የካቲት 1 ፣ 2015

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ፍሬያማ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች

ዜናወቅታዊ ጉዳዮች

የኦልማ አዳሪ ትምህርት ቤት 76 ተማሪዎችን በማስፈተን በትምህርት ቤቱ 650 ከፍተኛ ውጤት ሲመዘገብ 21 ተማሪዎች ደግሞ ከ600 በላይ ውጤት አምጥተዋል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ፍሬያማ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚድያ

ተማሪ ሚኪያስ አዳነ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ ነዉ። ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች የተሰጠዉን የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ  ፈተና  በተፈጥሮ ሳይንስ ከ700 አጠቃላይ ዉጤት 666 በማምጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዉጤት ሆኖ ተመዝግቧል። 

ተማሪዉ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረገዉ ቆይታ ለዚህ ዉጤት መገኘት  በትምህርት ቤቱ ውስጥ የነበረው መልካም የሚባል የተማሪዎች ፉክክር እንዲሁም በፈተና አሰጣጥ ሂደት ወቅት  የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እንዳይገቡ መደረጉ ውጤቱ እንዲያምር አስችሏል በማለት ገልፆ ወደፊት አስትሮ ፊዚክስ የማጥናት ፍላጎት እንዳለዉ ይናገራል። 

ትምህርት ሚኒስትር የፈተና ስርቆትና ኩረጃ ለማስቀረት በሚል በ2014 ዓ.ም. የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመድበው መልቀቂያ ፈተና እንዲወስዱ ማድረጉ ይታወቃል። ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተማሪዎችን የፈተና ውጤት ይፋ ባደረጉበት መግለጫቸዉ እንዳሉት ፈተናዉን በሁለቱም የትምህርት መስክ ከወሰዱት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ዉስጥ 29 ሺህ 909 የሚሆኑት 50 ፐርሰንት እና ከዛ በላይ ወይም 3.3%  በማምጣት ወደ ዩኒቨርስቲ እንደሚገቡ ተናግረዉ የተገኘዉ ዉጤት ግን አስደንጋጭ ነዉ ብለዉታል። 

በ2014 ዓ.ም የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን በማስፈተን ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካስገቡ 7 ትምህርት ቤቶች መካከል በባህርዳር የሚገኘዉ ስቴም ኢኖቬሽን ማዕከል (STEM)፣ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የአዳማዉ ኦልማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የወላይታ ሊቃ የአዳሪ ትምህርት ቤት እንዲሁም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ትምህርት ቤት ይገኙበታል። በአብዛኛው በልማት ማህበር ስር የሚተዳደሩት እነዚህ ትምህርት ቤቶች በ2014 ዓ.ም. የተመዘገበው ዉጤት ከዚህ ቀደም ከነበረዉ የፈተና ሂደት ጋር የተለየ አለመሆኑን በማንሳት ነገር የተማሪዎቻችን እንዲሁም የትምህርት ቤቱን አቅም የታየበት በመሆኑ ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሮልናል ይላሉ።

ትምህርት ቤቱ ድሮ ድሮ የናዝሬት መሠረተ ክርስቶስ አዳሪ ት/ቤት ይባል እንደነበርና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ አቶ ሌንጮ ለታ፣ ፕ/ር ላጲሶ ጌዴሌቦ እንደተማሩበት ይነገራል። ከዘመነ ደርግ መባቻ እስከ 2006 ዓ/ም ድረስ በተለያዩ አገልግሎት ላይ የዋለው ተቋም ዳግም ወደ ቀደሞ ተግባሩ ተመልሷል።

ትምህርት ቤቱ በወርሃ ጥር 2006 ዓ.ም. በአቶ አባዱላ ገመዳ አማካኝነት በተጀመረው የኦሮሚያ ልማት ማህበር (ኦልማ) አማካኝነት በ200 ተማሪዎች አሃዱ ብሎ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራዉን የጀመረ ሲሆን አሁን ላይ በአዳማ ከ9 እስከ 12ኛ ከፍል እንዲሁም በቢሾፍቱ ከተማ ደግሞ  ከ9 እስከ 10ኛ በአጠቃላይ 800 ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል።

