መጋቢት 14 ፣ 2014

በአዳማ ከተማ ለአረንጓዴ ስፍራ ከተለየው መሬት ግማሽ ያህሉ ለሌላ አላማ መዋሉ ተነገረ

City: Adamaመልካም አስተዳደር

የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ከማስተር ፕላን ትግበራ ቁጥጥር ጋር በ17 ቦታዎች ባካሄደው የናሙና ጥናት ዘጠኙ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውሉ ስምንቱ ከታለመላቸው አገልግሎት ውጭ ውለው መገኘታቸው ታውቋል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በአዳማ ከተማ ለአረንጓዴ ስፍራ ከተለየው መሬት ግማሽ ያህሉ ለሌላ አላማ መዋሉ ተነገረ
Camera Icon

ፎቶ፡ ተስፋልደት ብዙወርቅ

የሙቀት መጠኗ እስከ 31 ዲግሪ ሴሊሺየስ የሚደርሰው አዳማ ከፍ ያለ ሙቀት ከሚያስተናግዱ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ ነች። ነዋሪዎቿ ከባዱን የሙቀት መጠን ተቋቁመው መኖር እንዲችሉ 31 ሺህ ሔክታር ከሚገመተው ስፋቷ ቀንሳ 6ሺህ 6መቶ 65 ሔክታሩን ወይም 21.1 በመቶውን ለአረንጓዴ መሬት እንዲውል ለይታ ማዘጋጀቷን ከከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዘርፉ የተካሄደ ሌላ ጥናት ደግሞ ለአረንጓዴ ልማት የታቀደ 181 ሄክታር መሬት ለመኖርያ ቤት መዋሉን ያስረዳል።

የአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አረንጓዴ ልማት ቡድን መሪው አቶ ሀብታሙ በዳሳ እንዳሉት ባለፈው አመት ከማስተር ፕላን ትግበራ ቁጥጥር ጋር በ17 ቦታዎች ባካሄዱት የናሙና ጥናት ዘጠኙ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውሉ ስምንቱ ከታለመላቸው አገልግሎት ውጭ ውለው መገኘታቸውን ገለጸዋል።

የማስተር ፕላን ትግበራ ቡድን መሪ አቶ ጸጋዬ አበራ በ1996 ዓ.ም. ሥራ ላይ የዋለውን የከተማዋን ማስተር ፕላን መሰረት በማድረግ ለማስተርስ ማሟያ በሰኒያ ናስር EVALUATION OF URBAN GREEN SPACE DEVELOPMENT USING GEOSPATIAL TECHNIQUES: A CASE OF ADAMA በሚል ርእስ የተሰራ ጥናት እንደተመለከተው በወቅቱ ከነበረው ለአረንጓዴ ልማት የታቀደ 13,665 ሔክታር መሬት ውስጥ 181 ሔክታር ወደ መኖርያ መንደርነት እየተቀየረ ይገኛል። አረንጓዴ ልማትን የሚዳስሰው ጥናቱ አረንጓዴ ልማት ላይ የማኅበረሰቡ ግንዛቤ አናሳ ነው ብሏል። የአስተዳደር አካላት ዝቅተኛ አፈጻጸም፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር በጉልህ የሚታዩ ችግሮች ስለመሆናቸው አንስቷል።

ፋያ ከማል በከተማዋ ኮሌጅ ተክለሐይማኖት ማዞሪያ አካባቢ ነዋሪ ናት። ባነሳነው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በምትኖርበት አካባቢ የገጠማትን ነግራናለች። “ለአረንጓዴ ልማት የተለየው ክፍት ቦታ ላይ አንድ ሰው መጥቶ መቆፈር ጀመረ። ቤት ለመስራት መሰረት አወጣ። የአካባቢው ሰው ተባብሮ የሕግ ቦታ በመሄድ አስቆመው” ብላናለች።

