መጋቢት 12 ፣ 2015

የአዳማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የደንብ ልብስ እንዲለብሱ አስገዳጅ መመሪያ ወጣ

City: Adamaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

በከተማው ያልተመዘገቡና ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸው ተሽከርካሪዎችን ተጠቅመው ግድያ፣ ዝርፊያና ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ሰርተው ሚሰወሩም አሸከርካሪዎችን ለመቆጣጠር” አገልግሎት ሰጭዎች የደንብ ልብስ አንዲለብሱ መመሪያው ያስገድዳል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የአዳማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የደንብ ልብስ እንዲለብሱ አስገዳጅ መመሪያ ወጣ

የአዳማ የህዝብ ትራንስፖረት አገልግሎት ሰጭዎች ከሰኞ መጋቢት 11/2015ዓ/ም ጀምሮ በታቀፉበት የታክሲ ማህበር ስር ሆነው የደንብ ልብስ እንዲለብሱ አስገዳጅ መመሪያ መውጣቱ ተሰማ።

“በአዳማ ከተማ 701 ሚኒባስ ታክሲዎች፣ 12723 ባለሶስት እግር ታክሲዎች እና 173 የጭነት አገልግሎት ሰጪ የባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች” መኖራቸውን የገልጹት የአዳማ ከተማ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አደም ፊቆ “በከተማው የሚታው የተሽከርካሪ ፍሰት ለመቆጣጠር አገልግሎት ሰጭዎች የደንብ ልብስ እንዲለብሱ” መስፈለጉን ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

“በከተማው ያልተመዘገቡና ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸው ተሽከርካሪዎችን ተጠቅመው ግድያ፣ ዝርፊያና ሌሎች  ከባድ ወንጀሎች ሰርተው ሚሰወሩም አሸከርካሪዎችን ለመቆጣጠር” እስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች የደንብ ልብስ መልበስ አስገዳጅ ሆኖ በመገኘቱ መመሪያውን ማውጣት ማስፈለጉን ሃላፊው ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል፡፡ “ህገ-ወጥ ተሽከርካሪዎች እና አሽከርካሪዎች በመለየት የከተማውን ጸጥታና ደህንነት ለመጠበቅ ይረዳል” ያሉት ኃላፊው ይህንን መመሪያ የማያከብሩ አሽከርካሪዎችም ላይ ፈቃድ  እስከመንጠቅ ሚያደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ረ/ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ በበኩላቸው “በአዳማ በተሽከርካሪ የሚሰራውን ወንጀል ለመቀነስ፣  ለመለየትና ለመቆጣጠር” የመመሪያው ተግባራዊ መሆን አስፈላጊነትን ለአዲስ ዘይቤ አብራርተዋል።

መመሪያውን ተከትሎ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች አረንጓዴ፣ ሰማያዊ እና ቀይ ቀለም ያላቸው ጋወን እና ሸሚዝ የለበሱ አሽከርካሪዎች እና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች መኖራቸውን የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በቦታው ተገኘቶ ለመታዘብ ችሏል።

በደንብ ልብሶቹም ላይ በዋናነት የታክሲ ማህበራትን ሎጎ፣ የተሽከርካሪውን ታርጋ፣ በማህበሩ ለተሸከርካሪው የተሰጠውን  የጎን  ቁጥር እንዲሁም የአዳማ ከተማ አስተዳደር ነጻ የስልክ ቁጥር የሆነውን 9141 ያካተተ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ለማወቅ ችላለች።

በባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማራው ወጣት የመመሪው ተግባራዊነት በስራው ላይ ምን አይነት በጎና አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያመጣ እንደሚችል አዲስ ዘይቤ ለጠየቀችው ጥያቄ በሰጠው መልስ “ማህበረሰቡ ለባጃጅ ያለው አመለካከት ጥሩ አለመሆኑን ጠቅሶ በደንብ ልብሱ ጀርባ ላይ በተቀመጠው ቁጥር የሚደረጉ ጥቆማዎች ትክክለኛነት” ከወዲሁ ስጋት እንደፈጠረበት ይናገራል።

በአዳማ ከተማ በተደጋጋሚ በባጃጅ ነጥቆ  ማምለጥ፣ ተሳፋሪን በባጃጅ አሳፍሶ በቡድን መስረቅ የመሳሳሉ ወንጀሎችና መሠል የማጭበርበርና የስርቆት ወንጀሎች መስተዋላቸውን ተከትሎ ለባጃጅ አሽከርካሪዎች የሚሰጠው ጅምላ ፍረጃ በመመሪያው አተገባበር ላይ ችግር እንዳይፈጠር ከወዲሁ ታሳቢ ሊደረግ እንደሚገባም ወጣቱ ጥሪውን ያቀርባል።

በሌላ በኩል የደንብ ልብስ መልስ እስገዳጅ መመረያ መውጣቱና ተግባራዊ መሆን በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎችና ተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሰውን ስርቆት፣ ማጭበርበርና፣ ልዬ ልዬ ወንጀሎችን በመቆጣጠር የተሻለ የትራንስርት ፍሰት በከተማዋ እንዲኖር ለማስቻል ጥሩ የመፍትሄ አካለ ሊሆን እንደሚችል አዲስ ዘይቤ ከምንጮቿ ለማረጋገጥ ችላለች።

አስተያየት