ጥቅምት 21 ፣ 2015

ከ8 ሚልየን በላይ ሰዎች አሁንም አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የአማራ ክልል አስታወቀ

ዜናማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

11 ነጥብ 6 ሚሊዮን በጦርነት ሳቢያ የተጎዱ ሰዎች የነበሩበት የአማራ ክልል ቁጥሩን ወደ 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዝቅ ማድረጉን የገለፀ ሲሆን አሁንም ግን በሚልየን የሚቆጠሩ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አሉ

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ከ8 ሚልየን በላይ ሰዎች አሁንም አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የአማራ ክልል አስታወቀ
Camera Icon

Credit: Social media

በጦረነቱ ሳቢያ ተጎድተው የነበሩ ከ11 ነጥብ 6 ሚልየን በላይ ተጎጂዎች ውስጥ ከ3 ሚልየን የሚበልጡትን እስካሁን መድረስ ተችሏል ተባለ።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው ቀደም ሲል በክልሉ በጦርነቱ  በደረሰው ጉዳት የተረጂዎችን ቁጥር ከ11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ወደ 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ ታውቋል።

አሁንም በክልሉ በነበረው ጦርነት ለምግብና መድኃኒት እጦት ለተዳረጉ 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ የዕለት ምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።

250 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው መመለስ መጀመራቸውን ያስታወቀው አማራ ከልል፤ በሰሜኑ ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ከ250 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ቀዬአቸው መመለስ መጀመራቸውን የክልሉ አደጋ መከላከልና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን እንደገለጹት የተፈናቀሉ ዜጎች በተለያዩ በክልሉ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች በጊዜያዊነት ተጠልለው የቆዩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ከዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ወሎና ሰሜን ጎንደር ዞኖች የተፈናቀሉት ወገኖች ላለፉት ሁለት ሳምንታት ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ እንደሚገኙ አቶ እያሱ ተናግረዋል።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከቆቦ አካባቢ ተፈናቅለው በመርሳ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ 81 ሺህ ሰዎች ሙሉ በሙሉ መመለሳቸውን ገልጸዋል ኮሞሽኑ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ መጠለያ ካምፕ ተጠልለው የነበሩ ማህበረሰቦች ወደ ቦታቸው እየተመለሱ ነው። የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ የአላማጣ ከተማ እንዲሁም የጨርጨርና ኮረም ነዋሪዎች በሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ድጋፍ ከካምፑ ወደ መኖሪያ ቀያቸው በመመለስ ላይ ናቸው።

በፌደራል መንግስት እና በህውሓት ሃይሎች ሁለት አመታትን ባስቆጠረው ጦርነት ከወልዲያ ወደ ራያ ቆቦ የሚወስደው የአላውሃ የድልድይ መንገድ ከፍተኛ አደጋ ደርሶበት እንደነበር ይታወቃል።

በአላውሃ ድልድይ ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ከወልዲያ ቆቦ ወደ አላማጣ የሚወስደው ይህ ድልድይ ቶሎ ባለመጠገኑ በወንዙ በኩል ጊዚያዊ መንገድ ተዘጋጅቶ ለትራንስፖርት ክፍት ተደርጎ የቆየ ሲሆን ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ ከ ጊዚያዊ መንገዱ በተጨማሪ የአላውሃ ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራ መሆኑን የወልዲያ ከተማ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ገልጿል።

አስተያየት