“ክራውድ ዋን” የሚሸጥ ነገር የሌለው ነጋዴ፤ ብዙዎችን ለኪሳራ የዳረገው “ቢዝነስ”

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅመስከረም 27 ፣ 2014
City: Adamaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች
“ክራውድ ዋን” የሚሸጥ ነገር የሌለው ነጋዴ፤ ብዙዎችን ለኪሳራ የዳረገው “ቢዝነስ”

ከኮቪድ-19 ክስተት ጋር ተያዝዞ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ከተሞች ብዙም ያልተሰራበት አዲስ የግብይት አማራጭ የመስፋፋት ዕድል አግኝቷል። በእንቅስቃሴ ገደቡ እና በስብሰባዎች ክልከላው ሰበብ በበይነ መረብ አጋዥነት የሚካሄዱ ግብይቶች በዓይነትም በቁጥርም ጨምረዋል። በዚህ ሂደት የ‘ዴሊቨሪ’ ወይም የማድረስ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ተቋማት ተፈጥረዋል። ምርታቸውን በራሳቸው አድራሻ ለደንበኛቸው የማስረከብ ተጨማሪ አገልግሎት የጀመሩም ይገኛሉ። የኢንተርኔት ግንኙነትን በመጠቀም መደበኛ ሥራን በቤት ውስጥ መከወንም በዘመነ ኮቪድ በሰፊው የተዋወቀ የአሰራር ሂደት አማራጭ ነው። በአካል ሳይተያዩ በበይነ መረብ መገበያየትም አዲስ የአኗኗር ባህል ነው።

በተለይ በአዳማ ከተማ ይህንን መሰል እቅስቃሴዎች መበራከታቸውን ተከትሎ የተዋወቀው የ‘ቢዝነስ’ አማራጭ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ነው። የበርካታ ወጣቶችን ቀልብ የገዛውና ዓለም አቀፍ የ‘ዲጅታል’ ግብይት እንደሆነ የተነገረለት ቢዝነሱ ክራውድ ዋን (Crowd 1) በተሰኘ ተቋም በተግባር ላይ የዋለ ስለመሆኑ ተነግሯል።

እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ከዓመታት በፊት ቀደም ብሎ የተዋወቀው ይህ የግብይት መላ ተቃራኒ ሐሳቦች ተሰንዝረውበታል። ጥቂቶች ትርፋማ ሆነንበታል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ለኪሳራ እንደዳረጋቸው እና ማኅበራዊ ትስስራቸውን እንዳበላሸ መስክረውበታል። አሁን አሁን በአዲስ አበባ ያለው እንቅስቃሴ እየተዳከመ ቢመጣም በአዲስ አበባ አጎራባቾች እና በሌሎችም የኢትዮጵያ ከተሞች በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ የሚያረጋግጡ ማሳያዎች አሉ።

ክራውድ ዋን ማን ነው?

ክራውድ ዋን እውን የሆነው እኤአ በ2019 እንደሆነ ይነገራል። ራሱን በ“ክራውድ ማርኬቲንግ” ላይ የተሰማራ ተቋም ስለመሆኑ በድረ-ገጹ አስታውቋል። ግዙፍ የደንበኛ ስብስብ በመፍጠር ከሦስተኛ ወገን የሚያገኛቸውን ምርትና አገልግሎቶት ያገበያያል። ለአገልግሎቱ የማሻሻጥ ስራቸውን ካቀላጠፈላቸው ድርጅቶች ጋር ትርፍ ይጋራል። ይህ አካሄዱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት ይታወቁ የነበሩ የኔትወርክ ማርኬቲንግ አሰራሮች ለየት ያደርገዋል። በግብይት ሰንሰለቱን የሚቀላቀል ሰው የሚያገኘው ምንም ዐይነት ምርት የለም። “ጊፍት ኮድ” የሚል ስያሜ ያለው የሚስጥር ቁጥር ብቻ ይቀበላል።

ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች ስለ “ክራውድ ዋን” የቢዝነስ እንቅስቃሴ ግንዛቤ ለመስጠት በአማርኛ ቋንቋ ተመስገን በተባሉ ሰው የተዘጋጀው የ44 ደቂቃ ቪድዮ እንደሚያስደምጠው “ፌስቡክን፣ አሊባባን፣ ዑበርን የመሳሰሉ የኢንተርኔት ግብይት ተቋማት ያላቸው ትልቅ ሃብት የደንበኛ ስብስብ ነው። ስብስቡን በመጠቀም የሦስተኛ ወገን ምርቶችን የማሻሻጥ ወይም የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራሉ።”

