የወሲብ አቅምን እንደሚጨምሩ የተነገረላቸው የሕገ-ወጥ መድኃኒቶች ንግድ በአዳማ

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅጥቅምት 17 ፣ 2014
City: Adamaጤናማህበራዊ ጉዳዮች
የወሲብ አቅምን እንደሚጨምሩ የተነገረላቸው የሕገ-ወጥ መድኃኒቶች ንግድ በአዳማ

ኢትዮጵያ የመድኃኒት ፍላጎቷን በመንግሥት፣ በግል ተቋማት፣ በለጋሽ አካለት እርዳታ ትሸፍናለች። በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሐገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶች ቁጥርም በቀላል የሚታይ እንዳልሆነ በልዩ ልዩ ጊዜ የወጡ የጉምሩክ ኮሚሽን ሪፖርቶች ያሳያሉ። የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና እንክብካቤ ባለሥልጣን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ፣ የሚመረቱ እና አገልግሎት ላይ የሚወሉ መድኃኒቾችን ለይቶ አስቀምጧል። ባለስልጣኑ የምግብ እና የመድኃኒት አሰራርን ለመወሰን በወጣው በአዋጅ ቁጥር 1112/2001 ዓ.ም. በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ይቆጣጠራል። ቁጥጥሩ መድኃኒቶቹ ፈቃድ ሳይሰጣቸው ወደ ሐገር ውስጥ እንዳይገቡ፣ ከጥራት ደረጃ በታች እንዳይመረቱ፣ ተገቢውን የአሰራር ሂደት ተከትለው ወደ ሀገር እንዲገቡ ማስቻልን ያጠቃልላል።

ሕገ-ወጡን የግብይት መስመር ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ መድኃኒቶች መካከል ወሲብ አበርቺ (ኃይል ሰጪ)፣ የሰውነት ጡንቻዎችን ገንቢ፣ ዳሌ እና መቀመጫን አሳማሪ ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው መድኃኒቶች ይገኙበታል። የኢንተርኔት እና ‘ስማርት’ የስልክ ቀፎዎች መስፋፋት ደግሞ መድኃኒቶቹን በድብቅ ለመሸጥ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። በእንክብል፣ በቅባት፣ በሽቶ፣ በማስቲካ መልክ የሚገቡት መድኃኒቶቹ “ያለ ተጨማሪ የትራንስፖርት ክፍያ ቤትዎ ድረስ እናመጣለን” በሚሉ የማኅበራዊ ሚድያ ማስታወቂያዎች በስፋት በመዘዋወር ላይ ናቸው። የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለ ተገልጾ አጓጊ የምስል፣ የድምጽ እና የቪድዮ ማስታወቂያዎች የሚሰራላቸው እነዚህ ምርቶች በተለይ በወጣቶች ዘንድ እየተዘወተሩ ለመሆኑ የማስታወቂያዎቹን ብዛት በመመልከት መገመት ይቻላል የሚሉ አሰርተያየት ሰጪዎች በርክተዋል። አብዛኛዎቹ ተጠቃሚዎች መድኃኒቶቹን የሚወስዱት ከሀኪም ትእዛዝ ውጭ ነው። The Weekend Drug; Recreational Use of Sildenafil Citrate and Concomitant Factors የሚሰኘው በአራት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራን የተዘጋጀ የጥናት ጽሑፍ ዕንደሚያሳየው የወሲብ አቅምን እንደሚያዳብሩ የሚነገርላቸውን መድኃኒቶች ከታዳጊ ወጣትነት እስከ ጉልምስና የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ዋነኛ ተጠቃሚዎች ናቸው።

በአስመጪዎች ዘንድ በንግድ (ብራንድ) ስያሜአቸው የሚታወቁት መድኃኒቶቹ በኬሚካላዊ ይዘታቸው “ሲልደናፊል ናይትሬት” በሚሰኝ ሳይንሳዊ ስያሜ/“ጽንሰ ስም” ይታወቃሉ። በአዋጅ ቁጥር 1112/2001 ዓ.ም. መሠረት “የመድኃኒቱ ጽንሰ ስም” ማለት የአንድ መድኃኒትን ኬሚካላዊ ይዘት መሠረት በማድረግ የሚሰጥ መጠሪያ ሲሆን የምርቱን የንግድ ስም አያመለክትም፤ የሚል ትርጓሜ አስቀምጧል። የዘርፉ ሙያተኞች በጥናታቸው እንዳረጋገጡት በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት መድኃኒቶች የንግድ ስያሜ ቬጎ ፣ ቪያግራ፣ ቫይማክስ ነው።      

በአዳማ  ምን መልክ አለው?

