ኅዳር 8 ፣ 2014

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሩብ ዓመቱ በ4.4 ቢሊየን ብር የግብርና ምርቶችን ማገበያየቱን አስታወቀ

City: Addis Ababaዜናኢኮኖሚንግድ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት፤ 51 ሺህ 640 ሜትሪክ ቶን የግብርና ምርቶችን በ4.4 ቢሊየን ብር የግብይት፤ ምርት ቅበላና ርክክብ መፈጸሙን ለአዲስ ዘይቤ በላከዉ መግለጫ አሳውቋል።

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሩብ ዓመቱ በ4.4 ቢሊየን ብር የግብርና ምርቶችን ማገበያየቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት፤ 51 ሺህ 640 ሜትሪክ ቶን የግብርና ምርቶችን በ4.4 ቢሊየን ብር የግብይት፤ ምርት ቅበላና ርክክብ መፈጸሙን ለአዲስ ዘይቤ በላከዉ መግለጫ አሳውቋል።

ምርት ገበያው 17,690 ቶን ቡና፤ 15,445 ቶን ሰሊጥ፤ 3,024 ቶን ነጭ ቦሎቄ፤ 4,731 ቶን አኩሪ አተር፥ 3,368 ቶን አረንጓዴ ማሾ፤ 1,904 ቶን ዥንጉርጉር ቦሎቄ፤ 215 ቶን ቀይ ቦሎቄና 5 ቶን የርግብ አተር በሩብ ዓመቱ አገበያይቷል።

ባለፉት አራት ወራት የአረንጓዴ ማሾ ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ የጨመረ ሲሆን በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ አማካይ የግብይት ዋጋው ብር 7,235.00 በኩንታል የነበረው በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም. ወደ ብር 7,841.00 አድጓል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የአረንጓዴ ማሾና የቀይ ቦሎቄ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል ሲል ምርት ገበያዉ በመግለጫ አስታዉቋል።  

በቅርቡ ጥቁር አዝሙድ፣ ድንብላል፣ አብሽ እና ቁንዶ በርበሬ፤ እንዲሁም ጓያ ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ እንደተካተቱ ተገልጾ ከተያዘው ምርት ዘመን ጀምሮ ግብይታቸው የሚካሄድ ይሆናል። በቅርቡ ደግሞ እጣን፣ ከርቤና አብከድ ወደ ግብይት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 3 ቀናት ይፈጅ የነበረውን የቡና ምርት ቅበላ፣ ርክክብና ግብይት የአሰራር ሂደት ወደ አንድ ቀን ማሳጠሩን የምርት ገበያው በመግለጫዉ አስታውቋል።

እንዲሁም በቡና ናሙና አወሳሰድ ወቅት የሚሟሉ መስፈርቶችን ለመለካት በቤተ-ሙከራ ይመረመር የነበረበትን ሂደት ናሙናው በተወሰደበት ቦታ/መጋዘን ላይ ማጣራት እንዲቻል በመደረጉ በቡና ጥራት እና በአቅራቢዎች ጊዜ ላይ መሻሻል ፈጥሯል።

በቡና ግብይት ላይ የተደረገው ሌላኛው ማሻሻያ የቡና ደረጃ አመዳደብ ስርዓቱን ከዓለም አቀፍና ሃገር አቀፍ ደረጃ አወሳሰን እርከኖች ጋር ተቀራራቢና ወጥ እንዲሆን ማድረግ ሲሆን ከነበረበት ዘጠኝ ደረጃዎች ወደ አምስት ዝቅ ተደርጓል። የምርት ገበያው የደንበኞችን ድካም የሚቀንሱና የግብይት ስርዓቱን የሚያዘምኑ ማሻሻያዎች እንደሚከውን ገልጿል።

በ2013 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ614 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶችን በ39.6 ቢልየን ብር ያገበያየ ሲሆን ቡና እና ሰሊጥ ከፍተኛውን ድርሻ ወስደው ነበር።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ራዕይ ዋላ ቀር እርሻ ላይ የተመሰረተውን የሃገሪቱ ግብርና ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከገበሬው እስከ ነጋዴው፣ ከነጋዴው እስከ አቀናባሪው፣ ከአቀናባሪው እስከ ላኪው ሁሉንም ተገበያዮች የሚያገለግል አዲስ ዘመናዊ  የግብይት ስርዓት ከሚያዚያ 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በስራ ላይ የሚገኝ ተቋም ነው።

አስተያየት