ነሐሴ 27 ፣ 2013

በኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ የ100 ዓመት ጉዞ ሲዘከር

City: Addis Ababaየጥበብ ዐውድ

በያዝነው ሳምንት ከነሃሴ 21 እስከ 25 የቴአትር መቶኛ አመት ለመዘከር እንዲሁም ቴአትርን እናነቃቃ በሚል እሳቤ የአምስት ቀን ፌስቲቫል በትያትር ባለሙያዎች የተሰናዱ ከክልሎች የመጡ የአማተር ከያኒያን ስራዎች ለታዳሚ ሲቀርቡ ሰንብተዋል።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

በኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ የ100 ዓመት ጉዞ ሲዘከር

በጥቅምት ወር አጋማሽ በፌስቡክ ማህበራዊ ገፅ ላይ “በኢትዮጵያ ውስጥ ቴአትር አለ ወይስ ሞቷል?” በሚል መነሻ ሀሳብ ላይ መወያያ አጀንዳ ተከፍቶ የተለያዩ አንጋፋ እና ወጣት የቴአትር ባለሞያዎች ሀሳብ ሲሰጡበት ሰነበቱ።

ውይይቱ በብዛት “ቴአትር ሞቷል” ወደሚል ሃሳብ ማጋደሉን የታዘቡ እና ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን የተገነዘቡት ባለሙያዎች “ሞቷል ካልን መቀስቀስ የምንችለው እኛው ነን በማለት” ከማህበራዊ ድረ ገፆች ወርደው በመሰባሰብ መወያየት ጀመሩ። ውይይቱ ላለፉት ስድስት ወራት ዘወትር ዕሮብ በአስር ሰዓት በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ያለማቋረጥ ተከናወነ። የውይይቱ ዋና ማጠንጠኛ ሞያን መሰረት ባደረገ የበጎ ፍቃደኞች ስብስብ ቴአትርን እንዴት ማነቃቃት ይቻላል? የሚል ነበር። ይህ ውይይትም አድጎ እና ጎልብቶ ብዙዎችን እያቀፈ፤ የኢትዮጲያ ስለቴአትር የ100 ዓመት ጉዞ በተለያየ መልኩ ተዳሰሰ፤ ተዘከረ።

በያዝነው ሳምንት ከነሃሴ 21 እስከ ነሀሴ 25፣ 2013 ዓ.ም. የቴአትር መቶኛ አመት የአምስት ቀን ፌስቲቫል በሚል ስያሜ የዝግጅቱ ማጠቃለያ መሰናዶ በትያትር ባለሙያዎች የተሰናዱ፤ ከክልሎች የመጡ የአማተር ከያኒያን ስራዎች ለታዳሚ ሲቀርቡ ሰንብተዋል። 

በአምስቱ ቀናት ማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ አባ ጂፋር ለመፎ፣ ኢልማ ገልማ፣ ባዶ እግር፣ እቴጌ ጣይቱ፣ አንቲገን፣ ባቢሎን በሳሎን እና እያዩ ፈንገስ የተሰኙ ሌሎችም ትያትሮች ለተመልካች ቀርበዋል። 

የሀገራችን የቴአትር ጥበብን፣ ጠቢባን እና አፍቃሪዎችን ለማነቃቃት በተሰራው በዚህ “ስለ ቴአትር” በተሰኘው እንቅስቃሴ ከተነሱት ሃሳቦች መካከል አሁን ላይ ለሚታየው የቴአትር መቀዛቀዝ፣ ባለሞያዎችንም ከቴአትር ቤቶች እና መድረኮች መራቅ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች በዝርዝር የተለዩ ሲሆን ችግሩ መንግስት ጋር፣ ባለሙያዎች ጋር እና ታዳሚያን ጋር ሆነው መገኘታቸውን ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ብርሃኑ ለአዲስ ዘይቤ ነግሮናል። አክሎም እነዚህ ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፈታት ከቻሉ የቴአትር ጥበብ በሀገራችን አድጎ ለማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችየሚያበረክተው ሚና እጅግ ከፍ ያለ እንደሚሆንም ገልጿል።

“የቴአትራችንን ችግሮች ስንመረምር ዋነኛ ብለን ከምናነሳቸው ጉዳዮች አንዱ በሀገራችን ለቴአትር እንዲሁም በሰፊው ለኪነጥበብ ያለው የተዛባ አመለካከት አንዱ ነው። ለቴአትር ያለው አመለካከት ቴአትርን መውደድ፣ ቴአትርን መተግበር፣ በቴአትር መጠቀም እና ስለ ቴአትር መመራመርን ያጠቃልላል። በመንግስት በኩል ቴአትሩን ለልዩ ልዩ ህዝባዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ማነቃቅያ መሳርያ ብቻ አድርጎ ከመመልከት ጀምሮ በህብረተሰቡ ዘንድ የቴአትር ስራ የማዝናናት ዓላማ ብቻ ያለው አድርጎ መውሰድ በሀገራችን ሁለት በዋናነት የተለመዱ ጥግ የያዙ ሀሳቦች ናቸው።” የሚለው ዘሪሁን በነዚህ ሀሳቦች መሀል ያለው ይህ ጥበብ ምንም እንኳን ለፖለቲካውም ሆነ ለማዝናናቱ ያለው ጠቀሜታ የሚካድ ባይሆንም ሁሌም ፖለቲካ በመስራት እና በማዝናናት የተገደበ አለመሆኑን በመጥቀስ እና የቴአትር ሀሳብ እና ጥንተ ተፈጥሮ ከዚህ ይልቃል ብሏል። 

