ነሐሴ 16 ፣ 2010

የሰው ሰውነት፡- የከተሜነት ወግ ማዕረግ

ታሪክ

1998 ዓ.ም፡፡ ‘ISTANBUL, Memories and the City’ የተሰኘው መጽሐፍ ለንባብ ሲበቃ ቱርክ ገንጣዮቼ ከምትላቸው የፒኪኬ Partiya…

1998 ዓ.ም፡፡ ‘ISTANBUL, Memories and the City’ የተሰኘው መጽሐፍ ለንባብ ሲበቃ ቱርክ ገንጣዮቼ ከምትላቸው የፒኪኬ Partiya Karkerên Kurdistanê ( PKK) ልጆች ጋር ትንፋሽ በሚያሳጥር ውጊያ ላይ ነበረች፡፡ የኦቶማን ኢምፓየር ልጆችም ቀልብ በሚነሳ ጦርነት ተጠምደዋል፡፡ ነፋሱ ባሩድ ባሩድ ይሸታል፡፡በአንድ ሀገር፣ በአንዲት ከተማ፣ በአንድ ህንጻ ለ40 ዓመታት የኖረው ኦርሀን ፓሙክ (Orhan Pamuk) ይህን የሞት ትርክት ገለበጠው፡፡ ሬሳ ሲቆጥሩ የነበሩት የምዕራብ ሚዲያዎችንም ወደራሱ ከረበታቸው፡፡ ቦስተን ግሎብ «አጅሬ ኢስታንቡልን በሸራ ላይ ሳላት» ሲል (Insightful, eclectic, whimsical.… Pamuk is not writing İstanbul, he is painting it) ፋይናንሽያል ታይምስ ደግም « የእርሱን ከተማ ባንረግጥ እንኳ የፓሙክን መሳጩ መጽሐፍ በምናብ ይዞን ይነጉዳል» አለ (Remarkable… even those of us who have never set foot in [Istanbul] will be transformed by reading Pamuk’s extraordinary and moving book)፡፡ ባለ 37 ምዕራፍ መጽሐፉ እንደ ሀዋሳ ፍሊቶ ዓሳ ነው፤ አንጀት ጠብ አይልም፡፡ ትኩሳቱ እጅህ አለ፣ ቅባቱ ከንፈርህ ላይ አለ፣ ጣዕሙ ምላስህ ላይ አለ፣ ስሜቱ ሆድህ ውስጥ አለ፤ ግን አጠግብም፡፡ ያለህ አማራጭ እንደ ቤተክርስቲያን ሰንበቴ እየጠበክ ዓሳ ገበያ መመላለስ ነው፡፡ የፓሙክ መጽሐፍም እንደዚያው ነው፤ በኢስታንቡል ጓዳ-ጎድጓዳ ያንከራትተሀል፣ በኢስታንቡል እድሜ-ጠገብ መስጊዶች ሳሎን ውስጥ ያመላልስሀል፣ በኢስታንቡል አውራጎዳናዋች ላይ ያንሸራሽርሀል፣ በኢስታንቡል የታሪክ-ኩሽና ቤቶች ውስጥ ይቀረቅርሀል፡፡ አትሰለችውም፤ አይንህ እስኪዝል ድረስ አጅህን ጉንጭህ ላይ ጥለህ ትከተለዋለህ እንጂ፡፡2006 ዓ.ም፡፡ ‘ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ድሬዳዋ’ ከአንባብያን እጅ ሲደርስ፤ ጓደኛየ«ሮቤል ድሬዳዋ ሄደህ ታቃለህ?» ብሎኝ ነበር፡፡«አላውቅም!…ግን ለመሄድ አስባለሁ፡፡» አልኩት«አትድከም! ይልቅ እድሜ ለአፈንዲ በል፤ ድሬ እጅህ ጋ መታለች» አለኝ፡፡ጓደኛየ በርግጥም ትክክል ነበር የ’ገለምሶው’ ሰው ከተማውን ከልብ ቀርጾታል፣ ካንጀቱ ነድፏታል፣ መረጃ አንተርሶ ከትቧታል፡፡Dirre dhawaatu dhuga bishaan lega harreeJaalala akkanaa takkaatuu hin agarre እንዲል አሊ ቢራ፤ አፈንዲ ከድሬ ጥንስስ አንስቶ እስከ ልጆቿ፣ ጥበብ፣ ኮንትሮባንድ፣ ሀላዋ፣ ሽልንጌ፣ በሻንፈር…እና ሰው ሰው በሚሸቱ ህልቆ መሳፍርት ትዝታዎች በመጽሐፉ አቋድሶናል፡፡ከተማ እወዳለሁ፤ የከተማ ትርክት ይስበኛል፣ የከተማ ዙረት ይመቸኛል፣ ከተሜነት እንደ ሩቅ ወዳጅ ይናፍቀኛል፡፡ በቅርብ  የወጡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት 20 በመቶው ወይም ከ25 ሚሊዩን በላይ ኢትዮጵያውያን