ታህሣሥ 10 ፣ 2015

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሞባይል ስልክ መጥለፊያ ቴክኖሎጂን ከእስራኤል አምራቾች መግዛቱ ተዘገበ

ዜናወቅታዊ ጉዳዮች

እስራኤላዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ለኢትዮጵያ መንግስት የሚደረግ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ድጋፍ መቆም እንዳለበት ለእስራኤል መንግስት ጥያቄ እንዳቀረቡም ተነግሯል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሞባይል ስልክ መጥለፊያ ቴክኖሎጂን ከእስራኤል አምራቾች መግዛቱ ተዘገበ
Camera Icon

ፎቶ፡ ሃሬትዝ

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሴሌብሪት ከተባለ የእስራኤል የግል የሶፍትዌር አበልፃጊ ድርጅት የሞባይል ስልክ ለመጥለፍና ቁልፎችን ሰብሮ ለመግባት የሚያግዝ መሳሪያ መግዛቱን ሃሬትዝ የተባለው ግዙፉ የእስራኤል ጋዜጣ ዘገበ።

ጋዜጣው ትላንት ባወጣው ዘገባ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እስራኤል ሀገር ከሚገኘው የሶፍትዌር እና ቴክኖሎጂ ድርጅት የሞባይል ስልኮችን መጥለፍ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ምርት መግዛቱን ዘግቦ መሳሪያው “በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን ስልክ ለመጥለፍ እንደሚውል” አስነብቧል። 

የዘገባ ምንጩ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፌስቡክ ገፅ እንዳገኘው በገለፀው ፎቶ የፌዴራል ፖሊስ አመራር ናቸው የተባሉ ሰዎች ይህን የስልክ መጥለፊያ መሳሪያ ይፋ ሲያደርጉ ያሳያል ያለውን ምስል ተጠቅሞ ባሰራጨው መረጃ፣ “በተለያዩ ሪፖርቶች መሰረት ለበርካታ ሰዎች የጅምላ እስር እንዲሁም የተቃዋሚ ሃይሎች እና ጋዜጠኞች ስደት ተጠያቂ የሆነው የፖሊስ ተቋም ከእስራኤሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ኩባንያ የእስረኞችን ሞባይል ለመጥለፍ ጥቅም ላይ የሚውል ቴክኖሎጂን ገዝቷል” ብሏል።

ሃሬትዝ ጋዜጣ ከፌዴራል ፖሊስ የፌስቡክ ገፅ አገኘሁት ያለውን ፎቶ አዲስ ዘይቤ ከፌዴራል ፖሊስ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ ላይ ማግኘት አልቻለም። የሃሰተኛ መረጃዎችን የሚያጣራው ሃቅቼክ ይህን ጋዜጣው በሪፖርቱ የተጠቀመበትን ፎቶ ለመመርመር ባደረገው ጥረት ፎቶው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋራው በጋዜጣው ዘገባ ላይ መሆኑን እንዲሁም ከዚያ ቀደም ምንም አይነት የመረጃ ምንጮች ላይ እንዳልተጋራ ማረጋገጥ ችሏል። 

ይህን መሳሪያ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የገዛበት ትክክለኛ ጊዜ በዘገባው ባይጠቀስም የኢትዮጵያ መንግስት የሴሌብሪት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም የጀመረው ከፈረንጆቹ 2021 ዓመት ጀምሮ መሆኑን የጠቀሰው ሃሬትዝ ጋዜጣ፤ “ይህም ማለት የፌደራል መንግስት እና የህወሓት ኃይል ጦርነት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው” በማለት ዘግቧል።

የሴሌብሪት ኩባንያ ድረ-ገፅ ላይ የሰፈረው መረጃ እንደሚያሳየው “ኩባንያው ዲጂታል መረጃን ለመሰብሰብ፣ ለመገምገም፣ ለመተንተን እና ለማስተዳደር የሚያግዙ ሶፍትዌሮችና መሳሪያዎችን ለመንግስታት እና ለህግ አስፈፃሚ አካላት እንዲሁም ለድርጅቶች እና አገልግሎት አቅራቢዎች የሚያቀርብ የእስራኤል ዲጂታል መረጃ ኩባንያ” ነው። 

ኩባንያው የስልክ መጥለፊያና ሰብሮ የመግቢያ መሳሪያውን ለኢትዮጵያ መንግስት መሸጡን በመግለጫው እንዳመነም በዘገባው ተጠቁሟል። 

Universal Forensic Extraction Device (UFED) ተብሎ የሚጠራው እና ዓለም አቀፍ የፎረንሲክ መረጃን የሚያጋልጥ እንደሆነ የተነገረለት መሳሪያ በይለፍ ቃል ወይም ፓስወርድ የተዘጉ የስልክ ቀፎዎችን በመጥለፍ በስልኩ ውስጥ የነበሩ የድምፅ፣ ቪድዮ እና የፅሁፍ መልዕክቶችና መረጃዎችን እንዲሁም በቀፎው የተደረጉ የስልክ ልውውጦችን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘት ያስችላል።

የእስራኤሉ ጋዜጣ እንዳስነበበው የዚህ ኩባንያ ምርቶችን የሚጠቀሙ ሀገራት በርካታ ሲሆኑ ከእነዚህም በተለያዩ አለም አቀፍ አካላት ማዕቀብ የተጣለባቸው እንደ ቤላሩስ፣ ቻይና፣ ሆንግ ኮንግ፣ ኡጋንዳ፣ ቬንዙዌላ ያሉ ሃገሮችና ሌሎችም ይገኙበታ

ኢታይ ማክ የተባሉ እስራኤላዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የህግ ባለሙያ ለእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር እና ለሴሌብሪት ኩባንያ በፃፉት ደብዳቤ በርካታ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለኢትዮጵያ መንግስት የሚደረግ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሽያጭም ሆነ ድጋፍ መቆም እንዳለበት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ” ማለታቸውን ሃሬትዝ አስነብቧል።

የሃሬትዝ ዘገባ እንደገለፀው ከኢትዮጵያ የተገኙት ሪፖርቶች መሳሪያው በኢትዮጵያ መንግስት ጥቅም ላይ መዋሉን የሚያረጋግጡ መረጃዎች ግን እስካሁን አልተገኙም ብሏል። 

አስተያየት