ኅዳር 1 ፣ 2015

ደማቁ የሰርከስ አዳማ ጉዞ

City: Adamaባህል ማህበራዊ ጉዳዮች

በአስገራሚ የመተጣጠፍ ችሎታው በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ (Guinness World Records) የራሱንና የኢትዮጵያን ስም ማስጠራት የቻለው ኪሮስ ሃድጉ የሰርከስ አዳማ ፍሬ ነው

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ደማቁ የሰርከስ አዳማ ጉዞ
Camera Icon

ምስል፡ ከሰርከስ አዳማ የፌስቡክ ገጽ (ሰርከስ አዳማ እ.ኤ.አ በ2018 በቱርክ ሀገር የሰርከስ ትርዓት ሲያቀርብ)

የአንድ ትውልድ እድሜን ያስቆጠረው ሰርከስ አዳማ በቀድሞ አጠራሩ ሰርከስ ናዝሬት የተቋቋመው በ1985 ዓ.ም ነበር። ከተመሰረተ 30 ዓመታትን ያስቆጠረው ሰርከስ አዳማ በአዳማ እና በዙሪያዋ ባደጉ እና በኖሩ ታዳጊዎች አዕምሮ ውስጥ ትልቅ ትውስታ ያለው ቡድን ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስራው ባይቋረጥም፣ የአዳማን ስም በመልካም ማስጠራቱ ባይቀርም የቀድሞ ስምናና ዝናው ግን ደብዝዞ ቆይቷል። ይባስ ብሎም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ለልምምድ እንዲሁም ለጽ/ቤትነት ሲጠቀምበት የነበረው ግቢ  መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም መታሸጉን ተከትሎ ለከተማዋ ነዋሪዎች እና የሰርከስ አፍቃሪዎች ዘንድ ቅሬታን አስከትሏል። 

የታሸገው የሰርከስ ቡድኑ ቢሮም ከ40 ቀናት መታሸግ በኋላ ጥቅምት 22/2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ መስተዳድር ውሳኔ ዳግም ተከፍቷል።

በ1980ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት በኢትዮጵያ የፈነዳው የሰርከስ አብዮት ከዳር እስከ ዳር የሀገሪቱን ወጣቶች ቀልብ መግዛት ችሎ ነበር። ሰርከስ አዳማና በዚያው ዘመን የተመሰረቱት ሰርከስ ጅማና ሰርከስ አዲስ አበባ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሰርከስ ቡድኖችም ለመመስረታቸው ምክንያት ሆነዋል።

በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሚባለው ሰርከስ ኢትዮጵያ በመከተል ሰርከስ አዲስ አበባ በ1983 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በመቀጠልም በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደርጉ ከነበሩት ሰርከስ ጅማ እና ሰርከስ ትግራይ ጋር ሰርከስ አዳማ ስሙ በጉልህ የሚነሳ የሰርከስ ቡድን ነው።

እነዚህ የሰርከስ ቡድኖች ከመንግስትና ከዓለም አቀፍ አጋሮች የሚደረግላቸው የፋይናንስና ሌሎች ድጋፎች ቀስ በቀስ እየተቋረጡ በመሄዳቸው እንቅስቃሴያቸው ሊደበዝዝ ችሏል።

በደርግ የአገዛዝ ዓመታት የነበሩትን የቀበሌ እና ከፍተኛ ኪነቶችን በአልጋ ወራሽነት የተቀበሉ የስነ-ጽሑፍ ክበቦች፣ የድራማ እና ቲያትር ክበባት እና የሰርከስ ቡድኖች ተጠቃሽ ነበሩ።

ሰርከስ ኢትዮጵያ፣ ሰርከስ ትግራይ፣ ሰርከስ ጅማ፣ ሰርከስ ደብረ ብርሃን፣ ሰርከስ ድሬዳዋ እና ሰርከስ ሐዋሳ በሀገሪቱ የሚጠቀስ ታሪክ የጻፉ የሰርከስ ቡድኖች ናቸው።

ሰርከስ አዳማ ትኩረቱን በዋናነት በአክሮባት እና በጅምናስቲክ ስፖርት ላይ አድርጎ በተጨማሪ ለስራዎቹ የሚደግፉትን  በቲያትር፤ በሙዚቃ፤ በባህላዊ ውዝዋዜና በዘመናዊ ዳንስ ስልጠናዎችን ለወጣቶች እና ታዳጊዎች በመስጠት የሚሰራ ቡድን ነው።

ሰርከስ ቡድኑ ሀገርን የሚወክሉ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች እና የአክሮባት እና ጅምናስቲክ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባለፈ በሙዚቃው ዘርፍ አገር አቀፍ እውቅና ያገኙ ድምፃውያን፤ ገጣሚያን፤ ደራሲያን፤ የዜማ ባለሙያን እና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችን ለማፍራት ችሏል።

