ሐምሌ 28 ፣ 2013

ዘርዓያዕቆብ፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የፍልስፍና ት/ቤት

ትምህርትማህበራዊ ጉዳዮች

የፍልስፍና ትምህርት የአስፈላጊነቱን ያህል ትኩረት አለመሰጠቱና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ውስጥ በሚገባው ደረጃ እየተሰጠ ባለመሆኑ ምክንያት የፍልስፍና ት/ቤት የማቋቋም ሃሳብ መጠንሰስ ምክንያት ሆኗል።

Avatar: Naol Getachew
ናኦል ጌታቸው

Naol is a journalist and fact-checker at Addis Zeybe for HaqCheck. He is a professional working in the fields of fact-checking, journalism, online storytelling, and translation.

ዘርዓያዕቆብ፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የፍልስፍና ት/ቤት
Camera Icon

(ምስል፡ የ6ተኛው ዙር ት/ቤቱ ተማሪዎች በከፊል ፡ ከዘርዓያቆብ የፍልስፍና ት/ቤት የፌስቡክ ገፅ፡)

በዓለም ታሪክ ውስጥ የአፍላጦን (የፕሌቶ) አካዳሚ የመጀመሪያው የፍልስፍና ት/ቤት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በመቀጠልም በአካዳሚው ለአስራ ሁለት ዓመታት ተማሪ የነበረው አሪስጣጣሊስ (አርስቶትል) ሊሲየም የተሰኘውን የፍልስፍና ት/ቤት በማቋቋም ፍልስፍናን አስተምሯል፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የፍልስፍና ት/ቤቶች በተለያዩ የዓለማችን ክፍል በየዘመናቱ እየተቋቋሙ የፍልስፍናውን ዘርፍ ስር የሰደደ እንዲሆን አድርገውታል፡፡

በኢትዮጵያ የፍልስፍና ትምህርት ከዓለም የፍልስፍና ት/ቤት ታሪክ አንፃር ሲታይ አጭር ዕድሜ ያለው ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ በርካታ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፍልስፍና የትምህርት ክፍል ያላቸው የአዲስ አበባ እና መቀሌ ዩኒቨርቲዎች ብቻ ናቸው፡፡

የፍልስፍና ትምህርት የአስፈላጊነቱን ያህል ትኩረት አለመሰጠቱና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ውስጥ በሚገባው ደረጃ እየተሰጠ ባለመሆኑ ምክንያት የፍልስፍና ት/ቤት የማቋቋም ሃሳብ መጠንሰስ ምክንያት እንደሆነ የዘርዓያዕቆብ የፍልስፍና ትምህርት ቤት መስራች ብሩህ ዓለምነህ ይናገራል፡፡ ት/ቤቱን ለመክፈት መነሻ የሆነውን ሃሳብ ጨምሮ ሲያስረዳም የፍልስፍና መምህር የነበሩት ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሐንስ የከፍተኛ የትምህርት ዘይቤ በሚለው መፅሐፋቸው ውስጥ ‹‹ፕሌቶአዊ አካዳሚ›› የሚለውን ሃሳብ ማንሳታቸውን፤ ነገር ግን ይህንን ሳያሳኩ በማለፋቸው በዚህ ትውልድ ፕሌቶአዊ አካዳሚውን የማቋቋም ሃሳብ ወደ ተግባር መለወጥ አለበት ከሚል ቁጭትም ጭምር ነው፡፡

ብሩህ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና የፍልስፍና መፅሐፍቶችን አዘጋጅ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ከሚሰጠው ትምህርት ዘርዓያዕቆብን በማደራጀትና ኮርሶችንም በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ብሩህ እንደሚለው ፍልስፍና ለሌሎች ትምህርቶችና ሙያዎች መሰረታዊ ዕውቀት በመሆኑ የሰው ልጅ በአለም የስልጣኔ ታሪክ ውስጥ ያሳለፋቸውን የሃሳብ ገድል ለማጤን ፣ ለሚያገኛቸው መረጃዎች ማስረጃ የሚጠይቅና ምክንያታዊ ሰው ማምረትን ዓላማው አድርጎ ነው ት/ቤቱ የተቋቋመው፡፡ 

ዘርዓያዕቆብ የፍልሥፍና ት/ቤት በ2008 ዓ.ም የተመሰረተ በየዓመቱ በክረምት መርሀግብር የአጫጭር የፍልስፍና ትምህርቶች የሚሰጡበት ፕሮግራም ነው፡፡ ዓላማው የፍልስፍና ትምህርትን ለመማር ፍላጎት ላላቸው፤ የተማሩት ትምህርትና የተሰማሩበትን የስራ መስክ ሳይለይ በየትኛውም ዕድሜ ላይ ላሉ ተማሪዎች እንደየደረጃቸው መስጠት ነው፡፡

(ምስል፡ ዶ/ር ዳዊት ወ/አገኝ የሕክምና ፍልስፍናና ታሪክ ኮርስ በመስጠት ላይ፡  ከዘርዓያቆብ የፍልስፍና ት/ቤት የፌስቡክ ገፅ፡)

