ኅዳር 26 ፣ 2015

ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት እና የነዳጅ ሰልፍ ያማረራቸው የአዳማ ከተማ ሹፌሮች

City: Adamaኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

ህገ ወጥ የነዳጅ ሽያጭ እና ክምችት መበራከቱ ስጋት ፈጥሯል። አሽከርካሪዎች በነዳጅ እጦት ሳቢያ ከህገ ወጥ ነጋዴዎች በእጥፍ መግዛት እና ህገ ወጥ ነዳጅ ክምችት ባለባቸው አካባቢዎች የአደጋዎች መከሰት ዋነኛ ችግር ሆነዋል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት እና የነዳጅ ሰልፍ ያማረራቸው የአዳማ ከተማ ሹፌሮች
Camera Icon

ፎቶ፡ ከማህበራዊ ድረ ገፅ የተገኘ ምስል

ስሙ ሔኖክ እንደሆነ የነገረን የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ‘ባጃጅ’ አሽከርካሪ ሲሆን “በቀን  150  እስከ 400 ብር አገኛለሁ” ብሎ ለባጃጁ ባለቤት የቀን ገቢ 150 ብር እንደሚያስገባ ይናገራል። በየአስር ቀኑ 1 ሺህ 5 መቶ ብር ለባጃጅ ባለቤቱ አስገባለሁ የሚለው ጌታሁን የነዳጅ እጥረቱ በአንድ ጊዜ 8 ሊትር ብቻ የምትይዘው የባጃጁን የነዳጅ ታንከር ለመሙላት ቀኑን ሙሉ ሊጠብቅ አንደሚችል ይናገራል። አንድ ቀን ሙሉ ተጠብቆ የቀዳው ነዳጅ ግን ግፋ ቢል ከሁለት ቀን በላይ እንደማያሰራው የሚገልፀው ሔኖክ “ሁለት ቀን ሰርቶ አንድ ቀን መሰለፍ ነው” ሲል ያለውን ቸግር ያስረዳል።

ነዳጅ ማደያዎች በከተማው ንግድ ጽህፈት ቤት ልዩ የፍቃድ ደብዳቤ ላላቸው አካላት በደብዳቤ ማስቀዳት ግዴታቸው ቢሆንም የተፈጠረው የቁጥጥር ክፍተት ግን ለህገ-ወጥ አሰራር ማጋለጡን አሽከርካሪዎች ይናገራሉ። የነዳጅ ማደያ ሰራተኞች ጉቦ እየተቀበሉ ከ6 እስከ 8 ጄሪካን በባጅጅ ውስጥ ይዘው የሚሄዱ ቀጂዎቸን ያስቀዳሉ የሚለው ሌላኛው አሽከርካሪ ጌታሁን “ይህ በህገ-ወጥ መንገድ የሚሸጥ ነዳጅ መልሶ አሽከርካሪዎችን እየጎዳቸው” መሆኑን ይናገራል።

በአዳማ ከተማ በየመንደሩ የሚገኙ ነዳጅ ሻጮች የግዙፎቹን እና ህጋዊዎቹን ነዳጅ ማደያዎች ስራ እየተቆጣጠሩ ነው። የነዳጅ ፍላጎታቸውን በቀጥታ ከማደያዎች ማሟላት ያልቻሉና በሁኔታው የተማረሩ የአዳማ ከተማ ታክሲ ሹፌሮች “ማጠራቀሚያ ገንዳውን እና ቦቴዎቹን በጄሪካን አልበው በትንንሽ የፕላስቲክ ጠርሙሶች ይቸበችቡታል” ይላሉ። 

ይሄንን ችግር በአስቸኳይ የሚፈታ አካል ባለመኖሩ ደግሞ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን እና ሹፌሮችን ለረጅም ሰዓት ከመሰለፍ እስከ እጥፍ ወጪ ማውጣት ድረስ እየዳረጋቸው መሆኑ እንደሚያሳስባቸው ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል። የነዳጅ አቅርቦት ጉዳይ በአዳማ አንገብጋቢ የኢኮኖሚ እና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ሆኗል። ከሰሞኑ ባለፈው እሁድ ለመጨረሻ ጊዜ የከተማዋ ማደያዎች ነዳጅ መጨረሳቸውን ተከትሎ አሽከርካሪዎች ከማደያ በግልፅ ያጡትን ነዳጅ ከመንደሮች ውስጥ ለመግዛት ተገደዋል። 

