ሚያዝያ 30 ፣ 2014

ነዋሪዎችን ወንዝ ያስወረደው የአሰላ እና በቆጂ የውሃ ችግር

City: Adamaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

የአካባቢው ህብረተሰብ የንፁህ ውሃ መጠጥ አቅርቦት ጥያቄ ከአዲሱ ፕሮጀክት ጋር ብቻ የሚፈታ እንደሆነ ነዋሪዎችም ሆነ የጉዳዩ ባለድርሻ አካላት ይስማማሉ

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ነዋሪዎችን ወንዝ ያስወረደው የአሰላ እና በቆጂ የውሃ ችግር
Camera Icon

Credit: Social Media

ከባህር ወለል በላይ 2430 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው የደጋማዋ አሰላ ከተማ ነዋሪዎች ላለፉት አራት ዓመታት በውሃ እጥረት የተነሳ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መቆየታቸውን ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

በሰባት ቀበሌዎች የተዋቀረችው አሰላ በአሁኑ ወቅት የውሃ አገልግሎት የምታገኘው በፈረቃ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ጭራሽ አገልግሎቱ መቋረጡም ታውቋል። 

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁን ወቅት ከአሸበቃ ወንዝ የምትጠቀመው አሰላ ከዚህ ቀደም በከተማዋ አቅራቢያ አርዶ ከሚባል ምንጭ ውሃ ታገኝ ነበር። ይህ ምንጭ በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት ጊዜውን ጨርሶ አገልግሎት መስጠት አቁሟል። የቀድሞ የአርዶ ውሃ ፕሮጀክት የውሃ መስመሮች በአሁን ሰዓት አገልግሎት ከሚሰጠው የአሸበቃ ውሃ ፕሮጀክት መስመር ጋር ተገናኝተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል። 

ከ20 አመት በፊት ለአምስት ዓመታት ብቻ ለአሰላ ከተማ ውሃ አገልግሎት እንዲሰጥ በዲገሉ እና ጢዮ ወረዳ አሸበቃ ወንዝ ላይ የተሰራው የውሃ ፕሮጀክት የማስፋፊያ እና እድሳት ስራ ሳይሰራለት በመቆየቱና በየጊዜው የነበረው የህዝብ ቁጥር መጨመር የውሃ አቅርቦቱ ወደ ፈረቃ ለመዞር ተገዷል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተመደበ በጀት 350 ሺ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የውሃ ፕሮጀክት ከሁለት ዓመታት በፊት ቁፋሮው ተጀምሮ ነበር። ይህ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም ተጠናቅቆ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀውና 1.4 ቢሊዮን ብር የተበጀተለት ፕሮጀክት በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራ ቢሆንም ለአራት ጉድጓዶች የሚሆኑ ከጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ስበው የሚያወጡ ራይዘር ፖምፖች ወደ ሀገር ውስጥ አለመግባታቸውና እንዳሰጋው የከተማው ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ገልጿል። 

ከፍተኛ የግብርና ምርት አምራች የሆነው የአሰላ ከተማ ዙሪያ ከራሷ ከከተማዋ የንግድ እና ትራንስፖርት ማዕከልነት ጋር ተዳምሮ የሰዎች እንቅስቃሴ የሚበዛበት አካባቢ እንደመሆኑ የውሃ ፍላጎቱም በዛው ልክ ከፍተኛ ነው። የውሃ ፈረቃው ርዝመት ከ10 እስከ 15 ቀናት ይደርሳል የሚሉት ነዋሪዎች የወንዝ ውሃ ለመቅዳት መገደዳቸውን ይናገራሉ።

አሰላን አቋርጠዋት ከሚያልፉ ወንዞች መሀከል ወልኬሳና ኮምቦልቻ የተባሉት ይገኙበታል። እነዚህ ወንዞች በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ እንደመሆናቸው ከፍተኛ የብክለት ደረጃ ቢኖራቸውም አማራጭ ያጡት ነዋሪዎች የወንዞቹን ውሃ እንዲጠቀሙ መገደዳቸውን ይናገራሉ።

የአሰላ ከተማ ቀበሌ 09 ነዋሪ የሆነችው ሐሊማ የተከሰተው የውሃ ችግር ከፍተኛ እንደሆነ ትገልጻለች። “በአቅራቢያችን ወልኬሳ ወንዝ ይገኛል፤ የውሃ መጥፋት እጅግ ስላስመረረን በዚህ ዘመን ውሃ ከወንዝ ወርደን ለመቅዳት ተገደናል” የምትለው ሐሊማ ውሃው ድፍርስ በመሆኑ ለመጠቀም ማጥለል እና ማፍላት ግድ ስለሆነ ለጊዜ እና ለገንዘብ ብክነት እንደዳረጋቸው ትናገራለች። 

