ሰኔ 18 ፣ 2014

ፊያስ 777፤ መልኩን በየጊዜው የሚቀያይረው የፒራሚድ ስልት

City: Adamaኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮችንግድ

ከጥቂት ሺህ ብሮች ጀምሮ እስከመቶ ሰማኒያ ሺህ ብር ድረስ ፊያስ-777 በተባለ ድርጅት ተጭበርብረናል ያሉ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ድምጻቸውን ሲያሰሙ ሰንብተዋል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ፊያስ 777፤ መልኩን  በየጊዜው የሚቀያይረው የፒራሚድ ስልት
Camera Icon

Credit: Social Media

ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ ብራችንን በአደባባይ ተሰረቅን የሚሉ ሰዎች ጉዳይ ነበር፡፡ ከጥቂት ሺህ ብሮች ጀምሮ እስከመቶ ሰማኒያ ሺህ ብር ድረስ ፊያስ-777 በተባለ ድርጅት ተጭበርብረናል ያሉ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ድምጻቸውን ሲያሰሙ ሰንብተዋል፡፡ ራሱን የማስታወቂያ ድርጅት ነኝ ብሎ የሚጠራው ፊያስ 777 የሚሸጠው ምንም ምርት እንደሌለና ይህ ነው የሚባል ቋሚ ቢሮም ሆነ ንግድ ፍቃድ እንደሌለው ለማወቅ ተችሏል፡፡  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሀገሪቱ የገንዘብ መደብ ብር በመሆኑ “በየትኛውም የክፍያ መፈፀሚያ ሰነድም ሆነ ስርዓት ያለ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ገንዘብ ነክ አገልግሎት መስጠት አይቻልም” ሲል ማሳሰቡን ተከትሎ የፒራሚድ ስልት ድረገጾች ላይ ይሰሩ የነበሩ ሰዎች እየጠፉ መሆኑ ታውቋል። ገንዘባቸው እንደተጭበረበረ የሚገልጹ ድምጾችም መሰማት የጀመሩት ከዚያ በኋላ ነው።

በኢትዮጵያ የፒራሚድ ስልት ሽያጭ ሲጀመር አሀዱ ብሎ አሰራሩን ያስተዋወቀው ክዌስት ኔት እንደነበር ይታወሳል። በመቀጠል የቻይናው ቲያንሺ (ቲያንስ) ተጠቃሽ እና በብዙ መልኩ ስሙ የሚነሳ ድርጅት ለመሆን በቅቷል። የተጨማሪ ምግቦች (ሰፕሊመንትስ) አምራች እንደሆነ የሚገለጸው ቲያንስ እስከ የካቲት 2008 ዓ/ም ድረስ ሲሰራ ቆይቶ የፒራሚድ ስልት ሽያጭን በመከተሉ ምክንያት በፍርድ ቤት ውሳኔ ስራው ታግዶ ከሀገር መውጣቱ ይታወቃል።

ይህ የፒራሚድ ስልት ሽያጭ በየጊዜው እራሱን እየቀያየረ በየወቅቱ የመገናኛ ብዙኃን እና የዜጎች መነጋገሪያ ጉዳይ ሲሆን ይታያል።  ለአብነትም የቢትኮይን ክለቦች ተብለው በአንድ ወቅት ተመስርተው ደብዛቸው የጠፋው ክለቦች አሰራራቸው የፒራሚድ ስልትን የተከተለ እንደነበር ይነገራል። በመቀጠል ደግሞ ክራውድ -1 የተባለ ድርጅት በኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ ክልከላ ወቅት በጣም ብዙ ወጣቶችን ሰለባ ማድረጉ የሚታወስ ነው። የአልፋ ብሬክ ስሩ ድርጅትም አሰራር እንዲሁ የፒራሚድን ስልት ተግብሮ የህይወት ክህሎት ስልጠና እሰጣለሁ ማለቱ በብዙዎች ዘንድ የመከራከሪያ አውድ ዘርግቶ ነበር። 