በከተሞች ይኖራል፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገሮች እንኳ 40 በመቶ (2012) ህዝባቸውን ከገጠር አስወጥተዋል፡፡ የመሰረተ ልማት መስፋፋት፣ ድንበር ዘለል ንግድ መበራከት፣ የቴክኖሎጂ መራቀቅ እና ከተሞች የብዘሀ ባህል አደባባይ መሆን ገጠሬው ከተማውን በስስት እንዲመለከት አስገድዶታል፡፡ከሶስት ምዕተ ዓመታት በፊት፡፡ በዛሬዋ ኢራቅ የሚገኘው ሜስጶታሚያ ከተማ የተጸነሰበት ቦታ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህ አካባቢ በታዋቂዎቹ የኢፍራጥስ እና ጤግሮስ ወንዞች መካከል ይገኛል። በወቅቱ ጥንታዊ የአካባቢው ነዋሪ /ኅብረተሰብ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የእርሻ ሥራ ላይ የተመሰረተ ስለነበር ከተሜነት በዚያም ሆነ በተቀሪው የዓለማችን ክፍል በፍጥነት የመስፋፋት ዕድሉ እስከ 18ኛው መቶ ክ/ዘመን ዘገምተኛ የሚባል ደረጃ ላይ ነበር (አዲስ አድማስ፣ 2006 ዓ.ም)። ይሁንና በ18ኛው ክ/ዘመን በእንግሊዝ የተከሰተውን እና ቀጥሎም መላው አውሮፓንና ሰሜን አሜሪካን ባደረሰው የኢንዱስትሪ አብዮት ምክንያት በከተማ የሚኖረው የዓለም ሕዝብ በአጭር ጊዜያት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምርና ከተሞችም እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል።የከተማ ሰው ይርበኛል፣ የከተማ እብድ ራሱ ይናፍቀኛል፣ የከተማ ዝናብ ሳጣ ቅርቅር ይለኛል፡፡ የከተማ ውሻ ካላየሁ ይደብረኛል፣ የከተማ አባኮዳ ካጣሁ ይጨንቀኛል፡፡ ሀዋሳ ሀይቅ አንድ አዝግ የሆነ አባኮዳ ነበር፡፡ በቃ መብረር የሰለቸው፣ መጮህ የታከተውና መሳቅ የደበረው አባኮዳ፡፡  የሚውለው ካፌ ለካፌ ከሰው ጋር ነበር፤ የሚበላው የሰው ምግብ ነው፣ የሚጠጣው የሰው መጠጥ ነው፣ የሚያውራው ከሰው ጋር ነው፡፡ ሁልግዜ ሳየው ከአባኮዳ ያጣው ሆኖም ከሰው ልጅ ያገኘው የሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ከተማ እንደዚያ ነው፡፡ ባዶ ሆነህ ልትመጣ ትችላለህ፣ እፍኝ ይዘህም ብቅ ልትል ትችላለህ፣ ሙሉም ሆነህ ከች ትልም ይሆናል፡፡ ከተማ የሆነ ነገር ይሰጥሀል፡፡ ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ “እመተክህሎ ለእግዚአብሄር ይፍጥረነ ፍጹማነ ወይረሰየነ ብጹዓነ ዲበ ምድር፡፡ ወባሕቱ ኢፈቀደ ይፍጥረነ ከማሁ፤ ወፈጥረነ ድልዋነ ለተፈጽሞትነ”፡፡ (እግዚአብሔር የተሟላን አድርጎ ሊፈጥረንና በምድር ላይ ብጽዓን ሊያደርግ ይቻለው ነበር፡፡ ግን እንዲህ አድርጎ ሊፈጥረን አልፈለግም፤ ለመሟላት ዝግጅዎች አድርጎ ፈጠረን እንጂ) ይላል፡፡ በርግጥ ከተማ ያለህንም ሊነጥቅህ ይችላል፡፡የከተሜነት ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥንታዊነት እንዳለው የሚመሰክሩ ብዛት ያላቸው የስነ-ጽሁፍና የኪነ-ህንጻ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ሽመልስ ቦንሳ (2010 ዓ.