የቤት ለቤት የማድረስ አገልግሎት “ዴሊቨሪ” በአዳማ

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅነሐሴ 7 ፣ 2013
City: Adamaቴክማህበራዊ ጉዳዮችንግድ
የቤት ለቤት የማድረስ አገልግሎት “ዴሊቨሪ” በአዳማ

ከአንድ ዓመት በፊት ባሉት ጊዜያት በአዳማ ከተማ የተለያዩ ቁሶችን ቤት ለቤት ማድረስ (ዴሊቨሪ) አገልግሎት እምብዛም የተለመደ አልነበረም፡፡ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ቁጥርም አነስተኛ ነበር፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ወቅት ግን የቤት ለቤት እቃዎችን በተለይም ምግቦችን የማድረስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥር ማሻቀብ፣ የአገልግሎት ዐይነቶቹ መበርከት እንደጀመሩ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ አገልግሎት ሰጪዎቹ በአብዛኛው በሞተር ሳይክል እና በባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) የሚጠቀሙ ሲሆን፤ አገልግሎት ፈላጊዎች በመደበኛና የሞባይል ስልክ ቁጥሮች ተጠቅመው ያዘዟቸውን ተቀብለው ደንበኞች ያሉበት ቦታ ድረስ የፍላጎታቸውን ያቀርባሉ፡፡ እንደ ስምምነታቸው በነጻ ዴሊቨሪ ወይም የዴሊቨሪውን አገልግሎት ጨምረው ክፍያ ይፈጽማሉ፡፡

በኢትዮጵያ በአንጻሩ አዲስ የሆነው እና በመስፋፋት ላይ የሚገኘው፣ የኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ እቀባን ተከትሎ ይበልጥ የተነቃቃው የ”ዴሊቨሪ” አገልግሎት እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የበሰሉ ምግቦችን በማቅረብ ይጀመር እንጂ የኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላም ባልበሰሉ የምግብ ሸቀጦች እና በሌሎችም ቁሳቁሶች እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ 

የአዳማው የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ተስፋልደት ብዙወርቅ የዴሊቨሪ አገልግሎቶች ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት፣ በኮቪድ 19 የእንቅስቃሴ እቀባ ወቅት እና ከዚያ በኋላ ያለውን ሁኔታ እንዲህ ያስቃኘናል፡፡

የ“አዳማ ዴሊቨሪ” የቤት ለቤት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ደንበኛ የሆነችው ምህረት ተስፋዬ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት 2ኛ ልጇን ነፍሰጡር በነበረችበት ወቅት ከጓደኛዋ ስለአገልግሎቱ ሰምታ መጠቀም እንደጀመረች ትናገራለች። “ወቅቱ እጅግ አስፈሪ ስለነበረ ለእኔ እንደነብስ አድን ናቸው” ትላለች። 

ከምግብ ትዕዛዝ፣ ከመድኃኒት ግዢ፣ የአገልግሎት ክፍያን ጨምሮ እስከ አስቤዛ ማሟላት ድረስ አገልግሎት ታገኝ እንደነበር ምህረት ትናገራለች። የአገልግሎት ሰጪዎቹ መስተንግዶም ሆነ ለአገልግሎታቸው የሚጠይቁት ክፍያ ተመጣጣኝ እንደነበረ ታስረዳለቸ። 

ሌላኛው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የቪዲዮግራፊ ሞያ ላይ የተሰማራው ወጣት ተስፋዬ ጣሰው በበኩሉ በተለያየ ጊዜ በተጠቀማቸው አገልግሎቶች ደስተኛ እንደነበረና ከፍጥነትና ከአገልግሎት ጥራት አንጻርም ጥሩ እንደሆኑ ይናገራል።

“ሼፍ መሳይ በርገር እና ፒዛ” በአዳማ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት የቤት ለቤት አገልግሎት በመስጠት ላይ ተሰማርቶ የነበረ ድርጅት ሲሆን  በአሁኑ ወቅት በራሱ የተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎቱን አቋርጧል፡፡ የሬስቶራንቱ ስራ አስኪያጅ ሳምሶን ለማ የመቋረጡ ምክንያት ናቸው ብለው የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቅሳሉ።ለአገልግሎት ያሰማሩት ሞተር ሳይክል ላይ የግጭት አደጋ በመድረሱ፣ ለዴሊቨሪ የሚያስከፍሉት 10 ብር ብቻ በመሆኑ እና ከሚያወጣው ወጪ ጋር ባለመመጣጠኑ፣ ቅርንጫፍ ሱቆቹን ወደ 4 በማሳደጉ ደንበኞቹን አገልግሎቶቹን በአቅራቢያቸው ማግኘት ስለሚችሉ በሚል አሳቤ አገልግሎቱ እንደተቋረጠ የሬስቶራንቱ ስራ አስኪያጁ ይገልፃሉ፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ የተቋቋመው “አዳማ ዴሊቨሪ” መስራቾቹን ጨምሮ ለስምንት ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል። ከሦስቱ መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ብርሃነአብ ዘለቀ ድርጅቱን በስራ አስኪያጅነት ይመራል፡፡ ድርጅታቸው ምግብ ነክ ምርቶችን ቤት ለቤት ከማድረስ በተጨማሪ መድሃኒቶችን ጨምሮ ማንኛውንም ትዕዛዝ እንደሚቀበል ይናገራል፡፡ እንደመብራት፣ ውሃ እና ስልክ የመሳሰሉ ወርሃዊ ክፍያዎችንም ደንበኞቹን ወክሎ ክፍያ ይፈጽማል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገደቡ ተነስቶ ሰዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ሲመለሱ በስራችሁ ላይ ምን አይነት ለውጥ አስተዋላችሁ?ለሚለው ጥያቄ ወጣት ብርሃነአብ ሲመልስ "ስራው የተጀመረው ኮሮናን ተንተርሶ ስለነበር ይቀንሳል የሚል ስጋት ነበረብን፡፡ ነገር ግን ስራው አልቀነሰምም ሰዉም ወደ እንቅስቃሴዬ ተመልሻለው ብሎ አገልግሎቱን አላቋረጠም። አገልግሎቱ ከሚሰጠው እረፍት አንፃር የምትከፍለው ዋጋ ተመጣጣኝ ነው" ይላል። አዳማ ዴሊቨሪ የአገልግሎት የሚያከፍለው በኪሎሜትር ነው፡፡ መነሻውን ብር 30 በማድረግ ኪሎሜትሩ በጨመረ ቁጥር የአገልግሎት ክፍያው የሚያድግበትን አሰራር ይከተላል፡፡ ከፍተኛው የአገልግሎት ክፍያ 50 ብር ነው። 

