ነሐሴ 20 ፣ 2013

ትኩረት የተነፈገው የጋሪ ፈረሶች አወጋገድ

City: Adamaጤናመልካም አስተዳደርአካባቢማህበራዊ ጉዳዮች

አዳማ ከተማ ከፈረስ ጋር የተሳሰረ ረዥም ታሪክ እንዳላት ከሚያሳዩ ሁነቶች መካከል “ባለጋሪው” የተሰኘው የሚወክላት የእግር ኳስ ቡድኗ ስያሜ  ይጠቀሳል፡፡ እንደ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ ወንጂ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ መቂ፣ አዋሽ መልካሳ...

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ትኩረት የተነፈገው የጋሪ ፈረሶች አወጋገድ

አዳማ ከተማ ከፈረስ ጋር የተሳሰረ ረዥም ታሪክ እንዳላት ከሚያሳዩ ሁነቶች መካከል “ባለጋሪው” የተሰኘው የሚወክላት የእግር ኳስ ቡድኗ ስያሜ  ይጠቀሳል፡፡ እንደ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ ወንጂ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ መቂ፣ አዋሽ መልካሳ፣ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች ሁሉ አውራ ጎዳናዎቿን በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ መኪና፣ ባጃጅ እና ሞተር ሳይክል ከማጨናነቁ በፊት ጋሪ የኑሮ ደረጃቸው ከፍ ያለ ሰዎች መጓጓዣ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ዳርቻ በሚገኙ እንደ ገላን፣ ጀሞ፣ ዓለም ባንክ፣ ሐና ማርያም ያሉ አካባቢዎች ደግሞ በአንድ ፈረስ የሚጎተት፣ ባለ ሁለት ጎማ፣ ጋላቢውን ጨምሮ 3 ሰው የሚጭን ጋሪ አገልግሎት አልተቋረጠም፡፡ 

የአብዛኛውን ነዋሪዎቿን የእንቅስቃሴ ፍላጎት የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) በሚያሟላባት አዳማ ከተማም ፒኮክ ፣ ቦሎ፣ 09 አካባቢ እና በሌሎችም አዳዲስ ሰፈሮች ጋላቢውን ጨምሮ ሦስት ሰው የሚያሳፍሩ ባለ አንድ ፈረስ ጋሪዎች የትራንስፖርት ዘርፉ ውስጥ አሉ፡፡ ከሐዋሳ እስከ ሻሸመኔ ባሉ ከተሞች እስከ 3 በሚደርሱ አህዮች የሚጎተቱ ጋሪዎች ቢኖሩም በአዳማ ከተማ የሚዘወተረው ባለ አንድ ፈረስ ጋሪ ነው፡፡ በከተማዋ ዙርያ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች፣ የአስፋልት መንገድ ተደራሽ በማይሆንባቸው ጥርጊያ መንገዶች፣ በውስጥ ለውስጥ በሚያስገቡ የከተማዋ የመንደር ውስጥ የእግረኛ መንገዶች፣ በተለይ የጭነት አገልግሎት በመስጠት ያገለግላሉ፡፡ አገልግሎት ሰጪዎቹ የጋሪ ፈረስ ባለቤቶች ዓመታዊ ግብር እስከ 400 ብር የሚከፍሉ ሲሆን ሕጋዊ ታርጋ እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸው ነግረውናል፡፡

የከተማዋን እድገት ተከትለው ቀስ በቀስ ከአገልግሎት መድረኩ እየተገፉ ወደ ከተማ ዳርቻዎች የተገፉትን የጋሪ ፈረሶች በተመለከተ አገልግሎታቸው እንጂ ስለ በማያገለግሉት ጊዜ ስለሚወገዱበት ሁኔታ የታሰበ እንደማይመስል ባለቤት አልባ ሕመምተኛ ፈረሶች የሞሏቸው የከተማዋ የእግረኛ እና የተሽከርካሪ መንገዶች ምስክር ናቸው፡፡ በዘመናዊው የአስፋልት መንገድ ላይ የተሽከርካሪዎችን መንገድ ተጋርተው የሚጓዙት የተጠጣለሉ ፈረሶች የትራፊኩን ፍሰት ከማደናቀፋቸው በተጨማሪ፣ በተለይ ጭነት አመላላሾቹ መንገድ ተጋሪዎቻቸውን ለአደጋ ከማጋለጣቸው በተጨማሪ ባለቤቶቻቸው አግልገሎት ጨርሰዋል ብለው ሲያምኑ መተላለፊያ መንገዶች ላይ ስለሚጥሏቸው ተጨማሪ የአደጋ ስጋት ሆነዋል፡፡

