ታህሣሥ 14 ፣ 2014

የዲጂታል የህክምና አማራጭ ተግዳሮቶች

City: Addis Ababaጤና

ቴሌሜዲሲን በታዳጊ አገሮችም የሆስፒታሎችን ሸክም ለመቀነስ ገንዘብንና ጊዜን ለመቆጠብ ሁነኛ መፈትሄ እንደሆነ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

Avatar: Mahlet Yared
ማህሌት ያሬድ

Mahlet is an intern at Addis Zeybe who explore her passion for storytelling

  የዲጂታል የህክምና አማራጭ ተግዳሮቶች

ዲጅታል የህክምና አገልግሎት በጤና ተቋማት ብቻ ተወሰኖ ላለዉ የህክምና አሰጣጥ ተጨማሪ አማራጭ ይዞ ብቅ ካለ አመታት ተቆጥረዋል። ታካሚዎች በስልክ፣ በበይነ መረብ፣ እንዲሁም በሞባይል መተግበሪያዎች አማካኝነት ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ሳያስፈልጋቸዉ የህክምና አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉባቸዉን መንገዶች ያካተተዉ የዲጂታል ህክምና በኢትዮጲያ በሚፈለገዉ መጠን አልተስፋፋም።

ከቅርብ አመታት ወዲህ በግል የጤና ተቋማት በኩል የተለያዩ ሙከራዎች ቢኖሩም የሚፈለገዉን ያህል ተደራሽ ሲሆኑ አይታይም። ባሳለፈነዉ አመት በስልክ ጥሪ አማካኝነት የቴሌ-ሜድስን የህክምና አገልግሎቶችን ለመስጠት አልሞ የተቋቋመዉ አይ-ጤና ለዚህ አንዱ ተጠቃሽ ነው።

ከህክምና ተቋማት ተመርቀዉ ስራ ማግኘት ባልቻሉ አራት የህክምና ባለሙያዎች ሀሳብ አመንጭነት የተመሰረተዉ አይ-ጤና የዲጂታል የጤና አገልገሎት አማራጮችን ከማስፋት ባለፈ የጤና ባለሙያዎች የስራ አጥነትን ችግር መቅረፍን አላማዉ አድርጎ መቋቋሙን መስራቾች ያስረዳሉ።

“ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱና የመጀመርያ የቴሌ ሜድስን አገልግሎት ሲሆን ከየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ስልካቸውን በመጠቀም ሃኪምን በቀጥታ አግኝተው ያጋጠማቸውን የጤና እክል ምክር ማግኘት የሚችሉበት ነው” የሚሉት  እየሩሳሌም ማሞ (ዶ/ር) የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ናቸዉ።                        

ደንበኞች ክፍያው አገልግሎቱን ፈልገው በሚደውሉበት ሰአት ከስልካቸው ላይ በደቂቃ ሁለት ብር ተቀናሽ ይደረጋል። በተጨማሪ  አይ ጤና ዲጂታል ሜድስን በተሰኘዉ የፌስቡክ ገጽ ታካሚዎች በቀጥታ ከሃኪሞች ጋር መገናኘት የሚችሉበት አሰራር አንዳለዉ እየሩሳሌም ያስረዳሉ።

የቴሌኮም አገልገሎት የጥራት ችግር ባልተቀረፈበት ሁኔታ በኢትዮጵያ የቴሌ ሜድስን አገልግሎት ተስማሚ አማራጭ እንዳልሆነ ተደረጎ የሚነሳዉ ሀሳብ በተመለከተ በተለይ በገጠራማው የኢትዮጵያ አከባቢ ከጤና ተቋም ተደራሽነት ይልቅ የእጅ ስልኮች ተደራሽነት በእጅጉ የላቀ ስለሆነ ይህን መሰል አገልግሎቶች ትልቅ ጠቃሜታ እንደሚኖረዉም ያነሳሉ።

በሌሎች አከባቢዎችም ቢሆን ሰዎች የጤና ችግሮችን ጤና ተቋም ላለመሄድ በሚል እሳቤ በቸልተኝነት ከሚያልፉት እና ለከፋ ችግር ከሚጋለጡ ይህን መሰል አገልግሎት በመጠቀም ለችግራቸው መውሰድ ያለባቸውን ትክክለኛውን እርምጃ በማወቅ እና በመገንዘብ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ያረጋል።

“ሁሉም የጤና ችግር ሃኪም ቤት አያስኬድም፤ በዚህ አገልግሎት ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱትን የታካሚ መጠን እና አይነት የሚወሰንበት እና ጤና ተቋማቶች ለተገቢው የታካሚ አይነት ትኩረታቸውን እንዲሰጡ ያረጋል” ሲሉ እየሩሳሌም  ይገልጻሉ።

አይ-ጤና አሁን ላይ ከህብረተሰቡ ባገኘዉ በጎ ምላሽ መሰረት ባንድ ጊዜ ብዙ ጥሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ሲስተም ከኢትዮ ቴሊኮም ጋር በመሆን በመዘርጋት ላይ ይገኛል። ተገልጋዮቻችን በአገልግሎቱ በጣም ደስተኛ ናቸው የሚሉት ዶ/ር እየሩሳሌም ደብቀውት የቆዩትን የጤና እክሎች ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መልኩ መወያየት መቻላቸው፣ ጤና ተቋም በአቅራቢያቸው የሌሉ ሰዎች ሃኪም ጋር ቀጥታ ተገናኝተው መመካከር መቻላቸው እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቅሞችን እንደሚያገኙበት ለማወቅ እንደቻሉ ይናገራሉ።