ድርጅቱን እና አገልግሎቶቹን የሚያስተዋውቀው የድርጅቱ ድረ-ገጽ ተቋሙ በበይነ መረብ ሽያጭ ላይ እንደተሰማራ ያስረዳል። የሚያቀርባቸው/የሚሸጣቸው ሦስት አገልግሎቶችም የትምህርት (የስልጠና)፣ የጨዋታ እና የአኗኗር ዘይቤ ስለመሆናቸው ተገልጾአል። በእያንዳንዳቸው ስር የተዘረዘሩ ሌሎች አገልግሎቶችም አሉ። በአጠቃላይ ከአነስተኛ የበይነ-መረብ ንግድ እስከ ግዙፉ የሪል ስቴት ሽያጭ ድረስ ባሉ የንግድ አማራጮች ስለመሰማራቱ በስፋት ያወሳል። በአጫጭር ስልጠናዎቹ ስራ ፈጠራ ላይ ያተኮሩ ሐሳቦች እንደሚነሱ ገልጾአል።

እንደ ድረ-ገጹ ማብራርያ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የሎተሪ ጨዋታዎችም ከተቋሙ ዘርፈ ብዙ አማራጮች መካከል ናቸው። እንደ ኤፒክ ሎቶ ያሉ በአውሮፓ ሀገራት የሚዘወተሩ ታዋቂ የሎተሪ ጨዋታዎችም በየትኛውም ዓለም የሚገኝ ዕድል ሞካሪ በድረ-ገጹ አማካኝነት የሎተሪ እጣውን አግኝቶ የዕድል ጨዋታው አካል የሚሆንበት አማራጭ ተመቻችቶለታል። ‘ሜግስተር’ን እና ‘ፕላኔት 9’ን የመሰሉ ጨዋታዎች፣ በአኗኗር ዘይቤ ሥር የተካተቱ ‘ላይፍ ትሬንድ’ እና ‘ትሪብዩት’ የተሰኙ አቅርቦቶችም ተጠቃሚዎችን የሚያማልሉ ጥቅሞች ስለመሆናቸው በቪድዮ እና በፎቶግራፍ ጭምር ተደግፈው በስፋት ተብራርተዋል።

የድርጅቱን ዋና መቀመጫ በተመለከተ ተመሳሳይ መረጃዎች የሉም። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የድርጅቱ ዋና መቀመጫ “ዱባይ” እና “ስፔን” እንደሆኑ የሚያሳዩ የተለያዩ መረጃዎች አግኝቷል። በሚከተለው የ“ፒራሚድ ስካም” የግብይት ስልት አማካኝነት የተለያዩ ሀገራት እንቅስቃሴውን አግደውበታል።

በ2019 ዓ.ም. ከኖርዌይ የሎተሪ አስተዳደር ተቋም የእግድ ውሳኔ ተላልፎበታል። በአፍሪካ፣ ኤሲያ እና አሜሪካ ሐገራትም በተለያየ ጊዜ ክስ እና እግድ ተላልፎበታል። በክራውድ ዋን ብቻ ሳይሆን እናት ድርጅት ነው የሚለው የ“ክራውድ ኢምፓክት ቴክኖሎጂ” ዋና ሥራ አስፈጻሚም ጭምር በተቋሙ ውስጥ እስካገለገለበት ዲሴምበር 2020 ደረስ ከየሐገራቱ በድርጅቱ ምክንያት ተባሯል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጆሀን ቮን ሆልስቴይን በድርጅቱ የዩቲዩብ ቻናል እና ሌሎችም ቪዲዮዎች በሚያስተላልፈው መልእክት በኔትወርክ ማርኬቲንግ የ20 ዓመታት ልምድ እንዳካበተ ይናገራል። ይሁን እንጂ በእርሱ አመራር ስር ያለፉ ተቋማት መጨረሻቸው እንደማያምር መንገዱን የተከታተሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ሰውየው የመሰረታቸው፣ የመራቸው፣ የተቀጠረባቸውና ያስተዳደራቸው ድርጅቶች መጨረሻ መፍረስ፣ መታገድ አለያም መባረር ነው። ከእነዚህ ካመለጡ ደግሞ መጨረሻቸው በኪሳራ ይደመደማል። ግለሰቡ አሁን በማወዛገብ ላይ ከሚገኘው “ክራውድ ዋን” በፊትም “icon media lab”፣ “I Qube”፣ “My Cube” የሚሰኙ በ“ኔትወርክ” ግብይት እና በዌብሳይት ማበልጸግ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ተቋማት የነበሩት ሲሆን ሁሉንም ከስሮ ዘግቷቸዋል።

