ኅዳር 9 ፣ 2015

ያልተነገረው የሰአሊ አለ ፈለገሰላም የአዳማ ቆይታና ደማቅ የኪነ-ጥበብ ጉዞ

City: Adamaኪነ-ጥበብ

ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም የማርያም ቤተክርስትያንን ሥዕል ለመሳል አዳማ ከመጡ በኋላ በ 2000 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እስኪመለሱ ድረስ እዚያው መሬት ገዝተውና ቤት ሰርተው ለአመታት ኖረዋል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ያልተነገረው የሰአሊ አለ ፈለገሰላም የአዳማ ቆይታና ደማቅ የኪነ-ጥበብ ጉዞ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚድያ

ከሀሳብ ምጥ አዋልደው ለቁምገር ካበቁት የአዲስ አበባ የሥነ-ጥበብ ት/ቤት ዳይሬክተርነት በ1967 ዓ.ም በፍቃዳቸው የለቀቁት ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም ኅሩይ በመቀጠል ወደ ባህል ሚኒስትር ተዛውረው ለአምስት ዓመታት የቅርስ ጥገና ክፍል ሰርተዋል። ከዚያም በወቅቱ ከነበረው መንግስታዊ አሰራር ጋር ባለመስማማት ስራውን አቋርጠዋል።  

ከዚህ በኋላ ሠዓሊው አለ  በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በግንባታ ላይ ከነበረው የናዝሬት ደብረሰላም ቅድስት ማርያም ካቴደራል አስተዳደር ጋር ባደረጉት ስምምነት ስራውን ለመስራት ወደ አዳማ መጥተው እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ  በአዳማ ቆይተዋል።

የአለ የቅድስት የማርያም ቤተክርስትያን የሥዕል ስራ በአዳማ 12 ቀበሌ ማርያም ቤተክርስትያን ጀርባ ላደገው አብይ ሰለሞን ልዩ ትዝታ አለው። “ከት/ቤት ስመለስ ማርያም ቤተ ክርስትያን ገብቼ ስራቸውን እመለከት ነበር”  የሚለው አብይ የተማረው በአዳማ የቀድሞው አጼ ገላውዴዮስ ት/ቤት ሲሆን በተለያዩ አለማቀፍ እና የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ውስጥ ሰርቷል።

“እርሳቸው የልጅ ፍቅርም ስላላቸውና በልጅነት ጉጉት ለምንጠይቃቸው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ስለማይሰለቹና፣ የጥበብ ስራቸው ምትሃት በጊዜው ለነበረኝ የልጅ አዕምሮ ከፍተኛ ዕርካታ ስለነበር ከስራቸው አልለይም ነበር። እርሳቸው በከፍታ ላይ ተቀምጠው ሥዕል ከሚሰሩበት የቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን ጉልላት በታች ወለል ላይ ቁጭ ብዬ እጃቸው የሚፈጥረውን ድንቅ ሥነ ሥዕል ከመመልከት በላይ ለኔ ፍስሃ አልነበረም” ይላል አብይ በትዝታ ወደኋላ በመመለስ። 

ዲያቆን ተፈራ በጋሻው የናዝሬት ደብረጸሐይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል አገልጋይ ናቸው። ካቴድራሉ መስከረም 21 ቀን1981 ዓ.ም የግንባታ ስራው ገና ሳይጠናቀቅ ቅዳሴ ቤቱ እንደተመረቀና አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ያስታውሳሉ። ከዚያን ጊዜ በኋላ ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም መምጣታቸውንና የሥዕል ስራው እንደተጀመረ ገልጸውልናል። 

"በካሬ ሜትር 500 ብር ክፍያ ነበር ውላቸው” የሚሉት ዲያቆን ተፈራ በጋሻው እርሳቸው በረዳትነት አብረዋቸው መስራታቸውን ይናገራሉ። 

"እንዳጫወቱኝ እዚህ (አዳማ) በመጡበት ሰዓት 67 ዓመታቸው ነበር፤ የሥዕል ስራው ስምንት ዓመት ፈጅቷል። እንደሌሎች ሰዓሊዎች መሬት ስለው በኋላ ግድግዳ ላይ መለጠፍ ሳይሆን ግድግዳው ላይ እንዳለ ነው የሚስሉት። ይህንንም እስከ ጉልላቱ ድረስ ወጥተው ነው የሳሉት" በማለት አብራርተውልናል ዲያቆን ተፈራ።  

