የአዳማ ወጣቶች የሥራ ፍለጋ እንግልት

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅጥቅምት 3 ፣ 2014
City: Adamaመልካም አስተዳደርኢኮኖሚ
የአዳማ ወጣቶች የሥራ ፍለጋ እንግልት

የወጣቶች ሥራ አጥነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚነሱ የከተማ ችግሮች መካከል አንዱ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሐገሮች ችግሩ ያይላል። ከዋና ከተማ ርቀው በሚኖሩ ወጣቶች ዘንድ ደግሞ ስራ የማግኘት አማራጩ ይጠባል። ከአዲስ አበባ በቅርብ እርቀት በምትገኘው አዳማ የሚኖሩ የዚህ ዓመት ተመራቂዎችን “ሥራ ፍለጋው እንዴት ነው” ሲል ያነጋገራቸው የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ተከታዩን ዘገባ አሰናድቷል።

ጀምበሩ ግርማ ይባላል። የአዳማ ከተማ ገንደ ሀራ ሰፈር ነዋሪ ነው። የተገናኘነው 15 ጋዜጣ ቤት ተብሎ በሚጠራው ጋዜጣ ማንበቢያ አካባቢ ነው። ስፍራውን ስራ ፈላጊዎች፣ ጋዜጣና መጽሔት አንባቢዎች ያዘወትሩታል። ከ አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ዩንቨርሲቲ በፓወር ኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት በ2013 ዓ.ም ተመርቋል። በፊልዱም ሆነ ከፊልዱ ውጭ ያለ የሥራ መስክ ቢያገኝ ለመስራት ፈቃደኛ ነው። ጀምበሩ በሐገሪቱ መዲና ታትመው በመላ ሐገሪቱ ከሚሰራጩት ጋዜጦች መካከል የሥራ ማስታወቂያ የሚበዛባቸውን ያነባል። “እዚህ ቦታ በሳምንት ሁለት ጊዜ እመጣለሁ” ይላል። “አዲስ ዘመን” እና “ሪፖርተር” የተባሉ ጋዜጦች ላይ የሚወጡ የሥራ ማስታወቂያዎችን እንደሚያነብ ነግሮናል። የጋዜጣ ነጋዴዎቹ ለአንድ ጋዜጣ ንባብ ከ2 እስከ 3 ብር ያስከፍሉታል። ወጣቱ ለሥራ ፍለጋው ከጋዜጦች ንባብ በተጨማሪ ልዩ ልዩ ድረ-ገጾችን እና ማኅበራዊ ሚድያዎችንም ይመለከታል። “እንደ ኢትዮ ጆብስ፣ ሀሁ ጆብስ፣ ፍሪላንሰር ያሉ ቻናሎች አሉ። ዌብሳይት አላቸው። ፌስቡክ እና ቴሌግራም ላይም አሉ። ከጋዜጣው በተጨማሪ እነሱንም በየቀኑ ዐያለሁ” ብሎናል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዳማ ወኪል አከፋፋይ ሰራተኛ የሆነችው መቅደስ ሙሉጌታ “ምን ያክሉ እንደሚሳካላቸው ባላውቅም በቀን ከ10 እሰከ 50 ሰው ስራ ለመፈለግ ጋዜጦች ያነባሉ። ክፍያው በተነበበው ጋዜጣ መሰረት ነው። አዲስ ዘመን በ2 ብር ሪፖርተር 3 ብር ይነበባል” ትላለች። አንድ ሰው በሳምንት እስከ ሦስት ቀን ሊጎበኛቸው እንደሚችልም ትናገራለች።

በሳምንት ለሁለት ቀናት እየተመላለሰ፣ በመጣበት ጊዜ ሁሉ ቢያንስ 10 ብር እየከፈለ ሥራ የሚፈልገው ወጣት ጀምበሩ “ከተመረኩ ዓመት ሆኖኛል። ሥራ ፍለጋን ስራዬ ብዬ የያዝኩት ከተመረቅኩ ጀምሮ ነው። እስካሁን የምፈልገውን ሥራ አላገኘሁም” ብሎናል። የሥራ ማግኘት ሙከራውን ያላቋረጠው ወጣቱ የፌደራል ተቋማት ካልሆኑ በስተቀር የግሎች እና የክልሉ ቢሮዎች የሥራ ማስታወቂያዎችን በጋዜጦች እና በኢንተርኔት የማስታወቂያ መንገዶች እያስተዋወቁ እንዳልሆነ መታዘቡን አጫውቶናል።

በአዳማ ከተማ ከተለመዱ ሥራ መፈለጊያ መንገዶች መካከል የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ይገኛሉ። አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከእነዚህ መካከል ይጠቀሳል። ዩንቨርሲቲው በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ሦስት የማስታወቂያ ሰሌዳዎች አሉት። ሰሌዳዎቹ በዩንቨርሲቲው የሚተዳደሩ ሲሆን በግቢው ውስጥ የሚገኙ ክፍት የሥራ ቦታዎች በቋሚነት ይለጠፉባቸዋል።