በአዳማ ከተማ ደጋፊ ታክሲ አገልግሎት ሰጪነት ላይ የተሰማራው የአዳማ ኗሪው አሽከርካሪ ፈይሳ መስፍን በፈረሶቹ  ምክንያት በተለምዶ ጨርቃጨርቅ አካባቢ የአደጋ አጋጠሚ እንደተፈጠረበት እና በጥንቃቄ ማሽከርከሩ መትረፉን ይናገራል፡፡ “ደርቤ ልወጣ ስል ፈረሱ ገብቶብኝ ፍጥነቴን በመቆጣጠሬ ተርፌያለው” ይላል፡፡ ሌሎች አሽከርካሪዎችም ይህ አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ይናገራል፡፡

የአመዴ ግብርና  አካባቢ  ኗሪዋ ወጣት ሄለን በለጠ በበኩሏ በየመንገዱ ስለተጣሉትም ሆነ ሌሎች ፈረሶች “ሲሞቱ እነሱን ማንሳት መከራ ነው፡፡” ትላላች፡፡ ከዚህ ሌላ አንድ ቦታ ስብስብ ብለው መንገድ መዝጋታቸው፣ መንገር ማቆሸሻቸውና የተተከሉ እጽዋትን ማበላሸታቸው በአካባቢው ችግር መሆኑን ትናገራለች፡፡

የከተማዋን ገጽታ እያበላሹ የሚገኙት የተጣሉ ፈረሶች በተለይ መሐል ከተማ አካባቢ የሚገኙትን ቀደም ብለው የተገነቡ ጠባብ መንገዶች ይበልጥ እንዲጣበቡ ምክንያት እየሆኑ እንደሚገኙ እግር ጥሎት በአካባቢው የተገኘ ሁሉ የሚረዳው ሀቅ ነው፡፡ የተጣሉበት የጎዳና አካፋይ ላይ የተተከሉ የመንገድ ማስዋቢያ እጽዋትን እየተመገቡ እዚያው ውለው እዚያው የሚያድሩት “ጡረታ የወጡ” ፈረሶች በተለይ በምሽት ወቅት የአደጋ ምክንያት እንደሆኑ ሐሳባቸውን የሰጡን የምሽት ፈረቃ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) አሽከርካሪዎች ይናገራሉ፡፡

ያለፉትን አራት ዓመታት በጋሪ ፈረስ ጋላቢነት ሥራ ላይ እንደቆየ ያወጋን አቶ ጌታሁን እንዳልክ የፈረስ ጋሪውን በመሥራት በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቡን ያስተዳድራል፡፡ በአዘቦት ቀናት እስከ 200 ብር እንደሚያገኝ ይናገራል፡፡ የጋሪ ፈረሶች በባለቤቶቻቸው የማይፈለጉት ሲታመሙ ወይም ሲያረጁ መሆኑን ነግሮናል፡፡ ከሕመሞቹ መካከል “ንድፍት” በሳይንሳዊ ስያሜው “ኢፒዞቲክ ሊንፋታይጀስ”፣ “እከክ” (ደርማይተስ)፣ “ጮቅ” (ፉት ዲስኦርደር)፣ “ቁርጠት” (ኮሊክ) እና “የሽንት መከልከል” (ኮሊክ) መሆናቸውን ይናገራል፡፡ 

“ከሁሉም የፈረስ በሽታዎች “ንድፍት” በአደገኝነቱ የሚታወቅና በጋላቢዎች የሚፈራ ነው” የሚለው አቶ ጌታሁን “ “ንድፍት” መድኃኒት ስለሌለው በ”ንድፍት” ተይዞ አልድን ያለ ፈረስ ካለ ያለው አማራጭ መጣል ነው” ይላል፡፡

“ንድፍት” (በአነስተኛ ቁስል መልክ ጀምሮ መላውን የፈረሱን አካል የሚያዳርስ ሕመም ነው።) በሕመሙ የተያዘን ፈረስ ለማከም የመጀመርያው እርምጃ ፈረሱን በሳሙና ማጠብ እንደሆነ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የጋሪ ፈረስ ባለቤቶች ይናገራሉ፡፡ ሁለተኛው እርምጃ የጸዳው የፈረሱ ቆዳ ላይ በተለይ የተጎዳውን ክፍል እየመረጡ የመኪና ባትሪ አሲድ መቀባት ነው፡፡ አሲዱ ቁስለኛውን አካል አቃጥሎ ፈረሱን ከሕመሙ የሚያሽረው ከሆነ ጥቂት የእረፍት ጊዜ ተሰጥቶት በደንብ ሲያገግም ወደ ስራው ይመለሳል፡፡ ያ ሳይሆን ቀርቶ ሕመሙ የሚባባስበት ወይም በነበረበት የሚቀጥል ከሆነ ግን ይጣላል፡፡ በዘመናዊው ህክምና ፖታሺየም አዮዳይድ የተባለ መድኃኒት ያለው ሲሆን የመድኃኒቱ ዋጋ እጅግ ውድና ሐገር ውስጥ የሌለ ነው፡፡