ሌላኛው በአዳማ ከተማ የቤት ለቤት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት “ዴሊቨር አዳማ” ባለቤትና መስራች ወጣት እስራኤል የኔሰው ከአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ጋር በነበረው ቆይታ ሰኔ 2012 ዓ.ም. የተጀመረው አገልግሎቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ እጅግ መወደዱን እስራኤል ያነሳል። እንዲሁም ካለው አሰራር አንፃር በስልክ ጥሪ ትዕዛዝ ብቻ በሙሉ ኃላፊነት መልዕክቶችን ይዘው እንደመስራታቸው የኅብረተሰቡን ጨዋነትንም የ“ዴሊቨር አዳማ” ባለቤት ያመሰግናል።

በአዳማ ከተማ ውስጥም በየትኛውም ርቀት ላይ ለሚገኙ ደንበኞች አገልግሎቱን በ40 ብር እየሰጠ ይገኛል።

"በሁለት ሳምንት ውስጥ ስራውን በ“ኦንላይን” እንጀምራለን። በውስጡ እንደምግብ እና መጠጥ፣ መድሃኒቶች፣ ለጋራጅ መለዋጫ እቃዎች ፣ የስጦታ እቃዎች፣ የአልባሳት፣ የተሽከርካሪ ሻጮች እና የአገልግሎት ክፍያን ያካተተ የሞባይል መተግበረያ ሙከራ ላይ ይገኛል።" ሲል ወጣት እስራኤል ስራውን  ይበልጥ ለማስፋት ስላለው እቅድ ያብራራል። 

ብዙ ርቀት ሳይጓዝ ሊፈታ የሚገባው የሁለቱ ድርጅቶች የስም መመሳሰል ላይ ያወራናቸው ሁለቱም የስራ ፈጣሪ ወጣቶች ስሙ ላይ ጊዜ ከማጥፋት ይልቅ በየግላቸው የተሻለ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ላይ ማተኮራቸውን ይናገራሉ።

ከአዳማ ዴሊቨሪ ጋር በትብብር የሚሰራው የቤኪ-ማፊ ሬስቶራንት ስራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ በረከት እያሱም ድርጅቱ የቤት ለቤት አገልግሎት ከሚሰጠው አዳማ ዴሊቨሪ ጋር በጋራ መስራት የጀመረው ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ጋር በተያያዘ እንደሆነና ከመጡለት ሁለት ድርጅቶች አወዳድሮ እንደመረጠና በአገልግሎቱም ደስተኛ መሆናቸውን ለደንበኞቻቸው ተጨማሪ የተደራሽነት አማራጭ እንደሆናቸውም ይናገራሉ። ሬስቶራንቱ ካሉት ብዙ ደንበኞች አንፃር በቤት ለቤት አገልግሎት ሰጪዎች የሚወጣው ትዕዛዝ በተጠቃሚዎች ከሚታዘዙ ወጪ ትዕዛዞች አንጻር አሁንም አነስተኛ እንደሆነ ያነሳሉ። ሬስቶራንቱ ግን በተቻለ ፍጥነት እነኚህን አገልግሎቶች በቅልጥፍና እየሰጠ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

አቶ በረከት ቢሻሻል የሚሏቸውን ሐሳቦችም እንዲህ ያነሳሉ፡፡ ከስድስት ወራት በፊት ወደ ስራ የገባው ሌላኛው አገልግሎት ሰጪ የፈገግታ በርገር ባለቤት አቶ ሐይማኖት ነጋሽ በዋናነት ከዴሊቨር አዳማ ጋር እየሰሩ እንደሆነ እንዲሁም ሌሎችም ሲመጡ እንደሚያስተናግዱ ነግረውናል። ይሁን እንጂ  በተጠቃሚዎች ዘንድ የዋጋ ተመን ላይ ቅሬታ እንደሚሰሙ እንዲሁም በተጠቃሚዎች ዘንድም በአካል ተገኝቶ መጠቀም ይበልጥ እንደሚመረጥና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ተበረታቶ የነበረው ገበያ መልሶ መቀዛቀዙን አክለው ይገልፃሉ።

አቶ ሐይማኖት እነኚህን ጉዳዮች ታሳቢ ባደረገ መልኩ በቅርብ ወራት  የድርጅታቸውን ምርቶች በተቻለ ዋጋ፣ ጥራት፣ የተሻለ አስተሻሸግ እና አቀራረብ ለተጠቃሚ ለማድረስ የራሳቸውን የቤት ለቤት አገልግሎት ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆኑ ነግረውናል። በዚህ ሒደት ግን ስራው ለሌሎችም የአገልግሎቶች ሰጪዎችም ክፍት እንደሚሆን ገልፀዋል።

Author: undefined undefined
ጦማሪተስፋልደት ብዙወርቅ