ሌላኛው ተደራጅተው የማስታወቂያ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች ያቆሙት ሰሌዳ ነው። ፍራንኮ፣ ፖስታ ቤት እና መብራት ኃይል  ማስታወቂያ መለጠፊያ ሰሌዳ አላቸው።

ተደራጅተው አገልግሎቱን ከሚሰጡ ወጣቶች መሀከል አንዱ ናኦል ይባላል። ማንኛውም ማስታወቂያ አስነጋሪ ማስታወቂያዎቹን በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋዎች አዘጋጅቶ መቅረብ እንደሚጠበቅበትና ለ5 ቀናት የሰሌዳ ላይ ቆይታ 100 ብር መክፈል እንደሚጠበቅበት ይናገራል። “ብዙ ማስታወቂያዎች ይመጣሉ። ልምድ ያላቸውም፣ በዜሮ ዓመትም አለ” ይላል።

በኤሌትሪክ ምህንድስና የተመረቀው ወጣት አብዲ ሂርጶ ማስታወቂያ የሚለጠፍባቸው ቦታዎች ውሱን መሆናቸው ሥራ አጡን ጎድቷል የሚል እምነት አለው። ራቅ ካለ ስፍራ ተጉዞ እዚህ የመጣበት ምክንያት ተቋማቱ በቴክኖሎጂ ስለማይጠቀሙና የማስታወቂያ ሰሌዳቸው ውሱን ቦታዎች ላይ ብቻ ስለሚገኝ ነው።

“አብዛኛዎቹ እዚህ ቦታ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች የከተማዋ ድርጅቶች የሚለጥፏቸው ናቸው” የምትለው  ኢማን ኸይሩ  መምህራን፣ካሸር፣ ጽዳት፣ ጥበቃ፣ አስተናጋጅ ነው የሚፈልጉት። "በሰው አልያም በዘመድ ካልሆነ የግል ድርጅቶች ማስታወቂያ አውጥተው አይቀጥሩም።  ይህ ደግሞ ብቃት ያላቸው ሰዎችን ስራ እንዳያገኙ አድርጓል ትላለች።" አሁን የምተገኝበትን ሥራ ያገኘችው በጓደኞቿ አጠያያቂነት መሆኑን በማስታወስ “በሰው ስታገኝ የተያያዥ አትጠየቅም። ከሰዎቹም ጋር የተሻለ መግባባት ይኖራል።" ትላለች። ስራ በራስ ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው የምትለው ኢማን "ለሴቶች ቁንጅና እንደ ልዩ ብቃት ተደርጎ ነው የሚታየው። ይኼ ደግሞ እጅግ ስብዕናን ይነካል” ስትል ሀሳቧን ትደመድማለች።

“ማስታወቂያ አስለጥፌ አላውቅም ለደላላ ነው ምደውለው። ቁንጅና ግን ዋነኛ መስፈርቴ ነው።” የሚለው ስሙ እና ቤቱ እንዳይጠቀስ የፈለገ የካፌ ባለቤት ቅልጥፍና አስፈላጊ ቢሆንም ውድድር ነውና ደንበኛ ለመሳብ ይህንን እንጠቀማለን ሲል ሀሳቡን ያጠቃልላል።

በዲጅታል አማራጮች የስራ ቅጥር ማስታወቂያ በመለጠፍ ከሚታወቁ ድረ-ገጾች አንዱ ኢትዮጆብስ ነው። ሌሎች በቴሌግራም መተግበሪያ ላይ የሚሰሩ እንደፍሪላንሰር፣ ሀርሜ ጆብስ፣ ኢትዮጵያን ጆብ ቦርድ አሉ። አብዛኞቹ የኦንላይን በተለይ የቴሌግራም ስራ አፋላጊ ገጾች አብዛኛውን የሚያቀርቡት ስራዎች አዲስ አበባ ላይ ያሉ ስራዎችን ነው።  

“አዳማ ላይ ያሉ ስራዎችን ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው። አዳማ አንድም በዲጂታል አማራጮች ስራ የሚያፋልግ ገጽ የላትም” ያለን ንጉሥ ደረሰ በ2013 ዓ.ም. ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተመርቋል። “እንደ ባንክ ያሉ ብዙ ሰው የሚቀጥሩ ተቋማት በበይነ-መረብ በራሳቸው ድረ-ገጽ መቅጠር ጀምረዋል። ነገር ግን ሲስተማቸው በጣም ደካማ በመሆኑ በተደጋጋሚ መራዘሙ ስራ ፈላጊዎችን ለአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት እየዳረገን ነው። በኢንተርኔት ካፌዎች ፎርሙን ለመሙላት በሰው እስከ 200 ብር እየተከፈለ ነው። እንደዛም ሆኖ የስም እና መሰል ስህተት በተደጋጋሚ ስለሚኖር ስራ ፈላጊው ለተጨማሪ ወጪና እንግልት እየተዳረገ ነው።" ሲል ምሬቱን ይገልጻል።