በአሁኑ ወቅት የፒራሚድ ስልት ሽያጭ አሰራሩ የዲጂታል ማስታወቂያ ድርጅት ናቸው ወደ ተባሉ ስራዎች ሲያዘነብል ይታያል፡፡ ለአብነትም fias777.vip፣ hulu61.com፣ hduhdu.com ፣workxon.com እና ሌሎችም ተጠቃሽ ድረገጾች ናቸው። እነዚህ ድረገጾች የፒራሚድን ስልት ከመተግበርና ሰዎችን ከማጭበርበር በዘለለ የሳይበር ደህንነት ስጋት አስተውለንባቸዋል ይላሉ የሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ባለሞያዎች። 

በቅርብ ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስሙ ሲዘዋወር እና የገንዘብ ደህንነት ባለሞያዎች እየመረመሩት እንደሆነ የተገለጸው ፊያስ 777 ምን ላይ ይገኛል?

"ፊያስ የአለማቀፍ የህይወት መድህን ኢንሹራንስ ሰጪ ነው ። እኛ የምንሰራው የድርጅቱን የማህበራዊ ሚዲያዎች ለማሳደግ ነው" የሚለው የአለምሰው የአዳማ ከተማ ኗሪ ሲሆን በአሁን ወቅት በስሩ 16 ሰዎች እንዳሉት፣ ክፍያውም በንግድ ባንክ በኩል እንደሚፈጸምለት አጫውቶናል። ይህ ከሚሰራው መደበኛ ስራ ተጨማሪ የሆነ የገቢ ምንጩ ነው። ስራው ፒራሚድ ስኪም እንደሆነ ቢያውቅም ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወካይ እንጂ ቋሚ ቢሮ ስለሌለው እንደማያስጠይቀው ያምናል። 

“የ1ሺህ ብር ፓኬጅ ገዝቼ ነው የገባሁት፣ ስራው እጅግ ቀላል ነው። ትርፋማ ስለሆንኩበት የ3 ሺህ ብር ፓኬጅ ገዝቻለሁ። በቀጣይ ደግሞ የ18 ሺውን እያሰብኩ ነበር” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል።

የፊያስ 777 የሽያጭ ጥቅሎች

ሌላው ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረገው አማኑኤል የእንጅባራ ኗሪ ነው። በጓደኛው ጉትጎታ በ6 ሺህ ብር ክፍያ ቪአይፒ 3 እንደተቀላቀለ ይናገራል። እሱ እንደሚለው በስሩ በ3 ሺህ ብር አንድ ሰው በማስገባቱ ኮሚሽን 400 ብር አግኝቶበታል። 

ፊያስ በስሩ የሚሰሩትን አባላቱን በዘጠኝ ደረጃዎች መድቦ ይከፍላቸዋል። እነኚህን ክፍሎች ቪአይፒ ተብለው ተሰይመዋል፤ ከቪአይፒ 0 እስከ ቪአይፒ 8 ። ቪአይፒ 0 ያለምንም ክፍያ አባል መሆን የሚቻልበት የመጀመሪያው ደረጃ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍያ የሚጀምረው ቪአይፒ 1 በ1000 ብር ነው። ትልቁ የቪአይፒ 8 መግቢያ 1 መቶ 80 ሺህ ብር ነው።

ከብሔራዊ ባንክ የክሪፕቶከረንሲ (ምናባዊ ገንዘብ) እገዳ መግለጫ በኋላ ግን የፊያስ ወኪል ናቸው የተባሉ ሰዎች ክፍያ ማዘግየት፣ ስልካቸውን መዝጋት እና የቴሌግራም አካውንታቸውን ማጥፋት መጀመራቸውን ገልጿል።

“ከአለማቀፍ የማህበራዊ ድረ-ገጾች ጋር እንደተዋዋሉ ገልጸው እኛ ደግሞ የማስታወቂያ ስራ እንድንሰራላቸው ነው ውላችን ፤ ነገር ግን እኔ እንደሚመስለኝ ፊያስ እዚሁ ሀገር ውስጥ የተፈጠረ ነው" ሲል አማኑኤል ጥርጣሬውን ገልጿል። 