በአገልግሎቶቹ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች

ተቋሙ አቀርባለሁ የሚላቸው አገልግሎቶች የእርሱ አይደሉም የሚል ቅሬታ ይቀርብበታል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት የትምህርት አገልግሎቱ ከሌሎች ምንጮች የተቀዳ ነው። ነባሩን የተለመደ አካሄድ “ባህላዊ” ብሎ የሚያጣጥለው ተቋሙ ዩንቨርሲቲ እና ኮሌጆች ውስጥ በአካል ሳይጓዙ መማርን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ የተለያዩ የትምህርት ‹ፓኬጆች› አዘጋጅቻለሁ ይላል። የ“ቢቢሲ ኒውስ አፍሪካ” ጋዜጠኛዋ አያንዳ ቻርሊ የድርጅቱን ሕጋዊ ያልሆነ አገልግሎት ባጋለጠችበት የ“ዶክመንተሪ” ቪድዮ የትምህርት ይዘቱ ከሌላ መጽሐፍ ሙሉ ለሙሉ የተቀዳ ስለመሆኑ ዐሳይታለች።

በአኗኗር ዘይቤ እና የጉዞ አገናኝ ድረ-ገጾቹ በአብዛኛው ወደ ሌላ ዌብሳይቶች የሚወስድ ማስፈንጠሪያ እንጂ አንድም የራሱ ይዘት እንደሌለው ቅሬታ ይቀርብበታል። የሐሳቡ ደጋፊዎች በበኩላቸው ቅሬታዎቹ የተቋሙን አደረጃጀት ካለመረዳት የተሰነዘሩ ናቸው ይላሉ። ተቋሙ የራሱ አገልግሎት እንደሌለው እና በደንበኛ ስብስቡ አማካኝነት የሌሎችን ምርትና አገልግሎቶች እንደሚያቀርብ ከመዘንጋት የመጣ ቅሬታ እና አስተያየት ስለመሆኑ ይከራከራሉ።

በዓለም ዓቀፍ የንግድ ተቋም ውስጥ የምጣኔ ኃብት ባለሞያ የሆነው ፍጹም ተስፋዬ “አብዛኛውን ጊዜ በእንዲህ ዓይነት ተቋማት የሚመረቱ ምርቶች ፋይዳቸው እዚህ ግባ የሚባልም አይደለም” ይላል። “ብዙውን ጊዜ ምርቶቹን መጠቀሙ ሁለተኛ ጉዳይ ሲሆን ይታያል” ሲል የታዘበውን ነግሮናል። 

የምጣኔ ኃብት ባለሙያው አቶ አብቧል ተክሌ በበኩሉ “እንደዚህ ዐይነት ድርጅቶች ሁለት ዐይነት ናቸው። አንዳንዶቹ በፊት የምታውቀው ምርት ተጨማሪ ግብአት ታክሎበት ልዩ አገልግሎት እንዲያበረክት ሆኖ መጥቷል ይላሉ። ለምሳሌ የሚሸጠው ሰዓት ቢሆን ሌሎች ገበያ ላይ ያሉ ሰዓቶች የማይሰጡትን የተለየ ግን ጠቃሚ አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ ይህንን ሰዓት ለመግዛት በዚህ ኔትወርክ ትስስር ውስጥ መግባት ግዴታ እንደሆነ እና እዚህ ውስጥ ያልገባ ሊያገኘው እንደማይችል ይናገራሉ። ሌሎቹ ደግሞ እቃው የትም የሚገኝ ቢሆንም ከፍ ባለ ዋጋ ይሸጡታል። ይህንን የሚያደርጉትም ለተመሳሳይ ሰዎች ኮሚሽን ለመክፈል እንደሆነ በመንገር ያሳምኑሃል” በማለት ከአስተውሎቱ እና ከገጠመኞቹ የተረዳውን ነግሮናል። “የሚገርመኝ ግን” ይላል አቶ አብቧል። “የሚገርመኝ ግን ሁሉም ተመሳሳይ ግብይት የሚከተሉ ተቋማት ሥራቸውን ከሞቲቬሽናል ግንግሮች ጋር ማዛመዳቸው ነው” ብሎናል።