አርክቴክት አብዲ ገበየሁ በበኩሉ “አዳማ ሁለት መልክ አላት” ይላል። በአዳማ ከተማ በግሉ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው አርክቴክቱ የቀድሞውን በተቀናጀ ፕላን ያልተሰራውን እና በጥናት የተሰሩትን አካባቢዎች ለሁለት ከፍሎ ይመለከታቸዋል። አዲሶቹ መንደሮች በወረቀት ላይ ባላቸው እቅድ ለአረንጓዴ ስፍራ እንዲሆን ታስቦ የተተወ ቦታ ቢኖራቸውም ከወረቀት ባለፈ ለምተው አለመመልከቱን ነግሮናል። አረንጓዴ ስፍራዎች መልማታቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ያለውን እምነትም አካፍሎናል።

አቶ መንግሥቱ መኮንን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ፕላን መምህር ናቸው። ለአረንጓዴ ስፍራ የተመደቡት ክፍት የተተዉ የከተማዋ ቦታዎች ያልለሙት እቅድ እና በጀት ባለመኖሩ ነው ይላሉ።

መምህሩ በቀደመ ጥናታቸው “የአረንጓዴ ልማት በጀት ከአጠቃላይ በጀቱ 0.1 በመቶ ብቻ” መሆኑን አረጋግጠዋል። “በከተማ ደረጃ ካሉት 5 ከተማ አቀፍ ፓርኮች ከ‘ደንበላ ቦታኒክ ጋርደን’ በቀር የትግበራ እቅድ (Urban Design) የላቸውም። እያንዳንዱ መሬት ላይ የሚከናወኑ ተግባራት በግልጽ የሚቀመጥበት እቅድ የለም” ብለዋል።

ጊፍቲ ማቲዎስ በበኩሏ “በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ላይ ለአረንጓዴ መሠረተ ልማት ተብለው የተለዩ ቦታዎች አሉ። ምን ያህሉ ጥቅም ላይ ውሏል የሚለው ግን አጠያያቂ ነው” ትላለች። በጥናቷ እንዳረጋገጠችው የከተማዋ ለጎርፍ ማስተንፈሻ የተለዩ ቦታዎች ሳይቀሩ በሕገ-ወጥ መንገድ ተወረዋል። ለአረንጓዴ ልማት በተዘጋጁ ቦታዎችም ተመሳሳይ ችግር አስተውላለች። እንደ ጊፍቲ አባባል "አንድ ቦታ ውበቱ በጨመረ ቁጥር የኢኮኖሚ አቅሙም ይጨምራል"

የአዳማ ከተማ ተፈጥሮ እና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአረንጓዴ ልማት ባለሙያው አቶ ፈቂ ደቀባ በበኩላቸው ለአረንጓዴ ልማት ከተከለለው 4ሺህ 1መቶ ሔክታር መሬት ውስጥ 9.3 በመቶ ያህሉ እንደለማ ይናገራል። "የተወሰዱ፣ ወደተለያዩ አገልግሎቶች የተቀየሩ እንደሚገኙ በስራ እንቅስቃሴአችን እንመለከታለን። የቁጥጥር ሥራው ግን የእኛ አይደለም፤ ስለዚህ ምንም ማድረግ አንችልም” ይላል። በተቋማቸው ቁጥጥር ስር ያለውን የተራራ ልማት የመሬት ወረራ ግን በአፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ መከላከል እንደቻሉ ነግሮናል።

“በከተማ ውስጥ ያለውን አረንጓዴ ስፍራ የማስተዳደር እና ማልማት ሥራ ኃላፊነት የመሬት አስተዳደር ጽ/ቤት እና የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ነው። የእኛ ቢሮ ኃላፊነት ምክር መስጠት ነው” ብለዋል አቶ ፈቂ ደቀባ።

የዓለም ጤና ድርጅት ለአንድ ሰው 9 ካ.ሜ. አረንጓዴ ሥፍራ እንደሚገባው አስቀምጧል። ለአፍሪካ ሐገራት 7 ካሬ የተቀመጠ ሲሆን በበለጸጉት ሀገራት ይኼ ቁጥር እስከ 20 ካ.ሜ. በነብስ ወከፍ ይደርሳል። የኢትዮጵያ የከተማ አረንጓዴ ልማት ስታንዳርድ ደግሞ 15 ካ.ሜ. እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አስተያየት