በስራው ላይ የተሰማሩ ሰዎች በየጊዜው ገንዘባቸውን በድረገጹ ላይ ወጪ በማዘዝ ወደ ባንክ አካውንታቸው እስከ 72 ሰዓታት ድረስ ገቢ ይደረግ ነበር። የዚህ ክፍያ መዘግየት ነው ሰሞኑን በርካታ ሰዎች ቅሬታዎቻቸውን ይዘው ወደማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲወጡ ያስገደዳቸው። አማኑኤልም የተፈጠረውን እንዲህ ያስረዳል።

"መጠራጠር የጀመርኩት ከዚህ ቀደም ገንዘብ ከድረገጹ ወጪ አዘህ ወደባንክ ቁጥርህ እስከሚገባ 24 ሰዓት ብቻ ነበር የሚቆየው፤ ቀስ በቀስ 72 ሰዓት ሆነ ከዛም ለተወሰነ ጊዜ ሲስተም አፕግሬድ ብለው ዘግተውት ነበር" የሚለው አማኑኤል ላለፉት 10 ቀናት ፊያስ 777 ክፍያ አቁመዋል ብሏል። ይህም የሆነው የብሔራዊ ባንክን የክሪፕቶከረንሲ እገዳ ተከትሎ ሰዎች ስራውን ለመስራት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው እንደሆነ ጠቅሷል። 

አማኑኤል እንደተናገረው በቅርቡ ብዙ የሚባሉ አዳዲስ መሠል ድርጅቶች ተፈጥረዋል ፤ ለአብነትም ሁሉ-61፣  ኦሎ፣ ኤፕ እና ሌሎች ብዙ ድርጅቶች ስራ ጀምረዋል። እነዚህ ድርጅቶች ስልክ ለደንበኞቻቸው ሲያስመዘግቡ የሀገራት ስምና የሀገራት የስልክ ቁጥር መግቢያ ኮድ ይጠይቃሉ። ነገር ግን ፊያስ 777 ስልክ ቁጥር ብቻ ይጠይቃል። ይህም ፊያስ ሀገር ውስጥ የተመሠረተ እና አለማቀፍ የሆነ መሰረት የሌለው ድርጅት እንደሆነ ምልክት ነው ይላል አማኑኤል። 

የድርጅቱ ኃላፊዎች ተብለው የሚታወቁ ኤልሳ እና ሊያ የተባሉ ሁለት ሴቶች ስልካቸውንም ፣ ቀድሞ ይጻጻፉበት የነበረውን የቴሌግራም አካውንት ማጥፋታቸው ታውቋል። “ወኪሎቹ ስለሚታወቁ የወኪሎቹን አካውንት ማስመርመር ያስፈልጋል” የሚለው አማኑኤል እርሱ በቅርብ የሚያውቀውን የፊያስ ወኪል ሰሞኑን ስላለው ሁኔታ ጠይቆት ማንንም ማግኘት እና ምንም ማድረግ እንዳልቻለ እንደነገረው ለአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ገልጿል።

“እኔ ባለሁበት ደረጃ ቪአይፒ 3 በቀን 176 ብር ያስብልኝ ነበር። አሁን ድረ-ገጹ ላይ ከ7 ሺህ የማያንስ ብር ነበረኝ" የሚለው አማኑኤል ቀሪ ገንዘቡን ማውጣት  እንዳልቻለ ይናገራል። እሱ የገንዘብ ደረጃውን ባለማሳደጉ የተጭበረበረው በትንሹ እንደሆነ ነገር ግን ሁለት ሶስት ግዜ ገንዘብ ተከፍሏቸው እምነት በማሳደር ደረጃቸውን ያሳደጉና ገንዘባቸውን በእምነት ሳያወጡ የቆዩ ሰዎች ብዙ ገንዘብ እንደተጭበረበሩ ገልጿል።   

አማኑኤል እንደሚለው በተመሳሳይ የድረገጽ ስራዎች በርካታ ሰዎች እየተጭበረበሩ ነው። በቅርብ የሚያውቀው ሰው አብሮት ሆኖ ለአንድ ተመሳሳይ ድርጅት 70 ሺህ ብር ሲያስገባ ማየቱን እንዲሁም ሌላ ተሽከርካሪውን ሸጦ 1 መቶ 80 ሺህ ብር በመክፈል ወደ እንደዚህ ዓይነት ስራ የገባ ግለሰብ እንደሚያውቅ አጫውቶናል። 

