ግንቦት 15 ፣ 2015

ኢዜማ ባለስልጣኑ ማኅብረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ላይ ያሰተላለፈውን እግድ አወገዘ

City: Addis Ababaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን በማህበረ ቅዱሳን ብሮድካስት ላይ የወሰደው የእግድ እርምጃ ህግን ያልተከተለ ነው ያለው ኢዜማ ኃላፊዎች ተጠያቂ ይሁኑ ብሏል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ኢዜማ ባለስልጣኑ ማኅብረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ላይ ያሰተላለፈውን እግድ አወገዘ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገለልተኛ መሆን ያለባቸው ተቋማትን ገዢው መንግስት አሁንም “ጠፍሮ” ይዟቸዋል ሲል ተችቷል።

ኢዜማ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ላይ የወሰደውን ሕገ ወጥ ውሳኔ እንዲሽር እና ይህን ውሳኔ ያሳለፉ አካላት ተጠያቂ ተደርገው ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ ጥሪ አቅርቧል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ “ከጉዳዩ አጣዳፊነት እና ሊያስከትለው ከሚችለው ችግር አንፃር” በቦርድ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ በሚል እሁድ እለት የማህበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎትን በጊዜያዊነት ፈቃዱ እንዲታገድ ወስኗል።

በማህበራዊ የትስስር ገፆች ከመንግስት ተቋማት ባልተለመደ መልኩ ከስራ ቀናት ውጭ በሆነ ቀን ውሳኔው መወሰዱ አነጋጋሪ ሆኖ እንደነበረ አዲስ ዘይቤ ታዝባለች። በተጨማሪም ከወራት በፊት ራሳቸውን የኦሮሚያ ቅዱስ ሲኖዶስ አድርገው ሾመዋል የተባሉ አካላት በሰየሟቸው ኤጲስ ቆጶሳት ምክንያት ተፈጥሮ የነበረውን የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በተወሰነ መልኩ እንዳዲስ ተጋርተዋል።

ፓርቲዉ እሁድ ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን በማህበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ላይ እግዳ መጣሉን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ “ተቋማት የሚወስዷቸው እርምጃዎች በእርግጥም ሕግን ከማስከበር መነሻነት ይልቅ በማን አለብኝነት ድርጅታዊ ፍላጎትን ብቻ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ” አሁን የተወሰደው እርምጃ ያመለክታል ብሏል።

ኢዜማ በመግለጫው የእግድ ውሳኔው ምክንያቱ ሕጋዊ ሆነም አልሆነ “በመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1238/2021 አንቀጽ 73፣ 76 እና 81(2) የተጠቀሱትን በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የመስጠትም ሆነ የሚዲያ ተቋሙ ራሱን እንዲከላከል ቀድሞ እድል የመስጠት ሕጋዊ ግዴታውን የጣሰ” ነው ሲል አሳስቧል። 

የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣኑ በህዝብ መገናኛ ብዙኀን ስም ተቋቁመው ለገዢዎች ፍላጎት የሚሯሯጡ መገናኛ ብዙኀንን “ከተልዕኳቸው ውጪ የገዢው ፓርቲ ልሳን ሆነው የህዝብን በደል እና የመንግሥትን ብልሹ አሰራር ጆሯቸውን ደፍነው ዘወትር የውዳሴ ዘገባ ለገዢው ፓርቲ እና መንግሥት በማቅረብ” ተጠምደዋል ብሎ ለነዚህ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ምንም አይነት “ተግሳጽ እንኳ ሳያቀርብ” አሁን በማህበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ላይ ህግን የጣሰ እርምጃ መውሰዱ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል ሲል ገልጿል።

 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን በኃይማኖት ተከታዮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳት ወይም በኃይማኖት ተከታዮች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር በመቀስቀስ ነው ፈቃዱን በጊዜያዊነት ያገደው

በግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም.  “በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ዓለማዊ አጀንዳ ቢያራምዱም በከፍተኛ ትዕግስት ስናልፋቸው የነበሩ አባቶች ዛሬም ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው ቤተክርስቲያንን ሲገፉ በዝምታ የምናይበት ሂደት አይኖርም” በሚል ርዕስ የማህበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ያቀረበው ዜና ለዕግዱ መነሻ መሆኑ ተግልጿል።

በዘገባውም የእምነቱ አባቶች በተለይም በኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ላይ መስማማት እንዳልቻሉ ገልፆ ነበር። ይህን መረጃ የያዘው ዘገባ ነበር በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን “የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክስርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሲያካሄድ የቆየውን ስብሰባ የሚያውክ እና ህዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ ሆኖ ተገኝቷል” በሚል የእግድ ምክንያት የሆነው።

የማህበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን በበኩሉ ትላንት ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን የቅሬታ ደብዳቤ ያስገባ ሲሆን ህግን የጣሰ እርምጃ መሆኑን ጠቅሶ “የተላለፈው ይዘት በቤተ ክርስቲያኗ ምእመናን መካከል እርስ በእርስ ግጭት የሚፈጥር ነው ብለን አናምንም” ሲል አስታውቋል።

ለቀናት ሲካሄድ የቆየው የግንቦት ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ በትላንትናው እለት ሲጠናቀቅ አወዛጋቢ የሆነው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በቅድሚያ ችግር ያለባቸውን ሀገረ ስብከቶች የሚለዩ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ ጥናት እንዲያቀርብ እና በጥናቱ መሰረት ሹመት እንዲካሄድ መወሰኑ ታውቋል። የሹመት ቀኑም ወደፊት እንደሚገለፅ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ትላንት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በየካቲት ወር የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕገ ወጥ ባለችው የኤጵስ ቆጶሳት ሹመት ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች በእርቅ ወደቤተክርስትያን መመለሳቸው እና ተላልፎባቸው የነበረው እግድ መነሳቱ ይታወሳል።

አስተያየት