ጥቅምት 6 ፣ 2014

ለቦረና መከራ የሆነው የተፈጥሮ ክስተት

City: Addis Ababaዜና

“ለቦረና ከብቶቹ ሁሉ ነገሩ ናቸው። ሰላምታቸው እንኳን ‘Rooba Quuftanii ፣ Isiniif Roobee፣ Loon Nagaa? (ዝናብ ጠገባችሁ፣ ዘነበላችሁ፣ ከብቶች ሰላም ናቸው?’) የሚል ነው” ይላሉ ቦረናንና ነዋሪዋን የሚያውቋት!

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

ለቦረና መከራ የሆነው የተፈጥሮ ክስተት

“ለቦረና ከብቶቹ ሁሉ ነገሩ ናቸው። ሰላምታቸው እንኳን ‘Rooba Quuftanii ፣ Isiniif Roobee፣ Loon Nagaa? (ዝናብ ጠገባችሁ፣ ዘነበላችሁ፣ ከብቶች ሰላም ናቸው?’) የሚል ነው” ይላሉ ቦረናን እና ነዋሪዋን በቅርበት የሚያውቋት ሰዎች የከብቶቹ ህልውና የአርብቶ አደር ነዋሪዎቿ ህልውና መሆኑን ሲናገሩ።

በደቡብ ኦሮሚያ ክልል በምትገኘው ቦረና ዞን ወቅቱን ጠብቆ መዝነብ የነበረበት ዝናብ በመዘግየቱ እስካሁን ድረስ ንብረትነታቸው የ1,916 አባወራዎች የሆኑ ከ4,000 በላይ ከብቶች መሞታቸውን እና ከ9 ሺ በላይ የቀንድ ከብቶች በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ የቦረና ዞን የእንስሳት ሀብት ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ነዋሪዎቹ ይህ ተፈጥሮዓዊ ክፉ ክስተት መታየት ከጀመረ አንድ ወር መሆኑን ሲናገሩ በዚህም በሺሕዎች የሚቆጠሩ ከብቶች በተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች እንደሞቱ ገልጸዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ወጥቶ የነበረው የቦረና ዞን የእንስሳት ሀብት ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው የቀንድ ከብት ሞት በብዛት እየተመዘገበባቸው ከሚገኙት ወረዳዎች መካከል በተልተሌ ወረዳ ከ1486 በላይ፣ በድሎ ወረዳ ከ992 በላይ፣ በምኦ ወረዳ ከ496 በላይ፣ በአሬሮ ወረዳ ከ219 በላይ፣ በጉቺ ወረዳ ከ216 በላይ እንዲሁም በያቤሎ ወረዳ ከ116 በላይ ከብቶች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን አሁንም ዝናብ ካልዘነበ ወይንም ደግሞ አስፈላጊው ድጋፍ ካልተገኘ በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ ከ9 ሺ በላይ የቀንድ ከብቶች መኖራቸውም መረጃው ያመላክታል።

የክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ኤጀንሲ በበኩሉ በጉዳዩ ላይ እያደረገ ስላለው እርምጃ ሲናገር የክልሉ መንግስት በቦረና ለተከሰተው ችግር በኦሮሚያ ካቢኔ የፅደቀ ለእንስሳት መኖ ግዢ የሚሆን ባጀት ወደ ቢሮው መድረሱን በመግለጽ፣ የሚፈፀመው ግን በመንግስት የግዢ ሂደት ውስጥ ካለፈ በኃላ መሆኑናንና በእንዲህ ያለ ክስተት ጊዜ ለከብቶች የሚሆን መኖ በባለሞያ መጠናት ስላለበት አዲስ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ መሆኑን አስረድቷል። በመሆኑም የሳር ግዢው ሂደት በፍጥነት ተጠናቆ ከቀናት ባነሰ ጊዜ ለአርብቶ አደሮች እንዲደርስ እንደሚደረግ ገልጿል።