ሰዓሊ አለፈለገ አዳማ በኖሩበት ወቅት በቤት ውስጥ የምታግዝ ሰራተኛ እንደነበረቻቸውና፣ አሳ ማጥመድ የሚወዱና ስፖርት የሚሰሩ እንደነበሩም ዲያቆኑ አጫውተውናል። 

ከስራቸው ውጪ ማህበራዊ ቅርርብ ብዙም ያልነበራቸው ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም አብዛኛውን ጊዜያቸውን በሥዕል ስራዎች ላይ ያሳልፉ ነበር።

በአዳማ ነዋሪ የሆነ ጸጋው አብርሐም የተባለ ወጣት ሰዓሊ ስለ አለ ፈለገሰላም ሲያወራ "አባባ" ይላቸዋል። ከታላቅ ወንድሙ ሰዓሊ አማኑኤል አብርሐም ጋር በመሆን በአዳማ ከሰዓሊና መምህር አለ ፈለገ-ሰላም ጋር ብዙ ማሳለፉን ይናገራል።  ጊዜው ረዝሞ ትውስታው ቢደበዝዝም ጸጋው ታላቅ ወንድሙ አማኑኤል በ80ዎቹ የመጀመሪያ አመታት አካባቢ ከሰዓሊ አለ ፈለገሰላም ጋር መተዋወቁንና እስከ 90ዎቹ መጀመሪያ ረዳታቸው ሆኖ አብሯቸው መቆየቱን አጫውቶናል።  

“አማኑኤል ወደ ሥነ-ጥበብ ት/ቤት ሲገባ እንደሱ ሆኖ የሚያግዛቸው ሰው ያስፈልግ ስለነበር ከእርሳቸው ጋር መስራት ጀመርኩ” ይላል ጸጋው ከአለ ጋር መስራት የጀመረበትን ጊዜ ሲናገር።  

ከዲያቆን ተፈራ በተለየ፣ ጸጋው እንደሚለው አለ የማርያም ቤተ ክርስትያንን የሥዕል ስራ ለመስራት ከአምስት ዓመት የበለጠ አልፈጀባቸውም።

“የቤተ ክርስትያኑን ሥዕል ሲሰሩ ልዩ የሚያደርጋቸው የሚስሉት ሸራውን ግርግዳው ላይ ከለጠፉ በኋላ ነው" የሚለው ጸጋው ይህ እርሳቸው ጋር የተመለከተው ልዩ ስራ እንደሆነ ይናገራል። 

ጸጋው እንደሚለው ሰዓሊ አለ የማርያም ቤተክርስትያንን ሥዕል ለመሳል አዳማ ከመጡ በኋላ እዚያው መሬት ገዝተውና ቤት ሰርተው ለአመታት ኖረዋል። እድሜያቸው በጊዜው በ60ዎቹ ውስጥ የነበረ ሲሆን ከማርያም ቤተ ክርስትያን ሥዕል በኋላ አዳማ ላይ ባይሰሩም እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ኖረዋል።  

ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም ከሥዕል ስራቸው በተጨማሪ አያሌ ልዩ የአኗኗር ዘይቤ እንደነበራቸው የሚናገረው ጸጋው አብዛኛውን ነገር በልጅነት አዕምሮው አብሯቸው ቆይቶ መታዘቡን ይናገራል። 

እሱም እንደዲያቆን ተፈራ ዓሳ ማጥመድ ይወዱ እንደነበር ያጫወተን ጸጋው አብሯቸው በወንጂ፣ ሶደሬ እና ቆቃ ድረስ በመኪናቸው ተንቀሳቅሰው ያጠምዱ እንደነበር ነግሮናል። ራቅ ሲልም ወደ ተወለዱበት ሰላሌ አካባቢ ያለው ጀማ ወንዝ ድረስ ተጉዘው አሳ ያጠምዱ ነበር። 

ጸጋው እንደሚለው ለመዝናኛ ከሚያጠምዱት ዓሳ በተጓዳኝ ንብ ያንቡ ነበር። ንብ የማነብ ስራ ይሰሩ የነበረው በተለምዶ ታንከኛ ተብሎ የሚጠራው የሀገር መከላከያ ካምፕ ጀርባ ያለ ግቢ ነበረ። 

"ጡረታ እንደወጡ ራሳቸውን ለመደጎም ነው የንብ ማነብ ስራውን የጀመሩት" የሚለው ጸጋው በተለምዶ 10 ቀበሌ በሚገኘው ቤታቸው ጭምር የተወሰኑ ቀፎዎችም ነበራቸው ብሎናል። 