በ2014 ዓ.ም ከፍተኛ ዉጤት በማምጣት ሁሉንም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ ካሳለፉት አንዱ የሆነዉ የኦልማ አዳሪ ትምህርት ቤት 76 ተማሪዎችን በማስፈተን በትምህርት ቤቱ 650 ከፍተኛ ውጤት ሲመዘገብ 21 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት አምጥተዋል።  

“ለመጣው ውጤት ምክንያት ናቸው የምንላቸው አራት መሠረታዊ ዕሴቶች (Core Values) አሉን” ያሉት የትምህርት ቤ/ቱ ርዕሰ መምህር እነዚህም ቁርጠኝነት፣ የቡድን ስራ፣ በጎ ፍቃደኝነት እና ስነ-ምግባር እንደሆኑ ገልጸው የኦሮሚያ ልማት ማህበር ቀጥተኛ ድጋፍ ደግሞ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የሆኑትና ከምስረታው ጀምሮ በመምህርነት ያገለገሉት መምህር አበበ ዘውዱ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት  “ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከተመሰረተ ጀመሮ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ትራንስክሪፕት ውጤት ከ20 በመቶ፣ የ8ኛ ክፍል የክልል አቀፍ ፈተና (በተለምዶ ሚኒስትሪ ) ከ30 በመቶ እና የኦሮሚያ ልማት ማህበር የሚያዘጋጀው ፈተና ከ50 በመቶ ተይዘው የተሻለ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች እየተቀበለ ይገኛል"። 

በደቡብ ክልል የሚገኘው የወላይታ ሊቃ አዳሪ ትምህርት ቤትም በ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ከፍል መልቀቂያ ፈተናን አስፈትነዉ ሙሉ በሙሉ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማስገባት ከቻሉት ትምህርት ቤቶች ዉስጥ ይገኝበታል። ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ማስፈተን የጀመረው ወላይታ ሊቃ ሲቋቋም ዓላማዉ “ተማሪዎች በትምህርታቸዉ አቅም እያላቸዉ ነገር ግን በቤተሰቦቻቸው የኢኮኖሚ ሁኔታ የተነሳ ጥራት ያለዉ ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ተማሪዎችን በወላይታ ልማት ማህበር አማካኝነት ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ እንዲማሩ ማድረግ እንደሆነ ት/ቤቱ ይገልፃል። 

የትምህርት ቤቱ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ግርማ ደነቀ በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት አቅም የሌላቸዉ ተማሪዎች ወጪያቸዉ ተሸፍኖ እንዲማሩ ከማድረግ በተጨማሪ በትምህርት ቤቱ የተዘጋጀውን የመግቢያ ፈተና አልፈዉ ግማሹን ወጪያቸዉን ሸፍነዉ የቀረዉን ማህበሩ ድጋፍ በማድረግ እያስተማረ ይገኛል። በ2014 ዓ.ም. ለፈተና የተቀመጡት 75 ተማሪዎች ሁሉም ያለፉ ሲሆን ከፍተኛዉ ዉጤት 643 ሆኖ እንደተመዘገበ አቶ ግርማ ደነቀ አስረድተዋል።

ተማሪ ሚኪያስ አዳነ በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዉጤት በማምጣት በአንደኝነት ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ለዚህ ዉጤት "መምጣት የመምህራኖቼ ድርሻ የጎላ ነዉ" ይላል። ተማሪ ሚኪያስን ጨምሮ "በትምህርት ቤቱ ውስጥ  በተማሪዎች መልካም የነበረዉ መልካም ፉክክርም ሌላው ለውጤቱ ማማር አስተዋጽኦ" እንዳደረገ ይናገራል፣ ወደፊት አስትሮ ፊዚክስ የማጥናት ፍላጎቱ እንዳለውም አጫዉቶናል።

ተማሪዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ በማስፈተን ወደ ቀጣይ የትምህርት መስክ ካስገብት እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዉጤት ሆኖ የተመዘገበው በደሴ የሚገኘዉ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ነዉ። ትምህርት ቤቱ  ካስፈተናቸው 65 ተማሪዎች መካከል 25 ተማሪዎች ከ600 መቶ በላይ ውጤት ያመጡ ሲሆን ከፍተኛዉ 666 ሆኗል።

የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ በለጠ ሀይሌ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት ለተማሪዎች ስኬት መምህራን ጉልህ ድርሻ አላቸው። "ትምህርት ቤቱ መምህራን ሲቀጥር በወሎ ዩኒቨርስቲ በሚሰጥ የመግቢያ ፈተና እና በማዕረግ የተመረቁ መምህራኖችን መቅጠራችን ለተማሪዎች ስኬት አንዱ ምክንያት ነዉ የሚሉት ዳይሬክተሩ በበጀት እጥረት ምክንያት የተማሪዎችን ቁጥር የመጨመር እቅድ የለንም። ነገር ግን በተያዘዉ ዓመት በተንቀሳቃሽ ቤተ ሙከራ በአካባቢው የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ተማሪዎችን ለማገዝ ታቅዷል” ይላሉ አቶ በለጠ።

ተማሪ ናትናኤል ሽታዬ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስር በሚገኘው ስቴምና ኢንኩቤሽን ማዕከል ተማሪ ሲሆን 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን 617 በማምጣት ከትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ሆኗል። የፋርማሲ የትምህርት ዘርፍን የማጥናት እቅድ ያለዉ ናትናኤል “በንድፈ-ሀሳብ የተማርነውን በተግባር ሁሉንም ነገር በቤተ-ሙከራ እናያለን፤ በተጨማሪም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንድንሰራ በመደረጉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ችለናል” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

በባህርዳር ዳር ዩኒቨርስቲ ስር የሚገኘው የስቴምና ኢንኩቤሽን ማዕከል 43 ተማሪዎችን በ2014 ዓ.ም. በማስፈተን ሁሉንም ማሳለፍ ችሏል። ተስፋዬ ተገኘ (ዶ/ር) የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር እና የማዕከሉ ዳይሬክተር ናቸዉ። ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ የ12 ክፍል ብሄራዊ ፈተና ማስፈተናቸውን ተናግረው በአራቱም ዓመት መሉ በሙሉ ተማሪዎችን ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛዉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ትምህርት ቤት በዩኒቨርሲቲው ለሚያገለግሉ ማህበረሰቦች ልጆች በሚል ታስቦ የተሰራ ሲሆን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ማስፈተን ከጀመረበት ከ1997 እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ለፈተና ያስቀመጣቸዉን ሁሉም ተማሪዎች አሳልፏል። 

ትምህርት ቤቱ ከአፀደ ህፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ አገልግሎት ይሰጣል። በዘንድሮው የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተናን 60 ተማሪዎችን አስፈትኖ ሁሉም ተማሪዎች ያሳለፈ ሲሆን ከፍተኛው ውጤት 625 ፣ ዝቅተኛው ደግሞ 351 መሆኑን መምህር ጌታቸው ታሪኩ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

የ12ተኛ ክፍል የተማሪዎች ዉጤት ላይ የታየዉ ሰፊ ልዩነት ባለፉት ዓመታት መንግስት ሲከተለዉ የነበረዉን የትምህርት ፓሊሲ በድጋሚ በማጤኑ ነዉ የሚሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ "የተገኘዉ የፈተና ዉጤት ከስርቆትና ከፈተና ኩረጃ በፀዳ መልኩ በትክክል የተመዘገበ መሆኑ ያሳየ" ነዉ ሲሉ በወቅቱ በሰጡበት መግለጫ ገልፀዋል። 

በሃገር አቀፍ ደረጃ የ12ተኛ ክፍል ፈተናን ካስፈተኑት ትምህርትቤቶች ዉስጥ ሰባቱ ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቻቸዉን ማሳለፋቸው የሚጠቁመው አንድ ነገር ቢኖር መንግስት ለትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባውና በትምህርት ላይ በአግባቡ የሚፈስ ኢንቨስትመንትና ጥረት አስደሳች ፍሬ እንደሚኖረውም ማሳያ ሊሆን ይችላል።

አስተያየት