ም) እንደሚተነትነው በትንሹም ቢሆን የአገሪቷን ታሪክ ማንበብ ከተቻለ የከተሜነት ስልጣኔዋን የሚመሰክሩ የከተሞች ፍርስራሾችን (ለምሳሌም የሃን፣ አዱሊስን፣ ቆሃይቶን)፣ ወይንም እስካሁን ያልጠፉትን ፣ ህይወት ያለባቸውን እነ አክሱምን፣ ሃረርን፣ ጎንደርን መመልከት ይበቃል። በስነ ህንጻ፣ በስነጽሁፍ፣ በስነ መንግሥትና በኪነጥበብ አክሱም የደረሰችበትን የስልጣኔ ከፍታ የተረዳው ማኒ የተባለው ፐርሻዊ ጸሓፊ አክሱማዊት ኢትዮጵያን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው ክፍለዘመን ከነበሩት አራት ታላላቅ ስልጣኔዎች አንዷ ናት ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ሃረርና ጎንደርም የከተማነት ዝናቸው በብዙ ቦታ የናኘ መሆኑ ሰፊው ታሪካቸው ቆመው የሚታዩትም የስነ-ህንጻ ቅሪቶችም ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ዛሬ እንደ ጃፓኗ ዋና ከተማ ቶክዩ ያሉ ትልልቅ ከተሞች ከ30 ሚሊዩን በላይ ሕዝብ ሰፍረውባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል እነ ዳካ፣ ሻንጋይ፣ ጃካርታ፣ ሙምባይ፣ ዴልሂ፣ ሚኒላ፣ እና ሴኡልን የመሳሰሉ ከተሞች እያንዳንዳቸው የ20 ሚሊዮን ህዝብ ባለቤት ለመሆን ችለዋል። እነ ኒውዮርክ፣ ሜክሲኮ፣ ሳኦፖሎ እና ከአፍሪካ ደግሞ ሌጎስና ካይሮ በተመሳሳይ በከተሞቻቸው የሚኖረው የህዝብ ብዛት ከ20 ሚሊዮን ዘሏል። ይህም ሳይበቃ በእነ ሻንጋይ፣ ቶኪዮ እና ዴልታ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ የነዋሪዎቻቸው ህዝብ ብዛት አሁን ካለው በእጥፍ አድጎ 40 ሚሊዮን ይደርሳል የሚል ግምት አለ። እንደ ተቋማቱ መረጃ በአሁኑ ወቅት ከአለም አጠቃላይ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በከተሞች ይኖራል።ሆኖም ከተሞች የሰው ብቻ ሳይሆን የሀሳብ፣ የፈጠራ፣ የስራ፣ የባህልና መሰል ጉዳዮች መነሀርያ ናቸው፤ ልክ እንደ  ገበያ፡፡ እዚህ ብዘሀ አመለካከት፣ ብዘሀ ቋንቋ፣ ብዘሀ ሀይማኖት ተሰናስለው ይገኛሉ፡፡ የግል የሆኑ እሴቶች እንዳሉ ሁሉ የጋራ የሆኑም ብዙ ትውፊቶች አሉ፡፡ በጊዜ ሂደት፣ በመቀራራበ ውስጥ፣ በመተዋወቅ ዓለም እንዲሁም በመዋደድ ሰዓት የራስን መስጠትና የሌሎችን መቀበል ይኖራል፡፡ በዚህ የመዋሀድ ‘ኬሚስትሪ’ ውስጥ የስነ-ሰብዕ (Anthropology) ምሁራን “Cosmopolitan” ወይም በጋሽ አሰፋ ጫቦ ተለምዷዊ ትርጓሜ “የሰው ሰው” ይፈጠራል፡፡Cosmopolitan is about the love of mankind, or about duties owed to every person in the world, without national or ethnic differentiation. For others, the word… connotes the fluidity and evanescence of culture; it celebrates the compromising or evaporation of the boundaries between cultures. And it anticipates a world of fractured and mingled Identities (Ben Habib, 2006).