ይህን የንብ ማነብ ስራ ግን በዋናነት የሚያከናውኑት ደንበላ አካባቢ በተለምዶ ታንከኛ ከሚባለው የመከላከያ ግቢ ጀርባ ባለ ግቢ እንደነበር ጸጋው ይናገራል። ይህ ግቢ የእነተዋናይ ጀማነሽ ሰለሞን እና የሙዚቀኛ አብዩ ሰለሞን ቤተሰቦች መኖሪያ ግቢ የነበረ ተራራ ስር የሚገኝ ስለሆነ ንብ ለማነብ ይመች ነበር። 

ሰዓሊ አለ ብዙ ጊዜ ከአብዩ ሰለሞን ጋር ተገናኝተው፣ ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ሲጨዋወቱ ያሳልፉ እንደነበር ያስታውሳል ጸጋው። 

ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ ወዲያ ግን አቅማቸው ስለደከመ ቀፎዎቹን ለተለያዩ ሰዎች በስጦታ እንደሰጡ ጸጋው ነግሮናል።

ስለዮጋ ስፖርት ወዳድነታቸው ሲናገርም "በጭንቅላታቸው ቆመው እግራቸውን እያንቀሳቀሱ እንዲሁም እግራቸውን አጣጥፈው ተቀምጠው ዮጋ ስፖርት ይሰሩ ነበር፤ ምንም እንኳን እድሜያቸው ቢገፋም ቀልጣፋና ፈጣን ነበሩ” ይላል ጸጋው።

"ከአባባ (ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም) ቁጥብነትን እና ለነገሮች በተለይም ለስራ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን ተምሬአለሁ" የሚለው ጸጋው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ እርሱም ወደ ስራ በመግባቱ ግንኙነታቸው መቀነሱን ነግሮናል። 

ሌላው ስለሰዓሊ አለ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ካነጋገራቸው መሃከል አቶ ዘውዱ ቢረዳ አንዱ ነው። ዘውዱ ሰዓሊ አለ ፈለገ ሰላምን በ1992 ዓ/ም አዳማ ውስጥ እንዳገኛቸውና አጭር ቆይታ እንዳደረጉ አጫውቶናል። 

"ቁጥብ ናቸው፣ ቤታቸው ሄጄ አንዳንድ አሳይመንቶች ይሰጡኝ ነበር። ብዙም ከሰዎች ጋር አይገናኙም ብቻቸውን ሲሰሩ ነው የሚውሉት" ይላል ዘውዱ የሞያ ህይወቱን እንደቀየሩት በማስታወስ። 

ዘውዱ ሥዕል እና ቅርጻቅርጽ ስራ ይሰራ የነበረ ሰዓሊ ሲሆን አለ አስተያየት እንዲሰጡት ይመላለስ ነበር። ይህም ክህሎቱን እንዳሳደገለት ይናገራል። 

ጥሩ መምህርነታቸውን የሚናገረው ዘውዱ የቅርጻ ቅርጽ መጽሐፍቶች እንደነበሯቸውና የእነ ሚካኤል አንጄሎን፣ ሊዮናርዶ ዳቪንቺን እንዲሁም የሌሎችንም ስራዎች ያሳዩት እንደነበርና የሚሰራቸውን ስራዎች ለማሻሻል የሚረዱ አስተያየቶችን ይሰጡኝ ነበር ይላል።  

“ሰዎችን ለማብቃት ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነው፤ ያለኝን ፍላጎት ተመልክተው አዲስ አበባ በተማሪያቸው ሰዓሊ እና መምህር እሸቱ ጥሩነህ ት/ቤት አስመዝግበውኝና ነጻ የትምህርት እድል አግኝተውልኝ በግል ጉዳይ ሳልማር ቀርቻለሁ” ይላል ዘውዱ። 

አለ እና ሐምሌ

አለ እና ሐምሌ የታሪክ ትስስር አላቸው። ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም ኅሩይ የተወለዱት ሐምሌ 24 ቀን 1915 ዓ.ም በያኔው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፍቼ ገነት ከተማ ነው። ሀ ብሎ ከፍቼ የሚነሳው የጠቢቡ አለ ፈለገሰላም የህይወት ታሪክ ድፍን ኢትዮጵያን በደማቅ ቀለም ውብ አድርጎ ስሎ፣ በትጋት የእድሜ ልክ ሀውልት አቁሞ በ2008 ዓ.ም ሐምሌ 4 ቀን የዓለም ጉዟቸው ይጠቀለላል። 

