የንባብ ባህል እና ተግዳሮቶቹ

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅጳጉሜ 3 ፣ 2013
City: Adamaማህበራዊ ጉዳዮች
የንባብ ባህል እና ተግዳሮቶቹ
Camera Icon

Image source: The Reporter

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የንባብ ባህልን ከክረምት ጋር ማያያዝ እየተለመደ መጥቷል። ተማሪዎች የአንድ እርከን የትምህርት ዘመናቸውን አጠናቀው ለሌላኛው የሚዘጋጁበት የሽግግር ጊዜ በመሆኑ ወቅቱን ተመራጭ አድርጎታል። የክረምቱን መግባት ተከትሎ በርካታ አዳዲስ መጻሕፍት ለንባብ የመብቃታቸው ሰበብም ይህ ነው። የኢንተርኔት ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ የመዝናኛ እና የዕውቀት ምንጭ የሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት በተለይም የማኅበራዊ ሚድያው የንባብ ባህልን አቀጭጯል፤ ከወረቀት ሕትመት ውጭ ያሉ የንባብ መንገዶች መበርከት፣ መረጃ አሳሾችን በመጠቀም መረጃዎችንና ማስረጃዎችን የማግኘት ልፋት መቀነሱ የንባብ ባህልን አዳክሟል፤ የሚሉ ቢኖሩም አባባሉ በጥናት ባለመደገፉ ሐሳቡን ተቃርነው የሚቆሙም አልጠፉም።

ሌላው ዓለም ይህንን ለውጥ ተመልክቶ መጻሕፍትን እና ሌሎች ዕውቀት ማስተላለፊያ ዘዴዎችን ወደ ዲጅታል ቴክኖሎጂው በመቀየር እያዘመናቸው ቢገኝም፤ በመላው ዓለም የሚሰራጩ፣ በብዙ ሺህ ቅጂዎች ለሕትመት የሚበቁ የሕትመት ውጤቶች አሁንም አሉ።

ወጣት ያቤጽዕ ኃይለማርያም የአዳማ ከተማ ኗሪ ነው። በ2013 ዓ.ም. ከአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በኮምፒውተር ሳይንስ ተመርቋል። ከጓደኛው ጋር በመሆን “ዞማ ቲዩንስ” የተባለ በዲጂታል መንገድ “ኢ-ቡክ” በወረቀት ያልታተሙ ሶፍት ኮፒ መጻሕፍት እና “ኦድዮ ቡክ” በንባብ የቀረቡ የድምጽ መጻሕፍትን ማንበብ የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ አበልጽገው አጠናቀዋል። በቅርቡም ሥራቸውን ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ እየሰሩ ነው። ወጣት ያቤጽ እንደሚለው “አብዛኛው ሰው የሚጠቀው ዲጂታል ቴክኖሎጂ ስለሆነ መጻሕፍቱን ምቹ በሆነው መንገድ አቅርበናል” ይላል።

ከጥቂት ወራት በፊት በማኅበራዊ ሚድያ (ፌስቡክ) የተካሄደ “የብርሃን መንገድ” የተሰኘ ንቅናቄ መስራች የሆነው ወጣት አወቀ ዘሩ “የብርሃን መንገድ በዋናነት መጽሐፍ የማንበብ ባህልን የሚያበረታታ ነው” ይላል። ዓላማው ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ታራሚዎች መጻሕፍት ማሰባሰብ፣ መለገስንና ማኅበረሰባዊ ንቃትን ለማምጣት መሆኑን እና ለዚህም እንደሚሰራ ይናገራል። “የንባብ አብዮት” በተሰኘ የመልእክት መለዋወጫ “ሜሴንጀር ግሩፕ”ም ንባብ ነክ መረጃዎችና የልምድ ልውውጥ እንደሚካሄድ ነግሮናል።

እየደበዘዘ ብሎም እየጠፋ መጥቷል የሚል ተደጋጋሚ አስተያየት የሚሰነዘርበት የ“ሒስ” ባህልም ለንባብ ባህሉ መዳከም የራሱን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ብዙዎች ያምናሉ። በሂስ ባህሉ መዳከም ወይም ሕጉን አለመከተል ሰዎችን ከንባብ አርቋል የሚል እምነት ያላቸው እነኚህ አስተያየት ሰጪዎች ሂስ “ውዳሴ” ወይም “ስድብ” መስሎ ታይቷል ሲሉ ይወቅሱታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመጻሕፍት ዋጋ መናር ካለው የኢኮኖሚ ጫና አንጻር የንባብ ባህልን እየጎዳው ይገኛል። በመጻሕፍት ማከፋፈል ስራ ላይ የተሰማራው የምንተስኖት መጻሕፍት መደብር ባለቤት ምንተስኖት ተካልኝ እንደሚለው “የታሪክ መጻሕፍት በብዛት ይነበባሉ” ከንባብ ባህል ጋር በተያያዘ የአንባቢ ቁጥር ቢጨምርም በኮቪድ-19 ወቅት ሥራቸው እጅግ ቀንሶ እንደነበር ይናገራል። በአሁኑ ወቅት የትምህርት መርጃ መጻሕፍት በብዛት እንደሚሸጡና በሌሎች ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሚሰሩት መጻሕፍት የዋጋቸው ውድነት በአንባቢዎች እንዳይመረጡ ስለማድረጉ ይናገራል። አቶ ምንተስኖት “የዋጋው መወደድ በንባብ ባህል ላይ ያለው ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ምንም ጥያቄ የለውም” ባይ ነው።

