መስከረም 7 ፣ 2014

አዳማ እና የ‘ሰልባጅ’ ገበያ

City: Adamaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች

ልባሽ ጨርቆች ወደ ሐገር ውስጥ እንዳይገቡ ከከለከሉ የምስራቅ አፍሪካ ሐገራት ውስጥ አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ወደ ሐገር ውስጥ ከሚገቡ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በሕገ-ወጥ መንገድ እንደሚገቡ መረጃ ያመለክታል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

አዳማ እና የ‘ሰልባጅ’ ገበያ

ያገለገሉ አልባሳት ንግድ በከፍተኛ መጠን ያደገው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው። የፋሽን ኢንዱስትሪው ፈጣን እና ተቀያየሪ የአለባበስ ዘይቤን መከተሉ ከጥቂት አገልግሎት በኋላ የማይፈለጉ አልባሳትን ቁጥር በእጅጉ ጨምሮታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የሚከማቹትን የማይፈለጉ አልባሳት ማስወገድ የመንግሥታት ፈተና እስከመሆን ደርሷል።

የቆሻሻ ክምችትን ይጨምራሉ፣ የአካባቢ ብክለትን ያባብሳሉ፣ ለምርት የወጣባቸውን ንጥረ-ነገር ያባክናሉ የሚባሉት የማይፈለጉ ልባሽ ጨርቆች አንዱ መዳረሻቸው በማደግ ላይ የሚገኙ የአፍሪካ ሐገራት ናቸው። የምእራቡ ዓለም የኢኮኖሚ አሻጥረኞችም ዝቅ ባለ ዋጋ የሚቀርበውን የቻይናን ምርት ስርጭት ለማዳከም እንደመሳሪያ እየተጠቀሙበት ነው የሚሉ ተንታኞችም አልጠፉም። እነኚህ ወገኖች የአፍሪካ ሀገራት በልባሽ ጨርቆች ንግድ ጉዳይ የእገዳ ሕጎች ሲያወጡ አሜሪካ እንደ አጎዋ ካሉ የንግድ ስምምነቶች የማስወጣት ውሳኔ ማሳለፏን የጉዳዩን ውስብስብነት ለማሳየት ተጠቅመውበታል። 

በኢኮኖሚ ካደጉት ምዕራባውያን ሀገራት የሚነሱት ልባሽ ጨርቆች (ሰልባጅ) መዳረሻቸው ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው። የገቢያቸውን አብዛኛውን ድርሻ ለምግብ ወጪ የሚያውሉ ብዙ ዜጎች ላላቸው ድሀ ሀገራት ሰልባጅ ዋነኛ የአልባሳት አቅርቦት ምንጭ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በንግድ ሰንሰለቱ ላይ የሚገኙ እንደ ጫኝና አውራጅ፣ ቸርቻሪ፣ አጣቢ፣ ጠጋኝ ያሉ የሥራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በሂደቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የልባሽ ጨርቆች ንግድ በሚፈቅዱ ሀገራት የገቢ ግብር የሚሰበሰብበት ሕጋዊ የንግድ ዘርፍ ሲሆን በተለይ የምስራቅ አፍሪካ ሐገራት አምራች እና አስመጪዎችን አያበረታታም በሚል በሕገ-ወጥነት ተፈርጇል።

አዳማና ሰልባጅ

ልባሽ ጨርቆች ወደ ሐገር ውስጥ እንዳይገቡ ከከለከሉ የምስራቅ አፍሪካ ሐገራት ውስጥ አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ወደ ሐገር ውስጥ ከሚገቡ የጨርቃጨርቅ ምርቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በሕገ-ወጥ መንገድ እንደሚገቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለማቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር አስናቀ ከፋለ ከዓመት በፊት ካሰናዱት ጽሁፍ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። እገዳ ስለተጣለባቸው በስውር ወደ ሐገር ውስጥ የሚገቡት ልባሽ ጨርቆች ለሽያጭ የሚቀርቡት በግልጽ በአደባባይ ነው። ከፍ ያለ የልባሽ ጨርቆች ግብይት ከሚካሄድባቸው የሐገሪቱ ከተሞች መካከል አንዷ አዳማ ናት።

