የሲኒማ ቤት ወግ ያላየው የአዳማ ሲኒማ ቤት

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅጥቅምት 26 ፣ 2014
City: Adamaመልካም አስተዳደርማህበራዊ ጉዳዮች
የሲኒማ ቤት ወግ ያላየው የአዳማ ሲኒማ ቤት
Camera Icon

Photo: Tesfalidet Bizuwork

“እንኳን እኔ ኃይለማርያም ማሞ ሆስፒታልም አጥር የለውም!” በ1982 ለዕይታ የበቃው የመስፍን ገብሬ “ስንብት” ቴአትር ላይ የሚገኘው ገጸ-ባህሪ የተናገረው ነው። “ለምን ቤት የለህም?” የሚለውን ጥያቄ የመለሰበት መንገድ ታዳሚውን አዝናንቶ ብቻ አላበቃም። የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ አስገድዷል። ሆስፒታሉ አጥር እንዲኖረው የመጀመርያው የማንቂያ ደውል የተደወለው በአዳማ ሲኒማ ቤት የተመደረከው ቴአትር ነው። 

አዳማ ሲኒማ ቤት ከ1970 ዎቹ አንስቶ እስከ 90ዎቹ ድረስ ከፍተኛ የቴአትር እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱበት የመዝናኛ እና የቁምነገር፣ የመማማሪያ እና የማንቂያ መድረክ ሆኖ አገልግሏል። ለአምስት አስርት ዓመታት በአገልግሎት የቆየው ሕንጻ/ አዳራሽ መደበኛ ተግባሩን ያቋረጠው በሙያተኞች እና በባለሥልጣናት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ስለመሆኑ በሰፊው ይነገራል። በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ እና በባህልና ቱሪዝም ቢሮ መካከል ተፈጥሮ በአጭር ያልተቋጨው አለመግባባት ሲኒማ ቤቱ ለግለሰብ እንዲከራይ፣ የውጭ ሐገር ፊልሞች ማሳያ እንዲሆን፣ አጭር ለማይባል ጊዜ ተዘግቶ ያለ አገልግሎት እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ታሪካዊ ሲኒማ ቤቱ ከትላንት ታሪኩ እስከ ነገ ተስፋው ያሉ ሁኔታዎችን ተመልክቷል።

“የአዳማ ከተማ የባህል አዳራሽ እና ሲኒማ” በሚል ስያሜ የሚታወቀውን ተቋም የከተማዋ የባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ያስተዳድረዋል። ሲኒማ ቤቱ የበርካታ ከያንያን መፍለቂያ መሆኑ ቀርቶ ስያሜውን መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ ወደ “ቦምቤ” ለውጦ ለአስር ዓመታት ቆይቷል። አማኑኤል አዱኛ “ሲኒማ ቤቱ በብዛት የህንድ ፊልሞች ይታዩበት ነበር። ‘ቦምቤ’ የሚለው ስያሜ የተሰጠው ከዚያ በመነሳት ነው” ሲል የመነሻ ሰበቡን አጫውቶናል። ከአዲስ ዘይቤ ጋር አጭር ቆይታ የነበረው ወጣት አማኑኤል “ለግለሰብ ተከራይቶ የሕንድ ፊልም በአነስተኛ ክፍያ ሲያሳይ የቆየው ሲኒማ ቤቱ እንደ ጫት እና ሲጋራ ያሉ ሱስ አስያዥ እጾች በፊልም ዕይታ ወቅት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አልከለከለም። ታዳጊ ተማሪዎች በትምህርት ሰዓታቸው እየገቡ  ጊዜያቸውን ጠቃሚ ባልሆነ አካሄድ ያጠፉበታል። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጫት እና ሲጋራ የሚለማመዱበት መድረክ እስከመሆን ደርሶም ነበር። የተማሪ ዩኒፎርም የለበሱ ደንበኞቹን እስከ ማገድም ደርሷል” ብሏል።

የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ኪያ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረችበት ወቅት በጓደኞቿ ግፊት ‘ቦምቤ’ን ታዘወትር እንደነበር ነግራናለች። “ከጓደኞቼ ጋር የከሰዓት በኋላውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ፊልም ዕያየን እናሳልፍ ነበር” ስትል ትውስታዋን አጋርታናለች።      

