መስከረም 14 ፣ 2015

የጦርነት ድባብ ያጠላበት ደማቁ የዓዲግራት የመስቀል በዓል

City: Addis Ababaባህል ወቅታዊ ጉዳዮች

“ለመስቀል በዓል የዓጋመ ህዝብ ማዕከል በሆነችዋ በዓዲግራት ከተማ የማይገኝ ሰው በህይወት እንደሌለ ይቆጠራል” -የአካባቢው ተወላጅ

Avatar: Kalayou Hagose
ኻልኣዩ ሓጎሰ

ኻልኣዩ ሓጎሰ የህግ ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን ይፅፋል። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የጦርነት ድባብ ያጠላበት ደማቁ የዓዲግራት የመስቀል በዓል
Camera Icon

ፎቶ፡ ሓድጊ ቱሪዝም

መስከረም 17 ጠዋት የመስቀል ደመራ ከመለኮሱ በፊት በገጠሩ የአዲግራት (ዓጋመ) አካባቢዎች አንድ ወይም ሁለት አባወራ ሆነው ከቤት ቤት በመዞር

ዓኩኽ ዓኳዃይ፣ 

ብርሃን ግዳይ መስቀል ግዳይ” ይላሉ። 

በከተማው ደግሞ ሰዎች ችቦ ለኩሰው በተመሳሳይ መልኩ “ዓኩኽ ዓኳዃይ ብርሃን ግዳይ መስቀል ግዳይ” እያሉ ደመራዉን ለመለኮስ ደመራ ወደተዘጋጀበት ስፍራ ያመራሉ። 

“ዓኩኽ ዓኳዃይ” ማለት “ችቦዉን አቃጥለው ወይም ለኩሰው” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ሰዎች “ብርሃን ግዳይ መስቀል ግዳይ” እያሉ ወደቤት ሲገቡ ወይም ደመራ ወደተዘጋጀበት ቦታ ሲሄዱ ደግሞ “ብርሃን (መስቀል) ይዤላችሁ መጥቻለሁ ተቀበሉኝ” የሚል መልእክት እንዳለው ደራሲ እና የታሪክ ተመራማሪው አቶ ገብረኪዳን ደስታ በ2011 ዓ.ም ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል። 

በመስቀል ጠዋት ወጣቶች ተሰባስበው ችቦ በማቃጠል “ሆያ ሆየ” እያሉ ይጫወታሉ። በዓዲግራት ከተማ “መይዳ ዓጋመ” ሜዳ የሚዘጋጀው ደመራም ሆነ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ደመራ የሚለኮሰው መስቀሉ በተገኘበት ቀን በመስከረም 17 እንደሆነ ዲያቆን ገብረማርያም ያስረዳል። 

ተናፋቂው እና ተወዳጁ የመስቀል በዓል በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች በደመቀ መልኩ የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል ሲሆን በክልል ደረጃ ደግሞ በዓዲግራት ይከበራል። የትግራይ መዲና በሆነችዋ በመቀለ ከተማ ደግሞ በጮምዓ ተራራ ላይ ይከበራል። 

ከነጭ ማር በሚሰራ ሜስ (ጠጅ)፣ ጥሕሎ፣ በለስ እና በመሳሰሉት የምትታወቀው የዓዲግራት ከተማ ከመቀለ በ138 ኪሜ ርቀት በሰሜን አቅጣጫ ትገኛለች። ጥንታዊው እና ታላቁ የደብረዳሞ ገዳም የሚገኝባት ይህች ከተማ ለነዋሪዎችም ሆነ ለጎብኚዎች ተሰማሚ የሆነ የአየር ሁኔታ እንዳላት ይነገርላታል።    

የመስቀል በዓል “የዓጋመ ህዝብ ማዕከል በሆነችዋ በዓዲግራት ከተማ የማይገኝ ሰው በህይወት እንደሌለ ነው የሚቆጠረው”  በማለት የመስቀል በዓል በዓጋመ ህዝብ ምን ያክል ተናፋቂ እንደሆነ የዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ገብረተንሳይ ያስረዳል። 

የመስቀል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ 

ዓዲግራት እንደተወለደ የሚናገረው ዲያቆን ገብረማርያም “መስቀል በዕለተ ዓርብ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትና በደሙ የቀደሰው ስለሆነ መስቀል ኅይላችን፣ መፅናኛችን፣ ቤዛችን እንዲሁም የነፍሳችን መዳኛ ነው ብለን እናምናለን” ይላል። 

የመስቀል በዓል አከባበር ሃይማኖታዊና  የራሱ የሆነ ታሪካዊ አመጣጥ እንዳለውም አጫውቶናል ዲያቆን ገብረማርያም። 

እንደዲያቆኑ ገለጻ መስቀሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት በኋላ በክርስቶስ ተከታዮች በኩል እንደምልክት እንዳይታይ ለሶስት መቶ አመታት ማንም በማያገኘው ቦታ ተቀብሮ ቆይቷል። 