ቡድኑ በአስገራሚ ችሎታ በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ (Guinness World Records) መመዝገብ የቻለ ባለተስጥኦ ወጣት ማፍራት የቻለ ነው፤ ሰርከስ አዳማ።

ሰርከስ አዳማ በሀገር ውስጥ ከሰራቸው ዘርፈ ብዙ ስራዎች በተጨማሪ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች በስዊድን ሃገር በተካሄደው የህፃናትና የሴቶች የሰርከስ ፌስቲቫል፣ ቤልጅየም በሚገኘው የአዛውንቶች ድጋፍ ማሰባሰቢያ የሰርከስ ዝግጅት ፣ በጀርመን አገር ፍራይበርግ ከተማ በተካሄደ የሰርከስ ዝግጅት፣ በሆላንድ፣ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደ የአፍሪካ ሰርከሶች ሲምፖዝየም፣ ታንዛንያና ኬንያ በተካሄደ የኦሞጃ የሙዚቃና የሰርከስ ፌስቲቫል ላይ ተሳትፏል በቅርቡም ከሁለት ዓመት በፊት በቱርክ አስር ከተሞች አባላቱን ይዞ በመዘዋወር ትርዒት ያቀረበ ሲሆን በ2019ዓ/ም ደግሞ በስፔን አልቫሴቴ የሰርከስ ፌስቲቫል ላይ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ስም በመልካም  አስጠርቷል።

ሰርከስ አዳማ ካገኛቸው እውቅና እና ሽልማቶች መካከል ውጤታማ የወጣቶች የልማት ድርጅት ተብሎ አቶ አባዱላ ገመዳ የኦሮሚያ ርዕሰ-መስተዳደር በነበሩበት ወቅት ዋንጫ እና የሜዳሊያ ሽልማት አግኝቷል። በተጨማሪም ሰርከስ ኢትዮጵያ ባዘጋጀው የሰርከሶች ውድድር የዋንጫ ሽልማት፣ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ(ኮካ ኮላ) ባዘጋጀው ውድድር የዋንጫ ሽልማት፣ በመላው ኦሮሚያ ጨዋታዎች ለአዳማ ከተማ መስተዳድር ዋንጫዎችና ሜዳሊያዎች፣ በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ለኦሮሚያ ክልል በአክሮባትና ጂምናስቲክ ዋንጫና ሜዳሊያዎች አግኝቷል።

ፋሲል ገዛኽኝ የሰርከስ አዳማ ዳይሬክተር ነው። 1996 ዓ.ም ጀምሮ ያለፉትን 19 ዓመት በሰርከስ አዳማ ቆይቷል። የኖርዌይ ካውንስል የሙዚቃ እና የክዋኔ ጥበባት ት/ቤት በሚዘጋጀው ኡሞጃ ካልቸራል ፍላይንግ ካርፔት (Umoja Cultural Flying Carpet -CFC) ስልጠና እንደወሰደ የሚናገረው ፋሲል በአንደኛ ደረጃ አሰልጣኝነት ከ60 በላይ ልጆች ማሰልጠኑን ይናገራል።

በተወዳዳሪነት  ከ1997 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ በኦሮሚያ ሻምፒዮና ለ8 ተከታታይ ዓመታት የወርቅ ሜዳሊያ እና በአገር አቀፍ የክለቦች ውድድር በ2003 ዓ.ም ላይ በወለል ተግባር ላይ ወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው ፋሲል፤ ሰርከስ አዳማ በአካል እና በአዕምሮ ጤናማ ወጣት እንድሆን፣ ኢንተርናሽናል ከርቲስ እንድሆን እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት ተዘዋውሬ እንድሰራ ረድቶኛል ይላል።

ከፍተኛ የሆነ የወጣቶች የሱስ ተጋላጭነት ባለባት አዳማ በሌላ በኩል ለወጣቶች ማዘውተሪያ የሚሆን ቦታ እጥረት መኖሩ መሠል ወጣቶች ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ማሳያ ነው ይላል ፋሲል።

'ሀገሬ ፣ብሔር ብሔረሰቦች' በሚሉ እና በብዙ የባህላዊ ሙዚቃው የሚታወቀው ድምፃዊ ታደሰ መከተ ሰርከስ አዳማ ካፈራቸው ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነው። 

“በ1991 ዓ.ም የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው ሰርከስ አዳማን የተቀላቀልኩት” የሚለው ድምጻዊው ታደሰ መከተ የሰርከስ ስራው በሙዚቃ ስለሚታገዝ ቡድኑ ድምፃዊያን እና ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችም ይይዝ እንደነበር ይናገራል።                  

ከ200 በላይ ወጣትና ታዳጊዎች ይዞ በዘጠናዎቹ መጀመሪያ በኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝን የመከላከል ማስተማር ስራ ላይ ተሰማርቶ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ጭሮ፣ አሰላ እና ሌሎችም ቦታዎች ድረስ ተጉዞ መስራቱን ይገልጻል።