“አሁን በስራ ላይ ያለው ፕሮጀክት የዛሬ ሃያ አመት የተሰራ ሲሆን አገልግሎት የመስጠት አቅሙ 18% ነው። “ይህ ባለበት ሁኔታ የውሃ ችግር የለም ማለት አንችልም" የሚሉት የአሰላ ከተማ ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ከድር አረባ መፍትሔው አዲሱን ፕሮጀክት በፍጥነት ማጠናቀቅ ነው ይላሉ። 

በእምነት በለጠ የዲንሾ አካባቢ ነዋሪ ስትሆን በመኖሪያ አካባቢዋ በክረምት ወቅት ካልሆነ በበጋ ወራት የውሃ አገልግሎትጭራሽ እንደሌለ ትናገራለች። “አንድ ባለ 20 ሊትር ጄሪካን ውሃ በ10 ብር ነው ገዝተን የምንጠቀመው” ትላለች በእምነት ብዙ ቤተሰቦች በተለይም ህጻናት በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ።

ይህ የውሃ አቅርቦት ችግር በአሰላ ከተማ ውስጥ በ2007 ዓ.ም የተመሠረተው አርሲ ዩኒቨርሰቲ ውስጥም ይስተዋላል። አልፊያ ጀማል በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ተማሪ ስትሆን በተማሪዎች መኖሪያ አካባቢ የውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ መቸገራቸውን ትናገራለች። “በየቀኑ ሁለት ሊትር የታሸገ ውሃ በ20 ብር ገዝተን ነው የምንጠጣው፤ በተማሪ አቅም እጅግ ከባድ ነው” የምትለው አልፊያ ለመታጠቢያ የሚሆን ውሃ በየጊዜው በውሃ ጫኝ መኪና እንደሚመጣላቸውና ብዙ ተማሪዎች በጋራ እንደመኖራቸው መጠን ከፍተኛ የንጽህና ችግር እንደፈጠረባቸው ገልጻለች። 

የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኛ የሆነው ናፍጋሪ ተቋሙ ለሰራተኞቹ ካዘጋጃቸው መኖሪያ ህንጻዎች በአንዱ ላይ ነዋሪ ሲሆን የውሃ አገልግሎት ከተቋረጠ ከአራት ዓመት በላይ እንደሆነው ተናግሯል ። እሱም እንደአልፊያ “ውሃ የምናገኘው ዩኒቨርሲቲው በውሃ ጫኝ መኪና አምጥቶ ለእያንዳንዳችን በበርሜል ሲገለብጥልን ነው" ይላል። 

የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የበጋ ወቅቱ መርዘም እና ተደጋጋሚ የመስመር ስርቆት ከዚህ ቀደም የነበረው የውሃ ችግር ላይ ተጨማሪ ተግዳሮት እንደሆነ የሚናገሩት ኃላፊው አቶ ከድር፣ ባለፉት ሁለት ወራት ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር ገጥሞን ነበር ይላሉ።

በአሁን ወቅት እየዘነበ በመሆኑ የአሰላ ከተማ በሁለት መንገድ እፎይታ አግኝቷል ያሉት አቶ ከድር ህዝቡ ዝናቡን በቀጥታ በማቆር እየተጠቀመ እንደሆነና ከአሰላ በ20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኙ የአሰላ የውሃ ምንጮች ያሉባቸው ዲገሉ እና ጢዮ የሚባሉ አካባቢዎች ላይ ያሉት ምንጮችም ስለሞሉ ውሃው ፓሞፕ ሳይደረግ ወደ ከተማዋ መምጣት መቻሉን ገልጸዋል። 

የኤሌክትሪክ ኃይል ማነስ ሌላኛው የአሰላ ውሃ አቅርቦት ችግር ነው። ከውሃ ምንጮቹ ወደ ውሃ ማጣሪያው ጥሬ ውሃን ለማድረስ እንዲሁም ለከተማዋ ነዋሪዎች ውሃ ለማቅረብ የተለያዩ ፓምፖች ጥቅም ላይ ይውላሉ። እነዚህ ፓምፖች በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ካላገኙ  ውሃ ማስተላለፍ ከባድ መሆኑን አቶ ከድር አረባ ያስረዳሉ።

“ችግሩን ለመፍታት ከአዳማ ዲስትሪክት ጋር ተነጋግረን ኃይል ቢጨመርም ለውጥ አላመጣም” የሚሉት ኃላፊው የኤሌክትሪክ ኃይሉ የፓምፕ ማሽኖችን እያስነሳ ያለው በምሽት ወቅት በሌሎች ኢንደስትሪዎች የኃይል ፍላጎት ሲቀንስ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት ለነዋሪዎች እየቀረበ ያለውን የውሃ አገልግሎት ከምሽቱ 6 ሰዓት በኋላ በለሊት ለመስጠት መገደዳቸውን ይናገራሉ።

