ታህሣሥ 5 ፣ 2015

የተፈናቃዮች ህይወት ያለፈበት በጎንደር ከተማ ቀበሮ ሜዳ መጠለያ

ዜናማህበራዊ ጉዳዮች

የስምንት ሰዎች ህይወት ባለፈበት እና 3 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች የተጠለሉበት ቀበሮ ሜዳ መጠለያ ጣቢያ በአመት 6 ዙር ድጋፍ ማግኘት የነበረበት ቢሆንም እስካሁን ግን 2 ዙር ብቻ እንደቀረበላቸው ታውቋል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የተፈናቃዮች ህይወት ያለፈበት በጎንደር ከተማ ቀበሮ ሜዳ መጠለያ
Camera Icon

ፎቶ፡ በጎንደር ከተማ ቀበሮ ሜዳ አካባቢ የሚገኘው የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ግጭቶች እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ በሚልየን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ። በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ እና በቤንሻንጉል ክልል ባለው ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጎንደር ከተማ አዘዞ ክፍለከተማ አቅራቢያ 'ቀበሮ ሜዳ' ተብሎ በሚጠራ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ህይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ።

በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ጦርነት ከተጀመረበት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ቁጥራቸው 3 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃች ከጎንደር ከተማ ህዝብ እና ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በስተቀር ድጋፍ ያደረገላቸው አካል አለመኖሩን ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት በመጠለያ ጣቢያው ከሚኖሩ ዜጎች መካከል በረሃብ እና በምግብ እጦት የ8 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተፈናቃዮቹ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

መንግስት በአምስት ወር አንዴ ለእያንዳንዳቸው 15 ኪሎ ግራም ስንዴ ብቻ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው የሚገልፁት እነዚህ ተፈናቃዮች ዘይትና አንዳንድ ማጣፈጫ ቅመማ ቅመሞችን ድጋፍ ባለመደረጉ ለተደራራቢ ችግር ተዳርገናል ብለዋል። 

አቶ መላሽ ታከለ ከትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ተፈናቅሎ በአሁኑ ሰዓት በቀበሮ ሜዳ መጠለያ ውስጥ አስተባባሪ ነው። “መንግስት በአምስት ወር አንዴ ለሚልከው 15 ኪ.ግ ስንዴ በገንፎ መልክ ወይ ቆሎ አድርጎ አዘጋጅቶ ለመመገብ እንኳ ማገዶ የሚሆን እንጨት የለም” ሲል የችግሩን አሳሳቢነት ያስረዳል።  

ከ2013 ዓ.ም ህዳር ወር ጀምሮ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ወደ መጠለያ ጣቢያው ከገቡት ተፈናቃዮች ውስጥ “በህክምና እና በምግብ እጦት 3 አባወራ እና 5 ህፃናት በአጠቃላይ 8 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን” አስተባባሪው ይናገራል። 

በመጠለያ ካምፑ 3 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃይ ዜጎች የሚገኙ ሲሆን 1 ሺህ 138 ያህሉ አባወራ እና እማወራ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 875 ሴቶች ናቸው። 1ሺህ 132 የሚሆኑት ደግሞ እድሜያቸው እስከ 5 አመት የሆኑ ህፃናት፣ 62 ነፍሰጡሮች እንዲሁም 160 ገደማ አጥቢ እናቶች ይገኛሉ። በተጨማሪም 40 የሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ተፈናቃዮች በቀበሮ ሜዳ ተጠልለው ይገኛሉ። 

የቀበሮ ሜዳ ካምፕ 15 ትልልቅ ብሎኮች ያሉት ሲሆን 2 ሺህ 100 የሚሆኑ ተፈናቃዮች ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ አካባቢ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል አካባቢ፣ ከሱዳን ድንበር እንዲሁም ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ናቸው። 

እንደ አቶ መላሽ ታከለ ገለፃ በካምፑ ውስጥ 150 ህፃናት በአካባቢው ባለው አፀደ ህጻናት የሚማሩ ቢሆንም “የትምህርት እድል ያላገኙ መኖራቸው፣ የትምህርት ክፍያ የሚጠይቁ ተቋማቶች መኖራቸው፣ ዩኒፎርም እና የመማሪያ ቁሳቁስ ችግር” መኖሩን ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። 

ወ/ሮ እሰየ አበበ ከሱዳን 'አውደራፊ' ጠረፍ ሰላምበር ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ ተፈናቅላ በቀበሮ ሜዳ መጠለያ ትገኛለች። ወደ መጠለያ ጣቢያው ተፈናቅለው ከመምጣታቸው በፊት በጣም ሃብታም እንደነበሩ ትናገራለች። 60 ሄክታር መሬት አርሰው በየአመቱ 1200 ኩንታል ማሽላ እያመረቱ ይተዳደሩ እንደነበር ገልፃ ቤታቸውን፣ መኪናቸውን እና ሃብት ንብረታቸውን ትተው እንደተፈናቀሉ ነግራናለች። 

