መስከረም 19 ፣ 2015

በቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎቶች በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ከ373 ሚልዮን ብር በላይ መዘዋወሩ ተገለፀ

City: Addis Ababaዜናንግድ

ቴሌብር ከላይ የተጠቀሱትን የብድር እና ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ማንቀሳቀስ የቻለው ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ እንደሆነ መረዳት ተችሏል

Avatar: Kalayou Hagose
ኻልኣዩ ሓጎሰ

ኻልኣዩ ሓጎሰ የህግ ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን ይፅፋል። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

በቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎቶች በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ከ373 ሚልዮን ብር በላይ መዘዋወሩ ተገለፀ
Camera Icon

ፎቶ፡ ኳርዝ አፍሪካ (የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ በቴሌብር አገልግሎት አገልግሎት ማስጀመሪያ ዝግጅት ላይ)

በኢትዮ ቴሌኮም ቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎቶች (ቴሌብር መላ፣ እንደኪሴ እና ሳንዱቅ) በተጀመሩ በሁለት ወራት ብቻ ከ373 ሚልዮን ብር በላይ መንቀሳቀሱ ተገለፀ።

በዚህም መሰረት በነዚህ ሁለት ወራት ውስጥ በቴሌብር ሳንዱቅ የአነስተኛ ቁጠባ አገልግሎት 192.1 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ መደረጉን፣ በቴሌብር መላ የአነስተኛ ብድር በአጠቃላይ 157.9 ሚሊዮን ብር ብድር መስጠቱን እንዲሁም ቴሌብር እንደኪሴ በተሰኘው ሌላኛው የብድር አገልግሎት ደግሞ 23,199,552 ብር ብድር መስጠቱን በዚህ ሳምንት ይፋ ባደረገው የሶስት ዓመታት የእድገት ስትራቴጂ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም  የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ቴሌብር ከላይ የተጠቀሱትን የብድር እና ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ማንቀሳቀስ የቻለው ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ እንደሆነ መረዳት ተችሏል። 

ቴሌብር አገልግሎቱን ሲጀምር ከነበሩት የአየር ሰዓት ግዢ፣ የገንዘብ መላክ እና መቀበል፣ ከባንኮች ገንዘብ የማስተላለፍ እንዲሁም  ከፍጆታ ክፍያ አገልግሎቶች በተጨማሪ በነሃሴ ወር በሞባይል ገንዘብ አገልግሎቱ ዉስጥ የተቀናጁ የፋይናንስ ብድርና ቁጠባ አገልግሎቶችን አካቷል። 

የቴሌብር አዲሶቹ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ቴሌብር እንደኪሴ (ለግዢ ብቻ የሚሆን ተጨማሪ ብድር)፣ ቴሌብር መላ (የአነስተኛ ብድር አገልግሎት) እና ቴሌብር ሳንዱቅ (የቁጠባ) ተብለው የሚጠሩ አገልግሎቶች ይገኙበታል።  

ቴሌብር ሳንዱቅ ምንድን ነው? 

ቴሌብር ሳንዱቅ የቴሌብር ደንበኞች በማንኛዉም ባንክ እንደሚደረገው ገንዘባቸው የሚቆጥቡበት እና ለቆጠቡት ገንዘብ ወለድ የሚያገኙበት የአገልግሎት አይነት ነው። ይህ ቴሌብር ሳንዱቅ የተሰኘው የቁጠባ አገልግሎት በወለድ እና ከወለድ ነፃ የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን በዚህ አገልግሎት ደንበኞች የሚቆጥቡት ገንዘብ 26 ብር ሲደርስ ወለድ መታሰብ ይጀምራል። 

ቴሌብር እንደኪሴ

እንደኪሴ ቴሌብር ካስጀመራቸው የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶች አንዱ ሲሆን ደንበኞች ግብይት በሚፈጽሙበት ጊዜ ገንዘብ ካጠራቸው በቀላሉ ሞባይላቸውን ተጠቅሞው ቀሪዉን ገንዘብ በብድር የሚያገኙበት መንገድ ነው። በተጨማሪም እንደኪሴ ደንበኞች የኤሌክትሪክ፣ የዉሃ እና የመሳሰሉ ክፍያዎችን በቀላሉ እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል። 

ቴሌብር መላ

ቴሌብር መላ የአነስተኛ ብድር አገልግሎት የሚሰጥበት የቴሌብር ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ሲሆን በዚህም ተጠቃሚዎች እስከ 10 ሺህ ብር መበደር የሚችሉ ሲሆን ድርጅቶች ደግሞ እስከ 100 ሺህ ብር ሊበደሩ ይችላሉ። 

እነዚህን አገልግሎቶች ኢትዮ ቴሌኮም ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በይፋ ባስጀመረበት ወቅት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ ከቴሌብር መላ የሚበደሩ ግለሰቦች የተበደሩትን ገንዘብ በቀን፣ በሳምንት እና በወር መመለስ እንደሚችሉና ለንግድ ተቋማት የሚሰጠው ጊዜ ግን ለግለሰቦች ከሚሰጠው ከፍ ያለ እና በሶስት፣ ስድስት እና ዘጠኝ ወር የሚመልሱበትን አሰራር እንዳለ አስረድተዋል።

ቴሌብር አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የ65.6 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ዝውውር መጠን አስመዝግቧል። የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር 24 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን 1.2 ሚሊዮን ዶላር በዓለም አቀፍ ሐዋላ ማስተላለፍ መቻሉንም ኢትዮ ቴሌኮም በመግለጫው አስታውቋል። 

ቴሌብር በግንቦት 2015 ዓ.ም 32.6 ሚሊዮን ተመዝጋቢ ደንበኞችን ለመያዝ እቅድ ይዟል። እንደ ብሄራዊ ባንክ መረጃ መሰረት እስከ ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ድረስ  በኢትዮጵያ ከ43 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ገንዘብ ተጠቃሚዎች ይገኛሉ። 

ከሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ የሆነዉ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ኤም-ፔሳ (M pesa) ለመጀመር አቅዷል። ሆኖም አዲስ ዘይቤ በሚያዝያ ወር እንደዘገበው ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለመጀመር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መመሪያ እስኪሻሻል በመጠበቅ ላይ ይገኛል። 

ሳፋሪኮም ባለፈው ወር ድሬዳዋና ባህርዳርን ጨምሮ በ8 ከተሞች የኔትወርክ አገልግሎት በመጀመር ከሀገሪቱ ግዙፍ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም ጋር የንግድ ተቀናቃኝ ለመሆን ተዘጋጅቷል። በተጨማሪም እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ድረስ አዲስ አበባን ጨምሮ በ24 የሀገሪቱ ከተሞች አገልግሎቱን ለመጀመር እቅድ ይዟል። 

አስተያየት