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አዳማ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ መደብሮችን ተዘዋውሮ ቃኝቷል። ሕገ-ወጥ የወሲብ አበርቺ (ኃይል ሰጪ) መድኃኒቶቹ ከብር 10 እስከ 20 ድረስ ያለ ሐኪም ትእዛዝ ሲሸጡ ተመልክቷል። በተለይ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የመድኃኒቶቹ ፈላጊዎች ቁጥር እንደሚጨምር እና ዕድሜአቸው ከ15 ዓመት በላይ የሚሆነው ወጣቶች ቁጥርም ከተጠቃሚዎቹ የሚልቀውን ቁጥር እንደሚይዝ ለመረዳት ችሏል። እንደ ቴሌግራም እና ፌስቡክ ባሉ የማኅበራዊ ሚድያዎች ደግሞ ጤናን የማይጎዱ፣ አቅምን የሚጨምሩ፣ ችሎታን የሚያዳብሩ፣ የወሲብ አካላትን ቁመት እና ውፍረት የሚጨምሩ መድኃኒቶችን “ያሉበት ቦታ ድረስ እናመጣለን” የሚሉ ነጋዴዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

አግባብነት የጎደለውን የመድኃኒቶቹን ስርጭትና አጠቃቀም አስመልክቶ ወደ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አዳማ ቅርንጫፍ ቢሮ አምርተናል። የቢሮው የሥራ ኃላፊ አቶ ከድር ኢደቶ “እኛም ቴሌግራም ላይ ማስታወቂያዎቹን ዐይተናል። እስካሁን በገበያ ላይ አላገኘናቸውም። ከውጭ በሚገቡት ላይም ተመሳሳይ መድኃኒቶች አግኝተን አናውቅም።” ብለውናል። በሕጋዊዎቹ መደብሮች የሚሸጡትን ስለሚቆጣጠሩበት መንገድ አስመልከቶ ሲናገሩ “የዚህ ዓይነት ቁጥጥር በዋና መስሪያ ቤት በኩል ነው የሚሰራው። እስከአሁን ግን ምንም መረጃ አላገኘንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና መስሪያ ቤት ያነጋገርናቸው የሰርቬላንስ ክፍል ባልደረባ አቶ ጌታቸው ገነቴ በበኩላቸው “የቁጥጥር ስራው እኛን ብቻ ሳይሆን የክልል ቢሮዎችንም ይመከታል። አብዛኛዎቹ “ድራግ ስቶሮች” ፈቃድ የሚያገኙት በዞን ደረጃ በመሆኑ ልንቆጣጠራቸው አንችልንም” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። 

ወንጂ ማዞሪያ አካባቢ በሚገኝ መደብር ያገኘነው የፋርማሲ ባለቤት የወሲብ አቅምን እንደሚጨምሩ ስሚነገርላቸው መድኃኒቶች ያቀረብንለትን ጥያቄ ሲመልስ በመደብሩ ውስጥ የሲልደናፊል ሲትሬት ዓይነት መድኃኒቶችን እንደማያቀርብ ይናገራል።  “የቪጎ” ይዘት ያላቸውን መድኃኒቶች ግን ያቀርባል። “ብዙ ደንበኛ ስላለኝ ደንበኞቼን ላለማጣት እይዛለሁ” ሚለው ባለሙያው ለደንበኞቹ የሚያቀርባቸው መድኃኒቶች ሁለት ዓይነት መጠን እንዳላቸው ነግሮናል። “የምይዛቸው መድኃኒቶች ባለ 50 እና ባለ 100 ግራም ናቸው።  ሁለቱም እሽጎቻቸው 4 ፍሬ ይይዛሉ።  በዋጋ ደረጃም ከ40 እና 60 ብር እንሸጣቸዋለን።  በ10 እና በ15 ብር ስለሚገቡ ትርፋቸውም ቀላል አይደለም” ብሎናል።  አራት ፍሬ ከሚይዘው አንድ እሽግ እስከ ሦስት እጥፍ ትርፍ ይገኝበታል።

“ከሰዓት በኋላ ብዙ ሰው መጥቶ ይገዛል። ባጃጅ አሽርካሪዎች ለደንበኞቻቸውሊገዙ ተልከው ይመጣሉ። ደውለው በብዛት ያዙኛል። በትዳር ውስጥ ያሉ ሰዎችም ይጠቀሙታል። አልፎ አልፎ ሚስቶች ባላቸው ላይ ስላስተዋሉት ችግር ያማክሩኛል። ነገር ግን ወደህክምና መሄድ ሳይሆን መድኃኒቱን መጠቀም ነው የሚፈልጉት።” ሲል ገጠመኙን አጫውቶናል።  