በጓደኛው አማካኝነት የክራውድ ማርኬቲንግን የተቀላቀለው ወጣት ኪሩቤል ተስፋዬ ተቋሙን የሚያውቀው ከሦስት ዓመታት በፊት መሆኑን ነግሮናል። በ14 ቀናት ውስጥ በስሩ ማስገባት የሚጠበቅበትን 4 ደንበኛ ማስገባት ማለመቻሉ ቢከስርም አተረፍን የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ሰምቷል። “ልጆቹ አተረፍን ይበሉ እንጂ ከድርጅቱ ብር ሲቀበሉ ዐላየሁም። ካስገቧቸው ሰዎች ገንዘብ እየተቀበሉ ብዙ ገንዘብ ያገኙ ሰዎች ግን አውቃለሁ” ብሎናል። አሁንም አልፎ አልፎ የድርጅቱን ድረ-ገጽ የሚጎበኘው ወጣቱ “የድርጅቱ እንቅስቃሴ ቢዝነስ ሳይሆን ማጭበርበር ነው” ይላል።

ቀድመው ደንበኛ በሆኑ ሰዎች ጋባዥነት የግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ የሚሆኑ ሰዎች 4 የፓኬጅ አማራጮች ይቀርቡለታል። አማራጮቹ ነጭ፣ ጥቁር፣ ወርቅ እና ታይታኒም የሚል መጠሪያ አላቸው። ለእያንዳንዳቸው የተመደበ የገንዘብ አማራጭም ይገኛል። ለነጭ 99፣ ለጥቁር 299፣ ለወርቅ 2,499 ዩሮ መክፈል የተመዝጋቢው የመጀመርያ ግዴታ ነው። ክፍያውን ፈጽሞ የሚቀላቀለው ግለሰብ ከሌላ ቀድሞ ከተቀላቀለ ተመዝጋቢ ስር እንደገባ ሁሉ እርሱም በስሩ ሌሎች ግለሰቦችንም ማስገባት ይኖርበታል። በግራ እና በቀኝ የሚሉ ሁለት አቅጣጫዎች የሚኖሩት ተመዝጋቢው አቅጣጫዎቹን እያመጣጠነ በእርሱ ስር ደንበኝነቱን የሚቀላቀሉ ሰዎች ይመለምላል።

የገበያ ጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሳሙኤል መሳፍንት “የአንዳንዶቹ አነሳስ የተለመደው የግብይት ስርአት ባህላዊ እንደሆነ ከማሳመን ይጀምራሉ። ምርቶቹም ሌሎች የሽያጭ አማራጮች ላይ እንደማይገኙ ይናገራሉ። በዚህ ትስስር ውስጥ መግባት ጥሩ ሰው የመሆን መገለጫ እንደሆነም ያብራራሉ። ይህንን “ቢዝነስ” የሚቀላቀሉት ሰዎች በከፍተኛ ጉጉት ስለሚቀላቀሉ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያወጡትን ገንዘብ እንደሚመልሱ ስለሚያስቡ ቶሎ ይሰበራሉ” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። መስራትም መማርም በአጭር ጊዜ በፍጥነት መከናወን ይችላል የሚለው ድርጅቱ የሚጠቀምበት ወጣቶችን የማማለያ ስልት ሲሆን ከቅርብ ቤተሰብ እና ዘመዶች በመጀመር የምታውቃቸውን፣ የሚያምኑህን፣ የሚወዱህን ሰዎች ወደ ስብስቡ ብትጋብዝ ሚልየነር ትሆናለህ በሚል ባዶ ተስፋ ብዙዎች ስለመታለላቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለው እንቅስቃሴ

“ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው የግብይት ስርአት የሚያራምዱ ተቋማት ኢትዮጵያ ውስጥ መስፋፋት የጀመሩት ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው። የሐገር ውስጥ እና የውጭ ቁሳቁሶችን በመግዛት ‹‹ራሳችሁን ለውጡ›› የሚሉትን እዚህም እዚያም ያሉ ሰባኪዎች ያስቆመው የመንግሥት ክልከላ ነበር። አሁንም ነገሩ የተፈቀደ አይመስለኝም” የሚለው የገበያ ጥናት ባለሙያው አቶ አብቧል ነው። እንደ አቶ አብቧል ማብራሪያ አሰራሩ ተመሳሳይ የግብይት መላዎች አክሳሪነታቸው ስለሚበዛ ክልከላ ተጥሎባቸዋል። ለመታገዱ ምክንያት የውጭ ምንዛሬን ከሐገር የሚያስወጣ በመሆኑ፣ ለግብር አከፋፈል ምቹ አለመሆኑ የሚሉት ይገኙበታል። መደበኛ እንቅስቃሴን ማዛባቱም በማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ዘንድ በበጎ አልታየለትም።

ተስፋሚካኤል ጥላሁን የቅርቤ የሚለው ጓደኛው ያቀረበለትን ግብዣ ተቀብሎ “ሥራውን” የተቀላቀለ የ“ክራውድ ዋን” ደንበኛ ነው። “የ99 ዩሮ ‘ጊፍት ኮድ’ ገዝቼ ሥራውን ጀመርኩ” (‘ጊፍት ኮድ’ ማንኛውም አዲስ ተመዝጋቢ አባል ወደ ግብይት ስርአቱን እንዲቀላቀል የሚያስችለው የሚስጥር ቁጥር “አክቲቬሽን ኮድ” ነው።) የሚለው ወጣቱ ‹ጊፍት ኮዱ›ን ሲገዛ መክፈል ይጠበቅብሃል የተባለውን 99 ዩሮ በኢትዮጵያ ምንዛሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት በእኔ ስር ትገባለህ ባለው ወዳጁ የአካውንት ቁጥር አስገብቷል። “ገንዘቡን ሳስገባ የኮድ ቁጥር ተሰጥቶኛል” ብሎናል። ሽያጩን ያካሄደለት ተቋም ምንም ዐይነት ደረሰኝ እንዳልሰጠውም ነግሮናል። ቀድሞ በተስማማበት የድርጅቱ ሕግ መሰረት ሁለት ሰዎችን ማስገባት ችሏል። በስሩ ካስገባቸው ሰዎች መካከል አንደኛው ሌሎች ሁለት ሰዎችን መልምሏል። 

“በ14 ቀናት ጊዜ ውስጥ 4 ሰዎች ካስገባው 125 ዩሮ እንደማገኝ ገልጾልኝ ነበር። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ሰው ባለማስገባቴ ሳይሳካ ቀረ። ስራው እጅግ አድካሚ ነው። ድርጅቱን እንደኔ እንዲቀላቀሉ የምመለምላቸው ሰዎች በቀላሉ ሐሳቤን የሚቀበሉ አልነበሩም። ፈቃደኛ ስላልሆኑልኝ ስራውን ተውኩት። ብሬም ከሰረ” ካለ በኋላ ኪሳራው የ99 ዩሮ ብቻ እንዳልሆነ ያስረዳል። “ሰዎችን ለዚህ ስራ ለመመልመል ስልክ መደወል ያስፈልጋል። ከስልኩ በተጨማሪ ተገናኝቶ ሻይ ቡና መባባል አለ። ሰዎቹ የማሰቢያ ጊዜ የሚፈልጉ ከሆነ ደግሞ በሌላ ቀን መገናኘት አለ። የታክሲ እና የባጃጁን የኢንተርኔቱን ጨምሮ ከታሰበ ብዙ ነው። እንደ ሥራ ይዤው ስለነበር አገኛለሁ ብዬ ያጣሁት ብዙ ነው። እኔን አምነው ስራውን የተቀላቀሉት የቅርብ ሰዎቼንም አጥቻለሁ። ይሄ ደግሞ ከገንዘብ እና ጊዜውም በላይ የሚቆጭ ኪሳራ ነው” ሲል በማኅበራዊ ሕይወቱ የደረሰበትንም ኪሳራ አብራርቶልናል። እርሱን ጨምሮ ወደ ድርጅቱ ያስገቡት ሌሎች ወዳጆቹ ጭምር አማላይ ትርፉን እንጂ ሂደቱን፣ ኪሳራውን አለማሰባቸውን እንዲሁም ስለ ድርጅቱ ምርቶች በቂ እውቀት እንደሌላቸው ትዝብቱን አካፍሎናል። ከድርጅቱ ጋር ተቀላቅሎ ሥራ ሲጀምር በ14 ቀናት ውስጥ የሚጠበቅበትን የሰው ብዛት ማለትም 4 ሰው ማስገባት ከቻለ የመጀመርያውን ዙር ክፍያ ያገኛል። ልክ በ15ኛው ቀን 125 ዩሮ ይገባለታል። ይህንን ክፍያ ማግኘት የቻለ ሰው ከኪሳራ መውጣቱን ያረጋግጣል። ከዚህ በኋላ በስሩ በሚያስገባቸው ሰዎች በሚከፈለው ክፍያም ከሥራው የሚያገኘውን ትርፍ መሰብሰብ ይጀምራል።