"ስም ከመቃብር በላይ ይውላል" እንዲል የሀገር ሰው ጠቢቡ አለ ፈለገሰላምን ከመቃብር በላይ፣ ከትውልድ አልፎ በሚሻገር አበርክቷቸው ከሚያሥነሳቸው ያቋቋሙት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውን የሥነ-ጥበብ ት/ቤት ተመርቆ የተከፈተው ሐምሌ 16 ቀን በንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የልደት በዓል ቀን ነበር።

ሌላው የሚገርመው የሠዓሊ አለ ፈለገሰላም እና የሐምሌ ትስስር ምንም እንኳን በአሰያየሙ ቅሬታቸውን በግልጽ እስከ ዩኒቨርስቲው ዲን ድረስ ያቀረቡበት የሥነ-ጥበብ ት/ቤት ከቀድሞ ስያሜው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጥበባት ት/ቤት ወደ አለ የሥነ-ጥበብ ት/ቤት የተቀየረው በሐምሌ ወር 2002 ዓ/ም ነበር።   

‘የሞት ፍርደኛው’ ታዳጊው አለ ፈለገሰላም

ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም ባደረጓቸው ቃለ-መጠይቆች እንደገለጹት አሳዳጊያቸው አያታቸው አለቃ ኅሩይ በልጅነታቸው ከሥዕል ይልቅ ወደ ቤተክህነት ትምህርት እንዲያተኩሩ ይገፋፏቸው እንደነበር ይናገራሉ። በዚህም በልጅነታቸው አለቃ ጥበቡ ከተባሉ መምህር ስር ቅኔ እና ዜማ የተማሩት ታዳጊው አለ በልጅነት እድሜያቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የድቁና ማዕረጋቸውን ተቀብለዋል። በወቅቱ የጣሊያን ወረራ በመጀመሩ ታዳጊው አለ ፈለገሰላም ወደ አያታቸው ተመልሰው መኖር ጀምረው ነበር።    

"ደማቆቹ" በሚል ርዕስ በሰለሞን ጥላሁን እና ሥምረት ገብረማርያም በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወቅት የታተመና የ20 ታዋቂ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ የያዘ መጸሐፍ ላይ አዘጋጆቹ ሠዓሊ አለ ፈለገሰላምን ቃለ-መጠይቅ አድርገውላቸው ነበር። 

መጽሄቱ ላይ ሰዓሊ አለ በወጣትነታቸው ስላጋጠማቸው አስገራሚ ሁነት ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል። 

ጣሊያን በወረራ ከገባ ብዙም አልቆየም፤ አንድ ቀን አያቴ እንደ ተኙ ሳያዩኝ ከቤት ወጣሁ። ከባልንጀራዬ ጋር አብረን ነበርን። ፈቅ ብሎ ልጆች ሲጫወቱ በማየታችን ተቀላቀልን። በመሐከል አንድ የጣሊያን አሽከር የነበረ ሰው እኔ እጅ ላይ የነበረችውን ዱላ አይቶ አማረችው መሰለኝ  አምጣ አለኝ። እኔ ምንም ከመናገሬ በፊት አብሮኝ ያለው ባልንጀራዬ  ለምን አምጣ ትለዋለህ በራስህ ዱላ ተጫወት ይለዋል። በዚህ ጊዜ አሽከሩ ተናደደና ባልንጀራዬን በያዘው ዱላ ጭንቅላቱን መታው። የመታው ክፉኛ ስለ ነበር መሬት ላይ ወደቀ። 

በዚያን ጊዜ እኔ ንዴትም ድንጋጤም ይዞኝ በያዝኩት ዱላ የመቺውን አናት ባለኝ ኃይል መታሁት፤ እሱም ወደቀ። ከባልንጀራዬ ጋር ተያይዘን በሩጫ ወደ ቤት ገባን። በኋላ ለካ ያ የጣሊያን አሽከር ጭጭ ብሏል። በማግሥቱ ቤት ድረስ መጥተው ወደ እስር ቤት ወሰዱኝ። አራት ቀናት ያህል ያለ እህልና ውሃ በእስር ቤት ካቆዩኝ በኋላ የሞት ፍርድ ተፈርዶብሃል ብለው ከሌሎች እስረኞች ጋር ይዘውኝ ወደ ገደል አፋፍና ጫካ ወሰዱኝ። 