የዋይ ኤች ኤም ኮንሰልቲንግ ባለቤት እና የኢንቨስትመንት አማካሪ የሆነው አቶ ያሬድ ኃ/ሚካኤል ስለፒራሚድ ስኪም ሲያብራራ “አሰራሩ አንድ ሰው በስሩ የተወሰኑ ሰዎች ያስገባል ፣ እነኛም እንዲሁ በስራቸው ሌሎች ሰዎች ያስገባሉ ይህ ሒደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን ስለሚሰበስብ በታችኛው መሠረት ላይ ከፍለው የገቡ ሰዎች ብራቸውን ሳያገኙ ይቀራሉ" ይላል። ይህ የሽያጭ ስልት ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የዓለም ሀገራት በህግ መታገዱንም አቶ ያሬድ ተናግሯል። 

ማንኛውንም ስራ የሰራ ሰው ስለሰራ ይከፈለዋል እንጂ ስራ ለመስራት ሊከፍል አይገባም የሚለው የፋይናንስ አማካሪው እነዚህ አሰራሮች ውስጥ ገብተው ገንዘባቸውን የሚያጡት ስለጉዳዩ በቂ እውቀት የሌላቸው ሰዎች ናቸው ብሏል። 

የኢትዮ-ቴክ ድረ ገጽ እና ዩቲዩብ ቻናል መስራች እንዲሁም ባለቤት የሆነውን ጄሰን ፒተርን (ጄይፒ) በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አነጋግረነው ነበር ፡፡ በተለያዩ ጌዜያት ስለ ፒራሚድ ስኪም እና መሰል ማጭበርበሪያ መንገዶች ላይ ትንታኔ የሚሰጡ የተለያዩ ቪድዮዎች ይሰራል፡፡ ከዚህ ቀደም በፊያስ 777 ላይ ቪዲዮ የሰራው ጄይፒ በአሁኑ ወቅት እየተሰሙ ያሉ ቅሬታዎች እና ጥያቄዎች ከስር መሰረቱ ሊፈቱ የሚችሉ እና የሚገቡ እንደነበሩ ይናገራል፡፡

“አንድ ሰው አዲስ ስራ አምጥቶ  እንዴት ነው የሚሰራው ብለህ ስትጠይቅ መልስ ሊሰጥህ ይገባል፡፡ እንደዚህ አይነት ስራ የሚሰሩ ሰዎች ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ከጠያቂ ሰዎች ጋር ጊዜህን አታጥፋ ነው መልሳቸው” የሚለው ጄይፒ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የነበረው የጎሎድ ክዌስት (ክዌስት ኔት) ፒራሚድ ስኪም ውስጥ መስራቱን እና ስራው ህገ-ወጥ በመሆኑ እንደተወው ከዚያ በኋላም ተመሳሳይ አስራሮችን በማጋለጥ እንደሚሰራ ገልጾልናል፡፡

ከፊያስ ሌላ መሰል ስራ ላይ የተሰማሩ ሌሎች ብዙ  ድረገጾች አሉ የሚለው ጄይፒ  workxon.com፣ hdudhu.com ፣ alphagenuin.com እና FBNን ለአብነት ይጠቅሳል፡፡  ድረገጾቹ  ካሏቸው መግለጫዎች እና ስያሜዎች በስተቀር መሰረታዊ አሰራራቸው ከፊያስ 777 ጋር ምንም ልዩነት የላቸውም እንደ ጄይፒ ገለጻ። እነዚህ ድርጅቶች ላይም ቁጥጥር በማድረግ እና በማስተማር ወደፊት የሚያመጡትን ችግር መከላከል ይገባል ብሏል፡፡  