የቴአትር ጥበብ ሀሳቦችን በመተንተን፣ ምናቦችን በመተግበር እና ፍልስፍናዎችን በማብሰልሰል በሰዎች ህይወት ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል ዘርፍ መሆኑን ጨምሮ የሚናገረው ዘሪሁን “በዓለም ላይ በየጊዜው የተነሱ ልዩ ልዩ የቴአትር ፍልስፍናዎችን ስንመለከት ዋነኛ ዓላማቸው በራሳቸው ጊዜ እና ቦታ ያጋጠሙ ሰብዓዊ ችግሮችን የመፍቻ መንገዶችን ከመፈለገ የመነጩ ሆነው እናገኛቸዋለን። እነዚህ መፍትሄ የመሻት ህልሞች ግን መፍትሄዎቹን ከፖለቲካ ሰልፎች ወይም ከማዝናናት ጋር ብቻ የተጣመሩ አይደሉም። ከዚህም በሰፋ መፍትሄዎቹ እንደነገሩ ሁኔታ ከማብሰልሰል፣ ከመተንተን፣ እና የተግባር መንገዶችን ከመተለም ጋር የተያያዘ ነው።” ሲል ሃሳቡን ያስረግጣል ይላል።

ሌላኛዋ የዝግጅቱ አስተባባሪ አርቲስት መዓዛ ወርቁ “ከህገ መንግስቱ ጀምሮ ልዩ ልዩ ህጎች ቢወጡም ያን ያህል ግን ጥበቡን ሲደግፉ አይታዩም። ይባስ ብለው አንዳንዶቹ የቴአትሩን ጥበብ የሚያቀጭጩ እና የሚያዳክሙ ናቸው። ለምሳሌ ሁሌም የኪነጥበብ ባለሞያው የሚጮህበት የቀረጥ ጉዳይ ብናነሳ ኪነጥበቡ ከመደገፍ ይልቅ መጉዳት ላይ የሚያተኩር ነው። የቴአትርን ስራ በደንብ ተገንዝቦ የሚያግዝ የቀረጥ ስርዓት የለንም” ስትል ትናገራለች። 

እንደ መዓዛ ገለፃ የጥበብ ባለሙያዎችም የኪነጥበብን ጠቀሜታ በተግባር በታገዘ መልኩ አለማስረዳታቸው ችግር መሆኑ አይካድም። በነዚህም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ከታክስ እና መሰል የኢኮኖሚ ፍሰት ጋር ተያይዞ ያለው የመንግስት ህግ የቴአትር እንቅስቃሴውን ከመደገፍ ይልቅ ማሸማቀቅ እና መስበር ላይ ያተኩራል። በእያንዳንዱ የቴአትር እና የኪነጥበብ ስራ ሰንሰለት ላይ ያለው የታክስ፣ የህግጋት፣ የድጋፍ ማነስ እና ልዩ ልዩ አላስፈላጊ ህጎች ምክንያት የቴአትር ሥራዎች በተፈለገው መንገድ ሊጓዙ አልተቻላቸውም። በዚህ እና መሰል ምክንያቶች በአንድ ወቅት በሰፊው እጅግ በርካታ የቴአትር ስራዎችን ይከውኑ የነበሩ የግል የቴአትር ኢንተርፕራይዞች በአሁን ሰዓት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ጠፍተዋል።

በሌላ በኩል በዝግጅቱ ላይ ተገኝተን ያነጋገርነው አርቲስት በፍቃዱ ከበደ በበኩሉ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በአጠቃላይ ኪነጥበብን ሳንሱር የማድረግ ጉዳይ በህግ የታገደ ቢሆንም በተግባር ግን ተቃራኒ ጉዳዮች እንዳሉ እና በቴአትር ጥበቡ ላይ የነበረው እና ያለው በተዘዋዋሪ የሚደረግ ሳንሱር የኪነጥበብ ባለሞያው ራሱም ሆነ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ሰርቶ ለመኖር እንደከለከለው ይናገራል። “መንግስት የቴአትር ጥበቡን ሲያሻው የሚጠቀምበት፣ ሳይፈለግ ሲቀር ዞር ብሎ የማያየው፣ ድጋፍ ለመስጠትም ብዙም የማይሳሳለት አካሉ መሆኑ ቲያትር እንዲቀጭጭ ምክንያት ሆኗል” ሲልም ሃሳቡን ያስረግጣል።