ስንደርስ አካፋ ሰጡንና የምንቀበርበትን ጉድጓድ እንድንቆፍር አዘዙን፡ ድንጋጤም ልጅነትም አለ፤ ብቻ ለመቆፈር እየሞከርሁ አካባቢዬን ቃኘሁ። ከምንቆፍርበት አጠገብ ትልቅ ገደል አለ። ከኋላዬ መሣሪያ የያዙ የጣሊያን ወታደሮች ቆመዋል። አንዳንዶቹ ያወራሉ። አንዱ ከጎኔ ራቅ ብሎ ሲጋራ ያጨሳል መሞቴ ካልቀረ ለምን አልሮጥም ስል አሰብሁ። አካፋን ጥዬ በገደሉ ቁልቁል እግሬ እንደ መራኝ ሮጥኩ፤ መሣሪያ የያዙት ሁሉ የተኮሱ ይመስለኛል። ከኋላዬ የተኩስ ድምፅ ይሰማኝ ነበረ። በኋላ ገደል ውስጥ ገባሁና በቅጠል ተሸፍኜ ድምፄን አጥፍቼ ተቀመጥሁ። ወታደሮቹ ቢያደምጡ ድምፅ የለም፤ ቢያዩ የሚንቀሳቀስ ነገር የለም። ስለዚህ ከጥይት ቢያመልጥ እንኳ ገደል ስለ ገባ ይሞታል ብለው ትተውኝ ሄዱ። ቤተሰቦቼ ታዲያ ሞቷል ብለው ለቅሶ ላይ ነበሩ። መትረፌን ያወቁት ዘግይተው ነው።

አለ ፈለገሰላም እና አሻራዎቻቸው

ጠቢቡ ሰዓሊ እና መምህር አለ ፈለገሰላም የዘመን ጓዶቻቸውም ሆነ ተማሪዎቻቸው በአንድ ነገር ተስማምተው ይመሰክሩላቸዋል፤ ዘመነኛውን የሥዕል እውቀት ከጥንቱ አገር በቀል የሥዕል ጥበብ ጋር አወዳጅተው ማሳየታቸውን።

በ1915 ዓ.ም በሰላሌ ፍቼ የተወለዱት ሰዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም የመሠረቱት የያኔው የአዲስ አበባ ሥነ-ጥበብ ት/ቤት፣ የዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የአለ የሥነ-ጥበብ እና ንድፍ ት/ቤት በቅኝ ገዢዎች ያልተመሠረተ አንጋፋ ተቋም መሆኑ ይመሠከርለታል።

በ1934 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቆ ከወጣ በኋላ አጎታቸውን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ገብተው እስከ 1940 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።

አለ ፈለገሰላ በዘመናዊ የሥዕል ትምህርት ከተመረቁት የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ናቸው። አለ በመጀመሪያ በ1943 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ቴክኒክ ትምህርት ቤት በማሽኒስትነት የተመረቁ ሲሆን ከዚያም ከአፄ ኃይለስላሴ በተቸራቸው ነጻ የትምህርት እድል አሜሪካ ከሚገኘው ቺካጎ የአርት ተቋም በ1946 ዓ.ም በፋይን አርትስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በኋላም እዚያው ለአንድ ዓመት የሥነ-ሥዕል ማስተማር ዘዴን ተምረው ወደ ሀገራቸው በ1947 ዓ.ም ተመልሰዋል። 

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ወዲህ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ተመድበው የህጻናት መማሪያ መጸሐፍትን ሲያዘጋጁ ቆይተዋል። 

በአሜሪካን ሀገር ለትምህርት በነበሩበት ወቅት ሰርተው ባጠራቀሙት ገንዘብ በበጎ-ፍቃድ መጋዘን ተከራይተው ታዳጊዎችን ማስተማር መጀመራቸውም ይነገርላቸዋል።

ይህ ጥረት እና ትግል ጥሩ ፍሬ አፍርቶ የትምህርት ቤቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር መሆን ከዛም ባሻገር ለመመስረት ላደረጉት ትልቅ አስተዋጽዖ ትምህርት ቤቱ በስማቸው የተሰየመ ሲሆን፣ እንጦጦን የማልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ዘመናዊ የዐውደ-ርዕይ ማሳያ በትምህርት ቤቱ እስከመገንባት ደርሷል።

ሥነ-ጥበብ በዘር ሀረግ?