የሰው የሆነ ሰው ፍቅሩ ድንበር የለውም፤ አክብሮቱ አጥር የለውም፤ ችሮታው ወሰን የለውም፡፡ የሰው የሆነ ሰው እጁ ረጅም ነውና ሁሉን ይቀበላል፣ ሁሉን ያቅፋል፣ ሁሉን ያስተናግዳል፣ ለሁሉም ያካፍላል፡፡ የሰው የሆነ ሰው በምናቡ ተጓዥ ነው፣ በሐሳቡ በራሪ ነው፣ በምክንያት አማኝ ነው፣ ለርዕዮቱ ቀናኢ ነው፡፡ Cosmopolitanism in this sense invites us, without rejecting connections rooted in cultural identity and practice or grasping at universalism, to find connection through, within, and beyond cultural diversity.“ምናቤ ነጻ ተጓዥ ነው፡፡ በራሪ ህልም አለኝ፡፡ በመንፈስ ስከንፍ የክልል ቀርቶ የሀገር ድንበር አያነቅፈኝም፡፡ ወገንተኝነት አይዘኝም፤ ብሄርተኝነት አይገድበኝም፡፡ የፍቅር እጄ በየአቅጣጫው እንደ ጨረር ይበተናል” እንዲል አለማየሁ ገላጋይ (2010) ፡፡Emphasizing this “love of mankind,” cosmopolitanism offers us the chance to become “citizens of the cosmos”, bound by a sense of shared humanity, mutual obligation to one another, and appreciation of human difference (Appiah, 2006).የሰው ሰው የሁሉም ነው፣ ከሁሉም ነው፣ እንደ ሁሉም ነው፣ ወደ ሁሉም ነው፡፡ የመጨረሻ ግቡም ሰበዓዊነትን ከፍ ከፍ ማድረግ ነው፡፡የጨረቃ ከተሞቸ‘The city is composed of different kinds of men; similar people cannot bring the city into existence’. (Aristotle)አዲስ አበባ ክረምትን እንደምትፈራ የአርሶ አደር ጎጆ ሆናለች፡፡ ቀዳዳዋ በዝቷል፣ መጣፊዋ በዝቷል፣ አናጺዋ በዝቷል፡፡ ቢሆንም ለክፍለ-ሀገር ልጆች ሸገር አሁንም የተስፋ ምድር ናት፡፡ መናጢ ድሀው፣ ነጋዲው፣ ሰራተኛው፣ ተማሪው፣ ተስፈኛ ፖለቲከኛው በየቀኑ ይጎርፋል፡፡ ደግሞም እውነት አለው 40% የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ 70% የሀገሬ እውቀት ጢቅ እንዲሁም 100% የእምየ ፖለቲካ የሚሾረው አዱ ገነት ነው፡፡ይህ በከተሞች አካባቢ ያለው የተሻለ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ብዙዎችን እንደሚስብ ይታመናል፡፡ ያለው የተሻለ የመሠረተ ልማት አውታርም ከተሞችን ከገጠር በተሻለ ለኑሮ ምቹ ያደርጋቸዋል፡፡ ሆኖም የከተሞች መስፋፋት በአግባቡ ማስተዳደር ካልተቻለ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ የአንድ ከተማ ዕድገት ከከተማው ሕዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ በማይሆንበት ጊዜ በቀላሉ የማይፈቱ ቀውሶችን ይፈጥራል፡፡ መጠለያ የማግኘት ችግር፣ የሥራ አጥነት መሥፋፋት፣ ሌሎችም የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ችግሮች ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ  ቀውሶች ናቸው፡፡ ከነዚህ በግልጽ ከሚታዩ ችግሮች ባሻገር በስውር ደግሞ ማህበራዊ ተቋሞቻችን  መሽመድመድና የማህበራዊ ኬላዎቻችን (Social Control) መበጣጠስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እኔ በሁለተኛው ወሳኝ ሀሳብ ላይ አተኩራለሁ፡፡የማህበራዊ ኬላዎችን እሴቶች በሶስት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ እነርሱም ስምምነት፣ አብሮነት እና ቀጣይነት፡፡ Deborah Stevenson እ.