ሌላኛው ለከተማዋ የውሃ አቅርቦት ተጨማሪ ችግር የሆነው የውሃ መስመር ስርቆት ነው። መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የአሰላ ከተማ ውሃ መስመር ላይ ከከተማው 20 ኪሜ ርቀት 'ዲገሉ' በተባለ አካባቢ በተፈጸመ ስርቆት የአሰላ ከተማ የውሃ አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ እንደነበር ታውቋል። 

የአሰላ ከተማ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ እንደገለጹት 'ዲገሉ' አካባቢ የሚፈጸመው የመስመር ስርቆት እና ጉዳት በስፍራው ባሉ ነዋሪዎች እርሻ እና መኖሪያቸውን አቋርጦ የሚያልፈው የውሃ መስመር ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም በሚል ሰበብ ሆን ተብሎ የሚፈጸም እንደሆነ ይናገራሉ።

ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው አቶ ከድር አረባ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ከተፈጸመው ስርቆት በኋላ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሁለት ጊዜ በአካባቢው ተመሳሳይ ስርቆት መከሰቱን ገልጸው መፍትሔ ለመስጠት የአሰላ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል። 

የአካባቢው ህብረተሰብ ጥያቄ ከአዲሱ ፕሮጀክት ጋር የሚፈታ እንደሆነ ነዋሪዎችም ሆነ የጉዳዩ ባለድርሻ አካላት ይስማማሉ። ሰኔ 30/2014 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ቃል የተገባለት የውሃ ፕሮጀክት የ350 ሺህ ነዋሪዎችን ጥም ይቆርጣል ተብሎ ይጠበቃል። ከ90% በላይ የተጠናቀቀው ፕሮጀክት አብዛኛው ስራ ተጠናቆ የኤሌክትሮሜካኒካል ስራውና ማሽኖቹ እንደቀሩ ለማወቅ ተችሏል።

“ለአራት ጉድጓዶች የሚሆኑ ራይዘር ፓምፖች ተሰርተው ቢያልቁም በኮቪድ-19 እና የተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገር ውስጥ አልገቡም” የሚሉት ኃላፊው ፓምፖቹ በጊዜው ከደረሱ ሰኔ 30/2014 ዓ/ም ፕሮጀክቱ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ሌላዋ የውሃ ችግር እየፈተናት የምትገኘው በቆጂ ከተማ ናት። ከአርሲ ዞን መቀመጫ አሰላ 54 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው እና ብዙ የኢትዮጵያን ስም ያስጠሩ አንጋፋ አትሌቶችን ያፈራችው ደጋማዋ በቆጂ ከባህር ወለል በላይ 2810 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች። የበቆጂ 150 ሺህ አካባቢ የሚገመቱ ነዋሪዎች እንደአሰላዎቹ በቂ የውሃ አቅርቦት ካገኙ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል። አንድ ጄሪካን ውሃ በ10 ብር ገዝተው እንደሚጠቀሙ ኗሪዎቹ ይናገራሉ።

“በቆጂ ውሃዋ የታሸገ ውሃን ያስንቅ ነበር” የሚሉት የበቆጂ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ ጸሐይ በአሁኑ ወቅት ግን የውሃ እጥረቱ እንደፈተናቸው ይናገራሉ። ሩቅ ከሚገኙ ሰፈሮች በጋሪ ውሃ ለመቅዳት እንደተገደዱ የነገሩን ወ/ሮ ጸሐይ በተለይ አቅመ ደካማ ሰዎች ለከፍተኛ ወጪ እና እንግልት መዳረጋቸውን ይጠቁማሉ።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የበቆጂ ከተማ አስተዳደር የውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ወሰኑ ለማ እንደሚሉት የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚፈታው ፕሮጀክት ስራው ተጠናቅቆ ርክክብ መጀመሩን ነግረውናል። አንዳንድ ርክክብ በተደረገባቸው አካባቢዎች ግን የኤሌክትሪክ ኃይል ማነስ ችግር እንደገጠማቸው ይናገራሉ።

“ውሃውን ለመግፋት የምንጠቀማቸው ማሽኖች ከ380 ቮልት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ይፈልጋሉ። አሁን ላይ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ግን ከ350 ቮልት በታች ነው” የሚሉት አቶ ወሰኑ አሁን ለሙከራ እየሰሩ ያሉት የተሻለ ኃይል ባለበት ሰዓት ከለሊቱ 6 ሰዓት በኋላ ሲሆን የኤሌክትሪክ ኃይሉ ችግር ከተቀረፈ ሙሉ ለሙሉ የበቆጂ የውሃ ችግር እንደሚፈታ ገልጸዋል።