“ቴአትር ቤት ለአዳማ” በሚል እንቅስቃሴ መሪነቱ የሚታወቀው መምህር ሰሎሞን ንጉሤ (ግሬስ) የንቅናቄውን መነሻ በተመለከተ ሲናገር “ጥበበኛው ኖሮ ማሳያው አለመኖሩ ነው” ይላል። በከተማው የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አነሳሽነት በምስረታ ላይ የሚገኘው የአደማ የጥበብ ባለሙያዎች ማኅበር መስራች ኮሚቴ አባል አቶ ሰሎሞን “ነገሩ የአዳማ ጥበበኞች ከተማዋን እንዲለቁ አስገድዷል። አሁን ያለው ሲኒማ እንጂ ቲያትር ቤት አይደለም። ከአዲስ አበባ የሚመጡ ቴአትሮች እዚህ የሚታዩት ከደረጃ በታች ነው። ይህ የሆነው ደረጃውን የጠበቀ ቴአትር ቤት ባለመኖሩ ነው” ሲል ያብራራል። የቢሮው ትኩረት ቱሪዝም ላይ እንጂ ባህል እና ኪነ-ጥበቡ ላይ እንዳልሆነ እና የዚህ ምክንያት ደግሞ ባህል እና ቱሪዝሙ በጋራበአንድ ቢሮ መመራታቸው እንደሆነ ያምናል። ከወራት በፊት “አብዲሳ አጋ” የተሰኘ መልቲሚድያ ቴአትር ለዕይታ ያበቃው ስብስባቸው ያጋጠመውን ችግር አስመልክቶ ሲናገር “ተዘግቶ ምንም ዓይነት አገልግሎት የማይሰጠውን የአዳማ ቴአትር እና ሲኒማ አዳራሽ አስፈቀድን። በጽ/ቤቱ ፈቃድ ለሁለት ቀናት ከተለማመድን በኋላ በጥበቃ ሰራተኛው እምቢተኝነት ምክንያት ልምምዳችን ተቋረጠ። ለጥያቄአችንም ሆነ ለኪነ-ጥበባዊው ጉዳይ ትኩረት እንዳልተሰጠ ለመረዳት አዳራሹ ተቆልፎበት ደጃፉ ለምግብ ቤት በኪራይ መተላለፉን መመልከት በቂ ነው።” ሲል ምሬት እና ሐዘኑን ገልጾልናል።

የፍካት ለጥበብ የቲያትር እና የስነ-ጽሑፍ ፕሮዳክሽን መስራች አማኑኤል ንጉሤ አንድ ገጠመኙን እንዲህ ያስታውሳል። “ከወራት ልምምድ በኋላ በርካታ እንግዶች ጠርተን 04 ቀበሌ ቴአትራችንን ለማሳየት ተዘጋጀን። እንግዶች ተጋብዘው ትርኢቱ ሊጀመር ሰዓታት ሲቀሩ ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ተከሰተ። አዳራሹን መጠቀም እንደማንችል ተነገረን። የከልካዮቻችን ምክንያት ‘ስብሰባ አለ!’ የሚል ነበር” ሲል ያለፈ መጥፎ ትዝታውን በፈገግታ አካፍሎናል።

ይህንን መሰል ተመሳሳይ ገጠመኝ ያስተናገዱት ከአራት ጊዜ በላይ መሆኑንም ነገሮናል። “ቦምቤ” ሲኒማ ቤት የህንድ ፊልም ዕያሳየ የቴአትር ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች በማሳያ እጥረት የመሰቃየታቸው ግራ አጋቢ ገጠመኝ የቴአትር ቡድኑ እንዲበተን፣ በውስጡ የነበሩ የተወሰኑ ወጣቶች ወደ አጎራባች ከተሞች እንዲሄዱ፣ የተወሰኑት ተስፋ ቆርጠው የስራ መስክ እንዲቀይሩ እንዳስገደደ ማሳያዎች እየጠቀሰ አጫውቶናል። እንደ አማኑኤል አባባል በወቅቱ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከ10 በላይ ክበባትና ቡድኖች ተበትነዋል።

በከተማዋ ሦስት የሲኒማ ማሳያ ሥፍራዎች ቢኖሩም ቴአትር ወይም ሲኒማ ለማሳየት የተገነቡ አይደሉም። በተጨማሪም ከ8-15 ሺህ ብር ክፍያ መጠየቃቸው በወጣቶች እና በጀማሪዎች የማይደፈሩ አድርጓቸዋል። የአማርኛ የቪድዮ ፊልሞችን በማሳየት የሚታወቁት ፖስታ ቤት አካባቢ የሚገኘው ኦልያድ ሲኒማ እና ፍራንኮ አካባቢ የሚገኘው ሞርሞር ሲኒማ ናቸው። የቲታስ ሆቴል አዳራሽም በአብዛኛው ጥቅም ሲሰጥ ዐይታይም።

የአዳማ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎሳዬ ቅሬታውን በተመለከተ ለአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ምላሽ ሰጥተዋል። በኮቪድ ምክንያት ሥራ ያቋረጠው አዳራሽ ከ9 ወራት ክልከላ በኋላ ሥራ ሲጀምር እድሳት ማስፈለጉን እና መድረኩን ጨምሮ የሚያፈሰውን ጣርያ ለማደስ ከ500 ሺህ ብር በላይ ማስፈለጉን የሚናገሩት ኃላፊው “ቢሮው ባለው ውሱን በጀት እድሳቱን ጀምሮ ከባለ ሐብቶች በሚገኝ ድጋፍ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እስከ ህዳር 30 ስራውን ለማስጀመር እቅድ ተይዟል። በእቅዱ መሰረት በሁለት ወራት ውስጥ እድሳቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን እየሰራን ነው” ሲሉ አብራርተዋል። አዳራሹ ከእድሳት በኋላ በዘላቂነት የሲኒማ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

Author: undefined undefined
ጦማሪተስፋልደት ብዙወርቅ

Tesfalidet is Addis Zeybe's correspondent in Adama.