የወሲብ ችግር ያለባቸው ሰዎች “ወደ ሕክምና ተቋማት ብሄድም የሚታዘዝልኝ መድኃኒት ነው” የሚል ግምት በማዳበራቸው ለተጠቃሚዎች መብዛት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው የፋርማሲ ባለሙያውና ባለቤቱ ሐሳብ ሰጪአችን ነግሮናል።

ትዕግስት ሙላቱ የተባለችው ፋርማሲ ባለሙያ በበኩሏ “በጀነሪክ ስሙ ሲልድናፊል ናይትሬት የተለያዩ ምርቶች አሉ ኩፒድ፣  በሕጋዊ አስገቢዎች ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ። ዋጋቸውም እስከ 40 ብር ድረስ ነው። እንደማንኛውም መድኃኒቶች በመደበኛ የኃኪም ማዘዣ የሚሸጡ ናቸው። የጥራት ደረጃቸው ተመዝኖ ስለሚገቡ አስተማማኝነታቸውም የተሻለ ነው። እነኚህን መሰል መድኃኒቶች ሊሸጡ የሚፈቀደው በመድኃኒት መደብሮች ደረጃ ነው” ትላለች።

“እንደቪያግራ፣ ቪጎ ያሉት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደሀገር ውስጥ የሚገቡ ናቸው። ፋርማሲዎች ውስጥ በመደርደሪያ ተቀምጠው ሊሸጡ አይችሉም። ነገርግን በሕገ-ወጥ መንገድ ይሸጣሉ። ዋጋቸው ከ10 እስከ 20 ብር ነው።” የሚል ምልከታዋን የነገረችን ትዕግስት ሙላቱ አሁን ካለው የመድኃኒቱ ተጠቃሚ ቁጥር አንጻር ነገሮችን ማስተካከል እጅግ ብዙ ልፋት እንደሚፈልግ ትናገራለች። "ወጣቶችን እና ታዳጊዎች በብዙ ማስተማር ያስፈልጋል። የስርጭት ስፉቱ ግን ብዙ ልፋት እንደሚፈልግ ነው የማምነው።" ስትል አስተያየቷን ትደመድማለች።

"በፊት በፊት እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ብቻ ነበሩ በብዛት የሚጠቀሙት አሁን ላይ ግን ከ16 ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎች ይጠቀሙታል። ዋነኛ ምክንያቱ የስነ-ልቦና ችግር ነው። የፍቅር ጓደኛቸውን አጣታለው የሚል ስጋት ነው ይህንን ያመጣው።" የሚል ትዝብቱን የነገረን የጤና ባለሞያው አሰግድ መሰለ "የሚያመጣውን የጤና ችግር ብትነግራቸውም ሊሰሙህ ፍቃደኛ አይደሉም። ይልቁንም ሰው ልኮኝ ነው ይሉሃል።" ሲል የተጠቃሚዎቹን ምላሽ ይናገራል።

"ፋርማሲዎች ሕገ-ወጥ መድኃኒቱን ይዘው ቢገኙም ዋነኛ የመከላከያ መንገዱ መድኃኒቱ ሀገር ውስጥ የሚገባበትን መንገድ ማስቆም ነው።" ብሎ መፍትሔ ሀሳቡን ያቀረበው አሰግድ መሰለ የዋጋው መርከስ ሰዎች እንዲያዘወትሩት ምክንያት ስለመሆኑ ነግሮናል።

የጎንዮሽ ጉዳት

እሱባለው ገበየሁ የተባለ የአዳማ ከተማ ነዋሪ በአንድ ወቅት የመድኃኒቶቹ ተጠቃሚ የሆነ ጓደኛው ላይ የደረሰውን ሲናገር "ከሦስት ሰዓት በላይ የብልት መወጠር አጋጥሞት ለቀናት መታመሙን አስታውሳለሁ።” ወሲብ አነቃቂ መድኃኒቶች በሽቶ፣ በማስቲካ፣ በከረሜላ፣ በክሬም፣ በቫኪዩም ፓምፕ እየቀረቡ ይገኛሉ። እነኚህ አብዛኞቹ የሚመጡት ከዱባይ ነው። በጉዳዩ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራና ታዳጊዎችን መከላከል ቢቻል የሚል አስተያየቱን ሰጥቶናል።