ሆኖም በአራተኛው ክ/ዘመን አካባቢ የሮማ ገዢ የነበረው የንጉስ ቆስጠንጢንዮስ እናት የሆነችዋ ንግስት እሌኒ ከብዙ ዓመታት በኋላ የተቀበረዉን መስቀል መፈለግ እንደጀመረች የንዋየ ቅዱሳት አቅራቢ የሆኑት ቀሲስ ተኽላይ (ስም የተቀየረ) ያስረዳሉ። 

“ንግስት እሌኒ የለኮሰችው ታላቅ ደመራ ተቃጥሎ ጭሱ መስቀሉ ወደ ተቀበረበት አቅጣጫ በመጨስ ቦታውን ጠቁሟታል፤ በዚህም የተነሳ ለሶስት መቶ ዓመታት ከተቀበረበት ቦታ መስከረም 17 ቀን አስቆፍራ አስወጥታዋለች” ይላሉ ቀሲሱ ስለ መስቀል መገኘትና ደመራ አጀማመር ሲያስረዱ። 

“መስቀሉንም የማይዝ ከኋላዬም የማይከተለኝ የኔ ሊሆን አይገባውም በማለት እየሱስ ክርስቶስ ምን ያክል ዋጋ እንደከፈለልን እና መስቀለ ሞቱን እለት እለት እያሰብን ልንኖር እንደሚገባን ወንጌል ይሰብካል” ይላል ዲያቆን ገብረማርያም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ለመስቀል የምትሰጠውን ቦታ ሲገልጽ። 

ትኋን ውጣ፣ ቁንጫ ግባ

እግር ጥሎት የመስቀል ወቅት ወደ ትግራይ በተለይም ወደ ዓዲግራት ያቀና ሰው “ዓኩኽ ዓኳዃይ ብርሃን ግዳይ መስቀል ግዳይ፤ ትዃን ውፃእ ቁንጪ እተው” የሚል ነገር መስማቱ አይቀሬ ነው። 

ከላይ እንደተገለጸው ሰዎች ቤት ለቤት እየሄዱ አልጋ ስርም ሳይቀር የተለኮሰ ችቦ ይዘው ትኋን ዉጣ፣ ቁንጫ ግባ ይላሉ።  ይህ የራሱ የሆነ ታሪካዊ አመጣጥና ትርጓሜ እንዳለው የሚናገሩት አቶ ገብረኪዳን ደስታ “ትኋን ጠላት ነው፣ ቁንጫ ደግሞ ሓበሻ” ነው ሲሉ ይገልፃሉ። 

በትኋን የተመሰለው በጥንት ጊዜ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣው ወራሪው ቱርክ ሲሆን በቁንጫ የተመሰለውና ግባ የተባለው ሓበሻ ደግሞ ወገን የሆነው የሃገር ልጅ እንደነበር የታሪክ ተመራማሪው አስረድተዋል። 

ደመራው የሚለኮሰው መስከረም 16 ወይስ 17?

ደመራ መስከረም 16 ቀን የሚለኮስባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ይታወቃል፣ ሆኖም በመላው ትግራይ የመስቀል በዓል የሚከበረው መስቀሉ ተገኘ ተብሎ በሚታመንበት ቀን በመስከረም 17 ሲሆን፣ ደመራውም የሚለኮሰው በዚሁ ቀን ነው። 

እንደማንኛውም የትግራይ አካባቢ በዓዲግራትም ደመራ የሚበራው በመስከረም 17 ሲሆን፣ መስከረም 16 ደግሞ ችቦ ተለኩሶ ሆያ ሆየ ይባላል። 

በመስከረም 16 ቀን የሚለኮሰው ችቦ እና ወጣቶች “ሆያ ሆየ” ሲሉ መስቀሉ እንደጠፋና ፍለጋ ላይ እንደሆኑ የሚያሳይ ሲሆን፣ 17 ላይ የሚለኮሰው ደመራ ደግሞ የመስቀሉን መገኘት የሚያበስር ነው። 

ወደ ራያ አካባቢ ደግሞ በተለየ ሁኔታ ወጣቶች መስከረም 16 “ሆያ ሆየ” እያሉ ሌሊቱን ሙሉ ቤት ለቤት እየዞሩ ብር ይሰበስባሉ። የአካባቢው ሰውም ያለውን ለወጣቶቹ ያለስስት ይሰጣል። በአንድ አነስተኛ መንደር ብቻ እስከ 3000 ብር እና ከዚያ በላይ ሊሰበሰብ ይችላል። 

ወጣቶቹ መስከረም 17 ቀን ጠዋት በአጥቢያቸው ወደሚገኝ ቤተ ክርስትያን በመሄድ የሰበሰቡትን ገንዘብ ያስረክባሉ። ከዚያም ከደብሩ ቀሳውስት ምርቃት ተቀብለው ቀኑን በሞቀና በደመቀ ሁኔታ ተሰባስበው ያሳልፉታል። 