የድርጅቱ መመርያ ማንኛውም የክራውድ ዋን ሰራተኛ አንድ ደንበኛ ወደ ድርጅቱ ከቀላቀለ በኋላ አዲስ ገቢው ከፍሎ ከገባው ገንዘብ መጠን 10 በመቶ ኮሚሽን ይታሰብለታል ይላል። የኮሚሽን ክፍያው የሚፈጸመው በሦስት ወራት ውስጥ ሲሆን ወጪ ማድረግ የሚቻልባቸው አማራጮች ተቀምጠዋል። ክፍያውን ከመቀበያ (ወጭ ማድረጊያ) አማራጮች መካከል እንደ ‘ቢትኮይን’ እና ‘ኢተረም’ ያሉ የዲጅታል ገንዘብ አማራጮች ይገኙበታል። ለክሬዲት ካርድ ተጠቃሚዎችም በ‘ዩሮ’ ይፈጸማል ተብሏል። ሌላኛው አማራጭ ደግሞ ይህንኑ ኮሚሽን አጠራቅሞ ወደ ጊፍት ኮድ መለወጥ ነው። ወደ ጊፍት ካርድ የተለወጠውን ክፍያ አዲስ ለሚገቡ ደንበኞች በመሸጥ ወደ ብር ቀይሮ ክፍያውን መቀበል ይቻላል። “ድርጅቱ አትራፊ ነው፡፡ ተጠቅመንበታል” በማለት የሚከራከሩት ደንበኞች ያጠራቁትን ኮድ ለሚያስገቧቸው ሰዎች በብር የሚሸጡት ናቸው፡፡ ድርጅቱን ሲቀላቀል በቀጥታ በዩሮ ክፍያ የሚፈጽም ሰው ተጨማሪ ጥቅሞች እንዳሉትም ድርጅቱ አሳውቋል።

ኢትዮጵያውያኑ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች የተቋሙን አሰራር ከሚተቹባቸው ሰበቦች ውስጥ አንዱም ይህ ነው አቶ አብቧል ተክሌ ይህንን ሐሳብ ከሚያራምዱ ባለሙያዎች መካከል ናቸው። “አንደኛው የዚህ ተቋም ችግር በመከራ የመጣን የውጭ ምንዛሪ ማስወጣቱ ነው” ይላሉ። እንደ ባለሙያው ገለጻ “በዚህ ሥራ ምክንያት ኪሳራ ውስጥ የሚገቡት ሰዎች ቁጥር ከሚያተርፉት ይበልጣል። ይህ ማለት ዶላር ወይም ዩሮውን ከሚያስገቡት ሰዎች ይልቅ የሚያስወጡት ይበልጣሉ ማለት ነው። ሐገሪቱ ደግሞ በተቻላት መጠን ዶላር የሚያስገባላትን ቢዝነስ አስፍታ ዶላር የሚያስወጣባትን ቢዝነስ መቀነስ ነው ፍላጎቷ። የድርጅቱ አሰራር ደግሞ ከዚህ አካሄድ ጋር ይጣረሳል። ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው የሚባልበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው” ሲል ያብራራል።

በዚህ ዓይነት ከተቀመጡት ፓኬጆች አንዱን ገዝቶ የገባ ሰው የከፈለውን ብር ለመመለስና ተጨማሪ ገንዘብ ለማትረፍ በስሩ ብዙ ሰዎች ማስገባት አለበት። እርሱ ብቻ ሳይሆን በስሩ የገቡት ደንበኞችም ሌሎች ሰዎችን በስራቸው ማስገባት አለባቸው። ይህም ከላይ ያለውን ሰው በገቡት ሰዎች ልክ የ10 በመቶ ኮሚሽን እንዲያገኝ ያስችለዋል። ይህ አሰራር “ፒራሚድ” ስኪም ይባላል።

ፒራሚድ ስኪም ምንድን ነው?

