መጋቢት 10 ፣ 2014

ኢትዮጵያ ከአለም ደስተኛ ሀገሮች ዝርዝር 131ኛ ተቀመጠች

City: Addis Ababaዜናማህበራዊ ጉዳዮች

እንደተቀረው ዓለም ሁሉ በወረርሺኙ ከመፈተኗ አልፎ የተራዘመ ጦርነት ያሳለፈችው ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚዘጋጀው የደስተኛ ሀገራት ደረጃ 131ኛ ላይ ተቀምጣለች።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ኢትዮጵያ ከአለም ደስተኛ ሀገሮች ዝርዝር 131ኛ ተቀመጠች
Camera Icon

Credit: Compassion International

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት መፍትሔዎች ጥምረት በየዓመቱ ይፋ የሚደረገው የአለም ደስተኛ ሀገሮች ዝርዝር ሠሞኑን ይፋ ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት አንድ ደረጃ ዝቅ ብላ ከ146 ሀገራት 131ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። 

ትላንት መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው የ2022 ሪፖርት ከአንድ እስከ 50 ባሉት ደረጃዎች ውስጥ የአፍሪካ ሀገራት የሉበትም፤ ሞሪሽየስ ከዓለም 52ተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሆናለች። 

ግብፅ፤ ቻድ እና ኢትዮጵያን በማስከተል 129ኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ዚምባብዌ፣ ሊባኖስ እና አፍጋኒስታን ደስተኛ በሆኑ ህዝቦች በቅደም ተከተላቸው የመጨረሻዎቹ ሶስቱ ሀገራት መሆናቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል።

ፊንላንድ ለተከታታይ አምስት ዓመታት ደስተኛ ህዝቦች የሚኖሩባት ሀገር በመሆን የአንደኛነት ደረጃን ይዛለች። ዴንማርክ በሁለተኛነት እንዲሁም አይስላንድ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።  

ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝና በርካታ አስከፊ ጦርነቶች እየታመሰች ባለበት በዚህ ወቀት የአለም ሀገራቱን የደስተኝነት ደረጃን ‘በጨለማ ወቅት ተስፋን ያመላከተ ነው’ በሎታል ሪፖርቱ። 

ደረጃዉ አማካይ ጤናማ የእድሜ ጣሪያ፣ ለዜጎች የሚደረጉ ማህበራዊ ድጋፎችን፣ ኑሯቸውን ለማሻሻል ያላቸውን ነፃነት እና እድል እንዲሁም ለሙስና ያላቸውን አመለካከትና ሌሎችንም መስፈርቶችን ታሳቢ በማድረግ ይዘጋጃል።  

በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም. በተደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የፀደቀው ‘ሪዞሉሽን 65/309- ደስታ፡ ሁሉን አቀፍ ለሆነ ልማት’ የተሰኘው ውሳኔን መሰረት አድርጎ የተጀመረው የደስተኛ ህዝቦች መገኛ ሀገራት ደረጃ ዘንድሮ 10ኛውን ሪፖርት አውጥቷል።

የሪፖርቱ አዘጋጅ የመንግስታቱ ድርጅት የሀገራት መንግስታት የህዝቦቻቸው ደስታ እና ደህንነት መረጋገጥ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ቁልፍ ነው ብሎ በማመኑ የሚዘጋጅ ዓመታዊ ሪፖርት ነው። 

አስተያየት