 ይህ ደግሞ ካለው የጀርባ እና ማከፋፈያ ዋጋ በላይም በመጻሕፍት አዟሪዎችም ሆነ ሌሎች አካላት ዋጋውን በምላጭ በመፋቅ የሚደረግ የዋጋ ማስተካከልም እንደሆነ ይናገራል። ይህ ሁኔታ በጊዜ ካልታረመ በሒደት ስራውን አቀጭጮ እንዳያጠፋውም ስጋቱን ገልጿል። ከእለት ወደ እለት የመጻሕፍት ዋጋ ማሻቀብ በተለይም ለወጣቶች እና ተማሪዎች የማይቀመስ እየሆነ መምጣት ከንባብ ባህሉ ባልተናነሰ ፈተና እየሆነ መጥቷል። ይህንንም ከግምት በማስገባት ይመስላል ወጣት ስንታየሁ ዘነበ እና ሌሎች 14 ጓደኞቹ ጋር ሆነው የመጸሐፍ እቁብ የመሰረቱት። በ15 ቀን መቶ ብር አዋጥተው ለባለእድሉ እንደፍላጎቱ የ1500 ብር መጻሕፍ ይገዙለታል። “ከእቁቡ የሚሰበሰበው ገንዘብ የሚውለው ለመጻሕፍት ግዢ ብቻ ነው። ብሩን በጥሬው መቀበል ወይም ለሌላ ዓላማ ማዋል አይፈቀድም” የሚለው ወጣት ስንታየሁ በወር አንድ ግዜ በተመረጡ መጻሕፍት ላይ ውይይት እንደሚካሄድም ነግሮናል። የመጻሕፍት ፍቅር ያሰባሰባቸው ወጣቶቹ የአባላቶቻቸውን ቁጥር በመጨመር መለስተኛ ቤተ-መጻሕፍት የማቋቋም እቅድ እንዳላቸውም አብራርቶልናል።

በ1994 ዓ.ም. የተመሠረተው “ብሩህ ተስፋ ቤተ-መጻሕፍት” አንድ ሰራተኛ እና እስከ 20 የሚደርሱ በጎ ፍቃደኞች አሉት። የሚገኘው በአዳማ ከተማ ቀበሌ 19 ብሔራዊ ሎተሪ አዳማ ቅርንጫፍ አካባቢ ነው። በሦስት ፈረቃ በጠዋት፣ ከሰዓት እና ማታ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት አገልግሎት ይሰጣል። ቤተ መጻሕፍቱ በቅርብ ጊዜ በአካባቢው ተወላጆች እድሳት ተደርጎለታል። የአዲስ ዘይቤ አዳማ ሪፖርተር በቤተመጸሐፍቱ ስትጠቀም አግኝቶ ያነጋራት ተማሪ ቤተልሔም ወንድሙ “ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በጥሩ ሁኔታ እያገዘኝ ነው” ትላለች። ታዳጊዋ መጻሕፍት ተውሳ ከማንበብ በተጨማሪ የዋይ-ፋይ ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኗንም ነግራናለች።

ከአዳማ በአሰላ መንገድ 20 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኘው አዋሽ መልካሳ በጥር 2006 ዓ.ም. የተመሠረተው “የአዋሽ መልካሳ የነገው ተስፋ ቤተ መጻሕፍት” ይገኛል። በቤተ-መጸሐፍቱ በጸሐፊነት የሚያገለግለው ወጣት በኃይሉ ኢቲቻ “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ት/ቤቶች ክረምቱን በሙሉ በማስተማር ላይ በመሆናቸው ምንም የተለየ ስራ አልተሰራም ብሎናል። አክሎም አገልግሎቱን መጠቀም የሚፈልግ ሰው ለመልሶ ማጠናከሪያ ይውል ዘንድ በቀን 1ብር መጻሕፍት እንሚያከራዩ ይናገራል። በአሁን ወቅት ከ1600 በላይ የመጻሕፍት ስብስቦች እንዳሉም ነግሮናል። የንባብ ባህል በአዋሽ መልካሳ ምን ይመስላል ያልነው ወጣቱ “ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ዕያሳየ ነው በየእለቱም የሚጠቀመው ሰው ቁጥር እየጨመረ ነው” የሚል ምስክርነቱን ሰጥቷል።

Author: undefined undefined
ጦማሪተስፋልደት ብዙወርቅ