ፒራሚድ ስኪም አንድን ምርት ለመሸጥ የሚያገለግል መላ ነው። የተለመደውን የሽያጭ ሰንሰለት አይጠቀምም። ከአምራች ወደ አከፋፋይ፣ ከአከፋፋይ ወደ ቸርቻሪ የሚሄደውን የግብይት ሰንሰለት አይከተልም። የማስታወቂያ እና የፕሮሞሽን ወጪም አያወጣም። እንደ ሐሳቡ አራማጆች ማብራሪያ ከሆነ ከምርት ሂደት በኋላ ያለውን የግብይት ሂደት እና በሂደቱ የሚወጣውን ወጪ በመተው ደንበኞች አፍርተው ምርቱን ለሚያሻሽጡለት ግለሰቦች ትርፉን ያጋራል ወይም ኮሚሽን ይከፍላል። አብዢ ዛፍ በመሰለው በዚህ ሰንሰለት ውስጥ የገባ ማንኛውም ግለሰብ አንድን ቁስ ከመሸጫው ዋጋ በላይ የገዛው ለሌሎች አባሎች ኮሚሽን ለመክፈል እንደሆነ ይነገረዋል። ገዝቶ እየተጠቀመበት የሚገኘውን ቁስ ጥሩነት እየተናገረ ሌሎች ደንበኞችን ለድርጅቱ እንዲያፈራም ይጠበቅበታል። ገዢው በአንድ ጊዜ የሸማችም የአሻሻጭም ሚና ይኖረዋል።

“በፒራሚድ ስኪም እሴትን ከመጨመር ይልቅ ሀብትን እንዳለ ማስተላለፍ ላይ በመሆኑ የሚሰራው በሒደት ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና ያመጣል። ሌሎች ዘርፎችንም እያዳከመ ከጨዋታ ውጪ የማድረግ እድሉ ሰፊ ነው” የሚለው ፍጹም ተስፋዬ ከዚህ ቀደም ዕንደታየው ተመሳሳይ ድርጅቶች ከሚያንቀሳቅሱት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አንጻር  እሴት አለመጨመር ለሀገር ከባድ ኪሳራ ነው ይላል።

ሕጉ ምን ይላል?

በኢትዮጵያም ተሻሻለው የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2013 ዓ.ም. መሰረት በፒራሚድ ስኪም በግልጽ ታግዷል። በአንቀጽ 22 የተከለከሉ ድርጊቶች በሚል ቁጥር 6 ላይ እንዲህ በጉልህ ተቅጧል።

“አንድ ሸማች አንድ የንግድ እቃ ወይም አገልገሎት በመግዛቱ ውይም የገንዘብ መዋጮ በማድረጉ እና በሸማቹ አሻሻጭነት ከእርሱ ቀጥሎ ሌሎች ሸማቾች የንግድ እቃውን ወይም አገልገሎቱን ሚገዙ ውይም የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ከሆነ ወይም በሽያጭ ስልቱ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ በሸማቹ ቁጥር ልክ የገንዘብ ወይም የዓይነት ጥቅም ሚያገኝ የሚገልጽ ፒራሚድ የሽያጭ ስልት ተግባራዊ ማድረግ ወይም ለማድረግ መሞከር ይህንን የተላለፈ ነጋዴ (ማንኛውም አካል) ከዓመታዊ ገቢው ከ7 እስከ 10 በመቶ እንዲሁም ከ3 እስከ 7 ዓመት ቢደርስ የእስር ቅጣት ይጣልበታል።”

“የዚህ ዓይነት አሰራር ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ በውል ለማወቅ ስለሚያዳግት፣ ስራው ለማንኛውም ተቀጣሪ ክፍት በመሆኑ ለግብር ስርዓት እጅግ አስቸጋሪ” ነው የሚለው ፍጹም ተስፋዬ። መንግስት ማግኘት የሚገባውን ግብር ያሳጣል ይላል።

