ጥር 24 ፣ 2015

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች በተገኙበት በሞቃዲሾ የቦንብ ጥቃት ተፈፀመ

City: Addis Ababaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

በሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ማስነሳት የሽብር ስጋትን ለማስወገድ የሚያግዝ በመሆኑ ማዕቀቡ እንዲነሳ የሚጠይቅ የጋራ መግለጫ ይጠበቃል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች በተገኙበት በሞቃዲሾ የቦንብ ጥቃት ተፈፀመ
Camera Icon

ፎቶ ምንጭ፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች በአልሸባብ ጉዳይ ለመምከር በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የተሰባሰቡበት በዛሬው እለት በሞቃዲሾ ከተማ የቦንብ ጥቃት መድረሱ ተሰምቷል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት መሪዎች በአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ በጋራ ስለሚያደርጉት ትግል ሊወያዩ የተገናኙ ቢሆንም ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት የሶማሊያ የፕሬዝዳንት ቤተ መንግስት አቅራቢያ ያሉ አካባቢዎች ላይ አራት የቦንብ ፍንዳታዎች መድረሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። 

በቅርቡ የሶማሊያ መንግስት በእስላማዊ ታጣቂዎች ላይ ያስመዘገበውን ወታደራዊ ድል ተከትሎ የኬንያ፣ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ መሪዎች በዛሬው እለት ጥምር ውይይት ለማድረግ በሞቃዲሾ ተሰብስበዋል።

አልሸባብ አሁንም ሰፊ የሶማሊያ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ እና መደበኛ ጥቃቶችንም እየፈፀመ የሚገኝ ቢሆንም በአሜሪካ እና በአፍሪካ ወታደሮች የሚደገፈው የሶማሊያ መንግስት ባለፈው ነሀሴ ወር ከጀመረው አዲስ የጥቃት እርምጃ ወዲህ የተለያዩ ግዛታቸውን አጥተዋል።

ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ በሞቃዲሾ በተፈፀመው ጥቃት ዙሪያ በሰው ህይወት ላይ ስለደረሰ ጉዳት ምንም አይነት መረጃ አልወጣም። ሶማሊያ በአልሸባብ ታጣቂዎች ላይ የምትወስደውን እርምጃ በተቀናጀ ፖሊሲ ለመንደገፍ የጎረቤት ሀገራትን የሰበሰበች ሲሆን ይህም ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ሶማሊያን ማስተዳደር ከጀመሩ በኋላ በዓይነቱ የመጀመርያው ስብሰባ ነው።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ጊሌህ ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ በሞቃዲሾ ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ ባለበት ተገኝተዋል። ዘ ኢስት አፍሪካን የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው የሀገራት መሪዎችን በከተማዋ መገኘት ተከትሎ ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ የሚደረጉ በረራዎች እና የህዝብ ማመላለሻዎች ሲከለከሉ የትምህርት ማዕከላት እና የንግድ ተቋማትም በብዛት ተዘግተዋል። 

በተጨማሪም በትላንትናው እለት ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ የመከላከያ ሚኒስትሮች እና የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች ሞቃዲሾ መግባታቸው ተዘግቧል።

የሶማሊያ የኮምኒኬሽን ሚኒስትር ዳውድ አወይስ ስብሰባው በአፍሪካ ቀንድ “ግንባር ቀደም ሀገራት” መካከል የተቀናጀ ስትራቴጂ ለመጀመር ያለመ ነው ብለዋል። ሚኒስትሩ እንደገለፁት ሶማሊያ ከስብሰባው በተጨማሪም ሶማሊያ ከኬንያ፣ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ የተውጣጡ የመከላከያ ሚኒስትሮችን እና የግንባሩ ጦር አዛዦችን ታስተናግዳለች። የግንኙነታቸው አላማ በተለይም ከአልሸባብ ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ ያተኮረ የጋራ ቀጠናዊ ስትራቴጂያዊ ቦታን መቀበል ነው።

"ይህ ስብሰባ ወሳኝ የሚሆንበት ምክንያት አሁን ያለው የሶማሊያ የፀጥታ ሁኔታ የሶማሊያን ጎረቤት ሀገራትም ሊጎዳ የሚችል በመሆኑ ነው" ሲሉም የኮምኒኬሽን ሚኒስትሩ ገልፀዋል። በስብሰባው የመከላከያ ሚኒስትሮች እና የጦር አዛዦች እንዲሁም የግንባሩ ሀገራት መንግስታት የሚወያዩበትን አጀንዳ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጋር በመሆን መሪዎቹ በሶማሊያ መንግስት ሃይሎች እየታገዙ በአሸባሪዎች ላይ የሚደረገውን ጥቃት እንዴት መደገፍ እንደሚቻል የሚወያዩ ሲሆን ይህም እስከ አሁን የተሳካላቸው ሰፋፊ ቦታዎችን ከአልሸባብ ቁጥጥር ውጭ ለማድረግ አግዟል ተብሏል።

በተጨማሪም በሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ማስነሳት የሽብር ስጋትን ለማስወገድ የሚያግዝ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለዚህ ርብርብ እንዲያደርግ የሚጠይቅ አንድ ወጥ መግለጫ ከስብሰባው በኋላ እንደሚወጣም ይጠበቃል።

ሦስቱ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በቀጥታ የሚዋሰኑ እና የሶማሊያ መንግስት በአልሸባብ ላይ በሚያደርገው ውጊያ ግንባር ቀደም አጋሮች ናቸው። እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ተልእኮ በሶማሊያ (አሚሶም)ን የተካው በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አቲምስ) የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ወታደሮቻቸውን የሚያዋጡ አገሮችም ናቸው።

አስተያየት