በ1915 ዓ.ም ሰላሌ ፍቼ ከሰዓሊ አባታቸው ፈለገሰላም ኀሩይ እና ከእናታቸው ወ/ሮ አጸደ ደስታ የተወለዱት ሰዓሊና መምህር አለ ፈለገሰላም ሥዕል የዘር ውርስ ይመስል አያታቸው፣ አባታቸው፣ አጎታቸው በሥዕል ጥበብ የተካኑ ነበሩ። የእውቅናቸውም አድማስ ቤተ-ክህነትን ተሻግሮ ቤተ-መንግስት የዘለቀ ነበር። ቀደምቶቹ በትውፊታዊ ሥዕላት ሲታወቁ አለ ደግሞ በዘመናዊ ሥዕል ስማቸው ናኘ።

አለቃ ኅሩይ ዘ ዲማ ጊዮርጊስ

ለሰዓሊ አለ ፈለገሰላም ፍቼ መወለድ ምክንያት ከሆኑት ሁኔታዎች አንዱ የአያታቸው አለቃ ኅሩይ ወልደ ጊዮርጊስ የፍቼ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ግድግዳ ሥዕላት መስራታቸው ተጠቃሽ ነው። በወቅቱ በራስ ዳርጌ ሣሕለ ሥላሴ ትዕዛዝ የፍቼ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን የሰሩት ሰዓሊ ኅሩይ ወልደ ጊዮርጊስ ከራስ ዳርጌ የአለቅነት ማዕረግ እና እና የመኖሪያ መሬት ተሰጥቷቸው በፍቼ ከተማ አግብተው ወልደው ኖረዋል።  

አያታቸው ሰዓሊ አለቃ ህሩይ በአጼ ሚኒሊክ ዘመን እጅግ ገናና ስም ከነበራቸው ጠቢባን መሀል ነበሩ። አለቃ ህሩይ የአጼ ምኒሊክን ምስል ፣ የታዋቂዎቹ ደብሮች የእንጦጦ ኪዳነ ምህረት እና  የእንጦጦ ራጉኤል ምስሎች  እና ሌሎችንም ምስሎች በመሳላቸው የሚታወቁ ናቸው። ከሥዕል ጥበባቸው ሌላ በቤተ-ክህነትም ትምህርት የተካኑት አለቃ ኅሩይ ሰዓሊ ብቻ ሳይሆኑ በታዋቂው የጎጃም ደብር ዲማ ጊዮርጊስም የቅኔ ሊቅ ነበሩ።

ፈለገሰላም እና እምአዕላፍ ኅሩይ

ታዋቂው የኢትዮጵያ ራዲዮ ጋዜጠኛ አቶ አበራ ለማ በማህበራዊ ትስስር የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ “አለ ፈለገሰላም  ከጠቢባን ምንጭ የፈለቁ ጠቢብ ናቸው” ይሏቸዋል። እውቁ ጋዜጠኛ አቶ አበራ ለማ እንደሚሉት እርሳቸው የተማሩበት የፍቼ  አበራ እና አስፋወሰን ት/ቤት ግድግዳ ስዕሎች በሁለቱ ወንድማማች ሰዓሊዎች ማለትም በአባታቸው ፈለገሰላም ኅሩይ እና በአጎታቸው እምአዕላፍ ኅሩይ መሳሉን ያስታውሳሉ። አክለውም የፍቼ ገነት ጊዮርጊስ እና የአዲስ አበባው አራዳ ጊዮርጊስ የግርግዳ ሥዕል በሁለቱ ወንድማማቾች መሳሉን ይገልጻሉ። አባታቸው ፈለገሰላም ኅሩይ በቅኔ እና በቁም-ጽኅፈት የታወቁ ባለሙያም ነበሩ።

አጎታቸው ሰዓሊ እምአዕላፍ ኅሩይ በአለማዊውም ሆነ በመንፈሳዊ ሥዕል የተመሠከረላቸው ሰዓሊ እንደሆኑ ይነገራል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ ማተሚያ ቤት ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤትም ይሰሩ እንደነበርም ይነገራል። 

በ1950ዎቹ አራዳ ጊዮርጊስን በሥዕል ያስዋቡት እምአዕላፍ ኅሩይ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥዕል ጥበብ ከተከታዮቹ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፣ ከሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ እና ከክቡር የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ጋር አብረው የሚጠቀሱ ናቸው።