የአዳማ ወረዳ ግብርና ቢሮ የእንስሳት ሀኪም ዶ/ር ተስፋዬ ቶላ ስለ ፈረሶች በሽታ ከአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ፈረስን በዋናነት ከሚያጠቁ በሽታዎች ውስጥ በሳይንሳዊ ስሙ ኢፒዞቲክ ሊፋታይጀስ አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ በተጨማሪም እንደ ቴታነስ እንስሳቱ በብረት ወይም በሚስማር በሚወጉበት ጊዜ የሚመጣ በሽታ ነው፣ አፍሪካን ሆርስ ሲክነስ (በተለምዶ "ልብ ድካም” የሚል መጠሪያ አለው፡፡) ዓይነት በሽታዎች ፈረስን የሚያጠቁ  ናቸው።” ይላሉ፡፡

በአዳማ ከተማ የሚገኙ በርካታ ፈረሶችን እያጠቃ የሚገኘው፣ ባለቤቶቻቸው መፍትሔ ከማጣት የተነሳ እንዲጥሏቸው የሚያስገድደው በሽታ በተለምዶ “ንድፍት” ተብሎ የሚጠራው (በሳይንሳዊ ስያሜው ‘ኢፒዞቲክ ሊንፋታይጀስ’) መሆኑን በማንሳት መንስኤው ምን እንደሆነ የጠየቅናቸው ዶ/ር ተስፋዬ በፈንገስ አማካኝነት የሚመጣ፣ በንክኪ እንደሚተላለፍና የእንስሳውን ስርዓተ-ሊንፍ  እንደሚያጠቃ ነግረውናል፡፡ ሊንፍ በማንኛውም እንስሳ ውስጥ የሚገኝ ከደም ውጪ ያለ ቀለም አልባ ፈሳሽ ሲሆን ይህ ፈሳሽ የሚዘዋወርበት ስርዓት ስርኣተ-ሊንፍ ይባላል፡፡ ይህ በሽታ የሚያጠቃው ይህን ስርዓት ነው፡፡ የዚህ ህመም መድኃኒት በሐገር ውስጥ እንደማይገኝና መፍትሔው መከላከል ብቻ መሆኑን ነግረውናል፡፡ “ተገቢውን ምግብ እንዲያገኙ ማድረግ እና ንጽሕናቸውን መጠበቅ ለጊዜው የሚመከር የጥንቃቄ መንገድ ነው” ብለዋል ሐኪሙ፡፡

በጋማ ከብቶች ላይ የሚሰራ “ብሩክ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ምግባረ-ሰናይ ድርጅት የአዳማ፣የጊምቢቹ እና አቃቂ ወረዳ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎችን ባሳለፍነው ሳምንት ‹በእንስሳት መድኃኒት እና አጠቃቀማቸው› ላይ የሚያተኩር ስልጠና አዘጋጀተው ነበር፡፡ በስልጠናው የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ላይ ያገኘናቸው የአዳማ ፕሮጀክት የቡድን መሪ አቶ ማንደፍሮ ስለሺ ባለቤት አልባ ፈረሶችን አስመልክቶ ለተግባራዊነት የተዘጋጁበት እቅድ እንዳለ ነግረውናል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ባለቤት አልባ ፈረሶች ከሕመማቸው ተፈውሰው ወደ ምርት የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚረዳ ፕሮጀክት ጀምረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እንስሳቱን ወደ ስራ ከመመለስ ባሻገር መዳን የማይችሉት እንስሳት ደግሞ ሰላማዊ እረፍት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡

“ብሩክ ኢትዮጵያ” በእንግሊዝ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ተቋም ሲሆን እንስሳቱን ለይቶ የማቆያ ሥፍራ ከማዘጋጀት ጀምሮ አክሞ ወደ ስራ ማሰማራት ይህም ካልሆነ ሰላማዊ እረፍት መስጠት ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡ የሥራው ባለድርሻ የሆኑት የአዳማ ወረዳ ግብርና ቢሮ ቆጠራ ማከናወን እና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ላይ ይሳተፋል፡፡

ይህ ስራ ከአዲስ አበባ ከተማ ከተሰራው የብሩክ ኢትዮጵያ ተሞክሮ የተጀመረ እንደሆነም ይናገራሉ። "በዚህ ስራ ላይ የብሩክ ኢትዮጵያ ድርሻ ለ“ዩቲኔሽያ (ታማሚውን በሰላማዊ መንገድ ማሳረፍ)” የሚሆነውን መድኃኒት ማቅረብ እና ለባለሞያዎች ሥልጠና መስጠት ነው።" የሚሉት አቶ ማንደፍሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ንግግር ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ። ለሥራው ውጤታማነት ከተሳታፊ ባለድርሻዎች ጋር የሥራ ድርሻ ክፍፍል በማከናወን ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉ ጥቂት ወራት ውስጥም ችግሩን የሚያቃልል ተጨባጭ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

አስተያየት