በፍቃዱ መንግስት ኪነጥበቡን ለመደገፍ ያወጣቸውን ልዩ ልዩ የባህል፣ ፊልም፣ የቋንቋ እና መሰል ፖሊሲዎች እያደነቀ ይህ ፖሊሲ የቴአትር ጥበብ ለሀገር ሊያበረክት የሚችለውን አቅም የሚገነዘብ እና እውቅና የሚሰጥ፣ መንግስት እና የመንግስት መዋቅር ለቴአትር እድገት የየራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችል፣ እንዲሁም የቴአትር ጥበብ በሀገሪቱ ልማት ላይ የድርሻውን እንዲወጣ የሚጋብዝ መሆን እንደሚገባውም ሃሳቡን አስተላልፏል።

በመሆኑም ቴአትር በኢትዮጵያ  ከተጀመረ ጀምሮ የነበረውን ሁኔታ በመዘከር ሲከናወን የቆየው ይህ ፌስቲቫል በሀገራችን የመጀመርያ ከሆነው ከሀገር ፍቅር ቴአትር ቤትን ጀምሮ በሰባት ልዩ ልዩ ቲያትር ቤቶች የተለያዩ ቆየት ያሉ እና አዳዲስ ቴትሮችን ሲያሳይ ቆይቷል። ‘ቴአትርን እንደግፍ፤ ቴአትርን እናልማ። መንግስት ስርዓታዊ በሆነ መልኩ ለቴአትር እድገት ማነቆ የሆኑ እንቅፋቶችን በማስወገድ የቴአትርን ልማት ዕውን ያድርግ።” የሚለው የስለ ቴአትር አስተባባሪ ቡድን ባለሞያዎችም ዘመኑ እና ጊዜው የዋጀውን የስልጣኔ ትሩፋት ሁሉ በመጠቀም ለተመልካች ቀልብ እና ልቦና የቀረቡ የቴአትር ውጤቶችን በማቅረብ ቴአትራችን ከገጠመው መቀዛቀዝ ለማንቃት በመርሃ ግብሩ ላይ ቃል ገብተዋል። 

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በጥናት እና ምርምር የታገዘ የቴአትር ዕድገት ሚናን በመተለም ለቴአትር ልማት ድጋፍ እንዲያደርጉ እንዲሁም ባለሀብቶች ቴአትርን እንደ አንድ የንግድ አማራጭ ተመልክተው ለእድገቱ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም ስለዚህ ዝግጅት ውጣውረድ እና ስኬት ያወራን አርቲስት አብዱልከሪም ጀማል “ለወራት በመመካከር እና ለባለድርሻ አካላትም ተከታታይ መድረኮችን በማመቻቸት ሀሳቦች፣ ጥያቄዎችና አስተያቶች ተንሸራሽረው። ለዚህ አላማ በተከፈተው የፌስቡክ ገጽ የቀድሞ ስራዎችን በፎቶ በማጀብ አንዱ ለሌላው በማጋራት ብዙ ትዝታዎች ተነስተው ለዛሬው ክብረበዓል ደረስን" ይላል።

እንደ አብዱልከሪም ገለፃ እንቅስቃሴው ሲጀመር ቲያትር ቤቶች በኮቪድ ምክንያት በስራ ላይ ያልነበሩ ቢሆንም በተፈጠረው መነቃቃት ብዙ ቲያትሮች ተሳታፊ ሆነው በሀገር አቀፉ የቲያትር ፌስቲቫል ላይ የተለያየ ዘውግ ያላቸው ከዚህ ቀደም የታዩ የሙሉ ጊዜ ቲያትሮች፣ ቅንጭብ ተውኔቶች፣ ከተለያዩ የክልል ከተሞች እና ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ቲያትሮች፣ የህጻናት ቲያትሮች፣ በኦሮምኛ ቋንቋ የተሰሩ ቲያትሮች እና የቀድሞ ቲያትሮች በስክሪን እና በፊትለፊት ለተመልካቾች ቀርበዋል፡፡ 

በዝግጅቱ የመዝጊያ ስነስርዓት ላይ ታድመን ካናገርናቸው ታዳሚያን መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ስንታየሁ ማሩ “የኢትዮጵያ ቲያትር እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ አሳስቧቸው እና ቲያትር ከየት ወዴት ብለው የኢትዮጵያ ቲያትር 100ኛ አመትን ለማክበር በ”ስለ ቲያትር” በራሳቸው ተነሳሽነት ተሰብስበው ይሄን ያሳዩን ባለሙያዎች ሊመሰገኑ ይገባል” ሲል ምስጋናውን አቅርቧል።

አስተባባሪ ኮሚቴው ለዚሁ ፌስቲቫል መሳካት የተሰባሰቡ ትርዒት አቅራቢዎች ፣ ይህንኑ ፌስቲቫል ለማስተናገድ ገበያቸውን ዘግተው አዳራሾችን የፈቀዱ ቦታዎችን እና ያለመታከትና መሰልቸት ቲያትርን ቀዳሚ ጉዳያቸው አድርገው፣ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ዝግጅቱ እውን እንዲሆን ያደረጉትን በጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎችን እና የቴአትር አክባሪዎችን አመስግኗል።

አስተያየት