ጥር 2 ፣ 2015

የአሜሪካ የፖሊሲ ተፅዕኖ የትግራዩን ጦርነት በድጋሚ እንዲያገረሽ ሊያደርገው ይችላል- በሩሲያ የኤርትራ አምባሳደር

ዜናወቅታዊ ጉዳዮች

አምባሳደር ጴጥሮስ ፀጋይ “አፍሪካውያን በነፃነት መተንፈስ ይችላሉ ከአሜሪካ እና ከፈረንሳይ ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ ነፃነታቸውንም ያገኛሉ” ብለዋል።

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የአሜሪካ የፖሊሲ ተፅዕኖ የትግራዩን ጦርነት በድጋሚ እንዲያገረሽ ሊያደርገው ይችላል- በሩሲያ የኤርትራ አምባሳደር
Camera Icon

(ፎቶ፡ ከሲ ኤን ኤን ድረ ገፅ)

በሩሲያ የኤርትራ አምባሳደር ጴጥሮስ ፀጋይ  ከሩሲያው ስፑትኒክ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የአሜሪካ የፖሊሲ ተፅዕኖ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል። “አሜሪካ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አማፂያንን የምትደግፍ በመሆኑ የዋሽንግተን ተፅእኖ እንደገና ወደ ትግራይ ግጭት ሊያመራ ይችላል” ሲሉ አምባሳደሩ አስጠንቅቀዋል።

አሜሪካ “በትግራይ ክልል የሚገኙ ኤርትራውያን ክልሉን ለቀው እንዲወጡ” ማለቷን ያስታወሱት አምባሳደር ጴጥሮስ፣ የኤርትራ መንግስት ዜጎቹን እንዲያስጠነቅቅ መጠየቅ የሚችለው የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ለሁለት ዓመታት በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው እና በተኩስ አቁም ስምምነት የተጠናቀቀው ጦርነት ላይ ህወሓትን  ለመታገል የኤርትራ ሠራዊት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ኃይሎችን ስትደግፍ ቆይታለች፤ በህወሓት በኩልም ኤርትራ የሠራዊት አባላቶቿ በርካታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈፅመዋል በሚል ተደግጋጋሚ ውንጀላዎች ቀርበውባታል።

በአፍሪካ ህብረት መሪነት በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከትግራይ ክልል እንዲወጡ መወሰኑንተከትሎ ባለፉት ሳምንታት የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ዋና ዋና ከተሞች ለመውጣት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በሩሲያ የኤርትራ አምባሳደር ጴጥሮስ ፀጋይ ከስፑትኒክ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአፍሪካ የሚስተዋለው የምዕራባውያን እና የአሜሪካ የፖሊሲ ተፅዕኖ እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል። አምባሳደሩ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “ፈረንሳይ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት በአፍሪካ ያላቸውን ተፅእኖ እያጡ ነው” ብለዋል። “በአሁኑ ጊዜ ሌላ ዓለም እየተገነባ ነው፤ አፍሪካውያን በነፃነት መተንፈስ ይችላሉ፣ ከአሜሪካ እና ከፈረንሳይ ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ ነፃነታቸውንም ያገኛሉ” ሲሉ አምባሳደሩ ለስፑትኒክ ጋዜጣ ተናግረዋል።

በዋነኝነት ምዕራባውያን እና አሜሪካ በአፍሪካ ውስጥ ያላቸውን ተፅዕኖ እንዲሁም የኤርትራ እና ሩሲያ ግንኙነትን በተመለከተ ባደረጉት ቆይታ አምባሳደሩ ሲገልፁ፣ የኤርትራ ልዑካን ቡድን እ.አ.አ በ2023 የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፍ አስታውቀዋል። “ከትግራይ ክልል ድንበር ጋር ያለው ሁኔታ የሚረጋጋ ከሆነ የኤርትራ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ራሳቸው በዝግጅቱ ላይ ሊገኙ ይችላሉ” ሲሉም አምባሳደሩ ገልፀዋል። በዓመቱ አጋማሽ በሴንት ፒተስበርግ የሚካሄደው ጉባኤ ላይ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች መጋበዛቸውን የዘገባ ምንጩ አስነብቧል።

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በህዳር ወር፤ የአሜሪካ መንግስት የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ካልወጡ ማዕቀብ እንደሚጥል አሳስቦ ነበር። 

ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የሩስያ መንግስት በኤርትራ ግዙፍ የሆነ የሎጂስቲክስ ማዕከል ለመገንባት ስምምነት ላይ መድረሱ ተገልፆ ነበር። 

አስተያየት