በዚህም ደግሞ በድብቅ ከሚሸጡ ሰዎች 2 ሊትር ነዳጅ ከሀገር አቀፉ ታሪፍ በእጥፍ እስከ 180 ብር እየገዙ ሲጠቀሙ የነበረ ሲሆን በአሁን ሰዓት ዋጋው በ3 እጥፍ ጨምሮ እስከ 250 ብር እየተሸጠ እንደሚገኙ አዲስ ዘይቤ ታዝባለች።

ከቀናት በፊት የአዳማ ፖሊስ በተለይም ለአዲስ ዘይቤ እንደገልለፀው፤ በአዳማ ከተማ ዳቤ ክፍለከተማ ሀንጋቱ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቀጠና 5 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግለሰብ ቤት ላይ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ የ18 ዓመት ታዳጊ ህይወት ሲጠፋ የ7 ዓመት ህጻንን ጨምሮ 3 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። ተጎጂዎቹም በአዳማ ሆስፒታል በህክምና ክትትል ላይ እንደሚገኙ ገልጸን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የእሳት አደጋውን መንስዔ በፖሊስ እየተጣራ እንደሚገኝ መረጃውን ያደረሱን ምክትል ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ “በስፍራው የህገ-ወጥ የነዳጅ ክምችት እንደነበር እና ህገ-ወጥ የነዳጅ ሽያጭ ይከናወን እንደነበር” ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደምም በተለምዶ ቀበሌ 10 በሚባለው አካባቢ መሰል እሳት ቃጠሎ ተነስቶ የሰው ህይወት መጥፋቱንም ምክትል ኢንስፔክተሯ ይገልፃሉ።

በአዳማ ከተማ በአጠቃላይ 18 የነዳጅ ማደያዎች ቢኖሯትም በቋሚነት የሚሰሩት ከ5 አይበልጡም፤ እነርሱም ከአንድ ቀን በላይ በተገቢው ሁኔታ አለመስራታቸው ለህገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አሽከርካሪዎች ይናገራሉ።

ቢያንስ ከ15 ሺህ በላይ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የሚገኙባት አዳማ፤ በከተማ መስፋፋት እና በህዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት በየጊዜው የትራንስፖርት አገልግሎቷ ላይ መጨናነቅ ይስተዋልበታል። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ ለነዳጅ ፍላጎት ንረት አስተዋፅዎ አድርጓል። 

ከትራንስፖርት ዘርፉ በተጨማሪም ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ጋር በተያያዘ የጤና ተቋማት፣ ካፌዎች፣ ሆቴሎች፣ የእጥበት አገልግሎት ሰጪዎች እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚያስፈልጋቸውን ነዳጅ በገበያ ላይ አለመገኘቱ ስራቸውን እያስተጓጎለ እንደሆነ ይናገራሉ።

ነዳጅ ለማግኘት በአማካኝ ከ6 እስከ 12 ሰዓታት ድረስ በነዳጅ ማደያዎች በሰልፍ ላይ እናጠፋለን ሲሉ ምሬታቸውን የሚገልፁት አሽከርካሪዎች ህገ-ወጡ ችፍቼ ግን በማንኛውም ሰዓት በእጥፍ ዋጋ ይገኛል ይላሉ። 

ከዚህ ቀደም ወርሃዊውን የነዳጅ እና የነዳጅ ምርቶችን የዋጋ ክለሳ ሰበብ አድርገው ነዳጅ ማደያዎች “ነዳጅ የለም” ይሉ ነበር የሚሉት ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት አሽከርካሪዎች “ያለፈውን አንድ ዓመት ግን በአዳማ ረጃጅም የነዳጅ ማደያ ሰልፎችን መመልከት”  የሰርክ ጉዳያቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

በግል መኪና ቀድተው የሚሸጡ እና በጄሪካን ቀድተው የሚሄዱ ነጋዴዎች ዋነኛ የህገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ተሳታፊ መሆናቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች ቁጥጥር ሊደርግባቸው እንደሚገባ ያሳስባሉ። ችግሩ ከዚህ ሲሰፋ ደግሞ ቢሾፍቱ ድረስ ሄዶ ነዳጅ ቀድቶ መመለሱን የነገረን ስሙን እንደሳይጠቀስ የፈለገ የባጃጅ አሽከርካሪም “ቢሾፍቱ 3 ማደያ አላት ነገር ግን ግፋ ቢል 30 ደቂቃ ብትሰለፍ ነው” ሲል አዳማ ላይ ያለውን የነዳጅ ግብይት ችግር ያስረዳል። ባለው አሰራር መሰረት የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከከተማ ክልል ውጪ መውጣት ባለመቻላቸው ወደ ሞጆ እና ቢሾፍቱ ሄደው በጄሪካን ለመቅዳት መገዳደቸውንም ይናገራሉ።

አስተያየት