አለ ፈለገሰላም

ሰዓሊ አለ ፈለግሰላምም የቀደምቶቻቸውን ፈለግ ተከትለው የመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ የጎፋ ገብርኤልን፣ በመርካቶ የቅዱስ ሚካኤል ካቴድራልን፣ በመርካቶ የቅዱስ ራጉኤልን ቤተክርስቲያን፣ የናዝሬት (አዳማ) ደብረጸሐይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል፣ የቁልቢ ገብርኤልን ቤ/ክ እንዲሁም ከባህር ማዶ በአሜሪካን ሀገር በዋሽንግተን ዲሲ የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንን የሥዕል ስራ ሰርተዋል።

በ1949 ዓ.ም ከወ/ሮ አስቴር ክፍለዝጊ ጋር በትዳር የተጣመሩት አለ ፈለገሰላም በትዳራቸው የአንድ ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሲሆኑ እነርሱም መሰረት አለ እና ቴዎድሮስ አለ ይባላሉ። 

በአዳማ ያገኘነውና ለብዙ ጊዜ የአለ ፈለገሰላም ቤተኛ እና ወዳጅ የነበረው ጸጋው አብርሀም እንዳጫወተን ልጃቸው መሰረት አለ ኑሮዋ ባህር ማዶ ጀርመን እንደሆነ እንዲሁም ወንዱ ልጃቸው ቴዎድሮስ አለ በህይወት አለመኖሩን አጫውቶናል።

ከልጆቻቸው የእርሳቸውን እና የዘራቸውን ፈለግ የተከተለ ስለመኖሩ ያውቅ እንደሆነ የጠየቅነው ሰዓሊ ጸጋው ከልጆቻቸው ሳይሆን ከልጅ-ልጆቻቸው ይህንን የሥዕል ሞያ የተከተለ እንዳለ ገልጾልናል።

አለ ዳግም ወደ ሥነ-ጥበብ ት/ቤት

ከዘውዳዊው ስርዓት ማብቃት ማግስት ከነበረው መንግስታዊ አሰራር ጋር ባለመስማማታቸውና ባቆሙት ደጅ ቅር ያላቸውና “እንካችሁ ወንበሩ” ብለው ጥለው የወጡት ሰዓሊ እና መምህሩ አለ ፈለገሰላም፣ ዳግም በሰማንያዎቹ አጋማሽ በባትሪ ተፈልገው ወዳቀኑት ት/ቤታቸው ተመለሱ።

ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን በተለያዩ የሥዕል እና ቅርጻቅርጽ ስራዎቻቸው እንዲሁም በግጥም ስራዎቻቸው የሚታወቁት ሰዓሊ እና ቀራጺ ረ/ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ስለ ሁኔታው ሲናገሩ "1986 ዓ.ም ከውጭ ትምህርቴን ጨርሼ ስመጣ አዳማ መሆናቸውን ሰማሁ" የሚሉት መምህሩ ሄደው አለ ፈለገሰላም ያሉበት ሄደው እንዳገኟቸውና ዳግም ከሁለት አስርታት ዓመታት ቆይታ በኋላ በክብር ጋብዘው ወደ ስነ ጥበብ ት/ቤቱ አምጥተዋቸው ትምህርት ቤቱን እንደጎበኙና ለተማሪዎችም ገለጻ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ።   

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ገለፃ በእድሜ ጫና ከአዳማ መኪና ነድቶ ወደ አዲስ አበባ መምጣት እስከከበዳቸው ጊዜ ድረስ አለ በተደጋጋሚ ወደ ት/ቤቱ ይመጡ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

የአለ ፈለገሰላም ዐውደ-ርዕዮች እና ሽልማቶቻቸው

ሰዓሊ እና መምህር አለ ፈለገሰላም ካሳዩአቸው ዐውደ-ርዕዮቻቸው ሁሉ ለአዲስ አበባ የሥነ-ጥበብ ት/ቤት መመስረት መሠረት የጣለው ዐውደ-ርዕይ ተጠቃሽ ነው።

