ኮሜርስ በ15 ቀን ውስጥ እንዲፈርስ ተወሰነ

Avatar:  አዲስ ዘይቤ
አዲስ ዘይቤ ሐምሌ 23 ፣ 2013
City: Addis Ababaአካባቢማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች
ኮሜርስ በ15 ቀን ውስጥ እንዲፈርስ ተወሰነ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት በተለምዶ ኮሜርስ ተብሎ የሚታወቀው አሁን ካለበት ሰንጋተራ አካባቢ በ15 ቀን ውስጥ እንዲነሳ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ማሳለፉ ተሰማ።

ትምህርት ቤቱ አሁን የሚገኝበት ቦታ ለባንኮችና ለፉይናንስ ተቋማት (ፋይናንሺያል ማእከል) ተብሎ የተለየ ቦታ በመሆኑ ተቋሙ እንዲፈርስና ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሄድ ከውሳኔ ላይ መደረሱ ነው የተሰማው።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የት/ቤቱ ዲን ዶክተር ወርቁ መኮንን "ምንም እንኳን ውሳኔው በደብዳቤ ባይደርሰንም ተቋሙ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ እንዲነሳ የትምህር ተቋማት ወደሚገኙበት አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ አካባቢ እንዲዛወር የሚል ውሳኔ መተላለፉን ሰምተናል" ብለዋል።

"ውሳኔው እጅግ የተቻኮለና ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ያላስገባ ነው" የሚሉት ዶክተር ወርቁ የንግድ ስራ ት/ቤት በጠቅላላ ስሙም ሆነ ነባር ሕንጻዎቹ በታሪካዊ ቅርስነት የተመዘገቡ መሆናቸውን ይገልፃሉ።

መነሳቱ ግድ ከሆነ እንኳን ከ100 በላይ መምህራን፣ ከ200 በላይ የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም ከ5,000 /አምስት ሺህ/ በላይ ተማሪዎች ለማዘዋወር ሰፊ ቦታና ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት የሚጠይቅ መሆኑን ይናገራሉ።

"ት/ቤቱ ለባንኮች ወይንም ለፉይናንስ ተቋማት ተብሎ በተለየ ቦታ መገኘቱ ለመፍረሱ እንደምክንያት መቀመጡን" የሚያነሱት ዶ/ር ወርቁ ት/ቤቱ ለፋይናንስ ተቋማት ልማት ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙና ለረዥም ዓመታት የቆየ አገልግሎትና የዓላማ ተመጋጋቢነት የተነሳ አሁን ያለበት ቦታው ስትራቴጂካዊ የስራ ግንኙነትና ጥምረትን ለመፍጠር እጅግ  ምቹ መሆኑን ያነሳሉ።

ትምህርት ቤቱ ትልቅ ስምና ታሪክ ያለው በርካቶችን ያፈራ የሀገር ቅርስ በመሆኑ የመፍረሱ ጉዳይ ሀገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር "ሌላ የንትርክ አጀንዳ ይዞ እንዳይመጣ" ሲሉም ስጋታቸውን ገልፀዋል።

የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ሀላፊው በተደጋጋሚ ቢደወልም ስልክ ባለማንሳታቸው የሚኒስቴር መስሪያ-ቤቱን ውሳኔውን በተመለከተ ሀሳቡን ለማካተት አልተቻለም።

የንግድ ስራ ትምህርት ቤት በ1935 ዓ.ም. በመካከለኛ ደረጃ ባለሙያዎችን ለማስመረቅ በአገሪቱ ታሪክ በንጉሱ /በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ/ የተቋቋመ የመጀመሪያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነው፡፡

Author: undefined undefined
ጦማሪ አዲስ ዘይቤ