መጋቢት 21 ፣ 2014

በሕገወጥ መንገድ ወደ ሐገር ውስጥ የገቡ ዋጋቸው 19.7 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሺሻ፣ ሲጋራ እና መድኃኒቶች በቁጥጥር ዋሉ

City: Adamaዜና

የአዳማ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት ሕግ ተገዢነት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዝናው ደረበ ለአዲስ ዘይቤ እንደተማገሩት የተያዙት እቃዎች ጠቅላላ ዋጋ ግምት 19 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሕገወጥ መንገድ ወደ ሐገር ውስጥ የገቡ ዋጋቸው 19.7 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሺሻ፣ ሲጋራ እና መድኃኒቶች በቁጥጥር ዋሉ
Camera Icon

ፍቶ፡ ጉምሩክ

ግምታዊ ዋጋቸው 19 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሆነ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሐገር ውስጥ የገቡ የተለያዩ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጉምሩክ ኮሚሽን አዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታወቀ። ዕቃዎቹ ከመጋቢት 16 ጀምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሕብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ነው፡፡

በደምበላ ክ/ከተማ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ተከማችቶ የተገኘው ቁሳቁስ ግምታዊ ዋጋ ከ14 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሺሻ እና ሲጋራ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ በከተማዋ ሌላኛው ክፍል ቦኩ ክ/ከተማ በግለሰብ ቤት ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ሊዘዋወሩ የተዘጋጁ 5.4 ሚሊየን ብር የሚገመቱ መድኃኒቶች፣ ሲጋራዎች እና የሞባይል ቻርጀሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የአዳማ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት ሕግ ተገዢነት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዝናው ደረበ ለአዲስ ዘይቤ እንደተማገሩት የተያዙት እቃዎች ጠቅላላ ዋጋ ግምት 19 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ 3 ሰዎች  በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ኃላፊው እንደሚሉት ሸቀጦቹ ወደ ሕብረተሰቡ እና ገበያው ቢሰራጩ አብዛኞቹ ሱስ አስያዥ ሸቀጦች በመሆናቸው በወጣቶች ጤና ጉዳት  ሊደርሱ እንደሚችሉ እንዲሁም አላስፈላጊ የገበያ ውድድርን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

አዳማ ከተማ የወጪ እና ገቢ ንግድ መተላለፊያ እንደመሆኗ መጠን እንደ ሺሻ እና ሲጋራ፣ የተለያዩ ዓይነት ተሽከርካሪዎች፣ ልባሽ ጨርቆች እና ጫማዎች የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች እንደሚስተዋሉባት የሚናገሩት ም/ስራ አስኪያጁ ሕብረሰተሰቡ ቅርቡ ለሚገኝ የጸጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የ9 ወር ግምገማ ለማድረግ እየተሰናዳ ያለው ጽ/ቤቱ የኮንትሮባንድ ንግድን ከመከላከል አንፃር  ቅ/ጽ/ቤቱ በ6 ወራት ውስጥ 75 ሚሊዮን ብር የግምት ዋጋ ያላቸዉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ለመያዝ አቅዶ 154 ሚሊዮን  ግምት ያላቸው እቃዎችን መያዙን ገልጿል። ይህም የእቅዱ 205.85% ነው። በባለፈው የበጀት ዓመት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ101 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም ገልጸዋል።

 ከገቢ አንጻር  የቅ/ጽ/ቤቱ የ2014 በጀት ዓመት የ6 ወር እቅዱ 4.1 ቢሊየን ብር የገቢ ዕቅድ አፈፃጸም ሲታይ ግን 5.1 ቢሊዮን ብር  ወይም የእቅዱን 125.35% ከዕቅድ በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል። በ2013 ዓ.ም. በተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ገቢ የ2ቢሊዮን ብር ጭማሪ እንዳለውም ገልጸዋል።

አስተያየት