የአዳማ ኗሪዋ ሀዊ ጌታቸው (ስሟ የተቀየረ) የኮሌጅ ተማሪ ስትሆን በትርፍ ጊዜዋ በተለይም በኮቪድ-19 ከፊል የእንቅስቃሴ ገደብ ወቅት እንደሰራች ትናገራለች። እስካሁን የገጠማት ችግር እንደሌለ የምትናገረው ሀዊ ሌሎችም ጓደኞቿ እየሰሩ እንደሆነም እንዲሁ። “እንዲህ ያለ ሕግ መኖሩን እንዳማታውቅ እና እስከአሁንም የጠየቀኝ የሕግ አካልም ሆነ ግለሰብ የለም” ትላለች። በገዛችው ፓኬጅ ምን እንደተጠቀመች እንደነበረ በውል እንደማታስታውስ የነገረች ሀዊ “በወቅቱ እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ዋነኛ ትኩረታችን ሰው አስገብቶ ገንዘብ ማግኘት ነው።” ብላለች።

በአፍሪካ እንደ ኢኮዋስ ያሉ ቀጠናዊ ተቋማት፣ ናሚቢያ፣ ቡሩንዲ፣ ኬንያ በመንግሥት ደረጃ በክራውድ ዋን ላይ ማስጠንቀቂያ እና እግድ ካወጡት መሃከል ናቸው። ከዚህ ቀደም ይታወቁ ነበሩት “ቲያንስ” እና “ክዌስትኔት” ይህንኑ የፒራሚድ ስኪም ይጠቀሙ እንደነበር ይታወቃል። እነኚህ እና መሰል ድንበር ተሸጋሪ ድርጅቶች በደሃ እና የሕግ ቁጥጥር ስርዓታቸው በላላ ሀገራት ላይ በስፋት ይንቀሳቀሳሉ።

ከዚህ ቀደም በነበረ ልምድ እነኚህ ሥራዎች ብዙ ግለሰቦችን ለመጭበርበር እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ጥቁር ገበያ መስፋፈት፣ ገንዘብ ከሀገር ለማሸሽ መንስዔ መሆናቸው ታይቷል። አሁን ሀገሪቱ ባለችበት ሁኔታም ለሽብር ስራ የገንዘብ ምንጭ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው።

የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ፍጹም ተስፋዬ “አብዛኞቹ ድርጅቶች መሰረታቸው ከሀገር ውጪ በመሆኑ ገንዘብ ከሀገር ማስወጣት እና ገንዘቡን ወደ ማዕድን ቀይሮ ለማውጣት የመሞከር እድላቸው ሰፊ ነው” የሚል ሀሳቡን ይደመድማል።

“ድርጅቶች ብዙውን ጊዜ የህግን ሳይሆን የአፈጻጸምን ክፍተት ተጠቅመው የሚሰሩ ናቸው። የፍቃድ አሰጣጥ፣ የቁጥጥር ስራ የተለያዩ አካለትን የቅንጅት ስራ የሚፈልግና በአንድ የመንግሥት አካል ብቻ የሚሰራ ተግባር መሆን የለበትም” የሚለው የሕግ ባለሞያው ይታፈሩ ሙላቱ  የሕግ ተጠያቂነቱ ተደራራቢ ሆኖ ስለሚገኝ ቅድሚያ በምን ዘርፍ የተመዘገበ ፍቃድ እንዳላቸው፣ በየትኛው አካል ብቃታቸው እንደተረጋገጠ  ማወቅ ያስፈልጋል” ሲል አስተያየቱን ይናገራል፤ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የተጠቀሰው ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ የተመዘገበ ወኪል ቢሮ እንዳልከፈተ ለማረጋገጥ ችሏል።

የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች በበኩላቸው ተመሳሳይ አሰራር ያላቸው የንግድ ተቋማት የወጣቶችን የስራ ወኔ በመስለብ፣ የሞያን እና የትምህርትን አስፈላጊነት በማጠልሸት በሀገር እና በህዝብ ላይ ከባድ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ? ይወተውታሉ።

አዳማ ከተማ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ንግድ ምዝገባ ቡድን መሪ አቶ ከረሳ ተስፋ “እንዲህ የሚባል ድርጅት እንደማያውቁና በእነርሱ በኩል ማጣራት እንደማይቻል ነግረውናል። የድርጅቱ የአዲስ አበባ ከተማ እንቅስቃሴ ተስፋፍቶ በነበረበት ወቅት ከፍለው በመቀላቀል አብረውት ሲሰሩ ከቆዩ ሰዎች መካከል አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው ሐሳብ ሰጪዎችም አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ እንዳልነበረው አረጋግጠውልናል።

Author: undefined undefined
ጦማሪተስፋልደት ብዙወርቅ