ቤዛዊት ውድነህ በአንድ የባዮሜዲካል እቃዎችን ወደ ሀገር በሚያስገባ ድርጅት ውስጥ ትሰራለች። ስለቫኪዩም ፖምፖቹ ላነሳንላት ሀሳብ እንደኪት ስለሚታዩ የሚገቡት በፋርማሲቲካል ቁሳቁሶች አስመጪዎች ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሌሎች መሰል ኪቶችን ከመድኃኒቶች ለይቶ የሚያስቀምጥ አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት ብዙ መሳሪያዎች በመድኃኒት አስመጪዎች እንደሚገቡ ትናገራለች። "ይኽም መሳሪያ እንደሌሎቹ እንደኪት ተቆጥሮ የሚገባ ይሆናል።" ስትል መላምቷን ነግራናለች።

በአዳማ ሆስፒታል ነርስ የሆነችው ረቂቅ ሳህሉ የአንድ ወቅት ገጠመኟን አጋርታናለች። "በግምት ሁለቱም የ17 ዓመት ወጣቶች ናቸው። ወንዱ ከመጠን በላይ መድኃኒት ተጠቅሟል፡፡ ሁለቱም ራሳቸውን ስተው ነው ሀኪም ቤት የመጡት፡፡ ድነው ወደቤታቸው የሄዱት ከ15 ቀናት የህክምና ክትትል በኋላ ነው። ረዥም ጊዜ ግንኙነት ላይ በመቆየታቸው ሁለቱም ከፍተኛ የሆነ ደም ፈሷቸው ለህይወት አስጊ ሁኔታ ውስጥ ቆይተዋል።" የምትለው ሲስተር ረቂቅ በወንዶች ላይ መድኃኒቱ እንደ አለርጂ፣ በዘላቂነት የብልት መስነፍ፣ ወሲባዊ ስሜትን ማጣት ሊያጋጥም ይችላል ያለችን ሲሆን በተቋሙ ባለው የማህጸን እና ጽንስ ድንገተኛ ክፍል በወር ውስጥ በትንሹ ከ10 ያላነሰ ተመሳሳይ ጉዳይ እንደሚያጋጥም ትናገራለች።

የሐኪም ትዕዛዝ እና ምክር ሳይኖር በዘፈቀደ እየተወሰዱ የሚገኙት የማነቃቂያ መድኃኒቶቹ ቁጥሩ የበዛ የጎንዮሽ ጉዳት እንደሚያስከትሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የተፈጥሮ ችሎታን ጨርሶ ማጣት እና የመድኃኒቱ ጥገኛ መሆን፣ የዕይታ መቀነስ፣ የነርቭ ችግሮች፣ የአፍንጫ መታፈን፣ ራስ ምታት፣ የሆድ ህመም፣ ማቅለሽለሽ፣ ተቅማጥ፣ የማስታወስ ችግሮች፣ የጀርባ ህመም፣ አረንጓዴ እና ሰማያዊ ቀለሞችን መለየት አለመቻል፣ የመስማት ችግር፣ የጆሮ መጮህ እና መፍዘዝ ይገኙበታል።

በአዳማ የሙሴ አጠቃላይ ሆስፒታል የጤና ባለሞያው ዶ/ር ታሪኩ ገለሼ “መድኃኒቶቹ በባህሪያቸው በወንድ ብልት ውስጥ ያለው ስፖንጃማ አካል ውስጥ የደም ስርን በማስፋት ለረጅም ጊዜ ደም ይዘው ማቆየት እንዲችል የሚያደርጉ ሲሆን ተገቢውን መድኃኒት ካልተጠቀሙ ግን ለጊዜያዊ እና መደበኛ የጤና እክል ያጋልጣሉ።” ሲሉ የሚያደርሱትን ጉዳት ይገልጣሉ። 

“ይኽ አይነት ችግር ሲከሰት ቶሎ ሀኪምን ማናገር ያስፈልጋል። እንዲሁም በራስ መድኃኒቶችንም መጠቀም እስከሞት ለሚያደርስ የጉንዮሽ ችግር እንደሚያጋልጥ መታወቅ አለበት። ከታዳጊ እስከ አዛውንት በወረርሽኝ መልክ የተስፋፋው የመድኃኒቱ የመጠቀም ፍላጎት የጎንዮሽ ችግሩን ያላገናዘበ ነው” ይላል።

"ደም ስር የሚያሰፋ መድኃኒት በመሆኑ በተገቢው መንገድ ካልተወሰደ ለልብ ህመም፣ ለከፍተኛ የደም መፍሰስ፣ ለዘላቂ የብልት መቀሰር፣ ለብልት በቋሚነት መስነፍ ይዳርጋል።" ሲሉ ዘለቄታዊ ችግሩን ነግረውናል።

Author: undefined undefined
ጦማሪተስፋልደት ብዙወርቅ

Tesfalidet is Addis Zeybe's correspondent in Adama.