በአምስት ኪሎ ዓፄ ናኦድ ት/ቤት ውስጥ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የሚገኘው የፍልስፍና ት/ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ስድስተኛውን ዙር ትምህርት እየሰጠ ሲሆን ከመጀመሪያው ዙር አንስቶ እስከ 2013 የክረምት መርሃ ግብር ድረስ በአጠቃላይ 300 የሚደርሱ ተማሪዎችን በመሰረታዊ ፍልስፍና ትምህርት ማሰልጠኑን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ ትምህርት ቤቱ በመደበኛነት ማስተማር ባለመጀመሩ ምክንያት ኮርሶቹን የሚሰጡት መምህራን በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን ናቸው፡፡ 

ትምህርት ቤቱ ለማህበረሰቡ ምን እያበረከተ እንደሚገኝ የፍልስፍና መምህሩ ብሩህ ሲናገር ‹‹የመጀመሪያው አበርክቶት ሶስቱ መፅሐፍት ናቸው፡›› ይላል፡፡ ለአንባቢያን ከቀረቡት መፅሐፍቶች አንደኛው “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የተሰኘውና በትምህርት ቤቱ ውስጥ በውይይት ዳብሮ ወደ መፅሐፍ የተቀየረው መፅሐፍ መሆኑን በመጥቀስ፡፡ የተቀሩት ሁለቱ መፅሐፍትም ‹‹የፍልስፍና ትምህርት ቅፅ 1 እና ቅፅ 2›› ናቸው፡፡ ሁለቱም መፅሐፍቶች በዘርዓያዕቆብ ት/ቤት ለተማሪዎች የተሰጡ ኮርሶች ወደ መፅሐፍነት የተቀየሩ ናቸው፡፡ በነዚህና ወደፊት በሚታተሙ መፅሐፍቶች በመማሪያ ክፍል ውስጥ ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች በተጨማሪ ማህበረሰቡ ፍልስፍናን አንብቦ እንዲማር አበርክቶ እያደረገ መገኘቱን ብሩህ ያስረዳል፡፡

ሁለተኛው የትምህርት ቤቱ አበርክቶት ደግሞ እንደ ብሩህ  እይታ ትኩረት የተነፈገውን ነገር ግን መሰረታዊ ነው የሚለውን የፍልስፍና የትምህርት ዘርፍ ተቋማት ትኩረት እንዲሰጡትና ግለሰቦች ወደው እንዲማሩት በማድረግ መስራቱንና ተማሪዎችንም በተከታታይ ዙሮች እያስተማረ መሆኑ ነው፡፡

(ምስል፡ ብሩህ አለምነህ)

በዘርዓ ያዕቆብ የፍልስፍና ትምህርት ቤት የ6ተኛው ዙር ተማሪዎች አንዱ የሆነው ዮናታን መሰለ የኦዲት ባለሙያ ነው፡፡ ‹‹ለረጂም  ጊዜ ፍልስፍናን ለመማር ፍላጎቱ ነበረኝ ፤ ዘርዓያዕቆብ የፍልስፍና ትምህርት አንደሚሰጥ ስሰማ ያለማመንታት ተመዝግቤ ትምህርቱን መከታተል ጀመርኩ›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ትምህርቱን መከታተል ከጀመረ በኃላ ከጠበቀው በተሸለ መልኩ እንዳገኘው ይናገራል፡፡ ዮናታን አስቀድሞ የንግድ ትምህርት ይማር እንጂ ፍልስፍና የህይወት ዘይቤ በመሆኑ ለመማር እንደወሰነ ያስረዳል፡፡ 

ዘርዓያዕቆብ በዩንቨርሲቲዎች ዉስጥ ከሚሰጠዉ የፍልስፍና ትምህርት በተለየ መልኩ ይዘቶችን በአማርኛ ቋንቋ መስጠቱ  ነው፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርቶች ሲሰጡ በተማሪውና መምህሩ እንዲሁም በተማሪውና በትምህርቱ መካከል ደንቃራ (barrier) ነው ይላል ብሩህ፡፡ ትምህርቱን በሚገባ ለመረዳት እንደጠቀመውም በማከል ዮናታን በሃሳቡ ይስማማል፡፡

ሁለተኛው ልዩ የሚያደርገው በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና በየትኛውም የስራ መስክ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ማስተማሩ እንደሆነ ብሩህ ያስረዳል፡፡ ጨምሮ ሲያብራራም በዘንድሮው ዙር አቶ ጉልማ የተባሉ በግምት ሰባ ዓመት የሚሆናቸው አዛውንት ትምህርቱን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ የጤና ባለሙያዎች ፣ የጋዜጠኞች ፣ የቴአትር ባለሙያዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ሙያዎች ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል፡፡

እንደ ብሩህ ማብራሪያ ት/ቤቱን ወደፊት የተለያዩ ዕቅዶች አሉት፡፡ በኮሌጅ ደረጃ ተቋቁሞ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተማሪዎችን በፍልስፍና አስተምሮ ከማስመረቅ አንስቶ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ትልልቅ የሚዲያ ተቋማት ፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችንና ሌሎች ድርጅቶች ሰራተኞች ፍልስፍናን የማሰልጠን ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ መስራቹ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል፡፡

አስተያየት