ዌብሳይቶቹ የሳይበር ደህንነት ስጋት ይኖራቸው እንደሆነ የጠየቅነው ጄይፒ “ የዚህን ያክል መወሳሰብ እና ጉዳት ያመጣሉ ብዬ አላስብም ፤ ከውጪ የመጣ ስራ ነው ቢባልም ከበስተጀርባው ያሉት ኢትዮጵያዊያን  ናቸው፡፡ አላማው በግልጽ ከሰዎች ገንዘብ መሰብሰብ ነው” በማለት አብራርቶ እነዚህ ከፊያስ ጀርባ ያሉ ሰዎች ከዚህም ቀደም የተለያዩ መሰል እንቅስቃሴዎች ላይ የተሳተፉ እንደሆኑና በህግ አስፈጻሚ አካላት በኩል ቁርጠኝነቱ ቢኖር ፊያስ 777 ስራውን የጀመረ ቀን ማስቆም ይቻል እንደነበር ቁጭቱን ገልጿል፡፡

“ቴክኖፎቢክ (ቴክኖሎጂ ጠል) የሆነውን ማህበረሰብ የበለጠ ቴክኖፎቢክ ነው ያደረጉት” በማለት የእነዚህ ድረገጾች የማጭበርበር ስራ ከዚህ በኋላ በዲጂታል (ኦንላይን) የሚሰራ ስራ ሲመጣ ህዝቡ እንዳያምን ያደርጋል ሲል ስጋቱን አሰቀምጧል፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድም ቀላል ገንዘብ (easy money) የማሳደድ ዝንባሌ ሊስተካከል የሚገባው እንደሆነና ህዝቡ ገንዘቡን ከማውጣቱ በፊት አረጋግጦ እና ተገቢውን መረጃ ወስዶ ቢሆን መልካም ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡  

በኢትዮጵያም የተሻሻለው የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2013 ዓ/ም መሰረት ፒራሚድ ስኪም በግልጽ ታግዷል። በአንቀጽ 22 የተከለከሉ ድርጊቶች በሚል ቁጥር 6 ላይ እንዲህ በጉልህ ተቀምጧል፤

“አንድ ሸማች አንድ የንግድ እቃ ወይም አገልገሎት በመግዛቱ ወይም የገንዘብ መዋጮ በማድረጉ እና በሸማቹ አሻሻጭነት ከእርሱ ቀጥሎ ሌሎች ሸማቾች የንግድ እቃውን ወይም አገልግሎቱን የሚገዙ ወይም የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ከሆነ ወይም በሽያጭ ስልቱ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ... በሸማቹ ቁጥር ልክ የገንዘብ ወይም የዓይነት ጥቅም እንደሚያገኝ የሚገልጽ ፒራሚድ የሽያጭ ስልት ተግባራዊ ማድረግ ወይም ለማድረግ መሞከር... ይህንን የተላለፈ ነጋዴ (ማንኛውም አካል) ከአመታዊ ገቢው ከ7 እስከ 10 በመቶ እንዲሁም ከ3 እስከ 7 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ይጣልበታል፡፡”

በግሉ የተለያዩ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ እሱባለሁ የተሰኘ የኮምፒውተር ባለሞያ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ በፊያስ 777 ላይ ያለውን ትዝብት እንዲህ አካፍሎናል “የፊያስ ድረገጽ ጥራቱ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ዲዛይኑ፣ ግራፊክሱ፣ መጫኛ ቁልፎቹ (buttons)፣ እይታው (front end) እንዲሁም የውስጥ መግለጫው (back end) በዘፈቀደ እንደተሰራ ያስታውቃል።”

ድረገጹን የገነባው ሲስተም ዴቭሎፐር አለመገለጹ፣ ያስገነባው ድርጅት አልያም ባለቤቱ አለመታወቁ እንዲሁም አንድ ድረገጽ ተገንብቶ አገልግሎት ለመስጠት ወደ በይነመረብ የሚጭን ፈቃጅ አካሉ (በዘርፉ አጠራር ዲፕሎይ ያደረገው አካል) በግልጽ አለመቀመጡ የፊያስ 777ን ህጋዊነት (እውነተኛነት) አጠራጣሪ ያደርገዋል፣ እንደ እሱባለው ማብራሪያ። 