ለእርጅና ሳይደርሱ ጥቂት ጊዜ አገልግለው ለአዳማ ገበያ ከሚቀርቡ መገልገያዎች ውስጥ አልባሳት (የወንድ፣ የሴት፣ የሕጻናት)፣ ጫማዎች፣ የወንድ እና የሴት ቦርሳዎች፣ የሕጻናት መጫወቻዎች ይገኙበታል። ቁሳቁሶቹ አዳማ የሚደርሱት በሁለት የድንበር መተላለፊያዎች ማለትም በሶማሌላንድ ድንበር ቶጎ ውጫሌ እና በኬንያ ሞያሌ በኩል ነው።

አልባሳት የታጨቀባቸው ግዙፍ የሸራ ጥቅሎች “ቦንዳዎች” እና ጫማዎች በጭነት እንስሳት፣ በሞተር ሳይክሎች፣ በጭነት ተሽከርካሪዎች ድንበሮቹን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። በድንበር ከተሞች ለሽያጭ በጅምላና በችርቻሮ ከቀረቡ በኋላ በሦስት ዓይነት ነጋዴዎች ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ይሰራጫሉ። 

የችርቻሮ ነጋዴዎች ልብሶቹን እና ጫማዎቹን በመደበኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መደበኛ ተጓዥ በመምሰል እቃዎቹን ለማሳለፍ የሚሞክሩበት የመጀመሪያው መንገድ ነው።

ወጣት ወንድም ደጀኔ የያቤሎ ከተማ ነዋሪ ነው። በተደጋጋሚ ወደ አዳማ ለትምህርት ጉዳይ ይመላለሳል። የነጋዴዎቹን ሁኔታ አስመልክቶ ሲናገር “ከመነኸሪያ ጀምሮ ነጋዴዎቹ እቃ አለመያዝህን ካዩ እቃዎችን ያዝልኝ ብለው ይጠይቁሀል። የያዙትንም እቃ ለሁሉም ሰው አከፋፍለው እንደማንኛውም ተሳፋሪ ኬላዎችን ያልፋሉ” ይላል። ይህ ከቶጎ ውጫሌ ተነስቶ የሚመጣው ሕጋዊ ያልሆኑ (የኮንትሮባንድ) ቁሳቁሶች የኢትዮጵያን ምድር የሚረግጡበት የተለመደ ሂደት ነው።

ሁለተኛው የጅምላ ነጋዴዎች በጭነት መኪናዎች ቁሳቁሶቻቸውን ጭነው በሕጋዊ ሽፋን የሚያልፉበት ነው። ለዚህኛው ዘዴ ከኬላ ጥበቃ ሰራተኞች ጋር መመሳጠር ያስፈልጋል። የገንዘብ ጥቅም ያገኙት ጥበቃዎች ያዩትን እንዳላዩ በማለፍ ነጋዴዎችን ይተባበራሉ።

የጭነት ተሽከርካሪውን ሕጋዊ ባልሆነ፣ ባልተፈቀደ መንገድ ማስጓዝ ሌላኛው አደገኛ መንገድ ነው። ከጠባቂዎች ዐይን እና ጆሮ ተሰውሮ ለማለፍ የሚደረገው ጥረት ላልታሰበ አደጋ የሚዳርግበት ጊዜ ብዙ ቢሆንም አሁንም ያንን መንገድ የሚከተሉ ደፋሮች አሉ። በዚህ መንገድ የተጓጓዘው ቁሳቁስ ኬላ ከመድረሱ አስቀድሞ ለሞተረኞች ይከፋፈላል። ከግዙፉ ጭነት ጥቂቱን የሚቆነጥረው ሞተገኛ ባልተፈቀደ አቋራጭ ኬላውን ያሻገረውን እቃ ከሌላው ወዲህ ማዶ ጠብቆ ለባለቤቱ ያስረክባል።