በኢንተርኔት መጓተቱ የምትስማማው በቤስት ኢንተርኔት ካፌ ተቆጣጣሪዋ ፍሬህይወት “ምናስከፍለው በሰው 200 ብር ነው። አንድ ሰዓት ሞክረህ ነው አንድ ሰው ሚገባልህ። ቀን ብዙ ሰው ስለሚሞክር  ዌብሳይቱ አይከፍትም ነበር። ስለዚህ ለሊት ነበር ሰው ተቀምጦ ይሞላ የነበረው" ስትል ሁኔታውን አስታውሳ የገንዘቡን መብዛት ብዙዎች ያነሱት እንደነበረም ትስማማለች። ዌብሳይቶቹ አክቲቭ አለመሆናቸው ስራ ፈላጊዎችን ለተደጋጋሚ ወጪ እና እንግልት መዳረጉን ትናገራለች።

ሌላው በከተማዋ ስራ ፈላጊዎች ዘንድ የሚነሳው ቅሬታ የመንግስት ቢሮዎች ውስጥ መረጃችንን ብናስገባም መቀጠር አለመቻላችን የእኛን ተጠቃሚነት  ሆነ ባለን እውቀት ሀገራችንን በአካባቢያችን እንዳናገለግል ችግርቶት ፈጥሮብናል ይላሉ።

ዮናስ ባህሩ (ስሙ ለዚህ ጽሑፍ የተቀየረ) ተወልዶ ያደገው በአዳማ ከተማ ሲሆን በሲቪል ምህንድስና ተመርቆ ስራ በሚፈልግበት ሰዓት የቋንቋ ጉዳይ እጅግ እንደፈተነው ይናገራል። የመንግስት ተቋማት ማስታወቂያ አውጥተው ዓለማየቱን የሚገልጸው የግል ድርጅቶች ጋር ለመቀጠር ያገጠውን ችግር እንዲህ ይናገራል። “ሊቀጥረን ማስታወቂያ ያወጣው ድርጅት ኦሮምኛ አለመቻላችንን ሲያውቅ ሲቪያችንን ሳይቀበለን ቀርቷል። ኦሮምኛ በትክክል የምትናገር ጓደኛችንን ተቀብለዋት ደውለውለውላትም ነበር። ሊቀጥሯትም ፍቃደኛ ነበሩ።" ሲል የደረሠበት ይናገራል። ይህ ችግር ምናልባት ድርጅቶቹ በመንግስት ቢሮ አካባቢ የሚደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም አስበው ያደረጉት ሊሆን እንደሚችልም ይናገራል። "ተመርቀህ ሀብታም ወይም ባለስልጣን ዘመድህን ፈልግ የሚል ያልተጻፈ ሕግ አለ። ዘመድ ስለሌለኝ እና ስራውን በራሴ ፈልጌ ማግኘት ስላልቻልኩ አዳማን መልቀቅ ሳልፈልግ ወጥቼ ለመስራት ተገድጃለሁ።”  የሚለው ዮናስ ባህሩ ስራ ቢያገኝ ተወልዶ ባደገባት አዳማ ቢሰራ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል።

ሌላኛው የስራ ፍለጋ መልክ የስራ እና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ጉዳይ ነው። የተለያዩ ቅሬታዎች በተጠቃሚዎች ዘንድ የሚነሳባቸው እነኚህ ድርጅቶች አሰራር ነው።

ከአንድም ሁለት ጊዜ በኤጀንሲዎች በኩል ሥራ ለማግኘት መሞከሩን የሚናገረው ሚካኤል መስፍን ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎቹ ከትልልቅ ድርጅቶች ጋር ሰራተኛ የማቅረብ ውል አላቸው። ስላስቀጠሩህ ከደሞዝህ የሚቆርጡት ገንዘብ ግን እጅግ ከፍተኛ ነው። በድርጅቱ ውስጥ እድገትም ይኑርህ ሁሉም ነገር በእነርሱ ዘንድ ነው ሚያልፈው። "ከ3,500 ብር ደሞዜ ላይ አገናኙ ድርጅት በየወሩ 500 ብር ለአንድ ዓመት ድርጅቱ እንዲወስድ ነበር ውሉ የሚያዘው። ልፋቴና ገቢው ባለመመጣጠኑ ስራውን በሳምንቱ ተውኩት።” ሲል ገጠመኙን አካፍሎናል።

ስራ ፈላጊዎችን የተለያየ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት አሰልጥኖ ወደ ስራ ማሰማራት ላይ እንደሚሰሩ የሚናገሩት የቱጌዘር የስራ እና ሰራተኛ  አገናኝ አነጋግረናቸው ነበር። የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ኤልኤዘር ወልዱ "በዋናነት ስልጠና ሰጥተን ሰራተኞችን ውል ለሰጡን ድርጅቶች እናቀርባለን። ክፍያ የምንቀበለው ለስልጠናው እና አንዴ ላስገባንበት ከድርጅቱ ነው።" ይላል ከአገናኝ ድርጅቶች ጋር በተገናኘ ስለሚነሱ ቅሬታዎች የጠይቅነው ኤልኤዘር ወልዱ  "እኛ ድርጅቱን የከፈትንበት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ የስራ እድል ለመፍጠር እና እንዲህ ዓይነት አሰራሮችን ለመተገል ነው" ሲል መልሷል።

Author: undefined undefined
ጦማሪተስፋልደት ብዙወርቅ