“አንድ ሰው ጤነኛ እስከሆነ ድረስ የተደመረው ደመራ እየተቃጠለ ቤት ቁጭ ብሎ የሚያይ ይኖራል ብየ አላምንም” የሚለው አቶ አብርሃ ገብሩ ሲሆን “ሰው ይቅር እና የቤት እቃዎችም የመስቀል ብርሃን ተሳታፊ እንዲሆኑ በአጥር ላይ ይሰቀላሉ” ሲል ያስረዳል። 

እንደአቶ አብርሃ ገለጻ ቤት ውስጥ ያለ ማንኛውንም በቀላሉ ሊነሳ የሚችል እቃ በእንጨት አጥሮች ላይ በማንጠልጠል “ብርሃን አየ” ይባላል። 

አብርሃ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆን በየአመቱ የመስቀል በዓል ለማክበር ወደተወለደባት የዓዲግራት ከተማ ያቀናል። “ሆኖም በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በዓሉን ለማክበር መሄድ ይቅርና ቤተሰቦቼ እንኳን በህይወት መኖራቸውን አላውቅም፣ ሁለት ዓመት ሊሞላኝ ነው” ሲል በሃዘን ይናገራል። 

ለሁለት አስርት አመታት ከአዲስ አበባ ወደ ዓዲግራት በመሄድ የመስቀል በዓል እንዳከበረ የሚናገረው ስሙ

እንዲጠቀስ ያልፈለገ የአዲስ አበባ ነዋሪ በበኩሉ እንደዩኒቨርሲቲ መምህሩ ገብረትንሳይ ሁሉ “ለመስቀል በዓጋመ መሬት የማይገኝ ሰው በህይወት እንደሌለ ነው የሚቆጠረው፣ በህይወቴ ከሚጸጽቱኝ ነገሮች አንዱና የመጀመርያው አሁን ለመስቀል በዓል ከቤተስቤ ጋር በምወዳት የዓጋመ ማዕከል በዓዲግራት ከተማ አለመገኘቴ ነው” ሲል ቁጭቱን አጋርቶናል። 

ለመስቀል በዓዲግራት ምን ይከናወናል?

ዓዲግራት ወደከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበልና ለማስተናገድ በዓሉ ከመድረሱ በፊት ዝግጅቷን ለማጠናቀቅ ሽር ጉድ ትላለች። 

በዚህ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ የመስቀል በዓል ተሳታፊ ለመሆን አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ የአካባቢው ተወላጆችም ሆኑ ጎብኚዎች በየአመቱ ወደከተማዋ ይጎርፋሉ።  

ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች፡ ከራያ እስከ ወልቃይት፣ ከዛላምበሳ እስከ ሽከት፣ ከኩናማ እስከ ኢሮብ ያሉ ሰዎችም የመስቀል በዓል ለማክበር በዓዲግራት ይከትማሉ። 

ከነዚህ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች የራሳቸው የሆነ ባህልና የአኗኗር ዘዬ ስላላቸው በበዓሉ በቋንቋቸው እና ባህላቸው መሰረት መድረክ ላይ በመውጣት ለህዝቡ ትዕይንት ያሳያሉ። 

በበዓሉ ዋዜማ ማለትም በመስከረም 16 የፈረስ ግልቢያ፣ ስፖርታዊ ውድድድሮች፣ ባህላዊ ትርዒቶች፣ የተራራ ሩጫ፣ የእግር ኳስ ጨዋታ እና የመሳሰሉ ውድድሮች ይከናወናሉ።

በተጨማሪም በበዓሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ያሬዳዊ ዝማሬዎች፣ ወረቦች፣ በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን የተዘጋጁ መዝሙሮችና ትምህርተ ወንጌል ስለሚቀርብ በዓሉ አሸብርቆና ደምቆ ይውላል።

መስከረም 17 ላይ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች ከተደረጉ በኋላ ደመራ ይለኮሳል፣ ደመራው በሚቃጠልበት ጊዜ ሰዉ በመዝሙር፣ በጭብጨባ፣ በዘፈን እና እልልታ ፈጣሪን ያመሰግናል።

ደመራው ከተቃጠለ በኋላ ሰዎች ቅቤና የደመራውን አመድ አንድ ላይ በመቀላቅል የመስቀል ምልክት በግንባራቸው፣ በእንብርታቸው እና በጉልበታቸው ይቀባሉ። ይህም የመስቀሉ ምልክት ከክፉ የመጠበቅ ሃይል አለው ብለው በማመን የሚያደርጉት ነው።  

ከከተማዋ ትንሽ ወጣ ብሎ ወደገጠሩ ማህብረሰብ ያቀና ሰው በየአካባቢው ደመራ ተሰርቶ፣ በአርሶ አደሩ ቤት የተለያዩ ለበዓሉ መብልና መጠጦች ተዘጋጅተው ማየቱ የግድ ይሆናል። ከነዚህም ውስጥ ጥሕሎ፣ ሜስ (ጠጅ)፣ እና ስዋ (ጠላ) ይገኙበታል። 

በእነዚህ አካባቢዎች መስከረም 16 በድንጋይ ላይ የበቆሎ እሸትን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን በመጥበስ እየበሉና እየተጫወቱ ያሳልፉታል። 

አስተያየት