“ድረገጹ የሚጠበቅበት የደህንነት ደረጃ  ላይ ባለመገኘቱ ከሌሎች የባንክ እና መሠል አገልግሎት ሰጪ ስርዓቶች ጋር የማስተሳሰር (Compatibility) ችግር አለበት። በድረገጹ ላይ ያሉ የገንዘብ ዝውውር መረጃዎች በሙሉ ስርዓቱ የሚያዘው ሳይሆን በአስተዳዳሪዎቹ (አድሚኖቹ) የሚሞላ ነው” ያለው የኮምፒውተር ባለሞያው ይህን ሲያብራራ አንድ ሰው በስሩ ሌላ ሰው ሲያስገባ የተከፈለውን ክፍያ የድረገጹ አድሚኖች ማን ምን እንደከፈለ ስለሚያውቁ ራሳቸው ጽፈው ያስገባሉ እንጂ ድረገጹ አውቶማቲክ የሆነ ይህንን የሚሰራበት ጥራት የለውም ብሏል። 

እያንዳንዱ ድረገጽ መተግበሪያ እና የራሱ የሆነ አላማ ይኖረዋል። እንደዩቲዩብ እና ቲክቶክ ያሉ ድርጅቶች በራሳቸው ግልጽ ፖሊሲ መሠረት በድረገጾቻቸው ላይ ለሚሰሩ ሰዎች ይከፍላሉ። ፊያስ 777ን የመሳሰሉ ድረገጾች ግን ግልጽ መመሪያ የላቸውም። በፊያስ ገጽ ላይ የሚታየው የፌስቡክ ፣ የቲክቶክ እና ሌሎችም ማህበራዊ ድረ-ገጾች ምስል ራሱ ፊያስ ያስቀመጠው እንጂ ከተጠቀሱት ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ ማስፈንጠሪያ (ሊንክ) የለውም ሲል ያብራራው እሱባለው ነው።

የባለሞያው ሌላው ስጋት የድረገጹ ደካማነት ለኮምፒውተር መረጃ ቀበኞች (ሀከሮች) የተጋለጠ ሊያደርገው ይችላል የሚል ነው። አንድ መረጃ ሰርሳሪ በቀላሉ የደህንነት ክልከላውን አልፎ ገብቶ ተጠቃሚዎች ከፊያስ ጋር ያደረጉትን የገንዘብ ዝውውር ሊመለከት ይችላል ይህም የተጠቃሚውን የተለያዩ አካውንቶች የመቆጣጠር አጋጣሚ ይፈጥርለታል። የድረገጹ ደካማ መሆን መሰል ችግሮችን ያስከትላል።  

ከሰሞኑ ይፋ በሆነው መረጃ ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ከ6 ሺህ በላይ  የሳይበር ጥቃቶች እንዳጋጠሟት ተገልጿል። 97 በመቶውን ማክሸፉን የገለጠው የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት (ኢንሳ) ሃገሪቱን ከ1.4 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ማዳኑን መግለጹ ይታወሳል።

ስካም ስካነር በአለማቀፍ ደረጃ አጭበርባሪ ድረገጾችን በአርባ መመዘኛዎች የሚዳስስ ድረገጽ ነው። እንደሰካም ስካነር ገለጻ ፊያስ እጅግ አነስተኛ ደረጃ የተሰጠው ድረገጽ ነው። በዚህም የትክክለኝነት ደረጃውን ሲያስቀምጥ 1% ይሰጠዋል። 

   

የስካም አድቫይዘር ምዘና በፊያስ 777 ላይ

እንደምክንያት የተቀመጡት ነጥቦች የባለቤቱ ድብቅነት፣ ከተመሰረተ አጭር ጊዜው ቢሆንም ብዙ ተጠቃሚ ማፍራቱ፣ በድረገጹ ላይ የተለያዩ አሉታዊ የዳሰሳ ጽሑፎች መውጣታቸውና በተለያዩ ሰዎች ይህ ነው የሚባል ምርት እንደማይሸጥ መጠቀሱ ናቸው።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትብብር ሚኒስቴር ፣ ጠቅላይ አቃቤ-ህግና ፣ ፋይናንሻል ኢንተለጀንስ ሰርቪስን በፊያስ 777 ጉዳይ ዙሪያ ለማነጋገር ያደርግነው ጥረት ባለመሳካቱ የተቋማቱን ምላሽ ማካተት አልቻልንም፡፡

አስተያየት