“ሰርከስ ቡድኑ በግላቸውም ሆነ ቤተሰባቸውን የሚደግፉ ብቁ ዜጎች አፍርቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራቸውን እና ከተማቸውን ስም ደጋግመው ያስጠሩ አባላትም አውጥቷል” ሲል ድምፃዊው ታደሰ መከተ ይናገራል።

ኪሮስ ሃድጉ አንዱ የሰርከስ አዳማ ፍሬ ነው። በሰርከስ አዳማ የነበረው ኪሮስ አድጉ በአሁኑ ወቅት በ30 የተለያዩ ሀገራት ተዘዋውሮ የሰርከስ ትርዒቶችን ያሳያል። ከዚህም ሌላ በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ (Guinness World Recordsበቴኒስ ራኬት ውስጥ ተጣጥፎ በማለፍ ራሱን እና ሀገሩን ስም በመዝገቡ ማስፈር ችሏል።

ምስል፡ ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ (ሰርከስ አዳማ ካፈራቸው ባለሙያዎች መካከል አንዱ ኪሮስ ሃድጉ በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ (Guinness World Records) ባለሪከርድ)

በጀርመን ኑሮውን ያደረገው ሰለሞን ሳህለ ሌላኛው በሰርከስ አዳማ ውስጥ ተጠቃሽ ባለሙያ ነው። ሰለሞን በሰርከስ አዳማ ተመልካቾች ዘንድ “ሶልጂት” በሚለው ስሙ ይታውቃል።

በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በሚዘጋጁ የሰርከስ ትርዒቶች ላይ የሚሳተፈው ሰለሞን ሳህለ (ሶልጂት)፣ ከሰርከስ ስራው በተጨማሪ በጓደኞቹ ጋር በመሆን 'ሰንኢኮ አርት ፎር ሶሻል ዴቭሎፕመንት' የሚል ድርጅት በማቋቋም የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።

በቅርቡ ከ44 በላይ በሚሆኑ የመድረክ ስራዎች ላይ በሰርከስ አርት መሳተፉን የነገረን ሰለሞን ዝግጅቶቹ በአማካኝ እስከ 2ሺህ 5 መቶ ሰዎች እየታደሙበት እንደነበር ይገልጻል።

የሀገርን ምስል በመልካም ለማስጠራት ሰርከስ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የሚገልጸው ሰለሞን፤ በሚወጣበት በእያንዳንዱ መድረክ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዞ ሀገሩን እያስተዋወቀ እንደሆነ ይናገራል።

“የሰርከስ አቅም ገና አልተሰራበትም” የሚለው ሰለሞን፤ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ ሰርከስ ትልቅ አማራጭ መሆኑን ይናገራል።

በአሁን ወቅት ሰርከስ ቡድኑ ለሀገር እና ለከተማዋ ያበረከተው ውለታ የታወሰ ይመስላል። ቡድኑ የተወሰደበት ቢሮ እና መለማመጃ ቦታ በከተማ አስተዳደሩ እንዲመለስለት ተደርጓል። በተጨማሪም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሰርከስ ቡድኑ ያለበት እዳ ተሰርዞ በነጻ እንዲጠቀምም በአዳማ ከተማ አስተዳደር ተወስኗል።

አቶ አላምረው ዳኜ የጥበብ ባለሙያ እና በኢህድሪ ጦር ውስጥ በውትድርና ያገለገለ ነው። በሰርከስ አዳማ ውስጥ ከመስራቾቹ እና በተለያዩ ጊዜያት ሰርከስ አዳማ ለገጠመው ፈተና ቀድሞ የሚገኘ አባል እንደሆነ ባልደረቦቹ የሚናገሩለት አቶ አላምረው ዳኜ፤ አሁን ላይ የሰርከስ አዳማ ፀሀፊ ሆኖ እየሰራ ይገኛል።

“በአዳማ ከተማ መስተዳድር ስራ አስፈጻሚ በተወሰነው መሰረት ከዚህ ቀደም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የነበረው የማዕከሉ ውዝፍ የቤት ኪራይ እዳ ሙሉ በሙሉ ተሰርዟል። ከዚህ በኋላም በየዓመቱ ፍቃዳችንን እያደስን በነጻ እንድንጠቀም ተፈቅዷል” የሚለው አላምረው የከተማ አስተዳደሩ የሰርከስን አስፈላጊነት አምኖ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቧል።

ላለፈው አንድ ወርና ከዛ በላይ ለሚሆን ጊዜ የአዳማ ሰርከስ ማዕከል በአዲስ መልክ በድርጅታዊ መዋቅር መደራጀቱንና በከተማው ከሚታወቁ የበጎ-አድራጎት አስተባባሪዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን ያካተተ ቦርድም ተሰይሞለት በአዲስ መልክ ወደ ስራ መግባቱ ተገልጿል።

አስተያየት