ወ/ሮ እሰየ አበበ ወደ ቀበሮ ሜዳ ጣቢያ የመጣቸው በ2013 ዓ.ም ከልጆቿ እና ከባለቤቷ ጋር የነበር ቢሆንም ሃብታቸው በመወረሱ እና ይሄ ቀረ የሚባል ንብረት የሌላቸው በመሆኑ ባለቤቷ ከካምፑ ወጥቶ ወዴት እንደሄደ አታውቅም። ልጆቿም ዩኒፎርም የሚያለብሳቸው ባለመኖሩ እና የመማሪያ ቁስቁስ ባለመሟላቱ ትምህርታቸውን እንዳቋረጡ ነግራናለች። 

አቶ አማረ ተክሉ ከትግራይ ክልል ተፈናቅሎ የመጣ እና በሰላሙ ጊዜ በግል ስራ ይተዳደር ነበረ። “ችግርን ካልኖርከው አይታወቅም" የሚሉት አቶ አማረ የራሳቸው መተዳደሪያ የነበራቸው ሰዎች ያላቸውን ንብረት ሁሉ ጥለው ተረጂነት ላይ መውደቃቸው እንዳሳዘነው ይገልፃል። ሰራተኛ ቀጥሮ የሚያሰራበት ትልቅ የግል ፀጉር ቤት እንደነበራቸው የሚናገረው አቶ አማረ አሁን ባለቤቱን ጨምሮ ከሁለት ልጆቹ ጋር በዚህ መጠለያ ጣቢያ እየኖረ ይገኛል። “ከምንም በላይ የሁለት ልጆቼ ከትምህርት ውጪ መሆን ያሳዝነኛል” ሲል ስጋቱን አስረድቶናል። 

“አብዛኛው በካምፑ ውስጥ ያለው ተፈናቃይ በትክክል እያሰበ አለመሆኑን እና ወደ ጎዳና መውጣት የጀመሩ አሉ” የሚለው አቶ አማረ አክለውም የተፈናቀለው ማህበረሰብ የስነልቦና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አፅንዖት ሰጥቷል። 

ከሱዳን ጠረፍ ተከዜ አካባቢ እንደ መጣች የነገረችን ወ/ሮ አልማዝ ሽፈራው ባሏ በ2008 ዓ.ም በሚኖሩበት አካባቢ በተቀሰቀሰ ጦርነት ህይወቱ ማለፉን ገልጻለች። አራት ቤተሰብ ይዛ ወደ መጠለያ ጣቢያ እንደመጣች የምትናገረው ወ/ሮ አልማዝ “በተለይ ሴት ተፈናቃዮች ችግር ላይ ናቸው” ብላለች። ለሴቶች የሚያስፈልጉ እንደ ሞዴስ እና ሳሙና ያሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች የሚያቀርብልን የለም ስትልም የችግሩን ስፋት አስረድታለች። ልጆቿ እንዳይራቡ የቻለችውን ለመሞከር በጎንደር ከተማ እየዞረች ልብስ በማጠብ እንደምትተዳደርም ወ/ሮ አልማዝ ገልፃለች። 

ቀበሮ ሜዳ መጠለያ ጣቢያ በአማራ ክልል ከሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች መካከል አንዱ ሲሆን በፌደራል መንግሥት የሚተዳደር ነው። በጣቢያው የሚገኙት ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው ስለመመለስ ፍላጎታቸው በጠየቅናቸው ወቅት “በአንድ ጎን መንግስት መቋቋሚያ ከሰጠን እና አካባቢው ሰላም ከሆነ እንመለሳለን” የሚሉ ሲኖሩ በሌላ ጎን ደግሞ በስጋት ምክንያት መመለስ እንደማይፈልጉ የሚናገሩ አሉ። 

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተወካይ አቶ ጌትየ ምህረቴ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ በቀበሮ ሜዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች ከተለያዩ ክልሎች የመጡ መሆናቸውን ገልፀው “የተፈናቃዮቹ ጥያቄ ትክክል ነው፤ ድጋፉ በቂ ነው ማለት አይቻልም” ብለዋል።

ይህም የሆነበት ምክንያት በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በሚነሱ ችግሮች ምክንያት ወደ አማራ ክልል የተፈናቀለው ሰው ቁጥር ብዙ መሆኑ እና የግብዓት እጥረት መኖሩ ነው ያሉ ሲሆን በአመት 6 ዙር ድጋፍ መቅረብ የነበረበት ሲሆን እስካሁን ግን 2 ዙር ብቻ እንደቀረበላቸው ይናገራሉ።  

ተፈናቃዮችን ወደ መጡበት እና ሰላም ወደሰፈነበት አካባቢ ለመመለስ ከፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አስተያየት