በአዲስ መልክ አገልግሎቱን ስንጀምር አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ እና ሶማሊኛ ቋንቋዎችን በመጨመር እና በክልል ከተሞች የማስተዋወቅ ስራ በመስራት ማስፋፋት አስበናል የሚሉት ዶ/ር እየሩሳሌም በአዲስና በተሻለ መልኩ ስራውን ለማስጀምር በምናደርገው ጥረት ላይ ከቴሌ በኩል ያለው አገልግሎት ቀልጣፋ ያለመሆኑ እንቅፋት እንደሆነባቸዉ ያነሳሉ።

ከወራት በፊት ወደ ስራ የገባዉ ዊኬር የተሰኘ ተቋም ተመሳሳይ የዲጂታል ጤና አገልገሎት ለመስጠት የተቋቋመ ነው። ታካሚዎች በሞባይል መተገበሪያ አማካኝነት ማግኝት የሚፈልጉትን አገልግሎት በመሙላት ቀጠሮ ማስያዝና አገለግሎቱን በቪዲዮ፣ በድምፅ እንዲሁም በጹሁፍ መልዕክት የጤና ባለሙያዎችን ማማከር የሚችሉበትን አገልግሎቶችን ይሰጣል።

ከዚህ በተጨማሪ በፌስቡክ ቴሌግራም ቲክቶክ ኢንስታግራም ገጾች ላይ በየቀኑ ከጤና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የሚለቀዉ ዊኬር ድንበኞቹ በአጭር የስልክ ቁጥር 9394 ላይ በመደወል የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራርም አለዉ።

የአከፋፈል ሁኔታዉ እንደ ታካሚው የህክምና ደረጃ ሲሆን ለምሳሌ ቀለል ያለ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች  ከ100 ብር እስከ 200ብር ድረስ እንደሚያስከፍሉ ከተቋሙ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል። ከበድ ያለ የህክምና ኬዝ እና እስፔሻሊስት ሃኪሞች የሚያስፈልጉ ሲሆን ደግሞ እንደ ህክምናው አይነት ታካሚዎች  እስከ 500ብር ድረስ ሊያስከፍሉ እንደሚችሉ ሰምተናል።

ታካሚው በሚፈልገው ቦታ እና ጊዜ የሚፈልገውን ህክምና በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል ይህም የህክምና ተቋማት ላይ የሚኖረዉን ጫና ከመቅነስም በላይ ታካሚዎች ቀለል ላለ ህክምና ሀኪም ቤት መሄድ ሳያስፈልጋቸዉ የሀኪም ምክረ ማግኘት መቻላቸዉ ተመራጭ ያደርገዋል የላሉ መስራቾቹ።

ሆስፒታል ሄዶ ለመታከም የሰው ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንደ አማራጭ መወሰድ እንደሚቻል ገልጸው እንዲሁም በባህላችን ምክንያት በአካል ሆስፒታል ሄዶ ለመታከም የሚከብዱ እንደ ወሲብ ችግር ያሉ የጤና ችግሮች ያላቸው ሰዎች መተግበሪያችንን ተጠቅመው የጤና ባለሙያዎችን ማማከር ይችላሉም ብለዋል።

 አሁን ላይ ኢንተርኔት አገልግሎት በሚደርስበት ቦታ ሁሉ ያሉ ታካሚዎች አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ የተናገሩት መስራቾቹ ከተለያዩ የኢትዮጽያ ክልሎች የተመዘገቡ የጤና ባለሙያዎች መኖራቸዉንም ይናገራሉ። ይህንንም አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ ባሉ ሆስፒታሎች ላይ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ የቀጣይ እቅዳችን ነው ሲሉም ሃሳባቸውን አጋርተውናል። 

ቴሌሜዲሲን በታዳጊ አገሮችም የሆስፒታሎችን ሸክም ለመቀነስ ገንዘብንና ጊዜን ለመቆጠብ ሁነኛ መፈትሄ እንደሆነ ባለሙያዎች ያነሳሉ። ይሁን እንጂ የቴሌሜዲሲን ትግበራ አሁንም በታዳጊ አገሮች ውስጥ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፣ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በታዳጊ አገሮች 90% የሚሆነው የቴሌሜዲሲን ፕሮጄክቶች የሚፈለገዉን ለዉጥ ማምጣት አልቻሉም።

በኢትዮጲያ የዲጂታል ህክምና አተግባብር ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የማህበረሰቡ የግንዛቤ እጥረት፤ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አናሳነት እንዲሁም የጤና ዘርፉ ከተለመደዉ አሰራር ያለመላቀቅ ሁኔታዎች የቴሌ ሜዲሲን አተገባበር ዉጤታማ እንዳይሆን ካደረጉ ምክኒያቶች ተደርገዉ ይጠቀሳሉ።

አስተያየት