አ.አ. በ2003 ለንባብ ባበቃችውና Cities and Urban Cultures  በተሰኘ ጥናታዊ መጸሀፏ ከተሞች ነዋሪዎቻቸውን ለብቸኝነት አሳልፈው ቢሰጡም የሚለግሱት ነጻነት ግን ከነፈጉት በላይ የሚያካክስ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ነጸነት በባዶ ቅል ሲሆን ትርጉም ያጣል፤ ወይንም ጩኸት ብቻ ይሆናል፡፡ ከራስ ጋር መታረቅ፣ ከማህበረሰቡ ጋር መግባባት፣ ከተፈጥሮ ጋር መስማማት ወሳኝ ነው፡፡ በርግጥ መግባባት ማለት መቶ በመቶ አንድ አይነት  አቋም መያዝ አይደለም፡፡ ዝብርቅርቅ፣ ድብልቅልቅና ውጥንቅጥ ሀሳቦችን አቀላቅሎና አበጥሮ የጋራ ቤት መገንባት ይቻላል፣ የጋራ ጊዜን ማሳመር ይቻላል፣ የጋራ ተስፋን ማለምለም ይቻላል፡፡ በባለፈው ጊዜ የወል የሆኑ ሀገር በቀል ትውፊቶች የሚወለዱባቸው፣ የሚያድጉባቸው እና የሚደረጁባቸው መደበኛ እንዲሁም ኢ-መደበኛ ተቋማት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ቄስ ትምህርት ቤት፣ ቁርአን ቤት፣ ቅሬ፣ እቁብ፣ ልዩ ልዩ ጨዋታዎች እና ሌሎችም፡፡ እነዚህ ማእከላት አንድን ብላቴና በእውቀትና በስነ-ምግባር ኮትኩተው ለፍሬ እንዲበቃ መንገድ ይጠርጋሉ፡፡ትምህርት መጀመርያ ሰብዓዊ ነው፤ ቀጥሎ መክሊታዊ ይሆናል፤ ከዚያም አዲስ ነገር ወደ መፍጠር ይሸጋገራል፡፡ ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሃንስ ‘የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ’ በተሰኘ ጥልቅ መጽሐፋቸው ሶስት የትምህርት ዓላማዎች/ጠባዮች እንዳሉ ይገልጸሉ፡፡ እነርሱም Humanistic, professional and scientific “ሰው የሚማረው ከዝቅተኛው እንስሶች ጋር የጋራ ከሆነው ስነ-ፍጥረታዊ ሁኔታ ወጥቶ በሃሳቡና በምኞቱ መሰረት ከከፍተኛነት የሙሉ ሰውነት ማዕረግ ደረጃ ለመድረስ ነው” ይላሉ ዶ/ሩ፡፡ በመማር ውስጥ ራስን ማወቅ አለ፤ ሌሎችን መረዳት ይቀጥላል፡፡ በማወቅ ጥረት ውስጥ ትላንትን ማስታወስ አለ፣ ዛሬን መተንተን አለ፤ ነገን መገምት ደግም ይመጣል፡፡ በመጨረሻም ራሰን የመገንዘብ ጥበብ አለ፡፡ The proper study of mankind is man እንዲል አሌከስአንደር ፖፕ፡፡ዛሬ የከተሞች ትምህርት ከራስ ርቆ ሌላን እንድናፍቅ፤ ከሌላ እንድንኮርጅ፤ በሌሎች እንድናሳብብ እና በሌሎች እንድንመካ አድርጎናል፡፡ ዶ/ር መሳይ ከበደ ‘Radicalism and Cultural Dislocation in Ethiopia, 1960-1974’ በተባለውና በ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ በሚያተኩረው መጽሐፋቸው እንዳሉት “አውሮፓ ቀድ ትምህርት አነብናቢነት የፈጠረበት ማኅበራዊ ሥር አልባነቱ፣ ባይተዋርነቱና የባዶነት ስሜቱ የተማረውን ልኂቅ ይበልጥ ለመናፍቃዊና አብዮታዊ አስተምህሮዎች አጋለጠው። የሥር አልባነት አንዱ መገለጫ ሉላዊነት ነው። የዚህ ወደውጭ የሚያጋድል ቀላዋጭ ዝንባሌ ተጽዕኖ እጅግ ጥልቅ በመሆኑ፣ ውጫዊ ክስተቶች የኢትዮጵያን ተማሪዎች በቀጥታ ይቆጣጠራቸው ነበር። ለሥር ነቀልነት የነበራቸውን ጭፍን አምልኮ ለመረዳት የምንችለው፣ ይኽንን የኢትዮጵያን ምሁራን አጎብዳጅነትና ኮራጅነት በዓለምአቀፍ የማርክሳዊነት-ሌኒናዊነት ልዕልና ማዕቀፍ ስናስቀምጠው ነው ይሉናል። ስለዚህም የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ግንባር ቀደም ድክመት በብሔራዊ ውርሶቹ ላይ ለመመርኮዝ ያለመቻልና ከባዕዳን የተዋሳቸውንም አገራዊ ያለማድረግ ናቸው” (ትርጉም-ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም)፡፡ስለ ራስ አለመነጋገር፣ በራስ በሆነ ጉዳይ ላይ አለማተኮር፤ በሌሎች እጅ ባለ ነገር ላይ መጠመድ ትርፉ ድካምና እራስን መጣል ነው፡፡ በርግጥ ድካም ብቻ አይደለም በአብዛኛው ከራስም ጋር ያጣላል፡፡ የማንነት ግጭት የሚባለው ይኸው ነው፤ ቀጥሎ ከማህበረሰቡ ጋር መቃረን ይመጣል፡፡የጨረቃ ከተሞች የዚህ ማህበረሰብ ግልባጭ ናቸው፡፡ እቅዳቸው የቁጥ ቁጥ፣ ህልማቸው መንደር አይሻገር፣ ጉዟቸው ድንገቴ ነው፣ ስራቸው የእውር የድንበር ነው፡፡ የስልጣኔ በር ይከፍቱልናል ብለን ስንጠብቅ ኩረጃ ያስተምሩናል፤ የነጻነትን ጎህ ያሳዩናል ብለን ስንመጣ ባርያ አድርገውን ቁጭ፤ የፍቅር ጸበል ይረጩናል ብለን ስንጓጓ እነሱ ጎራ ለይተው ጥላቻ ይረጫጫሉ፤ የአብሮነት ማእድ ያቃምሱናል ብለን ሞሰባቸውን ብናየውም እነሱ እቴ፡፡ ሌላው የቀጣይነት ጉዳይ ነው፡፡ የጨረቃ ከተሞች ግልጽነትን ሸሽተው የምሽት ምርኮኛ ናቸው፤ ከእውቀት ስለሚርቁ የቆርጦ ቀጥል እስረኛ ናቸው፤ በልምድ ስለማይታገዙ ሁሌ አፍርሰው እንደገነቡ ነው፤ በሀሳብ ልዩነት ስለሚሸበሩ አዲስ ሙከራ ይፈራሉ፡፡ከቴልጅ‘From Tribesmen in to Townsmen’ጀምስ ፈርጉስን  The Country and the City on the Copperbelt በተሰኘ መጣጣፉ የዛምቢያ የማዕድን ሰራተኞች  ከገጠር ይዘውት የመጡት ባህል እንዴት በከተማ እንደሚዋጥና እንደሚለወጥ ይተነትናል፡፡ በተቃራኒው ልብሳቸውና አነገጋራቸው የከቴ ልጅን ለመምሰል ቢጥሩም ልባቸውና ህልማቸው ግን እዚያው ገጠር መንደር ላይ እንደጣሉት ይከራከራል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ከተሞች የሚታየው ከዚህ ይለያል፡፡ ወይ ከገጠሩ ወይ ከከተማው አልሆንም፡፡ መደናገር እዚያም እዚህም ይታያል፡፡ ኢ-መደበኛ በሆነ ምልከታ ሙዚቃውን፣ ፊልሙን እና ሚድያውን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ እንደ ከሰረ ነጋዴ ግራ እንደተጋባ ነው፡፡ ሰው ከገጠር ወደ ከተማ በአካል ይፈልሳል ሌላው ከከተማ ወደ ገጠር በመንፈስ ይመለሳል፡፡ በዚህ መኃል የሰው ሰው የሆኑ እሴቶችን እናጣለን፤ በተቃራኒው ራስ ወዳድነቱ፣ ግለኝነቱ እና ግደለሽነቱ ይጎላል፡፡ ከፖለቲካ ወለድ ችግሮች ባሻገር በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የሀገራችን ታላላቅ እና ታናናሽ ከተሞች የምናየው ስደት፣ ስርዓት አልበኝነት፣ ተስፋ አጥነት፣ ዘውጌነት እና የመሳሰሉት ማህበራዊ ህመሞች የዚህ ውጤት ናቸው፡፡ መደሀኒቱ ከተሞችን የሰው ከተማ ማድረግ ነው፡፡[‘God made the country, and man made the town’.  William Cowper, 1785.]

አስተያየት