ከእነኚህ መንገዶች በአንዱ አዳማ የሚደርሰው ልብስና ጫማ በሦስት የጥራት ደረጃዎች ተከፋፍሎ በሦስት መንገዶች ለሽያጭ ይቀርባል።

በደጋጋ ቀበሌ ቁባ መስጊድ አካባቢ የሚገኝ ስፍራ የሚካሄደው የመጀመርያው ነው። ስፍራው “ጨረታ’’ የሚል ስያሜ ያገኘው የልባሽ ጨርቆች ጨረታ ስለሚካሄድበት ነው። አጫራቹ የልብሱን ፊት እና ኋላ አሳይቶ መነሻውን ዋጋ ይሰጣል። ተጫራቹም የተሻለ ዋጋ በማቅረብ ይጫረታል። ከፍ ባለ ስፍራ የቆመው አጫራች የተሻለ ዋጋ ላገረበው ገዢ ልብሱን ይወረውርለታል። ልብሱን የተረከበው ተጫራች በተራው የጠራውን ገንዘብ ጠቅልሎ ይወረውራል። አጫራቹ ለስራው የዋጋውን አስር በመቶ ከአቅራቢው ነጋዴ ይቀበላል። በዚህ ስፍራ የሚገበዩት አብዛኛዎቹ ገዥዎች ነጋዴዎች ናቸው።

የሱቅ፣ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በአዳማ ከተማ ዙሪያ ካሉ ከተሞች ለዚሁ ግብይት የሚመጡም አሉ። እንደነጋዴዎቹ ባይበዙም ተጠቃሚዎችም የቅንሽ ጨረታው ተሳታፊ ለመሆን “ጨረታ’’ን ይጎበኛሉ።

አጫራቾቹ የተደራጁ ወጣቶች ሲሆኑ ያጫረቱትን ከልብሶቹ ዋጋ ላይ 10% ለአገልግሎታቸው ክፍያ ይቀበላሉ። ሌሎችም በጫኝ አውራጅነት የተሰማሩ ወጣቶች ይገኛሉ። በሁለቱም የስራ መስክ የተሰማሩት ወጣቶች ለመንግሥት ግብር ይከፍላሉ። 

ሁለተኛው በሱቆች ውስጥ የሚሸጥበት መንገድ ነው። የ’ሰልባጅ’ ሱቆች በተለያየ የከተማዋ ክፍል ቢኖሩም “መብራት ኃይል’’ አካባቢ፣ አብዲ ጉዲና ህንጻ (ጨለማ ቤት)፣ ካራማራ ሆቴል አካባቢ ሳሚ የገበያ መዕከል፣ ናሽናል አካባቢ የሚገኝ የገበያ ማዕከል እና በቅርብ ጊዜ የተከፈተው ዱማል የገበያ ማዕከል ውስጥ በርከት ብለው ይገኛሉ። እነኚህ ነጋዴዎች አብዛኛው ምንጫቸው ግለሰብ ቸርቻሪ ነጋዴዎችና በየቀኑ የሚከናወኑ ጨረታዎች ናቸው። በጥራት ደረጃም የተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኙ አልባሳት እና ጫማዎች ይይዛሉ። 

እነኚህ ሱቆች ለችርቻሮ ገበያ የሚያቀርቧቸውን አልባሳት፣ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች እንደ ቴሌግራም ባሉ ለማኅበራዊ ትስስር ገጾች ያስተዋውቋቸዋል። ክፍያውን በባንክ በመፈጸም የመረጡት አልባሳት ወይም ጫማ በሌላ ገዢ እንዳይወሰድ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል።

በተለምዶ “ጨለማ ቤት’’ ተብሎ በሚጠራው ሕንጻ የወጣት ወንዶች ልብስ አቅራቢ ሱቅ ያለው ወጣት ዳንኤል ፍቃዱ አልባሳትን ለመሸመት “ቴሌግራም’’ የመጠቀም ልምዱ እያደገ እንደሆነም ይናገራል። ለስራው ሕጋዊ ንግድ ፍቃድ እና ለመንግስትም ግብር እንደሚከፍሉ ይናገራል። ባለትዳር እና ሌሎች ቤተሰቦቹንም በዚህ ስራ እንደሚያስተዳድር  ነግሮናል።

በአዳራሹ ልብስ ሲገዛ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ያነጋገረው ወጣት ሙሴ ተካ “ይህንን ገበያ በዋነኝነት እንድመርጠው ያደረገኝ ዋጋው ነው። ልብሶቹ ቶሎ ‘ፌድ’ ቢያደርጉም አዲስ ከሚሸጥባቸው ቡቲኮች አንጻር እነዚህ አቅምን ያገናዝባሉ” የሚል አስተያየቱን አካፍሎናል። 

በአዳማ ራስ ገበያ የንግድ ማዕከል የሴቶች ልብስ መሸጫ ሱቅ ያላት መቅደስ ላቀው “ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ልብሶች ባቀርብም በሰልባጅ ልብሶች የዋጋ አነስተኛነት እና በቀላሉ በመገኘት ብዙ ደንበኞቼ ሰልባጅ መጠቀም ጀምረዋል።”  ግብር ከሚፍለው ነጋዴ በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚሰሩ የተሻለ ገቢ እንዳለቸው ትናገራለች። ይህ አካሔድ በጊዜ ካልተገታ ሕጋዊውን ነጋዴም ወደ ሕገ-ወጥ መንገድ  እንደሚገፋፋ ትናገራለች።

ሦስተኛው የመንገድ ላይ ሽያጭ ሲሆን አብዛኛው ንግድ የሚከናወነው ከሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ ነው። የዋጋ ቅናሽ እና አነስተኛ ጥራትም ይስተዋልበታል። አብዛኛዎቹ ገዢዎች ለስብሰባ፣ ለትራንስፖርት እንዲሁም በተለያየ ጉዳይ አዳማን የሚጎበኙ እንግዶች ናቸው። 

ሮቢ ሆቴል አካባቢ ከሰኞ እስከ አርብ በአስፓልቱ ዳር፣ ቅዳሜ እና እሁድ በሮቢ ሆቴል አካባቢ ወደ ሥላሴ በሚወስደው መንገድ ቀኑን ሙሉ የአስፓልት መንገዱ ተዘግቶ የልባሽ ጨርቆች ገበያ ይከናወናል። 

ይህ ገበያ የህጻናት፣ የሴቶች፣ የወንዶች አልባሳት የሚያቀርብ ሲሆን ነጋዴዎች የተደራጁ መሆናቸውንም የአዳማ ሪፖርተራችን ለማጣራት ችሏል። እነኚህ በዚህ ቦታ ተደራጅተው የሚሰሩት ነጋዴዎች “ግንብ’’ ገበያ ከመፍረሱ በፊት ይሰሩ የነበሩ ናቸው። “ይህ ቦታ በጊዜያዊነት ነው የተሰጠን። መቼ ልቀቁ እንደምንባል አናውቅም መንግሥትም የቦታ ይሰጠን ለሚለው ጥያቄያችን መልስ አልሰጠንም።” የሚለው አቶ ቢኒያም ግርማ ነው። በአሁኑ ወቅት ማኅበሩ 168 አባላት እንዳሉት ይናገራል።

በቦታው ተደራጅተው ቢገኙም ነጋዴዎች የንግድ ፍቃድም ሆነ ሌላ ሕጋዊ ከለላ የላቸውም። ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት የሆነው ቢኒያም ግርማ ሁሉም የቤተሰብ ኃላፊነት እንዳለባቸውና የተረጋጋ የስራ አካባቢ እንደሚፈልጉ ይናገራል። 

የሀገር ውስጥ አምራቾች በምርት ግብዓት እጥረት፣ በዘመናዊ የማምረቻ ማሽነሪዎች እና ቴክኖሎጂ ያልተደገፈ አመራረት ዘዴ ስለሚጠቀሙ በቂ ምርት አያመርቱም።

“የሃገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ከአቅም በታች እያመረቱ ሲሆን ጠንካራ ስራ ለመስራት ጠንካራ ፖሊሲ ያስፈልጋል በመሆኑም መንግስት በበቂ ሁኔታ የተጠና እና ችግር ፈች የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የሃገራችንን ኢንዱስትሪዎች ከመሞት መታገድ ይገባዋል።” ያሉን የቴክስታይል ምህንድስና ባለሞያ እና መምህሩ ጀማል አስረስ ናቸው።

ተወዳዳሪ የጨርቃ ጨርቅ ኢንደስትሪ እንዲፈጠር በመንግሥት በኩል የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ፣ የሎጀስቲክ ወቅታዊ መረጃን ለአምራቾች በማቅረብ በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል፣ አንዲሁም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መሰጠት ካነሷቸው ሀሳቦች መሐከል ይጠቀሳሉ።

አስተያየት