ካስተማሯቸው ተማሪዎች ማለፊያዎቹን በመምረጥ ያዘጋጁትና በልዕልት ተናኘ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ የተመረቀው ይህ ዐውደ ርዕይም ትምህርት ቤት የመመሥረት ርዕያቸውን ዕውን የሚሆንበትን አጋጣሚ ፈጠረላቸው። በዐውደ-ርዕዩ ከተገኘው የሥዕል ሽያጭ ከተገኘ 28 ሺህ ብር እና  ከአንድ ግሪካዊ ከተገኘ የ50ሺህ ብር ልገሳ እንዲሁም ከመንግስት ከተሰጠ 150 ሺህ ብር የሃገሪቱን የመጀመሪያ የስነ ጥበብ ት/ቤቱ ለመመስረት በቅተዋል።

በ1953 ዓ.ም የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጥበብ (Contemporary Art of Ethiopia) በሚል በሩስያ ምስኮ እንዲሁም በ1960 ዓ.ም በካናዳ ሞንቴሪያል የሥዕል ዐውደ-ርዕይ አሳይተዋል። 

በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በህንድ፣ በሶቪየት ኅብረት፣ በቼኮዝላቫኪያ፣ በግሪክና በዩጎዝላቪያ የሥዕል ዐውደ-ርዕዮዎችን ያሳዩት ሰዓሊ አለ ፈለገሰላም የተለያዩ ሽልማቶችም አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ሚሊንየም በሚከበርበት ወቅት ሲድ (SEED) በተባለ አሜሪካን ሀገር ያለ ተቋም የሥዕል ጥበብን ለማስተማር ላደረጉት ጉልህ አስተዋጽዖ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

አከራካሪው የሥነ-ጥበብ ት/ቤት ስያሜ

የቀድሞው  የ “አዲስ አበባ ሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት” መስራች እና ዳይሬክተር ሰዓሊ እና መምህር አለ ፈለገ-ሰላም በብዙዎች ዘንድ የስማቸው አጠራር ግር ሲያሰኝ ይታያል። ይህ የስማቸው አጠራር ለአበርክቷቸው በተሰየመው የሥነ-ጥበብ ት/ቤት ስያሜም ላይ በተነሳው ቅሬታም ላይ ተስተውሏል። 

እንደ ረ/ፕሮፌሰር በቀለ ገለፃ በሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤቱ አነሳሽነት ለወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ ት/ቤቱ በአለ ፈለገሰላም እንዲሰየም ኃሳቡ የቀረበ ሲሆን ውሳኔውም በዩኒቨርሲቲው ሴኔት መፅደቅ ችሏል።

"በጊዜው ብዙ የታሪክ ሽሚያ ነበር" የሚሉት ረ/ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን፣ ሰዓሊ እና መምህር አለ ፈለገሰላም ለሥነ-ጥበብ ት/ቤቱ መመስረት ያበረከቱት ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊወዳደር እንደማይገባ በማሳመን ት/ቤቱ እንዲሰየምላቸው መደረጉን ያስረዳሉ።

በሥነ-ጥበብ ት/ቤቱ አሰያየም ላይ ተቃውሟቸውን ካሰሙ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት እውቁ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤቱ በተዘጋጀውና የሰዓሊና እና መምህር አለ ፈለገ-ሰላም የ40 ቀን መታሰቢያ ዝግጅት ላይ የሰላ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።

ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በወቅቱ ሲናገሩ፣ “ት/ቤቱ አለ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት መባሉ ያላስደሰታቸው አለ ፈለገሰላም፣ 'አየህ ደስታዬ ከፊል ነው። ስሜ ያለ አባቴ ስም ብቻውን ለአጠራር አይመችም፤ ከነአባቴ ስም ባለመጠራቱ ደስታዬን ከፍሎታል። ይህንንም ቅሬታዬን ለዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት በጊዜው አመልክቼያለሁ። አለበለዚያ ቢቀር ይሻላል' ” ብለው ራሳቸው እንደነገሯቸው አስረድተዋል።

ሊቁ፣ ጠቢቡ እና ታታሪው ሰአሊ አለ ፈለገሰላም ኅሩይ በ93 ዓመታቸው ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስትያን የክብር ሽኝት ተደርጎላቸው ሐምሌ 6 ቀን 2008 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ስርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል። 

እኚህ ብዙ ስራ የሰሩ የሀገር ባለውለታ በተገቢው መንገድ ታሪካቸው ባለመጻፉ እና ባለመሰነዱ ለብዙዎች መማሪያ መሆን አልቻለም። ይህን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብ ት/ቤት፣ የዘርፉ ምሁራን እንዲሁም ወዳጅና ቤተሰቦቻቸው እንዲሰሩበት ይመከራል።

አስተያየት