በበልግ እና በክረምት የተጠበቀው ዝናብ በማነሱ የተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ያሳሳባቸው በጎ ፍቃደኛ ዜጎች በማህበራዊ ሚዲያ በተለያየ መንገድ እርዳታ ለማሰባሰብ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ከነሱም መካከል አዲስ ዘይቤ ያነጋገረችው ጥላሁን ግርማ የተባለ ግለሰብ “ወሎ ሲጨነቅ የሚጨነቀው የወሎ ሰው ብቻ፣ ቦረናም ሲቸገር የሚጨነቀው የቦረና ሰው ብቻ መሆን የለበትም። በሰብዓዊነት አዛምድ ስለሌለ የአንዳችን ህመም የሌላችን መሆን ስላለበት ችግሩን ከሰማን ጀምሮ ከያቤሎ ከንቲባ አቶ ጃርሶ ጎሊሳ ጋር እና ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር እየተነጋገርን ድጋፍ እያሰባሰብን እንገኛለን” ሲል ያስረዳል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው የያቤሎ ከንቲባ ጃርሶም በዞኑ ከተከሰተው ድርቅ እና የመኖ እጥረት ጋር ተያይዞ አብዛኛው የአርብቶ አደር ማህበረሰብ በምግብ እጦት እየተሰቃየ ባለበት በዞኑ ደረቅ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በበጎ አድራጎት ድርጅቶች የምግብ ዕርዳታ በቋሚነት አለመድረሱን ገልጸው አሁን ከተከሰተው አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር በጥንቃቄ በመስራት የሚሰበሰበው እርዳታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

አያይዘውም የቦረና ጉዳት ለመላው ሀገሪቱ ጉዳት መሆኑን ሲያስረዱ የቦረና ከብት ማለት ኢትዮጵያ በዓለም የኤክስፖርት ገበያ ላይ በስፋት የምትንቀሳቀስበት ሀብቷ መሆኑን ይናገራሉ።

የቦረና ዞን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሊባን ከበደ በበኩላቸው ጽ/ቤታቸው ሁኔታውን ለመቅረፍ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለማሳተፍ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። “ዞናችን ከስድስት ሚሊዮን በላይ ከብቶች አሉት ፣ አብዛኞቹን በምግብ ማቅረብ አንችልም” ሲሉ አክለውም ፣ “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከጠቅላላው ከብቶች 10 በመቶውን በከፍተኛ ሁኔታ ለማምረት እየሠራ ነው። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማሳተፍ ወደ አምስት ወረዳዎች መኖ አከፋፍለናል” ብለዋል።

የቦረና አስተዳደር ፅህፈት ቤት በአሁን ሰዓት ነዋሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ በገለጸው መሰረት 539,679 ዜጎች የውሃ እጥረት አጋጥሟቸው ከነዚህም ውስጥ 177,553 ዜጎች ብቻ የቦቴ ውሃ ሊያገኙ ችለዋል። በምግብ እጥረት ደግሞ 6,398 ህፃናት፣ 9,078 እናቶች እና 2,226 አዛውንቶች ላይ የጤና ችግር ሲታይ ለ188,864 ሰዎች የምግብ እርዳታ ቢሰጥም አሁንም ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ 7,540 ከብቶች ሲሞቱ 13,641 ከብቶች በሰው ድጋፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። 

በመሆኑም የዞኑ አስተዳደር እንስሳቶቹን ለማትረፍ 2,463,213 ቤል ሳር ከመንግስት እንደተጠየቀ ገልጾ ከችግሩ ስፋት እና አሳሳቢነት አንፃር ግን የመንግስት እርዳታ ብቻ በቂ ስለማይሆን የሚመለከተው አካል ሁሉ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል። በ2009 ዓ.ም በዞኑ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ እንደነበርም በመግለጽ በመንግስት እና በህዝብ ትብብር መቆጣጠር እንደተቻለ አስተዳደሩ አውስቷል።

አስተያየት