውን ዋጋ በማይመጥን ደረጃና አግባብ” ብሎ በገለፀው ሁኔታ የመልሶ ማቋቋም ስራ እና ድኅረ-ጦርነት ላይ በመንግስት በኩል “ግልፅነት የሌለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እና ስጋት መፍጠሩን መተማመን ያስፈልጋል” ብሏል።

ኢዜማ በመግለጫው “መንግስት ከሕወሓት ጋር ድርድር አድርጌ ሰላም አውርጃለሁ ባለበት የፕሪቶሪያው ስምምነት እንደ ስምምነቱ ያልተፈፀሙ ጉዳዮችን አስተውለናል” ብሎ ሂደቱ ምን ላይ እንደሆነ አሁንም ድረስ በግልፅ አለመታወቁ በፓርቲው እና ሌሎችም አካላት ላይ ቅሬታ መፍጠሩን ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሳምንት ጀምሮ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጀው መንግስት “ኦነግ ሸኔ” ብሎ ከሚለው እራሱን “የኦሮም ነፃነት ሰራዊት” ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር በታንዛኒያ ለውይይት መቀመጡ ይታወሳል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በበኩሉ “በአማራ ሕዝብ በኩል መንግስት ፍፁም መወያየትና ማድመጥ የማይፈልግ አካል መሆኑ አንድምታ ከተወሰደ ቆይቷል” ያለ ሲሆን፤ “አጠቃላይ ፖለቲካው ግልፅነት የጎደለው በመሆኑ እና ማሕበረሰቡን የሚያስተዳድርበትን ፍኖት ስለማያሳይ” ዘወትር ጥርጣሬና የሴራ ትንተና የበላይነት እንዲኖር ከማድረግ አልፎ አሁን ለተፈጠረው የፀጥታ ችግር አስተዋፅኦ አድርጓል ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።

መንግስት ከዚህ ቀደም በለውጡ ሰሞን ኦነግ ከኤርትራ ወደ ሀገር ቤት ከገባ በኋላ በስምምነቱ መሠረት አልተፈጸመልኝም ሲል አንደነበረው ተመሳሳይ  ችግር እንዳይፈጠር በተለይም ከሕወሓት ጋር ከተደረገው ስምምነት ልምዶች መነሻ በማድረግ፣ የድርድሩን ሂደትና ስምምነቱን በተመለከተ ህዝቡ ሊኖረው የሚገባውን ግልፅ መረጃ ፤ እነማን እየተሳተፉ እንደሆነ፣ የስምምነቱን ይዘት፣ እንዴት እንደሚፈጸም እና በአፈፃፀሙም ጊዜ ተግባራዊነቱን ለዜጎች ተገቢና በቂ መረጃን በማስተላለፍ ከተጨማሪ ውዥንብርና ትርምስ ማኅበረሰቡን እንዲጠበቅ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

እናት ፓርቲ በተመሳሳይ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ግድያን ተከትሎ መንግስት አሁንም "ኢ መደበኛ አደረጃጀቶች"ን ትጥቅ በማስፈታት "ሰላም አስከብራለሁ" በሚል በክልሉ የጀመረው እንቅስቃሴ ከሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ጋር የታለፈበትን እና አገርን ውድ ዋጋ ያስከፈለ አካሄድ የሚደግም ነው ሲል ስጋቱን ገልጿል።

አብን የአማራ ክልል ሁኔታን በተመለከተ በመግለጫው እንዳስታወቀው መንግስት ከግጭት ምንም ፋይዳ እንደማይገኝ ተረድቶ አሁን ላይ እየታዬ የመጣውን መካረር በሰላም ማዕቀፍ የሚፈታበትን እድል እንዲተገብር በጥብቅ አሳስቧል።

ፓርቲው አክሎም በድኅረ ጦርነት ወቅት ከሕዝቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር “በመሰረታዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታታይነት ያለው ግልፅ ውይይት ባለመደረጉ” ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች ሲል የገለፀው የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፤ “ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው የፀጥታ ቀውስ ምክንያቶቹ ለረዥም ጊዜ የቆየው የፖለቲካ ችግር እና ወቅታዊው የመንግስት ፍላጎትና አቅም ማጣት ናቸው” ብሏል።

አስተያየት